የአዲስ አበባ ከተማ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት በመዲናዋ የሚያከናውናቸው ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች ለመዲናዋ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ናቸው። መልካም ገጽታን ከመገንባት አኳያም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል። ጽህፈት ቤቱ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራትም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት አብቅቷል። በሂደት ላይ ያሉትንም በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ጽህፈት ቤቱ ለአገልግሎት ባበቃቸው ሥራዎቹ፣ በሂደት ላይም ያሉትን ጨምሮ በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ አዲስ ዘመን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ምሬሳ ልኪሳ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጽህፈት ቤቱ እየተከናወኑ ያሉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ምንን ያካተቱ ናቸው?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚባለው የግንባታ የገንዘብ ወጪ መጠናቸው ከአንድ ቢሊየን ብር የሆኑ ናቸው፡፡ የገንዘብ መጠኑ ከፍ ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ግንባታንም እንዲያከናውን ጽህፈት ቤቱ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በመሆኑም የግንባታ ሥራው በአንድ የግንባታ ዘርፍ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ለአብነትም የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት፣ መስቀል አደባባይ፣ የገበያ ማዕከላት፣ የሕክምና ተቋማት የኢንዱስትሪ ክላስተሮች ይጠቀሳሉ፡፡ በደንብ ቁጥር 110/2012 የተቋቋመው ይህ ጽህፈት ቤት ለከተማ አስተዳደሩ የመልካም አስተዳደር ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉትን ፕሮጀክቶች በማስጠናት ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ወደ ትግበራ እንዲገባ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጽህፈት ቤቱን ሥራ ከፍ እንዲል ያደረገው የውል መጠናቸው አንድ ቢሊየን ብር በላይ ያላቸውን የግንባታ ሥራዎች በማከናወኑ ነው ወይንስ ሌላ መገለጫዎች አሉት?
ኢንጂነር ምሬሳ፡– የብሩ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የፕሮጀክት ክትትል ላይ የነበሩ ግድፈቶች በከተማ አስተዳደሩ ጥናት ተደርጎባቸዋል። ለዚህ የሚሆን መፍትሔ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ተወያይቶበታል። ካብኔው ፕሮጀክቶች በልዩ ክትትልና ቴክኖሎጂ፣ በተቀመጠላቸው ገንዘብ፣ ጥራት እና ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የተቋቋመው ለዚህ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጽህፈት ቤቱ ዋና ተልእኮና ተግባርስ ምንድነው?
ኢንጂነር ምሬሳ፡– ጽህፈት ቤቱ በደንብ ቁጥር 110/2012 ኃላፊነቱና ተግባሩ በዝርዝር ተቀምጧል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የሚገነቡት ፕሮጀክቶች በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በሀገር ደረጃ ብሎም በዓለም አቀፍ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጡ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተቋቋመው ከዚህ ቀደም በፕሮጀክት አፈጻጸሞች ላይ የሚስተዋሉ ግድፈቶችን እንዲቀርፍ ታስቦ ጭምር ነው፡፡ ይህን ዓላማ ለማሳካት ደግሞ በተቀመጠለት ወይንም በተመደበለት በጀት ማሳካት ይጠበቅበታል፡፡ ከበጀቱ ማለፍ የለበትም፡፡
የግንባታው ጊዜም የተራዘመ መሆን የለበትም፡፡ ጥራቱም መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የግንባታው ቴክኖሎጂ የሚጠይቀውንም መጠቀም ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ወደ 22ኛው ክፍለ ዘመን መሸጋገሪያ ላይ እንገኛለን፡፡በመሆኑም አሁን ላይ ጥረት የሚደረገው ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የውሉ ከነበሩ ቴክኖሎጂዎች አሁን ላይ የተሻሻለውን ጥቅም ላይ ለማዋል ነው፡፡ ጽህፈት ቤቱ የተቋቋመው ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን በተለመደው አሰራር ፕሮጀክቶች የጊዜ ገደብ አላቸው፡፡ሥራቸውን ሲያጠናቅቁ ሥራቸውም አብሮ ይቆማል፡፡ ጽህፈት ቤቱን ከዚህ ለየት የሚያደርገው ምንድነው? አያይዘውም ፕሮጀክቱ ከከተማ አስተዳደሩ ውጭ የገንዘብ ድጋፍ ካለው ይግለጹልን፡፡
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ጽህፈት ቤቱ ወደ ሥራ የገባው እንደተቋቋመ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የግንባታ ሥራዎችን አጠናቅቆ ለተጠቃሚው እንዲውል አድርጓል። አሁንም ለምረቃ ያዘጋጃቸው የተጠናቀቁ ሥራዎች አሉ፡፡ ያልተጠናቀቁና በእቅድ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ አንድ ከተማ ማደግ ካለበት፤ ማሟላት ያለበት መስፈርት አለ፡፡ እነዚህን መስፈርቶች በማሟላት ረገድ ደግሞ ጽህፈትቤቱ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
በመሆኑም በከተማ መስፈርት መሠረት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እስካሉ ድረስ ጽህፈት ቤቱ ይቀጥላል፡፡ፕሮጀክቶቹም በባህሪያቸው ተከታታይነት አላቸው፡፡ የግንባታ ፍላጎቱም ከፍተኛ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩም ሆነ በህብረተሰቡ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ከተማውን ገንብተን ውብ ከተማ አድርገን፣በአጠቃላይ ለከተማው የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከተሟላ በኋላ ነው ስለ ጽህፈት ቤቱ ጉዳይ መነጋገር የሚቻለው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የጊዜ ገደብ አልተቀመጠለትም፡፡
በጽህፈት ቤቱ በተያዘው እቅድ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ 20 ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ ነው፡፡ነገር ግን ጽህፈት ቤቱ ከቅዱ ቀድሞ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ከእቅዱ በላይ የግንባታ ሥራውን አጠናቅቆ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ ይሄ የሚያሳየው የፕሮጀክት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡
አንድ ወቅት ላይ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት(ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ እሱም ቢሆን አልቀጠለም። ከዚህ ውጭ የገንዘብ ድጋፍን በተመለከተ ጽህፈት ቤቱ ከየትኛውም አካል የገንዘብ ድጋፍ አይደረግለትም። ከተማ አስተዳደሩ በበጀተለት በጀት ነው ሥራውን እየሰራ የሚገኘው፡፡ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ሲቋቋም ሁለትና ሶስት ዓላማዎች አሉት። አንዱ በከተማ አስተዳደሩ የሚፈለጉ የመልካም አስተዳደር ፕሮጀክቶች የእርካታ ደረጃ ከፍ እስከ ማድረግ ደረጃ ባለው ይገለጻል። አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ እንደመሆኗ ከተማዋን የሚመጥን የግንባታ ሥራ ማከናወን ሌላው ተልእኮ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቶቹ በውል በእቅድ እንደሚከናወኑ ይታወቃል፡፡ ለእቅዱ ደግሞ የሚያዝዝ የገንዘብ መጠን አለ፡፡ ምን ያህል እንደሆነ ሊገልጹልን ይችላሉ?
ኢንጂነር ምሬሳ፡– ፕሮጀክቶቹ ውለታቸው ሲታሰር የዋጋ መጠናቸውም ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ከበቁት አንዱ የሆነው የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ የፈጀው ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ደግሞ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች ሲቀረጹና ውል ሲታሰር የበጀታቸው መጠን እና ተገንብተው የሚጠናቀቁበት ጊዜ በቅድመ ግንባታ ወቅት የሚታወቅ ሲሆን፣ ወደሥራ የሚገባው በከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስና በጀት ክፍል በጀታቸው ጸድቆ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ባለው የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ለውጭ ሀገር ባለሙያዎች ነው የሚሰጠው፡፡ የግንባታ ጽህፈት ቤቱ በሥራው ላይ ያሰማራቸው ሙያተኞች ሀገር በቀል ናቸው? ወይንስ ከውጭ የመጡ?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ባለሙያዎችንን በተመለከተ የሚታየው በሶስት መንገዶች ነው፡፡ አንዱ የግንባታ ሥራውን በባለቤትነት በመምራት እያሰራ ባለው የግንባታ ጽህፈት ቤት ውስጥ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛ የግንባታ ሥራውን የሚያማክሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ በሥራ ተቋራጭ ሙያ ላይ የሚገኙ ናቸው። በዚሁ መሠረትም በግንባታ ጽህፈት ቤት ውስጥ የሚሰሩትና የግንባታ ሥራውን የሚያማክሩት መቶ በመቶ ሀገር በቀል ባለሙያዎች ናቸው፡፡
የሥራ ተቋራጭ ሆነው የሚሰሩ ባለሙያዎች ላይ ግን በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ላይ የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ አብዛኛው ፕሮጀክቶች ላይ የሚገኙት ሀገር በቀል ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለአብነትም ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቃው መስቀል አደባባይና በግንባታ ላይ የሚገኘው ዓድዋ ዜሮ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ ከ90 በመቶ በላይ የተሳተፉት የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የውጭ ተቋራጭ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ የጉልበት ሥራውን እንዲሰሩ የተደረጉት ደግሞ መቶ በመቶ የሀገር ውስጥ ዜጎች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ዞር እንደረጋለን ከሚለው ቅሬታ በተጨማሪ ሀገራዊ እሴቶችን የማያውቁ የውጭ ኩባንያዎች ስለመኖራቸውም የሚያነሱ አሉ። ለአብነትም የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የማዘጋጃ ቤት እድሳት ላይ የታሪካዊ እሴቱን ገጽታ ላይ ጥንቃቄ እንዳልተደረገ ይነሳልና በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ኢንጂነር ምሬሳ፡– የማዘጋጃ ቤት እድሳት ላይ ለተነሳው ሀሳብ፤ ሥራው ሲሰራ የተደረገው ባህላዊና ታሪካዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ነው። ሥራው በዚህ መልኩ እንዲከናወንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆኖ እንዲሰራ ተደርጓል። ዩኒቨርሲቲው የታሪክ፣ የባህል፣ የአርትና የተለያየ ስብጥር የትምህርት ክፍሎች ያሉት በመሆኑ ነው እንዲሳተፍ የተደረገው፡፡ ሥራው የተሰጠው የውጭ ኩባንያ የግንባታ ጽህፈት ቤቱ የሚፈለገውን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተሰጠውን ሥራ እንዲሰራ ሲያደርግ፣ዩኒቨርሲቲው ደግሞ በሚያማክረው መሠረት እንዲያከናውን ተደርጓል። ኩባንያው የመጨመርም የመቀነስም ሚና አልነበረውም። በተለይ ደግሞ አሰሪው ባለቤት የሚያስፈልገውን ነገር በቅድሚያም ስለሚያሳውቅ ችግሮች ተፈጥረዋል ወይንም ይፈጠራሉ የሚባለውን ስጋት
በዚህ መንገድ ለመቅረፍ ጥረት በመደረጉ መቶ በመቶ በሚፈለገው ነው የተሰራው።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ኩባንያዎቹ የሀገር ውስጥ ባለሙያውን የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በሚያስፈልገው ልክ እያሳተፉ እንዳልሆነ የሚነሳውን ቅሬታ እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ይህን ያህል የተጋነነ ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ አንድ ሁለት የውጭ ኩባንያ ያን ያህል ለውጥ አምጥተዋል ማለት አይቻልም። በተወሰነ ደረጃ ከነርሱ የሚገኝ ልምድና ተሞክሮ አለ፡፡ ያንን ተጠቅሞ ወደተግባር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያ እይታው ላይ የውጭ ኩባንያዎቹ ቢሆኑም አብዛኛው ሥራ የሚሰራው በሀገር በቀል ባለሙያዎች ነው፡፡
በአብርሆት ቤተመጻሕፍትም ሆነ በዓድዋ ዜሮ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ግንበኛ፣ አናጺና በሌሎች ዘርፎችም ከውጭ አይመጣም። ስለቴክኖሎጂ ሽግግር ግንዛቤ መያዝ ያለበት አንደኛ የሚገኘው እውቀት ምንድን ነው የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፡፡ በከፍተኛ ባለሙያው በኩል በቢሮ ላይ በንባብና በተለያየ መንገድ የሚያልቅ ሥራ አለ። ሥራው በሚከናወንበት ቦታ የሚሰማሩ የቀን ሠራተኞችና ባለሙያዎች አሉ፡፡
በዚህ ፕሮጀክት የተገኙ ልምዶችና የተወሰዱ ትምህርቶች የቴክኖሎጂ ሽግግር ከመገኘቱ በተጨማሪ ሥራን በአግባቡ ካለመወጣት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በማስቀረትና የተሻለ የሥራ ባህልን በማዳበር ከፍተኛ ትምህርት ሰጥቷል፡፡ በጥራት የመገንባትና በወቅቱ
የመፈጸምን አቅም ጭምር ገንብተንበታል። በተለይ የሥራ ባህልን ከማዳበር አንጻር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ሥራ እየተሰራ ያለው ሰባት ቀናት፤ 24 ሰዓት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በነበሩ ተሞክሮዎች ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች ከውጭ በግዥ የሚመጡ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በሀገር አቅም መጠቀም፣ ወጪን መቀነስ የሚሉ አስተሳሰቦች ስላሉ የጽህፈት ቤቱ የግብዓት አጠቃቀም ሁኔታ ምን ይመስላል? የግብዓት አጠቃቀም ላይ ባለሙያው ከሚሰጠው ምክረ ሀሳብ የአስገንቢው ምርጫ የሚቀድምበት ሁኔታ እንዳለ ይነገራልና በዚህ ሀሳብ ላይስ ምን ይላሉ?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- የግንባታ ሥራ ዓለም አቀፋዊ ነው። በመሆኑም ዓለም አቀፉ አሰራር በሚያዘው መሠረት ነው እኛም የምንሰራው፡፡ ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶችንም የምንጠቀመው እንዲሁ በሀገር ውስጥ የሚገኘውን ከሀገር ውስጥ ሲሆን፣ ከውጭ የሚያስፈልግ ከሆነም በመግዛት ነው። ለምሳሌ ጠጠር፣አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ብረትም እንዲሁ የተወሰነ ካልሆነ በስተቀር ከሀገር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከውጭ የምናስመጣው የኤሌክትሮሜካኒካል ግብዓትን ነው። ይህም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ከሀገር ውስጥ የምንጠቀምበት ሁኔታ አለ፡፡ አሳንሰር ቀደም ሲል ዳን የተባለ ኩባንያ በሀገር ውስጥ ያቀርብ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን አቅርቦቱ ባለመኖሩ የምናስመጣው ከውጭ ነው። እንዲህ የግድ የሆኑ ነገሮች ያጋጥማሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጽህፈት ቤቱ ፕሮጀክቶችን በእቅዱ መሠረት እየፈጸመ ነው ማለት ይቻላል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- አዎ! ባደረግነው ግምገማ አፈጻጸሙ እንደሚያሳየው ከ90 በመቶ በላይ በእቅዱ መሠረት እየተፈጸመ ነው፡፡ የታላቁ ቤተመንግሥት የመኪና ማቆሚያ(ፓርኪንግ) እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ህንፃ (የህንፃ ኮምፕሌክስ)፣ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት፣ መስቀል አደባባይ እንዲሁም በድፍረት የተገባባቸው በኮልፌና አያት አካባቢዎች የተከናወኑት የገበያ ማዕከላት ግንባታዎች፣ በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ክላስተር ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም የኢንዱስትሪ ክላስተሩ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው ከእቅድ በላይ ነው የተፈጸመው፡፡ 35 ክላስተሮች ለመገንባት ታቅዶ 45 በመፈጸም ከእቅድ በላይ ተከናውኗል። ሁለተኛው ክፍል 20 ክላስተሮች ለመገንባት ታቅዶ 18 ነው የተፈጸመው። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤትም የግንባታ ጽህፈት ቤቱን አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት መልካም አፈጻጸም መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይህን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው ለሥራው ጊዜ በመስጠት፣ ጥራት ላይም እንዲሁ ትኩረት በማድረግ እና ቁርጠኛ በመሆን ነው፡፡ ይህ ትልቅ እምርታ ነው። አቅደን መፈጸም እንችላለን የሚል አስተሳሰብ ያመጣ ፕሮጀክት ነው። ሌላው መዘንጋት የሌለበት ዝናብ በግንባታ ሥራ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ነው፡፡የግንባታ እቃና የሲሚንቶ ዋጋ መናር ተጨማሪ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ይህንን በሚያካክስ ወይንም ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተስርቶ ውጤት ተመዝግቧል ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለግንባታ ሥራ መጓተት የግብዓት አቅርቦትና ዋጋ መናር እንደ አንድ ምክንያት ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ዘርፉ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር በመተግበር ረገድ ጽህፈት ቤቱ ምን ያህል ተወጥቷል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡– ጽህፈት ቤቱም ሲቋቋም ወደ ተቋም እናምጣው የሚል ነበር፡፡ ይህም ሙያዊ ሥነ ምግባርን ለመጠበቅ እንዲያግዝ ነው። በጽህፈት ቤታችን በኩል ተገቢው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ እስካሁን የሥነ ምግባር ችግር አላጋጠምንም፡፡ ፕሮጀክት ከእቅድ በላይ እየበዛ በመሆኑ ካሉን ባለሙያዎች ጋር አለመጣጣም ሁኔታን ነው ልናነሳ የምንችለው፡፡ አሁን ባለው አሰራር አንድ ሰው ለአንድ ፕሮጀክት ነው የሚመደበው፡፡ ለችግሮች መፍትሔ የመስጠት ልምምዶችም እያደረግን ስለሆነ በተቻለ መጠን ክፍተቶችን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን፡፡
ከዚህ ቀደም በዘርፉ ይነገሩ የነበሩ ክፍተቶች ጽህፈት ቤቱ ትምህርት የወሰደባቸው በመሆኑ ተጠቅሞበታል። በግንባታ ዘርፉ ካለፈው ትምህርት ተወስዶ አሁን ላይ የተገኘው መልካም ተሞክሮ ተቀምሮ ለወደፊቱም መሸጋገር አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተከናወኑ ሥራዎችን የመገምገም ባህሉ ካለና ማን እንደሚገመግመው ቢገልጹልን?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ግምገማው ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ሳይሆን፣ ፕሮጀክት የሚጀምረው ከሀሳብ ስለሆነ ፍላጎቱ ምን መሆን አለበት ከሚለው የመነሻ ግምገማ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ሰነድ ተቀይሮ፣ ወደ አማካሪ ተወስዶ በሂደት የሚፈጸመው። የግንባታ ሥራው ከመጀመሩ በፊትም ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያና ተያያዥ ችግሮች እንደሌሉበት ይጣራል፡፡ ጽህፈት ቤቱ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ የሚንቀሳቀሰው ቡድኖችን በማዋቀር ነው፡፡
ሥራውን የሚገመግመው ማነው ለተባለው ግንባታውን የሚያከናውነው ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ፣ ከፍተኛ አመራሮች ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ ባለድርሻ አካላት ዘንድም እንደአስፈላጊነቱ ምክክርና ውይይት ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ ያለው ሚናስ እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ፕሮጀክቱን መረዳት ዋናው ይመስለኛል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ጥቅም ላይ ሲውሉ ለትውልድም ጭምር የሚሸጋገሩ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃም ድርሻ አላቸው፡፡ ይህን ትልቅ ርዕይ ይዞ እየተከናወነ ያለውን ፕሮጀክት ኅብረተሰቡ በወሰን ማስከበርና የተለያየ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ሲያስፈልግ ተባባሪ በመሆን ማገዝ ይኖርበታል። ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃም እንዲሁ በመንከባከብና ከተለያየ አደጋ በመከላከል በመጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ለምሳሌ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት በመናፈሻ ስፍራዎች ለቆሻሻ መጣያ የተቀመጡ እቃዎችን፣ መቀመጫ ወንበሮችን፣ ለውበት የተተከሉ ዛፎችንና አበባዎችን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ አካባቢው ለከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆኑ ለነዋሪዎችም መዝናኛ ሆነዋል፡፡ እንደውም ‹‹ቲክቶክ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ቀደም ሲል ሰው በአካባቢው ሲያልፍ ካልሆነ አረፍ ብሎ ለመጨዋወትና ዘና ለማለት ምቹ አልነበረም። ይሄ የፕሮጀክቱን አስፈላጊነት ያሳያል። እይታን የሚስብ ነገ ቅርስ ስለሆነ የነገ ትውልድም በተመሳሳይ እንዲጠቀምበት ጠብቆ ማሸጋገር ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከተማ አስተዳደሩ ከሌሎች ሀገራት አቻ ከተሞች ጋር የትብብር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ለትብብሩ የሚኖረው አስተዋጽኦ ይኖራል ?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ከንቲባዎች ፎረም አለ፡፡ የዚህ ፎረም አባላት የሆኑ ከንቲባዎች በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ ግንባታዎችን ጉብኝተዋል። ልምድ የወሰዱበት ጉብኝት ነበር፡፡ የፌዴራል ከተማ ልማቱ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር በተገኙበት ውይይትና ምክክር ተደርጓል፡፡ የልምድ ልውውጥም ተካሂዷል፡፡ ከውጭ አቻ ከተሞች ጋርም እንዲሁ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግብጽ ሀገር ሄደው ውይይትና ምክክር አድርገዋል። ወደ ሌሎች ሀገራት በመሄድም በተመሳሳይ መክረዋል። ይህ የሚያሳየው እኛ በግንባታው ዘርፍ ለዓለምም ጭምር እየሰራን እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ያበረከተው አስተዋጽኦ እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታው ሲገቡም ሆነ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁም የሥራ እድል ይፈጥራሉ። በጽህፈት ቤቱ ግምገማ ፕሮጀክት ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በግንባታው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ከ10 ሺ 540 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ፕሮጀክቱ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣትም የራሱን ሚና ተወጥቷል፡፡ ሥራን አክብሮ መሥራት፣ በወቅቱና በጊዜው ማጠናቀቅ ልምድ ተገኝቶበታል፡፡ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርም እንዲሁ ተቀስሞበታል፡፡
በዘርፉ ላይ ለተሰማራው የሚከፈለው ደመወዝና የትርፍ ጊዜ ሥራ ክፍያ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ እንዲያስገኝ በማድረግ ረገድም ከፕሮጀክቱ ጥቅሞች መካከል ይጠቀሳል። ሠራተኛው በሚያገኘው ገቢ የኑሮን ጫናም ተቋቁሞ እራሱን መምራት እንዲችል በማድረግ በኩል ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ሚናውን ተወጥቷል፡፡
ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ባይያያዝም ለአብነት የአብርሆት ቤተ መጻሕፍትን መውሰድ ይቻላል፡፡ቤተመጽሐፉ ለአገልገሎት ከበቃ በኋላ የጎበኘው ሰው ብዛት ወደ ዘጠኝ ሚሊየን አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች አሳይተዋል፡፡ ለኔ ይህ ትልቅ እምርታ ነው። አንባቢ ትውልድ የለም ለሚሉ አንዳንድ ሰዎች መልስ የሰጠ ወይንም ትችትን የቀለበሰ ነው ብዬ እገልጻለሁ፡፡ በቤተመጻሐፉ ለመጠቀም ሰልፍ እየተጠበቀ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሥራ ውስጥ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሳይሆን በውጣ ውረድ ውስጥ ነው የሚታለፈው፡፡ከዚህ አንጻር ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ያለፈበት መንገድ እንዴት ይገለጻል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- የበለጠ ትኩረት አድርጌ የምገልጸው ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ውጤታማ መሆኑን ነው፡፡ልምድ የተቀመረበት ፕሮጀክት እንደሆነ በውጤት ማሳየት ችሏል። ውጤት ለማስመዝገብ ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ተግዳሮት የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ነው፡፡ ወረርሽኙ የተከሰተው ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ እንደተቋቋመ ስለነበር ትንሽ አስደንጋጭ ሆኖ ነበር።ሰራተኞች ላይ መደናገጥና የሥነልቦና ጫና ፈጥሯል። የሥራ ኃላፊዎች ሥራው በሚከናወንበት ስፍራ በመገኘት ሠራተኛውን በማበረታታትና ሞራል በመስጠት ሥራው እንዲሰራ ሲደረግ ነበር፡፡
በጊዜ ሂደትም ጥረት የተደረገው ወረርሽኙን ወደ እድል ለመለወጥ ነው፡፡ ወረርሽኙ ንክኪን የሚከለክል በመሆኑ ሠራተኞችን በመበታተን ነው ሥራዎች ሲሰሩ የነበረው፡፡ ይሄ ደግሞ ሥራን በፍጥነት ለመጨረስ አግዟል፡፡ ተበታትነው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ሥራቸውን በፍጥነት ለመጨረስ ነበር ሲሰሩ የነበረው፡፡
ሌላው ተግዳሮት የግብዓት አቅርቦት እጥረት ነው። በተለይም ሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ነበር። አምራች ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጡን ንግድ ሚኒስቴር፣ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርጉልን በደብዳቤም በአካልም ብዙ ጥረት አድርገናል። ግብዓቱ ከተገኘ በኋላም በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን ነው ማሳካት የቻልነው፡፡ የውሃ፣ መብራት፣ ቴሌና ሌሎችም መሠረተ ልማት የሚያሟላ ተቋማት ትብብር እንዲያደርጉ ተጨማሪ ጥረት ተደርጓል፡፡ ፕሮጀክቱን ለየት የሚያደርገውም በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ይሄ የቅንጅትና የመናበብ ውጤት፣ ቀድሞ የማሰብ ውጤት ተደርጎ ይወሰዳል። ችግሮች ሲያጋጥሙ ችግሮቹ ጋር አንቆምም፡፡የምንፈልገው መፍትሔ ነው፤ ይህ ውጤታማ አድርጎናል ባይ ነኝ፡፡
በተቀሩት የፕሮጀክት ግንባታዎችም በተመሳሳይ በመቀጠል ነው የምናከናውነው፡፡ አሁንም የግብዓት አቅርቦት ዋጋ መናር ፈታኝ ነው፡፡ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑም ተቋቁሞ ለመወጣት ነው ጥረት የምናደርገው። አሁንም ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብና በተበጀተላቸው በጀት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ጥረት እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ግብ በከተማዋ ላይ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር የነዋሪዎችም ኑሮ እንዲሻሻል ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻርስ የሚሰጡን ሀሳብ ይኖር ይሆን?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ምንም እንኳን ሙያዬ በግንባታው ዘርፍ ቢሆንም ሀሳብ ለመስጠት ያህል ፕሮጀክቱ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጨማሪ የተረሳ ታሪክን ያስታወሰ ፕሮጀክት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ የዓድዋ ታሪክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ የጥቁር ሕዝቦችም ጭምር ነው፡፡ ዓለምም የሚደመምበት ታሪክ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከኢኮኖሚም በላይ የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ ከገንዘብም አንጻር ለ10ሺ540 ዜጎች የተፈጠረው የሥራ እድልም በዜጎች ኑሮ ላይ ለውጥ ያስገኘ ነው። ዜጎች ሲሻሻሉ ሀገር ናት የምትሻሻለው፡፡
