ከተማን ከተማ የሚያደርጉት ሕንጻዎች ብቻ አይደሉም፤ እንደ መንገድና የመሳሰሉት መሰረተ ልማቶችና አረንጓዴ ስፍራዎችም ስለመሆናቸው የከተማ ልማት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።የከተሞች ማስተር ፕላንም ይህን ታሳቢ ተደርጎ እንደሚዘጋጅ ይታሰባል።አዲስ አበባም በእዚህ መልኩ ማስተር ፕላን እየተዘጋጀላት ስትገነባ ኖራለች፡፡
ይሁንና ማስተር ፕላኑን መሬት ላይ ከማሳረፍ አኳያ ሲታይ ከተማዋ በመሰረተ ልማትም ሆነ በአረንጓዴ ሽፋን በኩል ስትታይ የመሰረተ ልማቶቹ ድህነት በእጅጉ የጸናባት ሆና ኖራለች።በከተማዋ መሬት አስተዳደር ይሁን በሌላ በሚመለከተው አካል በኩል የከተማ መሬትን አስመልክቶ ለረጅም ጊዜያት ተንሰራፍቶ የቆየው አመለካከት ከሕንጻና ሕንጻ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል።በከተማዋ የተካሄደው ግንባታም ሲታይ ይህንኑ ያመለክታል፡፡
ለከተማ መሰረተ ልማት እንዲሁም ለአረንጓዴ ስፍራ ልማት ግንባታ የተከለለ መሬት በሙሉ ሊያሰኝ በሚችል መልኩ ለሕንጻ ግንባታ እንዲውል ተድርጓል።ከተማዋ ኮንክሪት በኮንክሪት ለመሆን ተገዳ ቆይታለች።የቀደሙት የከተማዋ አስተዳዳሪዎች የከተማዋን መሬት ለሕንጻ ግንባታ ብቻ ማዋላቸው አልበቃ ብሏቸው መንግስታዊ ተቋማት ባላቸው ራእይ መሰረት ይዘውት ከነበሩት መሬት ላይ ጭምር ወስደው ለባለስልጣናት ያድሉም ነበር።አሁንም ቢሆን በጋራ መጠቀሚያ መንደሮች ለተለያዩ መሰረተ ልማቶች በሚል የተተው ቦታዎች ለሌላ ዓላማ እንዲውሉ ሲደረግ እየተደረገ ነው፡፡
ግንባታ ያልተካሄደበት ቦታ በኪስ ቦታነት ተይዞ በውድ ዋጋ ሲቸበቸብ ኖሯል፤ ለቦታ ጠያቂዎች መሬት ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ መሬት ይኑረው አይኑረው የማያውቅበት ሁኔታም ነበር።ኪስ ቦታ ጠቁሙ እየተባለ መሬት ይሰጥ ነበር።የትኛውም አይነት መሬት ሲገኝ/ብቻ መሬት ይሁን እንጂ/ የወንዝ ዳርቻዎችም ጭምር በሊዝ ተሸጠዋል።ልብ በሉ እንግዲህ ሕንጻዎችን የሚገነቡ አካላት ግንባታዎችን ከወንዞች የተወሰነ ሜትር /25 ሜትር መራቅ አለባቸው ሲባል ሰምቻለሁ/ መራቅ ያለባቸው ስለመሆኑ በሚገባ እየታወቀም ወንዝ እና ገደል አፋፉ ላይ ያለን ቦታ ሳይቀር ሕንጻ እገነባበታለሁ ላለ አካል መምራት በተለመደበት ከተማ ውስጥ ቆይተናል፡፡
በማስፋፊያ ቦታም ቢሆን ግንባር ቦታ በሊዝ ለመሸጥ ይዘጋጃል።በራቸው ላይ ሰንጋ በሬ አስረው ሲያቁለጨልጩ እንደሚከርሙ ስጋ ቤቶች ባለቤቶች ሰፋፊ መሬቶች ፊት ለፊት ላይ ክፍት ተትተው ዓመታትን እንዲቆጥሩ ሲደረግ ቆይቷል።ሌሎች ሕንጻዎች ከጀርባቸው ተሰርተው አካባቢውን ከተማ ካደረጉ በሁዋላ ለባለሀብቶች ወይም ብር ይዘው ለሚመጡ አካላት ይተላለፋሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ነባሩ ክፍል/መሀል ከተማ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ/ ባለው የመሬት አስተዳደር አሰራር መሰረት የከተማዋን ደረጃ የማይመጥኑ መኖሪያ ቤቶችን፣ ድርጅቶችን ወዘተ ተሸክሞ እንዲቆይ ተደርጎ ኖሯል፤ እነዚህ ይዞታዎች በተለይ የቀበሌ ወይም በመንግስት ይዞታ ስር ያሉት ወይ አይለሙ፣ ወይ አይፈርሱ ደክመው ከተማዋን ሲያደክሟት ቆይተዋል።የግል ይዞታዎች ወይ በባለቤቶቻቸው አልያም በገዟቸው አካላት ፈርሰው የሚሰሩበት ሁኔታ ብዙ ቢሆንም፣ ካለው የግል ይዞታ ብዛት አኳያ ሲታይ የለሙት እጅግ ጥቂት የሚባሉት ናቸው።ከእዚህ የከተማዋ ክፍል ይልቅ ማስፋፊያ አካባቢዎች ይበልጥ ከተማ ከተማ የሚያውዱበት ሁኔታ ይታያል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ለእዚህ ሁሉ የከተማዋ ችግር መፍትሄ ይዞ መጥቷል።ልማቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የታየውም ይሄው ነው።የኮርደር ልማቱ እነዚህን የከተማዋን ገጽታ ያበላሹ ግንባታዎችን በሙሉ /ለባለ ይዞታዎች ቦታና ካሳ እየሰጠ፣ ለተከራዮች የኪራይ ቤትና የመሳሰለውን እያቀረበ/ እያነሳ ይገኛል።ልማቱ ግንባሩን ብቻ ሳይሆን ገባ እያለም ሰፊ ቦታዎችን አያጸዳ ነው። ለልማቱ ያስፈልጋሉ በተባሉ ቦታዎች ላይ የተጀመሩ የትላልቅ ሕንጻ ግንባታዎች ሳይቆሩ ተሰርዞ ቦታዎቹ ለኮርደር ልማቱ ዓላማ እንዲውሉ ተደርጓል።
በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ሰፋፊ ቦታዎች ማግኘት ችሏል።ከእነዚህ ቦታዎች መካከል እስከ አሁን የከተማ አስተዳደሩ ወደ ግሉ ዘርፍ በጨረታም ይሁን በሌላ መልክ ያስተላለፋቸው ቦታዎች አሉ ሲባል አልሰማሁም።ከዚህ ውጪ ግን የከተማ አስተዳደሩ ቦታዎቹን ከተማዋን በእጅጉ ለራባራትና ለጠማት ልዩ ልዩ መሰረተ ልማት ግንባታ እያዋለ ይገኛል።
እነዚህ ቁልፍ በሚባሉ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ የተገኙ ቦታዎች ለሕንጻና ለመሳሰሉት ግንባታዎች በጨረታ ቢቀርቡ የከተማ አስተዳደሩን ኃላፊዎች እጅ ስመው ከተጠራው ዋጋም በላይ አስበልጠው ሰጥተው ሊገዙ የሚችሉ በርካታ ባለሀብቶችና ባለገንዘቦች ሞልተዋል። ከተማ አስተዳደሩን ይህ በፍጹም አላጓጓውም።ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ከተማ አስተዳደሩን ያሳሰበው ከተማዋ ያለባት የመሰረተ ልማት ድህነት ነውና መሬቱን ይህን ድህነት ለመቀነሱ ተግባር አውሎታል፡፡
ለእዚህም ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ ቀበና መገናኛ ያሉትን አካባቢዎች መመልከት በቂ ነው።በእነዚህ አካባቢዎች የጸዱ ይዞታዎች ወይ ለተለያዩ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች፣ አልያም ለሰፋፊ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የመኪና ማቆሚያና የገበያ ማእከላት/ ሞሎችን ለመገንቢያ ነው እንዲውሉ የተደረጉት።ይህ የኮሪደር ልማት በሜክሲኮ መገናኛ ኮሪደርም ልማት እየታየ ነው።
ኪስ ቦታዎችን በወረንጦ በመልቀም በሊዝ በውድ ዋጋ ሲቸበቸብ የነበረበት ሁኔታን፣ እኔ የከተማ አስተዳደሩ ‹‹መሬት ለመሰረተ ልማት›› በሚል አሰራር ቀይሮታል እንድል አርጎኛል።ለእዚህም ነው መንገዶችን ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አድርጎ መስራት የተቻለው።የመኪና መንገዶች ብቻም ሳይሆኑ በከተማዋ በውስን አካባቢዎች ብቻ ይታዩ የነበሩ የተንጠለሉ የእግረኛ መንገዶች በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ በስፋት ማየት የተቻለውም ለእዚህ ይመስለኛል፡፡
