የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ማግስት ጀምሮ የህዝቡን ሕይወት በዘላቂነት መለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን አቅዶ በመተግበር ላይ ይገኛል። በዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ስለመሆናቸው በሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ሆነ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ስኬቶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
ቀደም ሲል አገሪቱ ከመጣችበት ፖለቲካዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች እና ምስቅልቅሎቹ ከፈጠሯቸው መንገጫገጮች አንፃር ፤ ላለፉት አራት ዓመታት ዜጎች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንዲያልፉ ፤ ፈተናዎቹን አሸንፈው ለመውጣትም ከፍ ያለ አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍሉ ተገድደዋል።
በተለይም ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ በመላው አገሪቱ በሚባል ደረጃ በተፈጠረ የሰላም እጦት ብዛት ያላቸው ዜጎች ለሞት ፤ ለአካል ጉዳት ፣ ለስደት እና ለሥነ ልቦናዊ ስብራት ተዳርገዋል። ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በዚህም ለሌሎች ይተርፉ የነበሩ ሳይቀሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የርዳታ እጆችን ጠባቂ ሆነዋል።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሰው ሰራሽ ከሆነው የሰላም እጦት ከፈጠረው ርዳታ ጠባቂነት በተጨማሪ፤ በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች /ድርቅ፣ ጎርፍ የመሬት መንሸራተት…ወዘተ/ ብዛት ያላቸው ዜጎች ለአስቸኳይ የምግብ ርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል።
ወቅታዊ ችግሮቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸውን በርዳታ ይገፉ ከነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ጋር ተደምሮ ፤ ለአገርና ለህዝብ ትልቁ የለውጥ ወቅት ፈተና ሆኗል። የነዚህን ዜጎች ሕይወት የመታደጉ ጉዳይ ከሁሉም ቅድሚያ የጠየቀ አገራዊ አጀንዳ ከሆነም ዓመታት እየተቆጠሩ ነው።
መንግሥት የእነዚህን ዜጎች ሕይወት ለመታደግ ካለበት የሞራልና የሕግ ሃላፊነት አንጻር የተለያ አማራጮችን ወስዶ ሲንቀሳቀስ ቆይተዋል። በችግሩ የዜጎች ሕይወት እንዳይቀጠፍ ዓለም አቀፍና አገራዊ አቅሞችን አሟጦ ለመጠቀም ረጅም ርቀት ተጉዟል ። በዚህም የብዙ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ችሏል።
በአንድ በኩል የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በማሳወቅ ለዜጎች የሚያስፈልጋቸውን የርዳታ አቅርቦት ለማሟላት ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሲያደርግ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ አቅሞችን በማቀናጀት የሕይወት አድን ሥራዎችን አጠናክሮ እየሰራ ነው።
በርግጥ አገሪቱ በምግብ እህል እራሷን ያለመቻሏ /ትርፍ አምራች ያለመሆኗ ፤ የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ አደጋዎች ባጋጠሙ ቁጥር ችግሮቹን ማግዘፉ ፣ ለመቆጣጠር የሚደረጉ አገራዊ ጥረቶችን ፈታኝ ማድረጉ የማይካድ ነው ።
አሁናዊ በሆነው ዓለም አቀፋዊ እውነታ ፣ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ፤ እውነታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት በተጎጂዎች ለመቆመር የሚደረጉ ሙከራዎች የሰብአዊ ርዳታ ሥራዎችን መፈታተናቸውም አዲስ ክስተት አይደለም ።
ጉዳዩን ከሰብአዊነት አውጥተው ፖለቲካ በማድረግ አትራፊ መሆን የሚፈልጉ ሃይሎች መኖራቸው ፤ በዚህም ርዳታ ጠባቂ ሰዎች ላልተገባ እንግልት እና ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውም የተለመደ ከሆነም ቆይቷል።
ለዚህ ደግሞ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የርዳታ ተቋማት በአገሪቱ ለሚገኙ ርዳታ ፈላጊ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ በማቋረጥ የፈጠሩትን ክፍተትና ክፍተቱ በተረጂዎች ላይ የፈጠረውን ጫና ማየት ይቻላል። በዚህም አላስፈላጊ ዋጋ ለመክፈል እየተገደዱ ያሉ ዜጎችን ማንሳት በቂ ነው።
በእርግጥ ርዳታ ፈላጊ ዜጎቻችን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ርዳታ የማግኘት መብት አላቸው ፤ይህ መብታቸው ከሰብአዊነት ፣ ከዓለም አቀፍ ሕግና ከተቋማቱ ከራሳቸው የአሰራር ሕግና መርህ የሚመነጭ ነው።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከሃያ ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ርዳታ ፈላጊዎች ናቸው ፤ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉት አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ጠባቂዎች ሲሆኑ አራት ሚሊዮኑ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡
የእነዚህን ዜጎች ሕይወት ለመታደግ መንግሥት ካለበት ሃላፊነት አንጻር ከራሱ የመጠባበቂያ የምግብ ክምችት ወጪ በማድረግ በመጀመሪያው ዙር ለአራት ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ አድርጓል፡፡ 115 ሺህ ኩንታል ምግብ ነክ ድጋፍን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት በድጋፍ መልኩ ሰጥቷል፡፡
መንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ የርዳታ ተቋማት ለተረጂዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ከማስተባበር ባለፈ በራሱ አቅም እያደረገ ያለው ድጋፍ ፤ የዜጎችን ሕይወት በመታደግ ተልእኮ ውስጥ እራሱን ግንባር ቀደም አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመላካች ነው ። በችግሩ ምክንያት የአንድም ዜጋ ሕይወት እንዳጠፋ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ነው ።
የመንግሥት ቁርጠኝነት በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በአግባቡ ሊደገፍ ይገባል። በተለይም ባልተገባ መንገድ የርዳታ አቅርቦቶችን ያቋረጡ ተቋማት ውሳኔያቸውን መልሰው በማጤን የመንግሥትን ጥረት በመደገፍ የዜጎችን ሕይወት መታደግ ይጠበቅባቸዋል። ይህንን የማድረግ የሞራልና የሕግ ግዴታም አለባቸው!።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2015