የግብፅ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና አጀንዳ በመስጠት መጠመድ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ኢትዮጵያ ገና የዓባይን ግድብ የመገንባት እቅዷን ይፋ ካደረገችበት ማግስት ጀምሮ ነው። በዚህም እኩይ ተግባር ከአስርተ ዓመታት በላይ ተሰማርተዋል። ዛሬም የግድቡ ግንባታ ተገባዶ ባለበት ሁኔታ በተመሳሳይ ዘመቻ ላይ ይገኛሉ።
በተለይም ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ እነዚህ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት የዘወትር ተግባራቸው ሆኗል። የሚገርመው ደግሞ ይህን የሚዲያ ዘመቻ የሚያደርጉት የግብፅ መንግሥትን የሚደግፉ ብቻ ሳይሆኑ የሚቃወሙና በሌላ ሀገር በስደት ላይ የሚገኙ የሀገሪቱ ሚዲያዎች ጭምር ናቸው። የዘገባዎቻቸው ዋነኛ ዓላማም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ማድረግ ነው።
በግብፅ ሰፊ ስርጭት ያለው አህራም ጋዜጣን ጨምሮ እንደ አሽሩቅ፣ አልጀሙሪያ፣ አል-ሙስጠቅበል አል- ሱልጣን፣ ሰደል-በለድና ሌሎችም በርካታ ጋዜጦች ላይ ኢትዮጵያ ከእለት ተእለት አጀንዳቸው ወርዳ አታውቅም። ጋዜጦቹ በዋናነት “ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ጥሳ ሀገሪቱን እንደወረረች” በማስመሰል ኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲበረታ ለማድረግ እየተጉ ነው።
በዚህም በተለይም የዓረቡ ዓለም ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ ምልከታ እንዲኖረው የማድረግ ሕልም አላቸው። ለአንዳንድ የምዕራባውያን ሚዲያዎችም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ አጀንዳ ለማቀበል ሲጥሩ እለት ተእለት የምናስተውለው እውነት ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የምትባለዋና ዛሬም ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር የጂኦ ፖለቲካ ፍጥጫ የቀጠለችው ግብፅ፣ ከራሷ አልፋ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚሠሩ ሚዲያዎችን ከከፈተች ከ50 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረች መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ. ከ1960 ጀምሮ የሬዲዮ ጣቢያዎች በኦሮሚኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች በግብፅ መከፈታቸውን ከዓመት በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ሰፊ ዘገባ ይዞ የወጣው አል ሞኒተር የዜና ምንጭ ያመላክታል።
ግብፅ ይህንኑ እኩይ ተግባሯን በአሁኑ ወቅት አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትፈልግ የሚገልጸው አልሞኒተር፣ በናይል ተፋሰስ አገሮች ቋንቋዎች የሬዲዮ ሥርጭቶችን ለማስፋፋት ሰፊ ሥራ እያከናወነች መሆኗን፤ ‹‹በአሥር ሬዲዮ ጣቢያዎች ሰባት የአፍሪካ ቋንቋዎችን ጨምሮ በ23 ቋንቋዎች›› ለዓባይ ተፋሰስ አገሮች ሥርጭት የሚያደርሱ የሬዲዮ ጣቢያዎችን እያቋቋመች ነው›› መሆኑንም፣ ከእነዚህ አገሮች ውስጥም ኢትዮጵያ እንደምትገኝና አማርኛና ኦሮሚኛን የመሳሰሉ ቋንቋዎች የፕሮጀክቱ አካል መሆናቸውን ጠቁሟል።
ይህን የግብፅ ዘመቻ ለመመከት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ለመገመት የሚከብድ አይደለም። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት መፍጠርም ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ስለመሆኑ መካሪ እና ተመካሪ የሚፈልግ አይደለም።
በተለይም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በዓረብኛ ቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት መሸጋገር አለባቸው። በዜጎች የግል ተነሳሽነት የሚደረጉ ጥረቶች እውቅና ሊሰጣቸው፣ ሊበረታቱ፤ አስፈላጊው የሎጂስቲክ ድጋፍ ሊደረግላቸውም ይገባል።
እንደ ሀገር ለሚያጋጥማት መሰል ችግሮች የሚዲያ ምላሽ አሰጣጥ ምን ይሁን ለሚለው መሠረታዊና ተጨባጭ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ መሥራትም ያስፈልጋል። በብዙ መልኩ ከድህነት ለመውጣት የምናደርጋቸው ጥረቶች በአሉታዊ የሚዲያ ዘመቻ በብዙ ጫናዎች ውስጥ እየወደቁ ስለመሆኑ ያለፉትን አምስት ዓመታት የለውጥ ጉዟችንን መመልከት በራሱ በቂ ነው ።
ይህ ሁሉ ጫና የተፈራረቁት ለኢትዮጵያ አስከፊ ሊባል በሚችለው በዚህ ወቅት፣ በተለይም በግብፅ በኩል የነበሩ የማፊያ ጫናዎችን ለመከላከል ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነ ዜጎች በግል ተነሳሽነት የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር ተንቀሳቅሰዋል። በዓረብኛ ቋንቋ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች እየቀረቡ ስለኢትዮጵያ ጥቅሞች በመሞገት በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት ጥረት አድርገዋል። የሚታይ ስኬትም አስመዝግበዋል።
