አንድ ሀገር ታላቅ ከሚያስብሏት ጉዳዮች መካከል የመከላከያ እና ደህንነት አቅሟና አቋሟ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይጠቀሳሉ። ምክንያቱም ሀገራት በኢኮኖሚ ቢፈረጥሙ፣ በሥልጣኔ ቢቀድሙ፣ በቴክኖሎጂ ቢራቀቁም ቅሉ፤ ይሄን የሚመጥን የመከላከያና ደህንነት መዋቅርና ኃይል መገንባት ካልቻሉ ጎድለው መገኘታቸው እሙን ነው።
ዛሬ ላይ ኃያላን የሚባሉት ሀገራት እንደ ሀገር ለመከበርና ለመፈራታቸው፤ ለመደመጥና ተጽዕኖ ለማሳደራቸው ዐብዩ ጉዳይ የመከላከያና ደህንነት አቅምና አቋማቸው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለዚህም ነው ሀገራት በኢኮኖሚና ቴክኖሎጂው ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ አቅም ግንባታው ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፤ በዚሁም እንዲፎካከሩና ትከሻ እንዲለካኩ እየሆኑ ያለው።
ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው የመከላከያና ደህንነት ተቋም ግንባታ ባለቤት ከመሆኗም በላይ፤ ይኸው ኃይሏ በተለያዩ ጊዜያት ለተጋረጡባት የሕልውና አደጋዎች ምላሽ እየሰጠ በክብር ለመዝለቅ አስችሏታል። በመከላከያ እና ደህንነት አቅሟ ታግዛም ለልማትና ዕድገቷ እንድትተጋ ዕድል ፈጥሮላታል።
በተለይ ከውጭ ወራሪዎች፣ ከውስጥ ጸረ ሰላም ኃይሎች የሚሰነዘርባትን የግዛትና ሉዓላዊነት አደጋ በልኩ መልክ በማስያዝ ከትናንት እስከዛሬ ያራመዳት ይሄ የመከላከያ ኃይል፤ ከጊዜው እና ሁኔታው ጋር ራሱን እያላመደና እያደራጀ ስለመሄዱ መመልከት ተችሏል። በተለይ ደግሞ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማት ላይ የተሠራው የሪፎርም ሥራ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዛሬ ላይ ለመገኘቷ ጉልህ አበርክቶ ነበረው።
ምክንያቱም ዘመኑን የመጠነና በቴክኖሎጂ የታገዘ፤ ቴክኖሎጂን መታጠቅ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል አቅምም ዕውቀትም ያለው ኃይል መፍጠር፤ ሀገሩን የሚወድድ፣ ለሕዝቡም ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ከፍ ያለ የጀግንነት ልዕልናን የተጎናጸፈ ሠራዊትን መገንባት ተችሏል።
ዓለማዊ ሁኔታውን ማዕከል በማድረግም የእግረኛ፣ የሜካናይዝድና በአየር ኃይል ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን ተቋማዊ አቅም፤ እግረኛውን በቴክኖሎጂ የማገዝ፣ ሜካናይዝዱን በሚሳይል ምድብ በማፈርጠም፣ አየር ኃይሉን በድሮን ቴክኖሎጂ በማሳለጥ እንዲሁም የባህር ኃይል ጭምር በማደራጀት ከፍ ወዳለ አቋም ማሸጋገር ተችሏል። ከዚህ በተጓዳኝ ሊሰነዘር የሚችል የሳይበር ጥቃትን መመከት የሚያስችል የሳይበር ቴክኖሎጂ ምህዳሩን ወደ መከላከያና በደህንነት ተቋማት ማስገባትም ተችሏል።
የእነዚህ ሁሉ ተግባራት ድምር ውጤት ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በከፍታዋ ላይ ማቆየት ነው። ምክንያቱም አቅሙ የተገነባ ኃይል፣ ጠንካራ አቋም የፈጠረ ተቋም በጠላቶቹ ዘንድ ቆም ብሎ ማሰብን ይፈጥራል።
ይሄ ሲሆን በቀላሉ በየትኛውም ኃይል የሚሰነዘር ጥቃት እንዳይኖር የሚያደርግ ስለሆነ ውጊያን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ልዕልናን ያጎናጽፈዋል። ይሄን ያልተገነዘበ እና በእብሪት ወደ ውጊያ ልግባ የሚል አካል ቢኖር ደግሞ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው በአጭር ጊዜ ውጊያን መጨረስ ይችላል።
ከለውጥ ማግስት የተገነባውና እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ የመከላከያ እና ደህንነት ኃይልም እነዚህን ሁለት ነገሮች እንዲያሟላ ታስቦ ነው። በዚህ መልኩ በርካታ የመከላከያ ኃይልን ማፍራት፤ የተቋማትንም አቅም መገንባት ተችሏል።
ከሰሞኑም የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በ41ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ዞብል ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶዎችና ልዩ የፀረ ሽብር ኃይል አባላትን ባስመረቀበት ወቅት የታየውም፤ የተሰማውም ይኸው ነው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ ያስተላለፉት መልዕክትም ይሄንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ «…የኢትዮጵያ ትልቁ ኤሊት ኃይል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘቴ ክብር ይሰማኛል። ይህ ኃይል ሁለት ዓላማዎች አሉት:- 1ኛ. ውጊያ ማስቀረት ነው። 2ኛው ገፍቶ ከመጣ ደግሞ ውጊያን የመጨረስ ተልዕኮ ያለው ነው፤» ነበር ያሉት።
አያይዘውም፣ «እንዲህ ያለው ኃይል ይህቺን ትልቅ ሀገር አጽንቶ ለትውልድ ያሻግራል፤» ነበር ያሉት። ይሄም አንድ ሀገር የምትገነባው ጠንካራ እና ወቅቱን የዋጀ አቅም የፈጠረ የመከላከያ እና የደህንነት ተቋምና ኃይል ሀገርን በልዕልናዋ ሰገነት ላይ የማኖር ብርቱ አቅም እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው።
ይሄን ዓይነቱ አቅምም፣ አቋምም ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የቆየ ማንነቱ መገለጫ ነው። ቀድሞም ጠላት ደጋግሞ እንዲያስብ አድርጓል፤ በትዕቢት ቃታ የሳበበትንም ክንዱን አሳይቶ እና የጠላትን አንገት አስደፍቶ ድሉን አጣጥሟል። ይሄንን ደግሞ በራሱ ምድር ብቻ ሳይሆን በዓለምአቀፍ ተልዕኮዎቹ ላይ ለዓለም ሕዝብ መግለጥ ችሎ ምስጋናና ምስክርነት ተችሮታል።
አሁንም ከዘመኑ ጋር እየተራመደ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የደህንነት ተቋማት ይሄንኑ ተልዕኳቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። አቅማቸውን ያስተዋለ ሰይፉን ወደ አፎቱ ሲመልስ፤ በእብሪት እንቢኝ ያለ ክንዳቸውን እንዲያውቅ እያስገደዱት ይገኛሉ። ይሄን መሰል አቅም እና አቋም ደግሞ እንዲሁ የሚመጣ አይደለም፤ ከሥልጠናና በቴክኖሎጂ በመታገዝ በዋናነት ደግሞ ሕዝባዊነትን በመላበስ የሚገኝ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደግሞ ውጊያን የማስቀረትም፣ የመጨረስም ተልዕኮው ዋነኛ ማጠንጠኛው ሕዝባዊነቱ መሆኑን መገንዘብ እና ለዚህ ሕዝባዊ ሠራዊት የሚገባውን ክብር መስጠት፤ ይሄን ማድረግ ደግሞ ዋጋው ለሀገርም ለራስም መሆኑን መገንዘብ የተገባ ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 ቀን 2015 ዓ.ም