የመሬት አቀማመጧ ለብስክሌት አይመችም ስትባል የኖረችው አዲስ አበባ የቸርችል ጎዳናን ዳገት ጨምሮ የኮርደር ልማቱ በሚያልፋባቸው ዋና ዋና መንገዶች ሁሉ የብስክሌት መንገዶች ተገንብተው ለትራፊክ ክፍት ተደርገው ብስክሌተኞችን እየጠበቁ ናቸው።ይህም ሊሆን የቻለው አንድም በቂ የብስክሌት መሰረተ ልማት መገንባት የሚያስችል ቦታ በመገኘቱ ነው፡፡
የመንገድ ዳር አረንጓዴ ስፍራዎች ብቻ አይደለም በኮሪደር ልማቱ እየተገቡ የሚገኙት።በጣም ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎች ተፈጥረዋል።ለእዚህም የዛሬዋን ግንፍሌ ማየት ነው፤ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ጽህፈት ቤት ወደ ፒያሳ እየተጓዙ መመልከትም ነው።ከተማዋ ባለፉት መንግስታት በማስተር ፕላኗ ላይ የተቀመጡ በቂ የአረንጓዴ ስፍራዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንድታጣ ብትደረግም፣ ማንም ሊገምተው ባልቻለ ጊዜና መልኩ ይህ ዘመን አረንጓዴ ስፍራዎቿን እያስመለሰላት ይገኛል።
ከተማዋ እየተስፋፋች፣ የሕዝቧም ብዛት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ነባሩ የከተማዋ አካባቢ በተለይ ትናንት የተፈጠሩ አንዳንድ አካባቢዎች ሳይቀሩ ከፍተኛ የትራፊክና የሕዝብ መጨናነቅ በሚታይባቸው በእዚህ ወቅት ችግሩን ቆም ብሎ በማሰብ በኮሪደር ልማት ለመፍታት መነሳት የከተማዋ መሪዎችም የፌዴራል መንግስቱም ለከተማ ልማት የሰጡትን ልዩ ትኩረትም ያመለክታል፡፡
የኮርደር ልማቱ ይዞት የተነሳው የመንገዶች ማስፋፋት፣ አዳዲስ የታክሲና አውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎችን የመገንባት ስራ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ፣ መጸዳጃ ቤቶችን፣ መዝናኛ ስፍራዎችን የማካተት ስራ ግዙፍ እንደመሆኑ የሚያስፈልገውም ቦታ ብዙ ሊሆን እንደሚችል በማመን አሁን በተያዘው መልኩ ከተማዋን መልሶ ለማልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር አድናቆት ሊቸረው ይገባል።
የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ በአረንጓዴ ስፍራዎች የታጀበች ያደርጋታል። በቂ የታክሲና የአውቶብስ መጫኛና ማውረጃ ያላት እንድትሆን ያስችላታል፤ ይህም በመንገድ ጥበትና በመሳሰሉት ሳቢያ እየተገፉ እየተገፉ ዳር ሲወጡ የነበሩት የታክሲ ወይም አውቶብስ ተርሚናሎችን በቅርብ ማግኘት ያስችላል፤ በአጠቃላይ የታክሲና የአውቶብስ ተርሚኖሎች ችግር በመሰረታዊነት ይፈታል።
ይህ ብቻም አይደለም ከተማ የበርካታ ግዙፍ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፓርኮች ባለቤትም እንድትሆንም ያስችላታል፤ በአራት ኪሎ፣ በፒያሳና ሰራተኛ ሰፈር የሚካሄዱትን የፓርኪንግ የገበያ ማእከላት/ሞሎች/ ግንባታዎች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው። የኮሪደር ልማቱ በሚያልፋባቸው አካባቢዎች የመጸዳጃ ቤት ጥያቄ በቀጣይ አይነሳም፤ እግረኞች ዘና ብለው የሚጓዙባቸው፣ ተሽከርካሪዎች ደረጃቸውን በጠበቁ መንገዶች የሚሽከረከሩባቸው፣ አካል ጉዳተኞች ጥያቄ የማያነሱባቸው መንገዶች እየተገነቡ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ይህን ሁሉ ለማከናወን አቅዶ በመስራቱ የመሬት ጉዳይ ስራውን አላቆመውም።ይበልጥ አጠናክሮ እንዲሰራ፣ አንድም ስራ ለነገ ሳይል እንዲያከናውን አስችሎታል ባይ ነኝ።