የነዚህ ጥቂት ዜጎች ጥረት፣ በፖሊሲና በስትራቴጂ ብንደግፈው ደግሞ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችለን ለመገመት የሚያስቸግር አይደለም። ለዚህም አቅሙና ብቃቱ ያላቸው ለቋንቋውም ለቴክኖሎጂውም ቅርብ የሆኑ ወጣቶች በብዛት መልምለን ተገቢውን ሥልጠና ሰጥተን ወደ ሥራ ማስገባት ብዙም የሚከብደን አይሆንም።
በነዚህ ዓመታት ሀገራችን ከነበረችበት አጣብቂኝ አኳያ ለውጭ ሚዲያዎችም ሆነ ለውጭ መንግሥታት የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በተደራጀ መንገድ ጠንካራ ምላሽ ለመስጠት ብዙ ፈተና ቢገጥማትም፣ ችግሩን አሸንፎ ለመውጣት ዜጎች በማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በስፋት ማሰማት የቻሉበት አጋጣሚ እንደነበርም ማስታወስ ተገቢ ነው።
በቅርብ ጊዜያት መፈጠር የቻሉት የ”No More” ዘመቻና ሌሎችም ጥረቶች በውጭ የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫናዎች ቁጭት፣ በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ግለሰባዊ ተነሳሽነት የተወለዱ ነበሩ ማለት ይቻላል። ለዚህ ሥራ ፈር ቀዳጅ መሆን የነበረባቸው ተቋማት አልነበሩም ወይ? የሚለውም ሆነ በግንባር ቀደምትነት ኃላፊነቱን መሸከም የሚገባቸው አካላት የሉም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳቱ በብዙዎች እምነት አሁን ጊዜው ላይሆን ይችላል። ጥያቄው ቢዘገይም ተገቢ ነው ባይ ነኝ፤ ከትናንት ስህተቶቻችን ተምረን ዛሬ ላይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የተሻለ ዕድል ሊፈጥር የሚችል ይመስለኛል።
በአሁነኛው የዲጂታል ዘመን አንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ከመደበኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎች እኩል የዲጂታል መገናኛ ብዙኃንን/ትዊተር፣ ፌስቡክ፣…ወዘተ/ በመጠቀም የዲጂታል ዲፕሎማሲ መሥራት የተለመደና ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ነው።
ሰጥቶ መቀበልና ተግባብቶ መኖርን በሚጠይቀው የዓለም ዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ሌሎችን ለማድመጥ ብቻም ሳይሆን፣ ተደማጭነትን ለማግኘት የዲጂታል ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሚና አለው። ዲጂታል ዲፕሎማሲ መደበኛ ዲፕሎማሲን አይተካም፣ የዲፕሎማሲ ተዋንያን በጨመሩበትና የመንግሥታት ግንኙነት በሰፋበት በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን መደበኛ ዲፕሎማሲ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ሊታገዝ እንደሚገባው ግልፅ ነው።
ስለኢትዮጵያ በተለይም በዓረብኛ ቋንቋዎች የሚሰራጩ ሚዲያዎች ላይ እየቀረበ የሚሟገተው መሐመድ አልአሩሲ በአንድ ወቅት ‹‹ኢትዮጵያ የውጭ ሚዲያዎች አጀንዳ ተቀባይ ሳትሆን የራሷ አጀንዳ ሰጪ መሆን አለባት›› ብሎ ነበር። ይህንን በመንተራስ ግብፆቹ ኢትዮጵያን ለመጫን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን በመጥቀስም ኢትዮጵያውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ሰጥቷል።
በምክሩን ‹‹እነሱ ለረዥም ጊዜ በመደራጀት ይበልጡናል። እኛን ለረዥም ጊዜ በሚዲያ የማጥቃት ሥራም ሠርተዋል። ነገር ግን እኛም አስበንበት ከተነሳን ጥቃታቸውን መመከት እንችላለን። ትንሽ የምንሆን ልጆች በዓረብኛ ሚዲያዎች ላይ እየገባን መልስ መስጠት በመቻላችን በአጭር ጊዜ ብዙ ለውጥ መጥቷል። በቀጣይ አቅማችንን አስተባብረን ከሠራን ደግሞ በሀገራችን ላይ የደረሰውን አደጋ ማስቆም እንችላለን። ዜጎች በራስ ተነሳሽነት ስለአገራቸው ጥብቅና መቆማቸውን በተደራጀ መንገድ መቀጠል አለባቸው›› ብሏል ።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ተቀባዮች ሳንሆን አጀንዳ ሰጪዎች መሆን ይገባናል። እኛ እነሱ ምን አሉ ስለሚለው ጉዳይ ትተን ስለራሳችን በራሳችን መንገድ መዘገብ መጀመር ይኖርብናል። ሌሎች አገሮች ሚዲያን የዲፕሎማሲና የፖለቲካቸው ዋና መገልገያ እንዳደረጉት ሁሉ እኛም እንችላለን አቅሙም አለን።
የሌሎች ሚዲያዎችን ሴራ በንቃት መከታተል አስፈላጊ ነው። ሲኤንኤን፣ ቢቢሲና ሌሎች የምዕራባውያን ሚዲያዎች ለራሳቸው ጥቅም ያጋደሉ አሠራሮችን እንደሚከተሉ ሁሉ ሳናውቀው የእነሱ ሰለባዎች እንዳንሆን የመረጃዎቻቸውን ተዓማኒነት መመርመር ይገባናል። በዚህ ረገድ ምሑራን ወደ መገናኛ ብዙኃን በመቅረብና በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን እውነት በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የሚዲያ ጫና መመከት ይጠበቅባቸዋል።
ልዑል ከ6ኪሎ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም