ሂዝቦላህ የሚቃጣበትን ማንኛውንም ርምጃ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። እሥራኤል እና ሄዝቦላህ ድንበር አካባቢ የሚያደርጉትን የተኩስ ልውውጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ ሁለቱ ወገኖች ከለየለት ጦርነት እንዲቆጠቡ እያሳሰበ ይገኛል።
የእሥራኤል ጦር ኃይል እንዳለው ቅዳሜ ምሽት እና እሑድ ንጋት 150 ሮኬቶች፣ ሚሳዔሎች እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ወደ እሥራኤል ተተኩሰዋል።
አንዳንድ ጥቃቶች ከዚህ ቀደም ከሚመቱት ዒላማ ዘልቀው በመውደቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ እሥራኤላውያን ከቦምብ አደጋ ለመከላከል በተሠሩ መጠለያዎች ውስጥ ተሸሽገው እንደነበር ተሰምቷል። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የደረሱት ሀይፋ ከተማ አቅራቢያ ነው።
እሥራኤል በአፀፋው በደቡባዊ ሊባኖስ በወሰደችው እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን አውድሜያለሁ ብላለች።
እሑድ ንግግር ያሰሙት የእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሀገራቸው “ፀጥታዋን ለማስከበር የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።
“ሄዝቦላህ ላይ ሊታሰብ የማይችል ኪሳራ አድርሰናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ያሉ እሥራኤላውያንን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ቃል ገብተዋል።
የሄዝቦላህ ምክትል መሪ የሆኑት ናይም ቃሲም በበኩላቸው “ማስፈራራቶች አያግዱንም። የትኛውንም ወታደራዊ እርምጃ ለመመከት ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
እስራኤል ባለፈው ዓርብ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በፈፀመችው ጥቃት ምክንያት የተገደሉት የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ኢብራሒም አቂል ቀብራቸው ተካሂዷል። በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ቃሲም “አሁን አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን። በግልፅ [ከእስራኤል ጋር] ተፋጠናል” የሚል ንግግር አሰምተዋል።
ሼኽ ናይም ቃሲም ለቡድኑ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት እሥራኤል ዒላማዎቿን እየሳተች ነው ብለው ነገር ግን ሄዝቦላህ ባለፉት ሦስት ቀናት ጥቃት ማድረስ መቀጠሉን ገልፀዋል።
አክለውም በሚቀጥሉት ቀናት በሰሜናዊ ሊባኖስ የሚኖሩ በርካታ የእሥራኤል ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንደሚፈናቀሉ እና እሥራኤል የቡድኑን ጥንካሬ መቋቋም እንዳቃታት ተናግረዋል።
ሄዝቦላህ የሐማስ አጋር ሲሆን ሐማስ ደግሞ ኢራን “አክሲስ ኦፍ ሬዚዝስታንስ” እያለች የምትጠራው ጥምር ቡድን አባል ነው።
የኢብራሒም አቂልን ቀብር ለመታደም በርካታ ቁጥር ያለው ሰው አደባባይ የወጣ ሲሆን የሄዝቦላህ አባላት የሆኑ ሰዎች “ሞት ለአሜሪካ” የሚሉ እና ሌሎች የተቃውሞ ድምፆችን ሲያሰሙ ነበር።
የሊባኖስ ባለሥልጣናት በተደረገ ጥቃት ኢብራሒም አቂልን እና 15 አብረዋቸው የነበሩ የሄዝቦላህ አባላትን ጨምሮ 45 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 14/2017 ዓ.ም