ጸያፍ ተግባራትን በግልጽ በማውገዝ ትውልዱን እንታደግ

 ‹‹ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው፤›› ይባላል። ይህ አባባል መነሻው ፊት ለፊት አትናገር ለማለት ቢሆንም፤ የማይፈልጉትን ሰው ለማራቅ በግልፅ መንገር ሲቻል በተዘዋዋሪ መንገድ ገሸሽ እንዲል ግፊት ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የማይፈልጉትን አንፈልግም፤ የሚፈልጉትን ደግሞ እፈልጋለሁ ብሎ በግልፅ መናገር የተሻለ ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ነገሮች የማይፈለጉ ከሆኑ፤ በግልፅ እነዚህ ነገሮች የማይፈለጉ በመሆናቸው መተው፣ መቆም ወይም መቅረት አለባቸው ተብሎ መነገር አለበት፡፡ ወይም መፈፀም የለባቸውም መባል አለበት፡፡

ሰሞኑን በተደጋጋሚ ማህበረሰቡ እየተነጋገረባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከባህልና ከሃይማኖታችን ያፈነገጡ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የሚሰሙ ጸያፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ ባህል ፍፁም ያፈነገጠ፤ ከኢትዮጵያ ባህል ብቻ ሳይሆን ከስብዕና ውጪ (ሰው ነኝ) ብሎ ከማመን እና ራስን ከማክበር በራቀ መልኩ በዓለም ዙሪያ በተለይም አድገዋል በሚባሉ አገሮች እየተስተዋለ ያለ ዕብደትን በጊዜ በግልፅ በፍፁም የማንቀበለው መሆኑን መግለፅ አለብን፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝብ አኗኗር፣ ባህል እና ወግ ፍፁም የሚቃረነው ይህ ጉዳይ፤ ያለምንም ማቅማማት በኢትዮጵያ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው መግለፅ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ የተገነባበት እሴት፣ ሥነምግባሩ እና አጠቃላይ ሞራሉ እንዲህ ዓይነት ከተፈጥሮ ያፈነገጠ፤ ዘር እንዲቆም መንገድ የሚከፍት ሳይሆን፤ ከተፈጥሮ ጋር በተጋመደ መልኩ ከሃይማኖት ጋር የተሣሠረ እና ከእንዲህ አይነት እብደት ፍፁም የራቀ ነው፡፡

በመገናኛ ብዙሃን በኩልም የኢትዮጵያውያንን መልካም እሴቶች ማጉላት እና ከሕዝቡ ባህልም ሆነ የተፈጥሮ ሂደት የሚገድቡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ፍፁም ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በአደባባይ መግለፅ ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ ተለምዶ ወደ ትውልዱ ዘልቆ ከገባ በኋላ ጉዳቱ ሲደርስ ከመጮህ እና ለማስተካከል ወይም የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ከመሯሯጥ፤ ከመነሻው ማገድ የግድ ነው፡፡

ካለፈ በኋላ ውግዘት ቢበረክት መግለጫ ቢንጋጋ ቀድሞ የነበረውን መመለስ ያዳግታል። ይሄንን ጉዳይ የሚያራምዱ አካላት አስቀድሞም ቢሆን የሰው ዘርን የሚረዱ መስለው የሚያጋድሉ፤ ቅኖች መስለው ቅንነት የጎደላቸው፤ ለዕርዳታ ቀርቶ ለብድር እንኳ በብድሩ ገንዘብ የሚሠራው ሥራ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሟላ ካልሆነ እንዲሁም የራሳቸው እምነት የሚስተጋባበት ሁኔታ ካልተፈጠረ የሚከለክሉ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ የታየ ሃቅ ነው፡፡

እንኳን ጉዳዩን የሚያራምዱ አገራት ዓለም አቀፍ ድርጅት ተብለው ያደጉ አገራት ፈረሶች ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አበዳሪዎችም መነሻቸው እና መድረሻቸው ያደጉት አገራት የፍላጎት ማራመጃ መሆን ነው፡፡ እያንዳንዱ ርዳታ እና ድጋፍ እንዲሁም በየትም በኩል የሚሰጥ ብድር መነሻው እና መድረሻው ከእነርሱ የባህል ወረራ እና የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡

በእርግጥም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ድሃ አገራት ለችግራቸው ደራሽ ባለውለታ ሊሆን የሚችል ያደገ አገር ወይም የማበደር አቅም ያለው ትልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅትን ይፈልጋሉ፡፡ ርሃብ እና ጦርነት ውስጥ እያሉ ፍፁም ርዳታ እና ብድር እንደማይፈልግ አካል መኩራራት እንደተራ ቀረርቶ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ነገር ግን በምንም መልኩ የአሁኑን ትውልድ የዜጎችን ክብር ከመንካትም በላይ ቀጣዩ ትውልድ ላይ ዘላቂ የስብዕና ቀውስ ሊያስከትል ለሚችል ነገር ፈቃደኛ መሆን እና እጅ መስጠት የታሪክ ተወቃሽነትን ያስከትላል፡፡

በእርግጥ ልንክዳቸው የማንችላቸው ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ በተጨማሪነት ደግሞ ችግሩ ስር እንዲሰድ እና እየሠፋ ቀጥሎ አገር አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚተጉም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የተለያዩ ሰዎችን ገንዘብን እንደማማለያ በመጠቀም በስፋት ይሠራሉ፡፡ በገንዘብ ለማማለል ራሳቸውን ያዘጋጁ ሰዎች ከተሰጣቸው አደራ እና ካለባቸው የዜግነት ሃላፊነት ባፈነገጠ መልኩ ሊስማሙ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ተስፋፍቶ ጉዳዩ አገር በዚህ የዕብደት አዙሪት ውስጥ እንድትዘፈቅ ካደረጋት ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡

በዚህ በኩል በዋናነት መንግሥታዊ ያልሆኑ የርዳታ ድርጅቶች ከርዳታ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ጥያቄ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ወሳኝነት አለው። ምንም ያህል ትልቅ እና የብዙዎችን ሕይወት ለመቀየር ያስችላል የሚባል ገንዘብ ይዞ የሚመጣ ርዳታ ሰጪ አገርም ሆነ ድርጅት፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ቡድን የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ባህል በተለይም ከእንዲህ ዓይነት የተፈጥሮ ሂደትን ለመግታት ከሚደረግ ትግል ጋር መተባበር ፍፁም ስህተት እና ምህረት ሊሰጠው የማይገባ ወንጀል ነው፡፡

ግለሰቦችም በተለያየ መልኩ ተልእኮውን አንግበው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ካለ በጊዜ እንዲወገዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው ሰዎቹ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሚመስል መልኩ ባልተረጋገጠ ወሬ ግለሰቦችን ለማውገዝ መንደርደር ደግሞ ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል። በተለይም ታዋቂ ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ከተፈጥሮ ያፈነገጠ የዕብደት አዙሪት ውስጥ ገብተዋል ብሎ ማስወራት ትልቅ ጥፋት ነው። በዋናነት ትኩረታችን ጉዳዩ በአገራችን ሕዝብ ዘንድ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ማሳወቅ እንጂ፤ ሰዎችን ማሸማቀቅ መሆን የለበትም፡፡

ታዋቂ ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ማስወራትም ሆነ ማውራት ልጆች ታዋቂ ሰዎችን የሚከተሉ በመሆኑ፤ ጭራሽ ትውልዱ ጉዳዩን እንደትክክለኛ ተግባር የሚወስድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ በኩል በተለይ በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የምናጋራቸው አጀንዳዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡

ገንዘብ ብቻ ለማግኘት የሚንገበገቡ እንዲህ ዓይነት ሃሳቦችን ደግፈውም ባይሆን በጉዳዩ ላይ ያልተሳተፉ ሰዎችን ስም በማጥፋት ብዙ ተመልካች እና አድማጭ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉት ላይ ተመልካች እንዳያገኙ ሃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል፡፡ በትንሹ ሃሳባቸውን ካለመቀበል በተጨማሪ ተከታይ እንዳይኖራቸው የእነርሱን ገፅ አለማጋራት የግድ ነው፡፡

በአጠቃላይ በሃይማኖት አባቶች እና በመንግሥት በኩል ጉዳዩን በተመለከተ በአገር ደረጃ ያለውን ግልፅ አቋም ማሳወቅ ያስፈልጋል። ድሮም እየተራብን እና እየተቸገርን የኖርን በመሆኑ፤ ይህንን ፍፁም ነውር የሆነ ቀጣይ ትውልድ ላይ ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ተግባር ይዘው ካራመዳችሁ ርዳታ እና ብድር ይዘን እንመጣለን የሚሉትን ከእነገንዘባችሁ ራሳችሁን ችላችሁ ኑሮ ብሎ ኢትዮጵያ ይህንን ተግባር በምንም መልኩ እንደማትቀበለው እና እንደማትደግፈው ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *