ሀገራዊ ተግባቦት ለሁለንተናዊ ተሀድሶ

ሀገራዊ ተግባቦት በአንድ ሀገር ላይ ቤት እንደሚሰራ ሲሚንቶና አሸዋ፤ ጽንቶ ለመቆም መሰረት። ችግር እንዴትም ሊፈጠር ይችላል ችግሮቻችን ዋጋ እንዳያስከፍሉን የቅድመ ጥንቃቄም ሆነ ከተፈጠሩ በኋላ ላሉ ግብረ መልሶች መፍትሄ የሚሰጥ የአንድነት እና የአብሮነት መንፈስ የሚፈጥር የተሀድሶ አካል ነው።

ከዚህ አኳያ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ተሀድሶ እንደሚያስፈልጋት ለማንም የሚሰወር አይደለም። ይሄን ሁለንተናዊ ተሀድሶ ተግባራዊ ለማድረግ አመታትን በፈጀ ዝግጅትና ንቅናቄ ሀገራዊ ምክክር ልታደርግ እየተሰናዳች ነው፡፡ አራት የሚሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ያለፈው ሀገራዊ ምክክር የመጨረሻ በተባለው የምክክር ምዕራፍ ላይ ቆሞ ቀናት እየጠበቀ ይገኛል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙኃነት በተንሰራፋባቸው ሀገራት የምክክር ባህል ዋጋው የላቀ ነው፡፡ ባልዳበረ ፖለቲካና ባልዳበረ የሀሳብ ሙግት ውስጥ ለሚኖሩ እንዲሁም በታሪክ ውስጥ ነውርን፣ በአብሮነት ውስጥ መለያየትን ለሚበረብሩ አእምሮና ልቦች፣ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ሀገራዊ መግባባት ሰላም የሚያወርድ የእርቅና የይቅርታ መድረክ ነው፡፡

በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ሥርዓት የሳቱ፣ ኢትዮጵያዊነትን የዘነጉ በራስ ወዳድነት የተቀለሙ የእኔነት አመለካከቶች መፈጠር ከጀመሩ ቆይተዋል። እኚህ አመለካከቶች ሀገራዊ አንድነትን በማላላት የትላንት የአብሮነት መልኮቻችንን አጠይመውታል፡፡

የሚያግባቡን እልፍ የጋራና የሕብረት ታሪክ እና ሥርዓት፣ ባህልና ወግ እያሉን ጥቂት በሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በማተኮር ግዙፉን ኢትዮጵያዊነት ባልተገቡ እሳቤዎች ለመቀየር የምናደርገው ትግል ዋጋ እያስከፈለን መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን መሠረት አድርገው የቆሙ የጋራ ታሪኮች ጥንፍ በረገጡ ብሔረተኛ አስተሳሰቦች እየወየቡ መጥተዋል። አንድነትን መሠረት አድርገው የተበጁ የአብሮነት መንፈሶች በእኔነት ካባ ሲላሉ ተመልክተናል፡፡

ይሄን መሰሉ ከዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችን ያፈነገጠ የጥፋት አካሄድ ሀገር ከመጉዳት ባለፈ ለማንም ሲበጅ አላየንም፡፡ እንዳልበጀንና እንደማይበጀን እያወቅን እንኳን ከዛ የጥፋት ድርጊት መመለስ አልቻልንም። እስከዛሬ ድረስ ባለማወቅ የሰራነው ስህተት የለም። ሀገር እየጎዱ ያሉ አብዛኞቹ ጥፋቶቻችን እያወቅን የሰራናቸው ናቸው፡፡

ወደጦርነት ስንገባ ጦርነት ዋጋ እንደሚያስከፍለን በማወቅ ነው፡፡ ወደጥላቻ ስንገባ ጥላቻ ፍቅራችንን እንደሚነጥቀን ገብቶን ነው፡፡ በዘርና በብሔር ተቧድነን የቆምነው ዘረኝነት መልካም እንዳይደለ እያወቅን ነው። ሆን ተብሎ ለሚሰራ ጥፋት መፍትሄው ምንድነው?።

ስህተት መፍትሄ የሚኖረው ባለማወቅ ውስጥ ሲሰራ እንደሆነ ሁላችንም የገባን ሀቅ ነው፡፡ አውቀን እያጠፋን፣ አውቀን እየዋሸን፣ አውቀን እየነወርን ከዚህ ዝቅታ የሚያወጣን ምንድነው? በማወቅ ውስጥ ለተሰራም ሆነ ለሚሰራ ስህተት ዓለም ያላት መፍትሄ አንድና አንድ ነው፤ ቆም ብሎ ማሰብ ነው፡፡

ስህተት ልክ የሚሆነው ባለማወቅ ውስጥ ሲሰራ ነው፡፡ ባለማወቅ የተሰራ ስህተት በማወቅ ይስተካከላል። በማወቅ የተሰራ ስህተት ግን በምንም አይስተካከልም። ለጥላቻ፣ ለመለያየት የዳረጉን አብዛኞቹ ስህተቶቻችን ከዚህ እውነት ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው፡፡

ድሮና ዘንድሮ መልካችን የተለያየ ነው፡፡ ተሳሳትን ካልን የድሮ ስህተቶቻችንን ባለማወቅ ነበር፡፡ የዛሬ ስህተቶቻችን ግን በማወቅ ውስጥ ነው፡፡ የእኛ ፖለቲካ አውቆ ከመሳሳት ሌላ እውቀት የለውም፡፡ በዛ መንደር የፖለቲከኞቻችን ትልቁ እውቀት አውቆ በመሳሳት ሀገርና ሕዝብን ዋጋ ማስከፈል ነው፡፡ አውቆ ከመሳሳት እስካልወጣን ድረስ ፖለቲካችንንም ሆነ ሕመምተኛ ወገናችንን ማከም አንችልም፡፡

ከተሳሳትንም ተሳስተን እንሳሳት፡፡ ያኔ ለመታረቅም ሆነ ለመግባባት አቅም አናጣም፡፡ ተነጋግሮ መግባባት ያቃተን፣ ተወያይቶ መስማማት ያልቻልነው ስህተቶቻችን እውቅና የተሰጣቸው ስለሆኑ ነው፡፡ እውቅና በተሰጠው ስህተት ውስጥ እርቅ እንደምን ይሆናል? ከፍታ ስፍራው እርቅ ነው፡፡ ስልጣኔ ተነጋግረው በሚግባቡ አእምሮና ልቦች በኩል የሚንጸባረቅ የፍቅርና የይቅርታ ብራቅ ነው፡፡

ብሔራዊ ምክክር ኢትዮጵያዊነትን ወደነበረበት የምንመልስበት የእርቅና የተግባቦት መድረክ ነው። በጋራ ሀሳብ የጋራ ስምምነት ላይ የምንደርስበት የሁላችን የተሀድሶ ማዕከል ነው፡፡ በዛ መድረክ ላይ ሰንኮፎቻችንን ካልጣልን፣ በዛ መድረክ ላይ ነውሮቻችንን ካላከምን ከማጥ መውጣትን ሳይሆን ወደድጦ መግባትን እንደመረጥን እንቁጠር፡፡

ብሔራዊ ምክክር የሕዝብ ጥያቄና መልስ የሚስተናገድበት፣ ከዛሬ የተሻለ ነገን የምናይበት የተስፋና የንቃት መድረክ ነው፡፡ ቃል ተግባርን የሚወልድበት፣ ተግባር እውነት እና እምነት ሆኖ በዘረኝነት ላይ የሚሰለጥንበት የጋራ ማዕድ ነው። ለዘመናት የማጥናት ኢትዮጵያ በእርቅና በፍቅር የምትወለድበት፣ ጥላቻና ዘረኝነት የሚቀበሩበት የትንሳኤ መድረክ ነው፡፡

ትናንት ሆነ ዛሬያችን በሀሳብ የበላይነት በዚህ መድረክ ላይ መጽዳት አለባቸው፡፡ እኛም በእርቅና በውይይት በዚህ መድረክ ላይ መንጻት አለብን፡፡ ተላልፎ እንዲሰጥ በእየሱስ ላይ ትዕዛዝ እንደሰጠው ጢላጦስ ”ከደሙ ንጹህ ነኝ ” ማለት ሳይሆን በያገባኛል እና በይመለከተኛል መንፈስ ውስጥ ሆነን ለችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ከወዲሁ መሰናዳት ለሀገራችን ውለታ የምንውልበት አንዱ መንገድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከደሙ ንጹህ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ ለመሆኗ ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን፡፡ ሁላችንም ደግሞ የመፍትሔው አካል ሆነን ሀሳብ እንድናዋጣ፣ አቅጣጫ እንድንጠቁም ጊዜው ደርሷል፡፡ ተነጋግረን ስንግባባ ብቻ ነው አብሮ መኖር የምንችለው፡፡ ሀሳቦቻችን ወደ ልዩነት እና ወደ አለመግባባት የሚወስዱን ከሆነ ኢትዮጵያን መሥራት አንችልም፡፡

ሀገር ያለችው ተለያይተው አንድ በሆኑ፣ ተቃርነው በተስማሙ ዜጎቿ ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነት፣ የፖለቲካ እሳቤ የትም አለ፡፡ የኢትዮጵያ መልክ የሰማኒያ እና ከዛ በላይ ብሔር ብሔረሰብ መልክ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ቅይጥ መልክ የተለያየ የሚያስብ፣ የተለያየ የሚኖር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በወግና ልማድ ተለያይቶ ነው አንዲቷን ኢትዮጵያ የሰራው፡፡ በብዙኃነት ውስጥ ሁልጊዜ አንድ አይነትነትን መጠበቅ መቼም ልክ አይሆንም፡፡

ልዩነታችን የሚጠቡበት፣ ጥያቄዎቻችን የሚመለሱበት የተግባቦት ልብ ነው የሚያስፈልገን። የተለያየ አስበን በየፊናችን መቆም ሳይሆን የተለያየ ባሰበ አእምሯችን የአንድነት ሀሳብን አምጠን ወደፍቅር መምጣት ነው ክብር የሚሰጠን፡፡ በልዩነት ውስጥ መቆም ጀግንነት አይደለም፡፡ ጀግንነት ልዩነትን ይዞ አንድ መሆን፤ በዚህም ሰላም ማውረድ ሲቻል ነው።

እኛም ለእርቅና ለይቅርታ ከዚህ ለሚመነጭ ሰላም እስካልተጋን ድረስ ጎስቋላዋን ሀገራችንን ከፍ ማድረግ አይቻለንም፡፡ ጀግንነታችንን አብሮ በመብላት፣ አብሮ በመኖር፣ አብሮ በመቆም ካልሆነ መንገዳችን፤ የሎጥ መንገድ፤ ፍጻሜያችንም ጥፋት መሆኑ የማይቀር ነው።

ፍቅር ባለበት ሁሉ ጀግንነት አለ፡፡ ፍቅር ጀግኖች የሚፈጠሩበት ማህጸን ነው፡፡ ከፍቅር ሌላ፣ ከይቅርታ ሌላ ዓለም ሁነኛ ጀግና መፍጠሪያ ማህጸን የላትም። በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ ሕይወታችን ከዛሬ ወደነገ የሚሻገር የክብር ስም መትከል ከሻትን ፍቅር ያለበት ልብ ይቅርታ የተዋሃደው አእምሮ ያስፈልገናል።

ጥላቻ እና ራስ ወዳድነት የተለበጠባቸው የስልጣን ወንበሮቻችን ይራገፉ፡፡ ዘረኝነት እና እኔነት የበነነባቸው እውቀት እና አስተውሎታችን በፍቅር ይመዘኑ፡፡ ፍቅር ከሌለን ምንም ቢኖረን አንሞላም። አይደለም ለሌላው ለራሳችን አንበቃም፡፡ ሀገርም ወገንም ማሻገር አንችልም፡፡

ሀገራችንን በተደጋገመ የፖለቲካ ሽንፈት ስንሸራርፋት ኖረናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያለበሳትን የፍቅር ሸማ አውልቀን ለማንም የማይበጅ የብሔርተኝነት ማቅ አልብሰናታል፡፡ ማቅ የሐዘን ልብስ ነው፡፡ ማቃችንን በካባና ላንቃ ቀይረን በታደሰ ፖለቲካ፣ በታደሰ አብሮነት ከፍ የምንልበት አዲስ የሥነ ልቦና ግንባታ ያስፈልገናል፡፡

የብቻ ታሪክ የለንም፡፡ ጥንተ አዳም ስልጣኔያችን፣ በኩረ ዘፍጥረት ልዕልናችን በአብሮነት አምጠን የወለድነው ነው፡፡ ታሪኮቻችን ሰማኒያና ከዛ በላይ እጆች፣ ልቦች እና አእምሮዎች የሸመኗቸው ናቸው። የለመድነው በአንድነት ታሪክ መሥራት ነው፡፡ የተማርነው በአብሮነት መቆም ነው፡፡ ከዝቅታችን ከፍ የምንለው ሆን ብለን ከምንሰራቸው ጥፋቶቻችን ስንታረም እና ከዚህ ወደዛ የሚወስድ የእርቅና የአብሮነት ድልድይ ስንገነባ ነው፡፡

ምክክር የተለያዩ ልቦች አንድ የሚሆኑበት ሥፍራ ነው፡፡ ሀሳብ ሰጥተን ሀሳብ የምንቀበልበት የመለያየትን እድፍ የሚያጠራ የልክ መሆን ጉባኤ ነው። ምንም ያክል ልክ ቢሆን የሰው ልጅ እስካልተነጋገረ ድረስ ከነውር አይርቅም፡፡ ከበሽታዎቻችን ለማገገም ምክክር የመጨረሻ መጀመሪያችን ነው፡፡ በጥላቻ እና በዘር እሳቤ የወየበችው ኢትዮጵያ የምትወለድበት። በጥላቻና በመለያየት አፉን የፈታው ትውልድ በሚታረምበት የተሀድሶ ንቅናቄ ነው፡፡

ብዙ ሀገራት በዚህ አይነት ሀገራዊ መግባባት ችግሮቻቸውን በጋራ ፈትተዋል፡፡ እኛም የነገ እጣ ፈንታችንን የምንወስንበት፣ ለአሁናዊ ተግዳሮቶቻችን መልስ የምንሰጥበት፣ ኢትዮጵያን ከነህልማችን የምናዋልድበት የሙግት፣ የውይይት፣ የእርቅና የተግባቦት መድረካችን ነው፡፡

ብሔራዊ ተግባቦት ብሔራዊ እርቅ ነው፡፡ ተግባቦት እርቅን ከሰጠን እርቅ ደግሞ የምንናፍቃትን ኢትዮጵያን ይሰጠናል፡፡ በምንናፍቃት ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሰላም እና ፍቅር፣ አንድነት እና ወንድማማችነት የክብር ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ያኔ ወደከፍታ እንሄዳለን፡፡ ከተረጂነት ወደረጂነት፣ ከልመና ወደ ራስን መቻል እንሸጋገራለን፡፡ የእስካሁኑ ራስን አለመቻላችን፣ የእስካሁኑ ተረጂነታችን በአንድ ቃል ቢገለጽ ተነጋግሮ አለመግባባታችን የፈጠረው ነው፡፡

የማይሰሩ እጆች ብቻቸውን በድህነት ላይ የበላይ አይሆኑም፡፡ ለድህነታችንና ለኋላቀርነታችን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት በፖለቲካው በኩል የሚፈጠሩት አለመግባባቶች፣ ታሪክ እና ትላንትን ታከው የሚመጡ የጥላቻ መንፈሶች ናቸው፡፡ እኚህ ፈር የሳቱ መሠረተ ቢስ አረዳዶች ናቸው በዝተውና ሰፍተው የአሁኗን ጎስቋላ ኢትዮጵያ የፈጠሩት፡፡

ነጋችን እንዲስተካከል ዛሬያችን እና ትላንታችን መስተካከል አለበት፡፡ ከትላንት ወደዛሬ የመጡ ወደነገም ለመሄድ የሚያኮበኩቡ ችግሮች አሉን። እኚህ ችግሮች የሚቀጩት በውይይት ብቻ ነው። ሰፊውን ማህበረሰብ የሚያሳትፈው የውይይት መድረክ በእኚህ ነባር እና ወቅታዊ ችግሮቻችን ላይ መልስ ይሰጣል የሚል የጸና እምነት አለን፡፡

እርቅ ደም አድርቅ ነው፡፡ እርቅ ነገር ያርቅ ነው። ሀገራዊ እርቅ ከዛሬ ወደ ነገ የሚሻገር በሚመጣው አዲስ ትውልድ ላይ የሚያርፍ የበጎ መንፈስ ንቃት ነው፡፡ የዛሬ መታረቃችን፣ የዛሬ መግባባታችን ኢትዮጵያን በተመለከተ አዲስ ልብና አእምሮ ያለውን ትውልድ በመፍጠር ረገድ ይሄ ነው የማይባል ድርሻ አለው፡፡ መታረቃችን፣ በፍቅር ስም መዋሃዳችን እንዳበላሹን ታሪኮቻችን ሁሉ የሚጠቅሙንን አዲስ ታሪኮች የምንጽፍበት እንደ የጅማሬ ርምጃ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *