ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በብዙ ፈተና እና ተግዳሮት ውስጥ ያለፈችና እያለፈች መሆኗ የሚታወቅ ነው፡፡ ሀገሪቱ ባጋጠማት ተፈጥሯዊ ክስተትም ሆነ የፖለቲካ ትርፍ ፈላጊ አካላት በፈጠሩትና እየፈጠሩት ባለው ቀውስ ውስጥ ሆኖም ቢሆን ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ያስመዘገባቸው ስኬቶች መኖራቸው የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ ከሰሞኑ ፓርቲው ያስገኛቸውን ስኬቶች ለመዘከር በማሰብ የተመሠረተበትን አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያካሔድ ቆይቷል፡፡ አዲስ ዘመንም ይህንኑ የፓርቲውን ክብረ በዓል አስመልክቶ ፓርቲው ባለፉት አምስት ዓመታት በኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊውና ፖለቲካው ዘርፍ ስላስመዘገባቸው ስኬቶችና ስላጋጠሙት ፈተናዎች አስመልክቶ ከብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል፡፡ እንደሚከተለውም አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የብልጽግና ፓርቲ በዚህ ወር “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል:: መርህ ሃሳቡ የያዘውን መልዕክትና የተመረጠበት ምክንያት ምንን ለማመላከት ነው?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡- የብልጽግና ፓርቲ በዚህ ወር “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያየ መርሃ ግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል:: የመሪ ሃሳቡ ዋና መልዕክት የሚያመላክተው የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ከጉልበትና ከመጠፋፋት፤ ከጦርነትና ከደም መፋሰስ መንገድ ወጥቶ ወደ ሃሳብ ልዕልና መሸጋገር አለበት ለማለት ነው::
በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የሚያስረክብና ሥልጣን የሚረከብ መሪ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ተጨባብጠው እና ተሳስመው ሥልጣን የተረካከቡበት ታሪካዊ ወቅት ስለሆነ የብልጽግና ምስረታ የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና የሚል መሪ ሃሳብ እንዲይዝ ተደርጓል::
ይህ ሃሳብ ለኢትዮጵያ የሰለጠነ የፖለቲካ ባሕል እንዲሁም ዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ መንገድ ሆኖ እንዲቀጥልም የሚፈለግ ነው:: ስለዚህም ሥልጣን የሚያዝበት መንገድ በሃሳብ ልዕልና እንዲሆን ካለን ምኞት በመነሳትም ጭምር ነው:: በርግጥም ባለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ ይህን በተግባር እያሳየ ያለፈ በመሆኑ ምክንያት በዚህ መርህ እንዲከበር እየተደረገ ነው::
ይህን ተከትሎም በዚህ ወር ከቀበሌ ጀምሮ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲያከብሩት ቆይተዋል:: ክብረ በዓሉም በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞን፣ በከተሞች እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ለምሳሌ በአባላት ውይይቶች፣ በሕዝብ ውይይቶች፣ በተለያዩ ፓናል ውይይቶች፣ በፎቶግራፍ አውደ ርዕዮች፣ በልማት ጉብኝቶች፣ በበጎ አድራጎት አገልግሎቶች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች እና በመሳሰሉት መርሃ ግብሮች በመከናወን እዚህ ደርሷል:: እስካሁንም በመከበር ላይም ይገኛል፤ በፌዴራል ደረጃም የፌዴራል ተቋማት አንድ ላይ በመሆን አክብረዋል::
አዲስ ዘመን፡- ያለፈው አምስት ዓመት መዘከር ያስፈለገበት ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡- ይህ የብልጽግና አምስተኛ ዓመት በዓል ዓላማው ባለፉት አምስት ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ ከመፈጠሩ በፊት የነበሩ አስጨናቂ ሁኔታዎች ለመዘከርና እነዚያ አስጨናቂ ሁኔታዎች ደግሞ ለብልጽግና ፓርቲ ውልደት ምክንያት መሆናቸውን በማሰብ ነው:: ከለውጡ በፊትና ከብልጽግና መፈጠር በፊት የነበሩ ፖለቲካዊ ገፊ ምክንያቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ገፊ ምክንያቶችና ማኅበራዊና ገፊ ምክንያቶች ናቸው:: ከዚህ የተነሳ አጠቃላይ ለብልጽግና ውልደት ምክንያት የሆኑና ብልጽግና ተፈጥሮ ለእነዚህ ገፊ ምክንያቶችና ስብራቶች መፍትሔ እንዲሰጥ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመዘከር ሲከበር ቆይቷል::
ብልጽግና እንዲፈጠር ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በሀገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ባለፉት ሥርዓታት በአግባቡ ባለመመለሳቸው ነው:: ከዚህ የተነሳ ኅብረ ብሔራዊ የሆነ ሀገር ለመመሥረት አልተቻለም:: ሀገረ መንግሥቱና ብሔረ መንግሥቱ የነበሩት እጅግ በጣም ፈተና ውስጥ ነው:: የዜጎች መሠረታዊ ጥያቄዎችና መብቶች የእኩልነት፣ የነፃነትና የፍትህ ጥያቄዎች ያልተመለሱበት ጊዜም ነበር:: በዚህ ምክንያት ሕዝቡ አደባባይ እስከ መውጣት ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው:: እነዚህ ፖለቲካዊ ምክንያቶቹ እነዚህ ናቸው:: በአጠቃላይ የብልጽግና ውልደት በዋናነት የእኩልነትን፣ የነፃነትን የሁሉም፣ በሁሉም ከሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያለመ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ብልጽግና ፓርቲ ከኢኮኖሚውና ከማኅበራዊው ዘርፍ አኳያ ያሳካው ምንድን ነው ይላሉ?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡– በኢኮኖሚ ዘርፍም ኢኮኖሚያችን ከብልጽግና ውልደት በፊት እጅግ በጣም ከፍተኛ ስብራት ውስጥ የነበር እንደሆነ የሚታወቅ ነው:: በዚህ ምክንያት የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል የማይችልበት ጊዜ ላይ ተደርሶ ነበር:: ሌላው ቀርቶ የሕይወት አድን መድኃኒቶችን እንኳን ገዝቶ ወደ ሀገር ማስገባት ያልተቻለበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር::
ብልጽግና የተወለደው ሀገሪቷ በእዳ ጫና የተዘፈቀችበት እና እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገባችበት ጊዜ በመሆኑ ይህን መመከት በሚያስፈልግበት ወቅት የተወለደ ነው ማለት ይቻላል:: በዚህ ረገድ ሲታይ በኢኮኖሚውም ትልቅ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው፤ ብልጽግና ኢኮኖሚውን የታደገ ፓርቲ ነው::
የእዳ ማስተካከያ እና የእዳ ሽግሽግ እንዲሁም በአንዳንዶቹ ላይ የእዳ ስረዛ በማስደረግ የሀገሪቱን የእዳ ጫና ያቀለለ ነው:: በተለይም የነበረውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ የቻሉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የተካሔዱበት ጊዜ መሆኑ የሚታወቅ ነው::
ከዚህ ቀደም ዝም ብሎ ግብርና መር ብቻ ይባል የነበረው የኢኮኖሚ እሳቤ የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ እንዲሆን ትልቅ ሥራ መሥራት ተችሏል:: ግብርናን፣ ማኑፋክቸሪንግን፣ ማዕድንን፣ ቱሪዝምን እና የዲጂታል ኢኮኖሚን አንድ ላይ በማጣመር የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሚዛናቸውን ጠብቀው እና ተደጋግፈው እንዲያድጉ ለማድረግም ችሏል:: ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀደምት ትልልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረገ የኢኮኖሚ ሪፎርም በመደረጉ ነው::
በግብርናው ዘርፍም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በስንዴ ልማት እንዲሁም በሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ አዳዲስ እሳቤዎችንም በማምጣት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ከውጭ ሀገር ማስገባትን እንድታቆም ያስቻለ ነው:: እንዲሁም አቅሟን አጠናክራ ስንዴን ወደ ውጭ ሀገር መላክ የምትችል ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየችበትና ያስመሰከረችበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: ስለዚህም በአረንጓዴ ዐሻራ እና በስንዴ ልማት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና እና ምስጋና ያገኘችበት መሆኑ የሚታወቅ ነው:: ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢኮኖሚውን ከውድቀት መታደግ እና ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚን ልዕልና ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም በተግባር የታየበት ለውጥ ነው ብሎ መናገር ይቻላል::
በማኅበራዊ ዘርፉም ሲታይ አጠቃላይ የማኅበራዊ መስተጋብሩ የተበላሸበት፣ የዜጎች የትምህርት፣ የጤና እና መሠረታዊ የሆኑ የማኅበራዊ አገልግሎቶች ችግር ውስጥ የገባበት ወቅት ነበር:: ብልጽግና እነዚህ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች ሁሉ በአንድ ላይ ተደማምረው የጎሉ በመሆናቸው ለውጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለነበር የተፈጠረ ፓርቲ ነው::
በዚህ ምክንያት ብልጽግና ከተፈጠረ ወዲህ አንደኛ በሀገራችን የትርክት ለውጥ እንዲመጣ መንገድ ከፍቷል:: ኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ነፃነታቸውን ጠብቀው በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እናታችን ናት ብለው ማመን እንዲጀምሩም ያደረጋቸው ነው ማለት ይቻላል:: ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እና አብሮነትን የሚፈጥሩ ትርክቶች እንዲጠናከሩ መገንባት ተችሏል፤ ብልጽግና ፓርቲ በባህሪው ሁሉንም ኢትዮጵያ የያዘ፣ አጋር ፓርቲ የነበሩትን በሙሉ አቅፎ ኅብረ ብሔራዊ፣ ሀገራዊና ወጥ ፓርቲ ሆኖ የተፈጠረ ነው:: ስለዚህም ፓርቲው ኢትዮጵያውያን በአንድ ጥላ ስር መሰባሰብ የቻሉበት ነው:: በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በብሔር፣ በኃይማኖት እንዲሁም በማንነት ሁኔታ ውስጥ ገብታ ዜጎቿ ይበታተናሉ ተብሎ ሲሰጋ የነበረውን ጥያቄ የመለሰና ኢትዮጵያውያንን ልክ እንደ እናትነት ያሰባሰበ ፓርቲ ነው ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲው ከዲፕሎማሲው አኳያ ያስገኘው ውጤት እንዴት ይገለጻል?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡– በዲፕሎማሲው ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ደፍራ እና አንገቷን ቀና አድርጋ ጎልታ የታየችበት ነው ማለት ይችላል፤ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በጣም በርካታ ሀገሮች የብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን በብዙ ሲጥሩና ሲፈልጉ እንደነበር ይታወሳል:: ኢትዮጵያ ግን ይህን ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠውን ስብስብ በቀዳሚነት መቀላቀል የቻለች መሆኗ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው::
በተጨማሪም በዓለም አደባባይ በድፍረት የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ማንንም ሳትለምንና ሳታስፈቅድ መጠቀም የምትችል መሆኗን ተከራክራ ያሳመነች እና የራሷን መብት ማስከበር እንደምትችል ያስመሰከረች ሀገር ሆናለች:: ያለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የራሷን መብት ማስከበር የምትችል ደፋር ዲፕሎማሲን የምትከተል እና ለዜጎቿ ክብር፣ ለሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ጥቅም ከማንም ይሁንታ ሳትጠይቅ በራሷ መቆም የምትችል ሀገር መሆኗን ያሳየችበት ወቅት ነው ብሎ መናገር ይቻላል::
በአጠቃላይ ሲታይ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው እና በዲፕሎማሲው መስኮች ባለፉት የብልጽግና ዓመታት የታዩ ለውጦች እጅግ በጣም ተስፋ ሰጪ ናቸው:: በመሆኑም እነዚህን ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን መዘከር በጣም አስፈላጊ ነው:: በመሆኑም ሰሞኑን እየተከናወኑ የሚገኙ መርሃ ግብሮች ብልጽግና በአምስት ዓመታት ውስጥ ያስገኛቸው ውጤቶችን የሚዘክሩ ናቸው:: በቀጣይም የተገኙትን ውጤቶች አስቀጥለን በሚመጡት ዓመታት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋለን የሚለውን አቅም ለመፍጠር ነው::
በተጨማሪም በዚህ ወር እስካሁን ሲከናወን የቆየው አባሎቻችን፣ አመራሮች እና ደጋፊዎቻችንን እንዲሁም መላውን ሕዝብ በሙሉ ተስፋ እና በሙሉ አንድነት እንዲሁም በሙሉ ቁርጠኝነት በጋራ እንዲሰለፍ ለማድረግ የሚያስችል የበዓል አከባበር ነው:: ከፊታችን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ሀገራዊ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ይኖራል:: የሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች እና ኃላፊዎች በሚገኙበት ከዚህ በፊት ከቀበሌ ጀምሮ ሲከበር የነበረውን የአምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል በሚያጠቃልል ደማቅ በሆነ መልኩና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል::
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲው እርስዎ የጠቀሷቸው ውጤቶች ላይ ለመድረስ አጋጥሞት ያላፋቸው ተግዳሮቶች ነበሩ? ካሉ ምን ምን ናቸው?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡- ያለፉት አምስት ዓመታት ስኬቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው:: አባላቱን፣ አመራሩን እንዲሁም ሕዝቡም በተስፋ ሰጪ ጎዳና መጓዝ የጀመርን መሆናችንን ያመላከቱ ናቸው:: የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና አይቀሬ መሆኑን ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮቿ ተፈትተው በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትኖር መሆኗን ያስመሰከረ አምስት ዓመት ነበር:: ይህን ማስቀጠል ደግሞ ያስፈልጋል::
ይሁንና እነዚህ ስኬቶች እና ድሎች የተገኙት በተመቻቸ ጎዳና በመጓዝ አለመሆኑ የሚታወቅ ነው:: ስኬቶችን ለማስመዝገብ የታለፈው በተለያዩ ችግሮችና በተግዳሮቶች ውስጥ ነው:: በመሆኑም ከዚህ በኋላ የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች መፈታት መቻል አለባቸው:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካል መረባረብ ይጠበቅበታል::
ከፖለቲካው ዘርፍ ካጋጠመው ፈተና ውስጥ አንዱ የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ያልዘመነ በመሆኑ ምክንያት ዘመናዊ እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባሕልን እና በሃሳብ ልዕልና የሚመራ የፖለቲካ ታሪክ የሌለን መሆኑ ነው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ እዚህም እዚያም ብቅ የሚሉ ከጽንፈኝነት ጋር እና ከአክራሪነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በተለያየ ቦታ የሚታዩ ችግሮች ናቸው:: እነዚህን በጋራ ተረባርቦ መቅረፍ ያስፈልጋል::
መንግሥት ሙሉ አቅሙን ይህን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል:: በርካታ ቦታዎች ላይ ደግሞ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተገኙ ይገኛል:: ስለዚህ የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ ዴሞክራሲያዊ እና የሰለጠነ እንዲሆን ይፈለጋል:: ከዚህ በኋላ በሀገራችን ውስጥ ወደኋላ ተመልሶ ቂም እና ቁርሾን የሚቆጥር አካል መኖሩ የሚያሻገር አይሆንም:: ከዚህ ይልቅ የወደፊቱን የትውልድ ተስፋ እና እድል አይቶ በጋራ መሆን የሚፈልግ ነው::
ስለሆነም መሰባሰብና ሃሳብን ሸጦ ሃሳብ በመግዛት የሚያምን የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት:: ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የገጠር ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ከሆነ ብልጽግና ፓርቲ እነዚህን አቅሞች አሰባስቦ በጋራና በትብብር መሥራት ይፈልጋል::
የሀገራችን የፖለቲካ ድባብ የሚቀየርበት፣ የሰው ልጆች መብት የሚከበርበት እና ሰላም የሰፈነበት ጊዜ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይጠበቅበታል:: የሰዎች እኩልነት፣ ነፃነት እና ፍትህ የተረጋገጠበት ሥርዓት ለመፍጠርና የተጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁላችንም መረባረብ አለብን:: በአሁኑ ሰዓት እዚህም እዚያም የሚታየው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት እና ሌሎች ከኢኮኖሚው ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል::
ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ በተለይ ደግሞ በልዩ ሁኔታ ፓርቲያችን ይህን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ለመፍታት እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እየታዩ የሚገኙት ተስፋ ሰጪ ለውጦች ናቸው:: ለአብነት ያህል በሥራ እድል ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ በጥቅሉ የሕዝቡን የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች በጣም ተስፋ ሰጪ እና አበረታች ውጤት ማሳየት ጀምረዋል:: እነዚህን ውጤቶች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል:: ምርት እና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ ሁሉም ሰው አምራች እንዲሆን፣ ሁሉም ሰው በቻለው አቅም ኢኮኖሚው ላይ እሴት እንዲጨምር፣ እንዲያምርት፣ ኢኮኖሚውን እንዲያግዝና የራሱን ዐሻራ እንዲያስቀምጥም በሚያስችል መንገድ ዜጋው መረባረብ አለበት::
የተጀመረውም የዲፕሎማሲ ጉዞ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል:: ኢትዮጵያ የምትከተለው ደፋር የዲፕሎማሲ መንገድ ነው:: መብቶቿን ጠንቅቃ ታውቃለች:: በተመሳሳይ ግዴታዎቿንም ጠንቅቃ የምታውቅ ሀገር ናት:: መብቶቿን ለማስከበር የማንንም ይሁንታ የምትጠይቅ አይደለችም:: ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በሚገባ ትጠቀማለች:: እንደ ዓለም ሀገራት አካል ደግሞ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገባትን በአግባቡ ትጠይቃለች::
ይህን በመጠየቅ የባሕር በር ይገባናል የሚል ጥያቄ፣ የብሪክስ አባል መሆን ይገባናል የሚል ጥያቄ፣ ዓባይን አልምተን ለሕዝባችን ልማት መጠቀም አለብን የሚሉት ጨምሮ በጣም ደፋር ዲፕሎማሲ ማሳያ የሆኑ ናቸው:: የዜጎቻችንን መብት እና ክብር ከፍ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች አሁንም ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል::
በዲፕሎማሲው ረገድ ይህ እንዲሳካ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሱን ሚና የሚወጣ ከሆነ የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ ነው:: ዜጎቻችን ከኢኮኖሚ ችግር ወጥተው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ተምሳሌት፣ የልማት እና የብልጽግና ተምሳሌት ይሆናሉ::
ያለፉት የአምስት ዓመታት ጉዞ የሚያሳየው ይህንን ነው:: ስለዚህ ፓርቲያችን ወገቡን ጠበቅ አድርጎ የሚሠራ ይሆናል:: ዛሬም እየተረጋገጠ ያለው ይኸው ነው:: ባለፈው ከቀበሌ ጀምሮ ሲከበር የነበረው ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ላይ አባላቱና አመራሩ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው:: በዓሉ እየተከበረ ያለውም የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታትና ኢትዮጵያን ወደ ልዕልና ለማምራት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ እንከፍላለን በሚል እሳቤ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ራስ ገዟ ሱማሌላንድ አዲስ ፕሬዚዳንት መምረጧ የሚታወቅ ነው፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ያደረገችው ከራስ ገዟ ሱማሌ ላንድ ጋር ይሁን እንጂ ፊርማቸውን ያኖሩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ናቸውና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነገር ይኖር ይሆን?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡– የፓርቲያችን የውጭ ግንኙነት እሳቤ የሚመራው በመርህ ነው:: ይኸውም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚመራ ነው:: አብሮ በማደግ መርህ የሚመራ እንጂ በጉልበት የሚመራ አይደለም:: የፓርቲያችን የአምስት ዓመት አከባበር ክብረ በዓል መርህ “የሃሳብ ልዕልና ለሁሉንተናዊ ብልጽግና” የሚል መሆኑንም እዚህ ላይ ለመጥቀስ እሻለሁ::
ስለዚህ የትኛውም ኢትዮጵያን የሚያጋጥማት ችግር የሚፈታው በሃሳብ ልዕልና ነው:: የውጭ ግንኙነት ፕሮግራማችን ለጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ ነው:: ልዩ ትኩረትም የሚሰጥ ነው:: ጎረቤቶቻችንም እጅግ በጣም ወሳኝ አጋሮቻችን ናቸው ብለን እናምናለን:: ይህንን መርህ በማድረግ የትኛውም ጎረቤት ሀገር ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው በሚል መርህ የሚመራ ስለሆነ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ክስተቶችን እና ችግሮችን ሳይሆን መርህን እና ስትራቴጂያዊ የሀገራዊ ጥቅምና የጋራ ጥቅማችንን መሠረት አድርገን የምንሠራ ነን::
ይህንንም በፕሮግራማችን ግልጽ አድርገን ያስቀመጥን ከመሆናችን ጋር ተያይዞ አሁን ያነሳሽውን ጥያቄ ጨምሮ ወደፊትም የሚያጋጥሙ ጉዳዮች ካሉ በሃሳብ ልዕልና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለጋራ ተጠቃሚነት መርህ እየተፈታ ይሄዳል ማለት ነው:: ኢትዮጵያ በዚህ መንገድ ብዙ ችግሮቿን እየፈታች መጥታለች፤ ወደፊት የሚያጋጥሟትን ሀገራዊ ጉዳይ እና ጥቅም ጉዳይም በዚሁ መርህ እየፈታች ትሄዳለች::
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲው እስካሁን የመጣባቸው መንገዶች ፈተናዎች የተሞሉበት ቢሆንም ስኬታማ መሆን የቻለ ነው፤ በቀጣይስ በፓርቲው በኩል የታሰበው ነገር ምንድን ነው?
ቢቂላ (ዶ/ር)፡- ፓርቲው ያሳለፋቸው አምስት ዓመታት ተስፋ የታየባቸው፣ ተጨባጭ ድሎች፣ ስኬቶችና ውጤቶች የታዩባቸው ናቸው:: ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት ያገኛቸው ስኬቶችና ውጤቶች የተገኙት በተመቻቸ ሁኔታ አይደለም:: ለውጡም ሆነ የብልጽግና መመሥረትና እዚህ መድረስ እንዲሁም ስኬቶችን ማስመዝገብ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጦ እና አሸንፎ በመሆኑ ነው:: በቀጣይም ፓርቲያችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ካሉ ከሕዝብ ጋር በመሆን በመነጋገር እንዲሁም በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ብሎም በመፍታት እየተሻገረ የሚሄድ ይሆናል::
የኢትዮጵያ የፖለቲካም ሆነ አጠቃላይ ችግር በጉልበት የሚፈታ አይደለም:: በመሳሪያ አፈሙዝ ወይም ደግሞ ጫካ በመግባት የሚገኝ ውጤት የለም:: ደም በማፋሰስም የሚፈታ ችግርም አይደለም:: በጎዳና ላይ ነውጥም ድል አይገኝም:: በምንም ዓይነት መንገድ የጉልበትና የነውጥ አማራጮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር የማይፈቱ መሆኑን መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ:: የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው ግን በሃሳብ ልዕልና ብቻ መሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው:: የትኛውም የፖለቲካ ጥያቄ አለኝ የሚል እንዲሁም ያልተፈቱ ችግሮች አሉኝ የሚል ማንኛውም አካል መንግሥት የከፈተውን የሰላም አማራጭ በር ተጠቅሞ ወደ ውይይት በመምጣት፣ በሃሳብ ልዕልና በማመን፣ ሃሳብ ካለው ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሃሳቡን በማንሸራሸር የፖለቲካ ችግሮች እንዲፈቱ ማድረግ ይቻላል::
የዜጎቻችንን ችግር የምንፈታው እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ተባበረንና በጋራ ሰርተን ሀገራችንን ከድህነትና ከጉስቁልና በማውጣት ነው:: ስለሆነም እዚህም እዚያም የሚታዩ የአክራሪነት እና የጽንፈኝነት ኃይሎች እንቅስቃሴ መቆም ይገባዋል:: ወደሰላማዊ ትግል መምጣት ይኖርበታል:: የመንግሥት በር ደግሞ በየትኛውም ጊዜ ቢሆን የሚዘጋ አይደለም፣ አልተዘጋምም:: ስለዚህ አማራጩን መጠቀም የሚቻል ነው::
ፓርቲያችን ይህንን በር መክፈቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ይፈቱ የሚለው የምንጊዜም ጥሪውና ፍላጎቱ መሆኑ የሚታወቅ ነው:: ነገር ግን ጽንፈኛ እና አክራሪ ኃይል የኢትዮጵያን ሰላም ማደፍረስ ስለማይገባቸው፣ የዜጎችን ሕይወት መቅጠፍ ስለማይቻላቸው፣ የዜጎችን ሰላማዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማወክና ሰቆቃቸውን ማራዘም ስለማይገባቸው መንግሥት ሕግ የማስከበር ርምጃውን እየወሰደ ይገኛል:: በዚህም ምክንያት ብዙ አካባቢዎች የሰላም ሁኔታው መሻሻል ጀምሯል::
ይህን ማስቀጠልና የጽንፈኛ እና አክራሪ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲነጋገሩ፣ ሕዝባችን ደግሞ የተጀመረውን ሰላም ማስከበር እና የዜጎቻችንን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ከመንግሥትና ከፓርቲያችን ጎን ሆኖ እንዲደግፍ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ::
በጋራ ከሠራን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች ይፈታሉ:: የኢኮኖሚም ሆነ የሰላምና የደህንነት ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ:: ኢትዮጵያ እንደ ጀመረችው ወደ ልዕልና እና ወደብልጽግና ማማ ከፍ እያለች ትሄዳለች የሚል መልዕክት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
ቢቂላ (ዶ/ር)፡- አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም