በተለያዩ ዓለማት በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ ሆነዋል።ይህ ወቅት እንደ ኦሊምፒክ እንዲሁም ዳይመንድ ሊግ ያሉ ውድድሮች የሚጠናቀቁበት እንደመሆኑ በተለያዩ ከተሞች የጎዳና እና የመም ውድድሮች በስፋት የሚከናወኑበት ነው።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄዱት የሩጫ ውድድሮችም በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ከእነዚህ ውድድሮች መካከል አንዱ በአምስተርዳም የተከናወነው የ10 ማይል የጎዳና ላይ ሩጫ ሲሆን፤ በቀድሞው የዓለም ቻምፒዮና ሙክታር እድሪስ አሸናፊነት ተጠናቋል።ሙክታር በ2017 የለንደን እንዲሁም በ2019 የዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረኮች በ5ሺ ሜትር በተከታታይ አሸናፊ በመሆን በእንግሊዛዊው አትሌት ሞሃመድ ፋራህ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የበላይነት ወደ ሃገሩ የመለስ ጀግና አትሌት መሆኑ ይታወቃል።ይሁንና አትሌቱ በተደጋጋሚ በሚገጥመው ጉዳት ምክንያት ያለውን ብቃት እንደ ኦሊምፒክ ባሉት መድረኮች አውጥቶ ማሳየት አልቻለም።እአአ በ2022 በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ድልን በተደጋጋሚ በተቀዳጀበት ርቀት ሃገሩን ወክሎ ቢሰለፍም ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት በውድድሮች ላይ እምብዛም ያልታየው ሙክታር አምስተርዳም ላይ በድል ብቅ ብሏል።ይህም አትሌቱ ፊቱን ከመም ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ማዞሩን የሚያመላክት ነው።
ፈጣን በነበረው ውድድር ሙክታር ፉክክሩ ከተጀመረ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ተፎካካሪውን በመቅደም በመሪነት እስከመጨረሻው መጓዝ ችሏል።ከዩጋንዳዊው የ10ሺ ሜትር ሶስት ጊዜ ቻምፒዮን ጆሹዋ ቺፕቴጊ ጋር በዚህ ውድድር መገናኘቱ ሩጫው ለሙክታር ሊከብድ እንደሚችልና በመካከላቸውም ከፍተኛ ፉክክር ሊኖር እንደሚችል አስቀድሞ ተገምቶ ነበር።ይሁንና ሙክታር ርቀቱ እየጨመረ ሲሄድ ፍጥነቱንም ይበልጥ እየጨመረ ተፎካካሪውን በ27 ሰከንዶች ቀድሞ ሊያጠናቅቅ ችሏል።የገባበት 45:44 የሆነ ሰዓትም በቦታው ከተመዘገቡት መካከል ከፈጣኖቹ ተርታ ተቀምጧል።ለአሸናፊነት በእጅጉ የተጠበቀው ቺፕቴጊ በበኩሉ 45:18 በሆነ ሰዓት ርቀቱን ሸፍኗል፤ ይህም ሰዓት አትሌቱ ከሶስት ዓመታ በፊት ካስመዘገበው በሶስት ሰከንዶች የዘገየ ነው።
በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሳየች አይቼው ኬንያዊቷን አትሌት አስከትላ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።በዚህ ውድድር የመሪነቱን ስፍራ ተቆጣጥራ ውድድሩን ስትመራ የቆየችው ግላድየስ ቼፕኩሩይ ብትሆንም አትሌት አሳየች ሳትጠበቅ የመጨረሻውን መስመር በቀዳሚነት መርገጥ ችላለች።ርቀቱን ለመሸፈን የፈጀባት ሰዓት 51:15 ሲሆን፤ ኬንዊቷ ከ19 ሰከንዶች መዘግየት ተከትላ ገብታለች።ሶስተኛ የሆነችው አትሌት ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት መብራት ግደይ 52:14 የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች።
በታይዋን በተካሄደው የማራቶን ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ተከታትለው በመግባት የውድድሩን የበላይነት ሊቆጣጠሩ ችለዋል።40ሺ ሯጮች በተካፈሉበት በዚህ ማራቶን ደሳለኝ ግርማ፣ ደጀኔ ደበላ እና አሰፋ ተፈራ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።ጠንካራ ፉክር በታየበት በዚህ ውድድር አትሌቶቹ ለመሸናነፍ ያደረጉት ፉክክር በሰከንዶች ብቻ የተለያየ መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው።በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድርም በተመሳሳይ ከፍተኛ ፉክክር የታየ ሲሆን፤ በሰከንዶች ብቻ ተለያይተው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።በዚህም መሰረት ኢትዮጵያዊያኑ ጫልቱ ጪምዴሳ እና ፋንቱ ዘውዱ ተከታትለው ሲገቡ ኬንያዊቷ ሞኒካ ቺቤት ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።
በሄንግሺ ሃይቅ በተደረገው ሌላኛው ማራቶን ደግሞ ኬንያዊው አትሌት በናርድ ኪፕኮሪር ሲያሸንፍ ኢትዮጵያዊው መኳንንት አየነው ሁለተኛውን ደረጃ ሊይዝ ችሏል።ሁለቱ አትሌቶች በአንድ ደቂቃ ተለያይተው የገቡ ሲሆን፤ ከውድድሩ አስቀድሞ ይጠበቅ እንደነበረው በኢትዮጵያውያኑ እና የኬንያ ተቀናቃኞቻቸው መካከል ብርቱ ፉክክር ተደርጓል።ኤርትራዊው አትሌት ብርሃኔ ጸጋይ ደግሞ ሶስተኛው አትሌት ሆኗል።በሴቶች አታለል አንሙት አሸናፊ ስትሆን፤ የሃገሯ ልጅ ደራርቱ ኃይሉ ደግሞ ሶስተኛ ሆናለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም