ሩዝ ሌላኛው የሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ተስፋ

በ1980ዎቹ ከሰሜን ኮሪያ በመጡ የልማት አጋሮች ሩዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ አካባቢ እንደተሞከረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ፎገራና አካባቢው ክረምት ክረምት በጎርፍ ስለሚሸፈንና ቦታው እረግረጋማ ስለሆነ ከጓያ ውጪ ሌላ አማራጭ ሰብል አይበቅልበትም ነበር። በአካባቢው የሚኖረው አርሶአደር አገላብጦ ማረስ የሚችል ክንዱን አጣጥፎ ተቀምጦ እጁን ለእርዳታ በመዘርጋት ለዘመናት በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ኖሯል።

አሁን ላይ ግን ለረዥም ዘመናት ጾሙን ያድር የነበረው የአካባቢው መሬት በሩዝ ተሸፍኖ ማየት የተለመደ ነው። የአካባቢውም አርሶ አደሮችም «ከውሃ በላኝ ወደ ውሃ አበላኝ» ብሂል ተሸጋግረዋል። አሁን ላይ በውሃማው አካባቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ሩዝ በስፋት እያመረተ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ላይ ነው፤ በእነዚህም ሕይወቱ ትርጉም ባለው መንገድ እየተለወጠ ነው።

በጥቅሉ ፎገራ አካባቢ ሩዝ የአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ የኢኮኖሚያዊ አቅም መሆን የቻለ ሰብል ነው። በሀገሪቱ ከሚመረተው የሩዝ ምርት ውስጥ 70 በመቶ በዚህ አካባቢ እንደሚመረትም መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህ አካባቢ የተገኘውን ውጤት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በመንግሥት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ትልቅ የአመጋገብ ለውጥ እየመጣ ነው። በዚህም ሩዝን የሚጠቀም የማኅበረሰብ ክፍል እጅግ እየበዛ ነው። በዚህም የሀገሪቱ የሩዝ ፍላጎት ከ500ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ተመርቶ እየቀረበ ያለው ግን ከ150 ሜትሪክ ቶን እንደማይበልጥ። ይህም 70 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የሩዝ ፍላጎት እየተሟላ ያለው ከውጭ በሚገባ ምርት ነው። ስለዚህ ሀገሪቱ የሩዝ ፍላጎቷን ለማሟላት በዓመት ከ170 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ።

እንደ ሀገር ከተረጂነት ለመላቀቅና በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል በተለይ በስንዴ ምርት ላይ በተሠራው ጠንካራ ሥራ ከስንዴ ተረጂነት በመላቀቅ ወደ ውጭ ምርቷን መላክ ጀምራለች። በተመሳሳይ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ መሠረት በቀጣይ አምስት ዓመት ሀገሪቱ ከውጭ ከምታስገባው 70 በመቶ የሩዝ ምርት 40 በመቶውን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ወደ 30 በመቶ ዝቅ ለማድረግ፤ እንዲሁም በ10 ዓመት ውስጥ ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው ምርት በማምረት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ፍጆታዋን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የሩዝ ሰብል ልማት «ኢንሼቲቭ» በሀገሪ ቱ ተጀምሯል።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት፤ ሀገሪቱ ሩዝን በስፋት ለማምረት ተስማሚ የእርሻ መሬት፣ አፈር፣ አየር ንብረት እና በቂ የውሃ ሀብት አላት። ሀገሪቱ ካላት ሰፊ ተስማሚ ሥነ-ምህዳር በመኸር ወቅት በዝናብ ብቻ ሊለማ የሚችል ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት አላት። ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ የአፍሪካ የውሃ ማማ እንደመሆኗ መጠን ያሏትን የወንዝ ተፋሰሶቿን በመጠቀም የሩዝ ሰብል ለማልማት የሚያስችል በትንሹ 3 ነጥብ 7 ሄክታር ተስማሚ መሬት አላት።

በድምሩ በዝናብና በመስኖ በ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሩዝን በስፋት ማምረት ከተቻለ አይደለም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ቀርቶ ለሌሎች ሀገሮች መትረፍ የሚቻልበት ዕድል አለ። ከዚህ የተነሳም መንግሥት ለስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት እንዳለው በሩዝ ሰብል ልማት ላይ መቀጠሉ ይበልጥ ሀገሪቱን ውጤታማ ያደርጋታል የሚል እምኔታ አላቸው።

ለሩዝ ምርት በጣም ተስማሚ የሆኑ ሰባት ማዕከሎች/ አካባቢዎች ተለይተው (በአማራ ክልል ፎገራ፣ በኦሮሚያ ክልል ጨዋቃ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና አቦቦ፣ በሱማሌ ክልል ጎዴ፣ በጋምቤላ ክልል ፓዌ እንዲሁም ማይጸብሪ) በስፋት የሩዝ ሰብል ልማት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ለአብነት በተያዘው የመኸር ወቅት በኦሮሚያ ክልል የሩዝ «ኢንሼቲቭ» ልማት በክልሉ በይፋ ተጀም ሯል።

በሩዝ ምርት ራስን ከመቻል አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በተያዘው እቅድ እንደ ክልሉ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ለመሸፈን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ800 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሩዝ መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። በዚህ ክልል ብቻ ከፍተኛ ምርት ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል። በተመሳሳይ ከላይ በተጠቀሱት ለሩዝ ተስማሚ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ባላት የተፈጥሮ ሀብት ልክ ምርታማ እንዳትሆን የሚያደርጋት ከቅድመ እስከ ድሕረ ምርት የሚታዩ ማነቆዎች እንዳሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሩዝ በሚመረትባቸው አካባቢዎች በቂ የሆነ የመስኖ መሠረተ ልማት አለመዘርጋት፤ በሩዝ ማምረቻ ማዕከሎች ተገቢ ያልሆነ የመሬት ዝግጅት እና የውሃ አያያዝ መኖር፤ እንደሌሎች ሀገሮች ለሀገሪቱ አየር ንብረት ተስማሚ የሩዝ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩም ሆነ በዘርፉ ለሚሰማሩ አልሚዎች በስፋት አማራጭ አለመቅረብ እና የዘር እጥረት መኖር በቅድመ ምርት ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው።

ሌላው ሩዝ ከእርሻ እስከ ማቀነባባር ባለው ሂደት ራሱን የቻለ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከድህረ ምርት በኋላ በተለይ በማቀነባበር ሂደት ላይ የተሻሻሉ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ጥራት ያለው ምርት እንደ ሀገር እየተመረተ አይደለም። በዚህም ምርቱ ገበያ ላይ ተወዳዳሪም፤ ተመራጭም አይደለም።

በቅድመ እና ድሕረ ምርት ባለው ሰንሰለት የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሱን ኃላፊነት በሚገባ ከተወጣ፤ ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት የሚያስፈልጉ የተሻሻሉ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂዎችን በተለይ መንግሥትና በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች የአንበሳውን ድርሻ ወስደው እንዲሟላ የበኩላቸውን ሚና ከተወጡ ጥራት ያለውና እሴት የተጨመረበት ምርት በስፋት እንደ ሀገር ማምረት ይቻላል። በዚህም ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ፍጆታዋን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማስቀረት ትችላለች።

ሀገሪቱ ባላት አቅም ልክ ማምረት ከቻለች ከራሷ አልፋ ምርቷን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበት አንድ ዘርፍ ነው። አብዛኞቹ ጎረቤት ሀገሮቻችን በስፋት ሩዝ ተመጋቢዎች መሆናቸው፣ ምርቱን በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት የገበያ ዕድል ይፈጥራል። ከዚህም ባለፈ ሩዝ ዓለም ላይ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ተብለው በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡ ሦስት ሰብሎች (ስንዴ፣ ሩዝ እና በቆሎ) አንዱ መሆኑ በራሱ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለሰብሉ በስፋት መመረት ሊያበረክት ከሚችለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆን የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *