በንፁሓን አሰቃቂ ግድያ ሕዝቦችን ለማጋጨትና ሀገር ለማፍረስ የሚደረግ ሴራ መቼም አይሳካም !

የሰው ልጅ ማሰብ የሚችል ከፍ ያለ የሞራል እሴቶች ያሉት ፍጡር ነው። ይህ ፍጥረታዊ ማንነቱ ከሁሉም በላይ ሠላማዊ የሆነ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲመራ፤ ከዚያም ባለፈ የተፈጥሮ አካባቢውን እየገራ ሕልውናውን እንዲያስቀጥል የሚያስችል ከፍ ያለ አቅም ባለቤት አድርጎታል።

ይህ የማሰብ አቅሙ በየዘመኑ እያደገ፤ አሁን ያለበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ አድርሶታል። በቀጣይም መድረስ ለሚፈልገው የእድገት ደረጃ፤ በተለይም ሠላማዊ እና ለሰው ልጆች በሙሉ የተመቸች ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ስኬት ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ እድገት ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።

ይህ አስተሳሰባዊ እድገቱ በየዘመኑ ዘመኑን በሚዋጁ የሞራል እሴቶች እየተገራ የሰው ልጅ ቁሳዊ ፍላጎቶቹን ከመንፈሳዊ ስብዕናው ጋር አስተሳስሮ እስከዛሬ ቀን ድረስ አንጻራዊ በሆነ ሠላም እና መረጋጋት ውስጥ ማለፍ፤ ግላዊ ፍላጎቱን ከማኅበረሰባዊ ፍላጎቶች ጋር አስታርቆ መኖር ችሏል።

ይህም ሆኖ ግን በሰው ልጅ ረጅም ታሪክ ውስጥ ከዚህ እውነታ ያፈነገጡ፤ የሰውን ልጅ ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ፤ እስከዛሬም ጠባሳቸው ያላገገመ የጥፋት እና የእልቂት ታሪኮች ተስተናግደዋል። ብዙ ለሰሚ እና ለተመልካች የሚዘገንኑ፤ ከሰብዓዊ ፍጡር የማይጠበቁ፤ ሰብዓዊነትን ያሳነሱ እና ትርጉሙን ያቀለሉ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

ጽንፍ የወጡ አስተሳሰቦች እና አክራሪ አመለካከቶች፤ የተዛቡ እና የተሳሳቱ ትርክቶች፣ ራስ ወዳድነት እና ልበ ደንዳናነት የፈጠሯቸው እነዚህ በሰው ልጆች ታሪክ አስከፊ የሆኑ ክስተቶች፤ በርግጥም የሰው ልጅ ያልተገራ ስብዕና ከፍተኛ ለሆነ ሰብዓዊ ጥፋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተጨባጭ ማሣያ ሆነዋል።

በእኛም ሀገር አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ጽንፍ የወጡ አስተሳሰቦች እና አክራሪ አመለካከቶች፤ የተዛቡ እና የተሳሳቱ ትርክቶች፣ ራስ ወዳድነት እና ልበ ደንዳናነት የፈጠሯቸው ችግሮች ሀገር እና ሕዝብን ቀደም ባሉት ዘመናት ባልታየ እና ባልተሰማ መልኩ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉ ነው።

በተለይም በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱት በፍጥረታቸው እና በድርጊታቸው አንድ የሆኑት ጽንፈኛው ፋኖ እና አሸባሪው ሸኔ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ንፁሐንን በአሰቃቂ ሁኔታ አሰቃይቶ በመግደል፤ ይህንኑ እንደ ጀብዱ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መልቀቅን እንደ ዋነኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ይህ ፍጹም እንስሳዊ የሆነ፤ እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ እና ማኅበረሰባዊ እሴቶች ባዕድ የሆነ፤ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ እና በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ የሚደረግ ወንጀል ሕዝባችንን ለብዙ የልብ ስብራት እየዳረገው ነው። በገዛ ልጆቹ የአውሬ ተግባር እንዲሳቀቅ እና አንገቱን እንዲደፋ እያደረገው ነው።

ትናንት አሸባሪው ሸኔ ንፁሐንን በአደባባይ በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲለቅ ዓላማው ግልጽ ነበር፤ የአማራን ሕዝብ ለእሱ እንስሳዊ ተግባር ለበቀል ለማነሳሳት፤ ይህ እኩይ ዓላማው በአማራ ሕዝብ አስተዋይነት ባይሳካለትም የዚህ የጥፋት ተልዕኮው ሰለባ የሆኑ ዜጎች ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።

ዛሬም የሸኔ ሌላኛው መልክ የሆነው ጽንፈኛው ፋኖ ሰሞኑን የፈጸመው አሰቃቂ ግድያ እና ግድያውን በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን የማሰራጨቱ እውነታ፤ ከሸኔ የተዋሰው፤ የኦሮሞን ሕዝብ ለእርሱ እንስሳዊ ተግባር በማነሳሳት ሁለቱን ሕዝቦች ግጭት ውስጥ በመክተት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ነው። ይህ ደግሞ ከኦሮሞ ሕዝብ አስተዋይነት የተነሳ መቼም ቢሆን የሚሳካ አይደለም ።

በርግጥ ጽንፈኛው ፋኖ እታገልለታለሁ ከሚለው የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ፣ መንፈሳዊ እሴቶች ባፈነገጠ መንገድ፣ ቀሳውስት እና የሀገር ሽማግሌዎች ሳይቀር በማዋረድ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፤ ለማንም የማይመለስ ሰብዓዊነት የሌለው የአውሬዎች ስብስብ መሆኑን በአደባባይ በተጨባጭ አሳይቷል።

በእርግጥ ላለፉት አምስት ሆነ ከዚያም በፊት በነበሩ ዓመታት የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን በማጋጨት ሀገርን ወደ ጥፋት ለመውሰድ በውጪ ኃይሎች፤ በተለይም በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተጠኑ የጥፋት ተልዕኮዎች ተግባራዊ ሆነዋል። በሀገር ውስጥ ያሉ ተላላኪ ኃይሎችም እነዚህን ተልዕኮዎች በባንዳነት ተሸክመው ሲያስፈጽሙ ተስተውሏል።

በተለይም ጽንፈኛው ፋኖ እና አሸባሪው ሸኔ ይህንን የጠላቶቻችንን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ በባንዳነት በማስፈጸም በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከእያንዳንዱ የጥፋት ተግባራቸው በስተጀርባም ያለው እውነታ ሁለቱን ሕዝቦች በማጋጨት ሀገርን ማፍረስ እና ዜጎችን ሀገር አልባ ማድረግ ነው። የጭካኔያቸው ደረጃም የቱን ያህል ለባንዳነት የተሰጡ መሆናቸውን አመላካች ነው።

ሁለቱ ሕዝቦች ከፍ ያሉ አብረው መኖር የሚያስችላቸው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ሞራላዊ እሴቶች ያላቸው ናቸው፤ በዘመናት ተጋብተው እና ተዋልደው በብዙ መንገድ መዋሓዳቸው፤ ማኅበራዊ መስተጋብራቸው በተዛቡ እና በተሳሳቱ ትርክቶች እንዳይበጠስ አድርጎታል። የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚጋሩ መሆናቸው ደግሞ የበለጠ እንዲቀራረቡ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የጽንፈኞች ከንቱ ሙከራ መቼም እንደማይሳካ ልብ ያለው ሁሉ ሊያስተውለው ይገባል!

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You