ባንኮቻችን ድሀውን የሚመለከቱት መቼ ይሆን ?

ባንኮኒ ሰው ገንዘቡን እየረጨ፣ መጠጡን እየተጎነጨ፣ ዓለሙን እየቀጨ በምጣኔም በሉት በጤና ራሱን እያቀጨጨ የሚስተናግደበት ‹አደባባይ› ይሉታል:: በተቃራኒው ባንኮ ሰዎች ቆጥበው ሰው የሚሆኑበት እና ራሳቸውን የሚያሻሽሉበት የፋይናንስ ዘርፍ ነው:: ስለዚህም በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ አንዱ አሉታዊ ሚና ሲኖረው ሌላው ደግሞ አወንታዊ ሚና ይጫወታል ማለት ነው::

ባንኮኒዎች ለጠጪዎች የባንክ ተቃራኒ ናቸው:: ሰው ገንዘቡን የሚረጭባቸው ቤቶች እንበላቸው:: ባንኮቻችንም የሚጠበቅባቸው ገንዘብ አንቀሳቅሰው አበድረው ከድህነት ካላወጡን የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ካልጣሩ ለዜጋው ባንኮኒ ሆኑ ማለት ነው:: መደበኛ ባንኮች ለግማሽ ሚሊየን ለሆነ ዜጋ እንኳን ማበደር አልቻሉም::

የድሀውን ብር ታቅፈው የተወሰን ባለሀብት እያበደሩ ከድህነት መውጣት የማይታሰብ ነው:: መኖሪያ ቤት እንደ ቁምጣ ላጠረባት አዲስ አበባ አንድም ባንክ የድሆችን ችግር ለመቅረፍና አደራጅቶ አበድሮ ለመንቀሳቀስ ሲጥር አልታየም:: በቅርቡ እያበደረ ቤት እገነባለሁ የሚል አዲስ ባንክ መመሥረቱ የምሥራች ቢሆንም እስከ ዛሬ በነበረው ልምድ እንደ ሪል እስቴቱ ባለሀብት ተኮር እንጂ ድሆችን ችግር ለመቅረፍ ታስቦ አያውቅም:: ባንክ በሀገራችን ከተጀመረ አንድ ምዕተ ዓመት ሞላው::

የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባንክ የሚለውንም ቃል ሲፈቱት ጥሬ ገንዘብና እንደ ወርቅ ያሉ ማዕድናት ተጠብቀው የሚቀመጡበት እንደ ሳጥን ያለ ዕቃ፤ ጥሬ ገንዘብን እንደ ውለታው ወለድ እየከፈለ ወይም ያለ ወለድ የሚያስቀምጥ ወይም ለደንበኞች በወለድ የሚያበድር፤ ልዩ ልዩ ሰነዶችንና ማዕድናትን በአደራ የሚያስቀምጥ የአገልግሎት ሒሳብ እያስከፈለ የሐዋላና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ድርጅት ይሉታል::

የኢትዮጵያ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ማኅበር አመራሮች 25ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓሉን ሲያከብሩ በሰጡት መግለጫ፣ መደበኛ ባንኮች ሲሰጡ የቆዩት ብድሮች ጥቂቶችን የሚደርስ ብቻ ሳይሆን በከተሞች አካባቢ በተለይም በአዲስ አበባ ላይ የተወሰነ መሆኑን በጉዳዩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል::

በ2014 የኢትዮጵያ ባንኮች ካሏቸው ሙሉ ቅርንጫፎች 35.5 በመቶ በአዲስ አበባ ብቻ እንዳሉ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል። ከዚህም የባንኮች ቅርንጫፍ በብዛት የሚታየው ፤ በመርካቶ ነው:: በጥናቱ መሠረት የመደበኛ ባንኮች ተበዳሪዎች ቁጥር 350 ሺህ አካባቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ከአጠቃላይ ተበዳሪዎች ውስጥም ከ70 በመቶ ያላነሰውን ብድር ሲያገኙ የቆዩት 1ሺህ የሚሆኑት ብቻ ናቸው:: ይህም ባንኮች ከብድር አንፃር ያላቸው ተደራሽነት ውስን መሆኑን ያሳያል::

የብድር ሥርጭቱም አነስተኛና መካከለኛ የቢዝነስ ዘርፎችን ያገለለ ነው:: የኢትዮጵያ ባንኮች 90 በመቶ የሚሆነውን ዝቅተኛውን ኅብረተሰብ የባንክ ፍላጎት ለማሟላት ምንም ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም:: ብዙኃኑን ወይም ደሀውን ታሳቢ ያደረጉ ብድሮች ወይም አገልግሎቶች የሉም:: ሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መበደር በሚችልባት ሀገራችን፤ ለሸማቹ የአንድ ሺህ ብር የሚያበድር ባንክ የለም::

የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለአነስተኛና መካከለኛ ቢዝነሶች ከብድር አቅርቦት እና ተደራሽነት አንፃር እጅግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል:: ከባንክ ከተበዳሪዎች ቁጥር ይልቅ የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሚሊዮኖችን መድረስ መቻላቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣው መረጃ ያሳያል:: በዚህም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተበዳሪዎች ብድር መሰጠቱን ተጠቅሷል:: አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ለቆጣቢዎቻቸውና አባሎቻቸው ብድር መስጠታቸው ተደራሽነታቸው ከመደበኛ ባንኮች የተለዩ እንደሚያደርጋቸው በጉዳዩ ዙሪያ የተደረገ ጥናት ያስረዳል::

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከሚንቀሳቀሱ ከ43 በላይ ከሚሆኑት ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሌላ ገጽ 10 ጎሜ ፖለቲካ እና ወቅታዊ አዲስ ዘመን ሐሙስ ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባንኮቻችን ድሀውን የሚመለከቱት መቼ ይሆን ? የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበራትም ለተለያዩ አነስተኛ ቢዝነሶች እንዲሁም ለቤትና መኪና ለሚሆኑ ግዥዎች የሚሆን ብድር በማቅረብ የሚገለጹ ናቸው:: እነዚህ ማኅበራት ከባንክ ብድር ለማግኘት ላልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብድር በማቅረብ የራሳቸው ሚና ያላቸው ናቸው:: የመሥሪያ ቤቶች ብድርና ቁጠባ ተቋማት ደግሞ ብድርን፤ የሚሰጡት ለቁጠባ አባሎቻቸው ብቻ ነው::

ወደ ባንክ የተሸጋገሩትን ስድስቱን ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጨምሮ በሥራ ላይ የሚገኙ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የሰጡት ብድር ክምችትም ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው:: አነስተኛ የብድር አቅርቦትን ከማስፋት አንፃር ኢትዮ ቴሌኮም ቴሌ ብር መላ በሚል እየሰጠ ያለው የብድር አገልግሎት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው:: ኢትዮ ቴሌኮም አነስተኛ ብድር አቅርቦትን ከማስፋት አንፃር ከተለያዩ ባንኮች ጋር በመሆን እያቀረበ ያለው በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት የአነስተኛ ብድር አቅርቦትን በማስፋት ላይ ይገኛል::

ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን አገልግሎት በጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በቴሌ ብር መላ ከ9.8 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደር መቻሉ በምሳሌነት ይጠቅሳል:: ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የሚሰጡ የፋይናንስ አገልግሎቶች ከብድር ሌላ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎትን ያካተተ ነው:: በዚህ አገልግሎት እንደራሴ በሚል የግለሰብ ደንበኞች እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ አነስተኛ ብድር እንዲያገኙ ያስችላል::

ለአነስተኛ ነጋዴዎችና አነስተኛ ቢዝነስ ለሚጀምሩ ተገልጋዮች ደግሞ እስከ 50 ሺህ ብር መበደር ያስችላል:: ለደመወዝ መዳረሻ የሚሆንና እስከ 50 ሺህ ብር መበደር የሚችልበት አሠራርም ያለው ነው:: እነዚህ የብድሮች በሦስት፣ በስድስትና በዘጠኝ ወራት የሚመለሱ ናቸው::

ከብድር አቅርቦት ጋር ያለው እውነታ ይህንን ቢመስልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ደርበው እንዲሠሩ ፈቃድ ያገኙ ተቋማት አነስተኛ ብድሮችን ለመስጠት የሚያስችላቸውንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ይዘው እየቀረቡ ነው:: ይህም ውስን የነበረውን የአነስተኛ የተበዳሪዎች ቁጥር እያሳደገ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል:: የነፃ ገበያ ሲከፈት በመንግሥት ከነበሩት ባንኮች በተጨማሪ የግል ባንኮች ተበራክቱ::

