ትራምፕ በመጪው ምርጫ ከተሸነፉ ዳግም ለፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደሩ ጠቆሙ

አዲስ አበባ፡- የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የካማላ ሐሪስ ተፎካካሪ ዶናልድ ጄ ትራምፕ በመጪው ምርጫ ካላሸነፉ በፈረንጆቹ 2028 እንደማይወዳደሩ ጠቆሙ።

የ78 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ትራምፕ ላለፉት ሦስት ተከታታይ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ሪፐብሊካንን ወክለዋል።

በቅርቡ ባደረጉት አንድ ቃለምልልስ በቀጣይ ምርጫ በካማላ ሐሪስ ከተሸነፉ ከ4 ዓመት በኋላ ዳግም ይወዳደራሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁ፣ “አይመስለኝም። አላደርገውም” ብለዋል። ይሁንና መጪውን ምርጫ እንደሚያሸንፉ በጽኑ ተስፋ አድርገዋል።

የአሜሪካ ሕግ አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ በዋይት ሐውስ መቆየትን ይከለክላል። ይህም ማለት ትራምፕ መጪውን ምርጫ ቢያሸንፉ እንኳ በ2028 በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችሉም።

ባለፈው ሐሙስ በአይሁድ-እሥራኤላውያን ካውንስል ጉባኤ ላይ የተገኙት ትራምፕ “ከተሸነፍኩ አንዱ ምክንያት እናንተ ናችሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ለመሆኑ እኔ ከተሸነፍኩ ምን ዓይነት መዓት ሊወርድ እንደሚችል ያውቃሉን?” ሲሉ ወደ ካማላ ሐሪስ ያዘነበሉ አይሁድ-አሜሪካውያንን ወቅሰዋል።

ይህ አስተያየታቸው በካማላ ሐሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን እና በገለልተኛ አይሁድ መራጮች ዘንድ ቅሬታን አሳድሯል።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ የመሸነፍ ዕጣ ሊገጥማቸው እንደሚችል የሚጠቁም ንግግር ከአንደበታቸው ወጥቶ አያውቅም። ያለፈው ምርጫም ተጭበርብሮ ነው እንጂ አሸናፊው ጆ ባይደን ሳይሆኑ እኔ ነኝ ሲሉ ይከራከራሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ትራምፕ መሸነፍም እንዳለ የገባቸው ይመስላል።

የፖለቲካ ተንታኞች ይህ የትራምፕ አስተያየት ከጆ ባይደን ገለል ማለት ወዲህ የመጣ አዲስ አመል ነው ይላሉ። በተለይም ካማላ ሐሪስ ከፍተኛ ተቀናቃኛቸው እንደሆኑ በመረዳታቸው እንደሆነ ይገምታሉ።

ካማላ ሐሪስ ጆ ባይደንን ከተኩ ወዲህ በዲሞክራቶች ዘንድ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል።

በታኅሣሥ ወር ብቻ በምርጫ ቅስቀሳ ካማላ ሐሪስ 190 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰብ የቻሉ ሲሆን ትራምፕ ግን 130 ሚሊዮን ብቻ ነው ማሰባሰብ የቻሉት።

ባለፈው እሑድ በተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት ሐሪስ ዶናልድ ትራምፕን 52% ለ48% እየመሩ እንደሆነ ተመላክቷል። ወሳኝ በሚባሉት ግዛቶች ግን ዶናልድ ትራምፕ እየመሩ ነው። ይሁንና ቀድሞ ይመሩበት ከነበረው ነጥብ ልዩነቱ እየጠበበ መጥቷል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ በሠራው የሕዝብ አስተያየት ቀመር በወሳኝ ግዛቶች ትራምፕ 51% ለ49% እየመሩ ነው። ኤንቢሲ ትናንት ይፋ ባደረገው ሌላ የሕዝብ አስተያየት ቀመር ደግሞ ሐሪስ ትራምፕን በ5 ነጥብ እየመሩ ነው።

48% የሚሆኑ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡ መራጮች ካማላ ሐሪስን በበጎ ማየት እንደጀመሩ አንድ ጥናት አመላክቷል።

ይህ የሕዝብ አስተያየት መራጮች በስደተኞች ጉዳይ፣ በምጣኔ ሃብት ጉዳይ እና በኑሮ መወደድ ጉዳይ ልባቸው ወደ ትራምፕ ያጋደለ እንደሆነ አሳይቷል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You