በኮቪድ ወረርሽ ወቅት የቱሪዝም መዳረሻ የነበረችው ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በዚህ ረገድ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑትን የተለያዩ ተግባራት መጥቀስ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግንባታ ዘርፍ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተፈጠረው አቅም ለሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ምን ተሞክሮ ሊሆን ይችላል? ጽህፈት ቤቱ ሊሰጠው የሚችለው ተሞክሮ ይኖራል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- ከተሞች ከንቲባውን ነው የሚመስሉት። ከንቲባዎች የመቀመር ብሎም ከተማቸውን የመለወጥ አቅም አላቸው፡፡ አካባቢያቸው ላይ ያለውን ሀብት ተጠቅመው ለከተማቸው ነዋሪዎች ምቹ ከተማ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተካሂዶ በነበረው የከንቲባዎች ፎረም ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሜጋ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት እያከናወነ ያለውን ሥራ በጎበኙበት ወቅት በተደረገው ምክክርም ልምድ የሚቀምሩበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግንባታ ሥራዎች ላይ ከሚተቹት አንዱ ጥቅም ላይ በሚውሉት ግብአቶች አንዱ የሆነውን ቀለም አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያየ የግንባታ ዲዛይን መጠቀምና መዘበራረቆች መኖራቸውን ነው።ጽህፈትቤቱ በዚህ ረገድ ያስወገዳቸው ክፍተቶች ይኖሩ ይሆን?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- በዚህ በኩል በከተማ አስተዳደሩ የግንባታና ፍቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን አለ፡፡ይህንን ይከታተላል። በእኛ ፕሮጀክት ሥራ በኩል አንዱ ለሌላው ግብዓት የሆኑ፣ ውበትም የጨመረ የተናበበ ሥራ ነው እየተሰራ ያለው። ከሌላ የተቀዳ አሰራርን የተከተለ አይደለም። ሁሉም የየራሳቸው እይታና ውበት አላቸው፡፡ ለአብነትም አብርሆት ቤተ መጽሕፍትን ከወዳጅነት ቁጥር ሁለት ጋር፣ ወዳጅነት ቁጥር ሁለት ከአንድ ጋር፣ በመቀጠል ደግሞ ሳይንስ ሙዚየም፣ የቤተመንግሥት መኪና ማቆሚያ፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት፣ ዓድዋ ዜሮ ፕሮጀክት ሁሉም የተናበቡ ናቸው። እንዲህ መሥራት የተቻለውም ከመጀመሪያው በነበረው ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ ጥሩ ሀሳብ ካለ አሸናፊ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግንባታ ሥራ ላይ የአርክቴክቶች ሚናም ሊኖር ስለሚችል ጽህፈት ቤቱ እንዲህ ያሉ ሙያተኞችን አሳትፏል?
ኢንጂነር ምሬሳ፡- እንደ ሜጋ ፕሮጀክት የደረግነው ሥራችን ላይ የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲሰጡና እንዲተቹ ነው፡፡ የማዘጋጃ ቤት ህንፃ እድሳትን በተመለከተም አንድ በጣሊያን ሀገር ውስጥ የሚታተም መጽሔት ላይ ‹‹ፐርፌክትሊ ሪንውድ ሪፐብሊሽመንት ኦፍ ፕሮጀክት›› ብሎ ርዕስ ሰጥቶ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ይህም ምን ያህል ትክክለኛ ሥራ መሥራቱን አመላካች ነው፡፡ አሁን ላይ በግንባታው ዘርፍ የነበርንበት ላይ ሳይሆን ለውጥ ላይ ነው ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን፡፡
ኢንጂነር ምሬሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2015