እንደ ባንኮቹ መብዛት ለኢትዮጵያ ያመጣላት ትሩፋት ብዙም የሚነገርለት አይመስልም:: የግል ባንኮች አገልግሎት መጀመራቸው የመንግሥት ባንኮችም በተወሰነ መልኩ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ እንዲያዘምኑ እንዲፎካከሩ ግን ረድቷቸዋል:: ብዙ ዜጎችም በዘርፉ ሥራ አግኝተዋል:: ፈክማ ወይም ፈጣን የክፍያ ማሽን አገልግሎት(ኤቲኤም) የጀመረው የግል ባንኮች ከመጡ ወዲህ ነው:: ባንኮች ለተቀጣሪዎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ ከፋዮች በመሆናቸው እና ጥቅማ ጥቅምም ስለሚሰጡ፤ ተመራቂዎች ባንኮችን ለመቀጠር ይመርጧቸዋል::

የዓመት ማለቂያ ላይ ለሠራተኞቻቸው ጉርሻ (ቦነስ) መክፈል በባንኮች ዘንድ የተለመደ ነው:: ይህም አንዳንዶች በችግር ውስጥ ባለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ባንኮች እያደረጉ ያሉትን ፉክክር በዘርፉ እየተካረረ የመጣውን ውድድር አመላካች ነው ይሉታል። ባንኮቹ በየቦታው ከብዙ ባለህንፃ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቤት እየተከራዩ ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተዋል:: በአዲስ አበባ ብቻ ከሰንጋ ተራ ጀምሮ ከብሔራዊ ባንክ በታች በቸርችል ጎዳና ለገሀር አካባቢ ጭምር ጎላ ጎላ ያሉት ረጃጅም ሕንፃዎች የባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅት ዋና ዋና መሥሪያ ቤት ናቸው:: ሕንፃዎቹ ሲሠሩ ለብዙ ዜጎች የሰጡትን ጊዚያዊ የሥራ ዕድልም አስቡት:: አሁንም በቦታው ሕንፃቸውን እያሠሩ ያሉም አሉ:: ህንፃዎቹ የከተማዋ ውበትዋ ሆነዋል::

እንደስሟ እያበበችና እንድትሔድ ረድተዋል:: ባንኮቹ ትርፋማ መሆናቸውን በየዓመቱ መጨረሻ የሚያወጡት ሪፖርቶች ያመለክታሉ:: በዚህም ባለአክሲዮኖቹ ተጠቃሚዎች ናቸው:: ሆኖም አሠራራቸው በሙሉ ድሀ ተኮር አይደለም:: ባንኮቹ የብዙ ድሀ ዜጎች ገንዘብ ቆጥበው አስቀምጠው ለባለፀጋዎች (ሀብታሞች) ያበድራሉ:: ባንኮቻችን ሲያበድሩ የግል ቤት ካርታ፣ የመኪና ሊብሬ ወዘተ እንደ መያዣ (Collateral) በመጠቀም ነው:: የድሀውን ገንዘብ አስቀምጠው ለሀብታም እያበደሩ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት የሚቻል አይመስለኝም::

መሥራት እየቻለ ማስያዣ ቤት የመሳሰሉት የሚበደረው ገንዘብ በማጣት አደገኛ ቦዘኔ የሚሆነውን ወገኔ ቤት ይቁጠረው:: በሰለጠኑት ሀገሮች ጥናትና ምርምር አውጥተው፣ ፕሮፖዛል ቀርጸው ጭምር ገንዘብ ላጠረው ባንኮች ያበድራሉ:: ባንኮቹ በግሉ ፕሮፖዛሉ የቀረጸውንም አይተው አዋጪ መሆኑን ገምግመው እና መዝነው ያበድሩታል:: በክትትልም ያበደሩትን ያስመልሳሉ:: ለተበዳሪውና ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ:: ባንኮቹም ተበደሪዎቹም ሀገሪቱም ትርፋማ ይሆናሉ:: አንዳንድ ባንኮች በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያመጡ ሰዎችን መርጠው በተመረቁበት ሙያ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ፕሮፖዛል ቀርጸው አበድረው በጋራ እንዲሠሩ ያደርጋሉ::

በዚህም የሥራ ዕድል የሚከፍቱ ሲሆን፤ ያበደሩትን ገንዘብም ከሥር ከሥር ክትትል አድርገው የማስመለስ ልምድ አላቸው:: የቤት ቁሳቁስም ሆነ ልብስ ለመግዛት ከባንክ የሚበደሩ አሉ:: ቴሌቪዥን፣ ማቀዝቀዣ ብሎም መኪናም ሆነ ባለቤት (ቤት የሚገዙት) በባንክ ብድር ነው:: የብድር አመላለስ ታሪካቸው እየታየ የበለጠ እንዲበደሩ ይመቻቻል:: እናም ዜጎች ባለሀብት የሚሆኑበት መንገዱ ምቹና ክፍት ነው:: በሀገራችን ባንኮቹ ብራቸውን ታቅፈው ሲተኙ ነው የሚታየው:: 120 ሚሊዮን ዜጋ ያላት ኢትዮጵያ ባንኮቹ ሁሉ ተደምረው 1 ሚሊየን የሚጠጋም ዜጋ አላበደሩም ሲሉ ዐቢይ ዶ/ር በአንድ ወቅተ ተናግረው ነበር:: በእኛ ሀገር ባንኮች ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች ፕሮጀክት እና ፕሮፖዛል ቀርፀው ማበደርን ሥራቸው ሊያደርጉ ይገባል::

ቴሌ ብር እንኳ የጀመረው አሠራር ባንኮቹን ካሸለቡበት እንዲነቁ ያደርጋል:: ጥቅምት 21 ቀን 2017 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዚዳንቱ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግር ተንተርሰው በተወካዮች ም/ቤት አባላት ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ‹‹የፋይናንስ ዘርፉ በ2010 ያለው አጠቃላይ ሀብት 1.3 ትሪሊዮን ብር ነበር:: አሁን ባንኮች ያላቸው ሀብት 3.5 ትሪሊዮን ነው:: በሀብት ደረጃ ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ አድገዋል:: የባንኮች ቁጥር 18 ነበር አሁን 32 ደርሰዋል:: ይህ ቁጥር ምን ያህል ጠንካራ ያደርጋቸዋል የሚለው ጉዳይ ተጨማሪ ሥራ የሚፈልግ ነው:: … ከስድስት ዓመታት በፊት ቅርንጫፎች በተደራሽነት 5500 ገደማ ነበሩ፤ አሁን 13 ሺህ ደርሰዋል፤ ከሁለት እጥፍ በላይ አድገዋል:: 450 ቢሊዮን ብድር ሰጥተዋል፤ ከዚህ ውስጥ 82ፐርሰንቱ የተሰጠው ለግሉ ዘርፍ ነው:: … የባንክ ሴክተሩ እመርታ አለው :: መታረም ያለባቸውና ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮችም አሉ:: ›› ብለው ነበር:: መታረም ካለባቸው አሠራሮች አንዱ የባንኮቹ ፉክክር ሠራተኞችን በመያዝ እና ሰዎችን የባንክ ሂሳብ በማስከፈት ላይ ያተኮረ ብቻ መምሰሉ ነው:: ለዚህም በከተሞቻችን አሁን አሁን ባንክ ሂሳብ ክፈቱልን የሚሉ በየመንገዱ ሰዎችን አስቁመው የሚወተውቱና የሚማፀኑ ሰዎች ማየት ይበቃል::

በግሌ መንገድ ዘግተውብኝ ወረቀት ነገር ሲያሳዩኝ ቸኩዬ ስለነበር ትኩረት ሳልሰጣቸውና ሳልሰማቸው ‹‹እግዜር ይስጥልኝ!›› አልኩዋቸው:: ሰዎቹ ሳቁብኝ ፤ ወደፊት እየሄድኩ እንዳለ የባንክ ደብተር የያዙ ሰዎች ሳይ ያለፍኩዋቸው ሰዎች አጋሮች መሆናቸውን ተረዳሁ:: የተማጸኑኝ እንድመጸውታቸው ሳይሆን የባንክ ሂሳብ እንደከፍትላቸው መሆኑን ተረዳሁ:: በየመንገዱ የባንክ ሂሳብ ክፈቱ እያለ የሚማጸነው ‹ተፎካካሪ› ባንክ ስለበዛ ያው ዞሮ ዞሮ ልመና አዘል ማባበል ታክሎበታል:: የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጥ አድርጎ የያዘው ግብርና ነው ሲባል እሰማለሁ:: ሆኖም ባንኮች ለገበሬዎች በማበደር የሚጠቀስ ሥራ አልሠሩም:: ገበሬው እርሻውን ላዘምን ቢል ሊያበድረው የሚችል ባንክ የለም::

ዘመናዊ ማረሻ፣ ማጨጃ፣ እና መከስከሻ መሣሪያዎች እንዲሁም ለመስኖ የሚሆን የውሃ ማጠጫ ጄኔሬተር ሊገዛ ቢፈልግ አቅሙ አይፈቅድለትም:: አርሶ አደሮች በጋራ ተበድረው የውሃ ማጠጫ ጄኔሬተር ቢገዙ የመስኖ እርሻው ይሳለጣል፣ ድህነት ይጠፋል ፤ ኑሮ ውድነት ይወድማል :: በመስኖ የሚለሙ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ድንችና ሽንኩርት፣ ጎመንና ካሮት እያመረቱ ለከተሞች ይተርፉ ነበር:: ከብቶቻቸው በመቀለብና በማደለብ እየሸጡ ከባለሀብቶች ጎራ ይቀላቀሉ ነበር:: ባንኮችም እያተርፉ ሂሳብ ክፈቱ ብሎ ሰዎችን ከመማጸን ይተርፉ ነበር:: በቅርቡ ግን ለገበሬዎች እንዲያበድሩ መመሪያ መተላለፉን ሰምቻለሁ:: የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣው መረጃ በሀገሪቱ 109 የፋይናንስ ተቋማት እንደሚገኙ ያስረዳል:: 31 ባንኮች ሲሆኑ አምስቱ ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ደረጃ፣ አንድ የጠለፋ ዋስትና የሚሰጥ ተቋምን ጨምሮ 18 ኢንሹራንስ ድርጅቶች አሉ::

አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት 44 ናቸው:: ካፒታል ጉድስ ሊዚንግ ኩባንያ (የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ) ስድስት ናቸው:: በሰኔ ወር 2014 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የግልና የመንግሥት የባንኮቹ ቅርንጫፎች ምጥጥን በሕዝብ ብዛት አንድ ቅርንጫፍ ለ11ሺህ 516 ሰዎች ያገለግላል:: የኢትዮጵያ ባንኮች ለአስቀማጮቻቸው ከዋጋ ንረት በእጅጉ ያነሰ ወለድ በመክፈል ይተቻሉ። በአማካይ 35 በመቶ በሆነ የዋጋ ንረት ባንኮች ለአስቀማጮች 7 በመቶ ብቻ ወለድ በመክፈል ተበዳሪዎች ከዋጋ ንረት በታች ብድር እየሰጡ ባንኮቹ በጣም አትራፊ ይሆናሉ። ሰው ባንክ ገንዘብ ማስቀመጡ ለወለድ ሳይሆን ለደህንነት በማሰብ ነው:: የወለድ መጠኑን ከፍ በማድረግ ሰዎች ከወጪ ይልቅ ብር ገቢ እንዲያደርጉ ፤ በዚህም ብዙዎችን የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ ማድረግ ይቻላል::

በተጨማሪም ብር ባንክ ማስቀመጥ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠሪያ አንዱ መንገድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት እውነታ ነው:: የኮረና ወረርሽኝ በመጣ ሰሞን ፤ ዜጋው ገንዘብ እጅ በእጅ ከመቀባበል በባንክ እንዲያስተላለፍ በመንግሥት መመሪያ በመውጣቱ ብዙዎች የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ አስችሏል:: በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በአፍሪካ እጅግ ወደኋላ ከቀሩት አንዱ ነው:: ፉክክር ወይም አዲስ አሠራር የሌለውና የተዘጋ ገበያ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ፣ ለኢኮኖሚው ትልቅ ማነቆ ነው:: የፋናንስ ዘርፉ ከእንቅልፉ እንዲነቃ ሁነኛ መሣሪያው ለውጭ ባንኮች በራችንን መክፈት ነው::

ባለፈው ዓመት በተካሄደ የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ባንኮች እንደሚከፍት ተነስቶ ነበር:: ቢተገበር ሸጋ ነው:: እናም ባንኮቻችን ካሸለቡበት ይንቁ:: ዜጋውን ለሥራ ብር ያስታጥቁ፣ ያነቃቁ:: ዜጋው ቤት መሥራት፣ የቤት ቁሳቁስ እና ሌሎች ነገሮችን መግዛት ይፈልጋል:: ማቀዝቀዣ፣ ልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ቴሌቪዥን፣ ወዘተ የሚሸጡ ድርጅቶች ከባንኮችና ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጋር ተነጋግረው ሠራተኛው ዕቃ የሚገዛበትንም ያመቻቹ በማለት ጽሑፋችንን እንቋጫለን::

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You