አዲስ አበባ ከተማ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ብቻም አይደለችም፤ የአፍሪካ ሕብረት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ የአያሌ ዲፕሎማቶች መገኛም ናት።እነዚህ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መቀመጫ የሆኑ የዓለም ከተሞች የሚያስፈልጋቸውን የከተማ መሰረተ ልማት በአዲስ አበባም እንዲያገኙ ማድረግ መቻል ፍላጎታቸውን ከማሟላት ባሻገር የኢትዮጵያን ገጽታ በእጅጉ ይገነባዋል።
ይህን ግዙፍ ስራ መስራት ውስጥ መግባት እንዲሁም መፈጸም መቻል ለእኔ ባለ ራእይነትን ያመለክታል።መንግስትን ያሳሰበው አሁን ያለው የከተማዋ መጨናነቅ፣ የዘመናዊ ከተማ መሰረተ ልማት ማጣቷ ብቻ አይደለም፤ መጪው ትውልድም መጪዋ አዲስ አበባ መምሰል ያለባትም ነው።
የአሁኑ ትውልድስ እየተጨናበሰም ባለው መሰረተ ልማት ሊኖር ይችል ይሆናል።መጪው ትውልድ ባለፉት መንግስታትና በአሁኑ መንግስት ጥፋት መላወሻ ማጣት የለበትም።ለሀገሪቱ ከፍታ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና ሌሎች አህገራዊ፣ ክፍለ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ደረጃቸውን የሚመጥኑ አገልግሎቶችን ማግኘት መቸገርም የለባቸውም።የሀገሪቱም የአዲስ አበባም ከፍታ እየመጣ ነው።ያንን ከፍታ የሚያስተናገድ መሰረተ ልማት መገንባት ብቻ ሳይሆን መገንቢያ ሊሆን የሚችል ቦታ ማዘጋጀት መቻል በራሱ ትልቅ ስራ ነው።ይህን ማድረግ እየተቻለ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግስቱ የከተማዋን መሰረተ ልማቶች ለማሟላት የያዙት ርብርብ ባለ ራእይነታቸውን ያመለክታል፤ የከተማዋን ስር የሰደደ ችግር መንግሎ መጣልንና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች የምትሰጥ አዲስ አበባን እውን ማድረግን አልመው መስራታቸውና ፍሬያማ መሆናቸው አሁን ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ የከተማዋን ታሪክ አንብቦ የሚረዳው መጪው ትልድም የተከበረ ስፍራ ይሰጣቸዋል ብሎ መገመትም ይቻላል።የልማቱ ሀሳብ ጠንሳሾች፣ አዳባሪዎችና ተግባሪዎች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል።
የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግስቱ ይህን ሁሉ መሰረተ ልማት ለመገንባት እንዲያስችል በመሬት ላይ ለተከተሉት አሰራር አድናቆቴን ሳልገልጽ አላልፍም፤ መሬትን ለመሰረተ ልማትና መሰረተ ልማት ብቻ ማዋላቸው ትልቅ ለውጥ ማምጣት አስችሏል።
መሬትን ለሕንጻና ሕንጻ መገንቢያ ብቻ ከማድረግ በመውጣት የአረንጓዴ ስፍራዎችና ዘመኑን የሚመጥኑ የገበያ አዳራሾችን /ሞሎችን/ እና የመኪና ማቆማያዎች፣ ወዘተ. የሚገነባባቸው ማድረግ መቻል ጀግንነት ነው። መሬት እንደ ትልቅ ሀብት በሚቆጠርባትና ለሀብት ማግኛ ሲውልባትም ለቆየችው አዲስ አበባ ይህን ሁሉ በአይን ስፍራ ላይ የሚገኝ መሬት ለእነዚህ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ማዋል በእርግጥም ጀግንነት ነው።
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም