ተተኪው ትውልድና የዕድሜ ባለፀጐች እየተመካከሩ፣ እየተራረሙ፣ እየተደጋገፉ የሚኖሩ የቅርብ ጎረቤታሞች ሊሆን ይገባል። አረጋውያን በዘመን የካበተ በጥበብ፣ በማስተዋልና በክህሎት የታነፀ ዕውቀታቸውን ለትውልድ ሳያስተላልፉና እንደእነሱ ተምሳሌት የሚሆን ትውልድ ሳይተኩ እንደዋዛ እንዳያልፉ፣ ትውልዱ ቅርስና ተምሳሌት አልባ ሆኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ መደረግና የዕውቀት ሽግግር መኖር አለበት።
የዕውቀት ሽግግር ሊኖር የሚችለው ተተኪ ትውልድንና አረጋውያንን የሚያገናኝ ድልድይ ሲሠራ ነው። ለዚህም በትውልዱና በአረጋውያን መካከል የዕውቀት፣ የልምድ፣ የጥበብ ቅብብሎሽና ትስስር እንዲኖር መድረክ መፍጠር አንዱ መፍትሔ ነው።
የተተኪ ትውልድና የዕድሜ ባለፀጐችን የዕውቀት ትስስር ለማጠናከር አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ “ የህይወት ገጽታ ” በሚል አምዱ ላይ የሀገር ባለውለታ የትውልድ ቅርስና ትምህርት ቤት የሆኑ ግለሰቦችን ያስተናግዳል። የዛሬው እንግዳችንም ተዝቆ የማያልቅ የህይወትና የሥራ ተሞክሮ ያላቸው አርአያነታቸውም የጎላው አቶ ወልደሔር ይዘንጋው ናቸው።
የተወልዱት ምስራቅ ጎጃም በእነብሴ ሳር ምድር ውስጥ በምትገኝ ድቦ ኪዳነምህረት በምትባል ቦታ ሲሆን፤ ያደጉት ደግሞ ፈረስ ሜዳ በሚባል የገጠር መንደር ነው። ለእናታቸው የመጀመሪያ ልጅ ለአባታቸው ደግሞ አምስተኛ ልጅ የነበሩት አቶ ወልደሔር፤ እናታቸው እርሳቸውንና ታናሽ ወንድማቸውን ከወለዱ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በቶሎ ነበር። የእናታቸውን ሞት ተከትሎ አቶ ወልደሔርና ወንድማቸውን የማሳደግ ኃላፊነት በአያታቸውና በአባታቸው ላይ ወደቀ።
“….አያቴ እናታችንን ተክታ ብዙ ነገር ሆና እኔና ወንድሜን አሳደገችን፤ እሷ ብትጎዳም እኛ ግን ጎበዞች፣ መንፈሰ ጠንካሮች፣ ሥራ ወዳዶች እና ሰው አክባሪዎች እንድንሆን አድርጋናለች። ይህ አስተዳደጓ እኔ ዛሬ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ መሰረት ጥሏል” በማለት የአያታቸውን ውለታ ይገልጻሉ።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፤ አያታቸው ወደቄስ ትምህርት ልከዋቸው ትምህርትን ጀመሩ። አንድ ደበሎ ከሰሌን ወይም ደግሞ ከቄጠማ የሚሰራ አኮፋዳ (የምግብ መያዣ ) በመያዝ እየለመኑ የቆሎ ተማሪም ሆነው የኔታ ጋር ፊደል ቆጠሩ፤ አቡጊዳ፣ መልዕክተ ዮሐንስ እያሉ መማራቸውን ቀጠሉ።
“…እኔ ትምህርት በጀመርኩበት ጊዜ የትምህርት መሰረቱና አሰጣጡ፤ ከአሁኑ ፍጹም የተለየ ነበር። ሃይማኖት ተጠግቶ በቤተክርስቲያን አስተምሮ ላይ የተገነባና በደጀሰላም በአድባራትና ገዳማት ውስጥ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ ይሰጥ ነበር” በማለት ያለፉበትን የትምህርት ሥርዓት ይናገራሉ።
የቆሎ ተማሪነት ህይወት ቀላል አይደለም የሚሉት አቶ ወልደሔር፤ በወቅቱ የ12 እና 13 ዓመት ልጅ ለትምህርት ብሎ ቤተሰቡን ተሰናብቶ ወደማያውቀውና ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ የሚማረው የእለት ጉርሱን እራሱ ጥሮ ተጣጥሮ አግኝቶ ነበር።
አቶ ወልደሔር ይህንን አስቸጋሪ የትምህርት ውጣ ውረድ ካሳለፉ በኋላ ዳዊት ደገሙና ድቁና ተሰጣቸው። (ድቁና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው የመመረቂያ ማዕረግ ነው)። ድቁናውን ካገኙ በኋላ በተለያዩ ቤተክርስቲያኖች ማገልገል ጀመሩ፤ ይህ አገልግሎታቸው ደግሞ መጠነኛም ብትሆን ገንዘብ ያስገኝላቸው ነበር። አቶ ወልደሔር የሚያገኟትን ገንዘብ ከማጥፋት ይልቅ ማጠራቀም ጀመሩ፤ በርከት ሲልላቸውም የሁልጊዜ ምኞታቸው የሆነውን አያታቸውን መርዳት ጀመሩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ልባቸው የፈቀደውንም ልብስም ገዝተው አለበሱ፤ ለበሱ።
በዚህ መካከል ግን ብዙ ዋጋ ከፍለው ያሳደጓቸው አያታቸውን እንዳሰቡት በደንብ ሳይጦሯቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ይህ ለእርሳቸው በጣም ከባድ ቢሆንም የተፈጥሮ ህግ ነውና ምንም ማድረግ ስለማይቻል አቶ ወልደሔር ራሳቸውን አጽናንተው የድቁና አገልግሎታቸውን እንደገና ቀጠሉ። የሚያገኙትንም ገንዘብ በተመሳሳይ መቆጠባቸውን አላቋረጡም። አሁን ኑሯቸው መሻሻል እያሳየ በመምጣቱ ስለቀጣዩ ህይወታቸው በደንብ ማሰብ ጀመሩ።
አቶ ወልደሔር ከድቁናም በላይ ያለውን የትምህርት እርከን ለመቀጠል ላቅ ያለ ፍላጎት ቢኖራቸውም፤ የአባታቸውን ይሁንታ ግን ማግኘት አልቻሉም ነበር። እንደውም በወቅቱ አባታቸው ሥራ እንዲሰሩ ከመፈለግ አልፈው ያስገድዷቸው ጀመር። ነገሩ ምንም ያልተዋጠላቸው አቶ ወልደሔር አባታቸውን ለማግባባት ሞከሩ። መምህራቸው እንዲያናግሩላቸው አደረጉ፤ አባት ግን “ልጁ መልመድ ያለበት ስራ ነው።” በማለት አሻፈረኝ ብለው ቀሩ።
ወቅቱ ከአባት ከቤተሰብ ፍላጎት ማፈንገጥ ትልቅ ነውር የነበረበት ጊዜ ነበር። አቶ ወልደሔር የመማር ፍላጎታቸውን ዋጥ አደርገው በአባታቸው ጎዳና ለመጓዝ ተስማሙ። ገና የትምህርቱ ጥማትና ፍላጎት ከውስጣቸው ያልወጣ ቢሆንም፤ እስኪ ስለ ሥራው ደግሞ ልስማ ብለው አባታቸውን ተጠግተው ለመሆኑ የምሰራው ሥራ ምንድን ነው?” በማለት ጥያቄ አቀረቡ። አባትም “ የውሃ ወፍጮ” በማለት መልስ ሰጧቸው።
አቶ ወልደሔር ስለ ውሃ ወፍጮ በጠቅላላው ስለ ወፍጮ አካባቢያቸው ላይ አይታወቅምና ሰምተውም ስለማያውቁ ምን ማለት ነው? ሲሉ አባታቸውን ጠየቁ። አባትም እህል የሚፈጭበት እንደሆነና ሞተሩ በውሃ ኃይል እየተገፋ እንደሚሠራ አብራሩላቸው። ‹‹…የተለየሁ ነኝ ማለት ባልችልም፤ አባቴ ግን በእኔ ከፍተኛ የሆነ እምነት ነበረው። ትምህርቴንም አቋርጬ ሥራውን እንድሠራለት የፈለገው በዚህ እምነቱ የተነሳ ነው። እኔም ሳልወድ በግድ ወፍጮው ከተተከለ በኋላ ስራዬን አንድ ብዬ ጀመርኩ” በማለት ሁኔታውን ያብራራሉ።
አቶ ወልደሔር የወፍጮ ሥራው ተከትሎ ገና በለጋነት እድሜያቸው የአመራርነት እውቀት አባታቸው እንደሰጧቸው ይናገራሉ። ይህንን ሲያብራሩ፤ ‹‹በዛ በትንሽ እድሜዬ ሰራተኞችን እቆጣጠር የወፍጮውንም ሥራ እመራ ነበር። ይህ ደግሞ በእኔ እድሜ የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ ሰራተኞቹም በእድሜ ከእኔ በጣም የሚልቁ ነበሩ። ሁለት ዓመት በጥንካሬ የወፍጮ ሥራውን ካከናወንኩ በኋላ፤ በድጋሚ የአባቴ አስገዳጅነት ታክሎበት ወደ ግብርና ሥራ ገባሁ።›› በማለት ይናገራሉ።
“…. አባቴ ከእህል ወፍጮ አስወጥቶ ገበሬ እንድሆንለት ፈለገ፤ የአባቴን ትዕዛዝ ለማክበር ብዬ ልቤ ፈጽሞ ያልፈቀደውን የግብርና ሥራ ለመስራት ተዘጋጀሁ። አባቴ ገበሬ እንድሆን የፈለገው ለአራሹ የሚከፈለውን ‹አርቦ› ለማዳን እንዲሁም አንድ ሰው ትዳር ከመመስረቱ በፊት ስለ ግብርና ሥራ ማወቅ አለበት የሚል እሳቤ ስለነበረው የግብርና ስራውን በደንብ ካወቅሁ በኋላም ሊድረኝ በማሰቡ ነበር።” ይላሉ።
አቶ ወልደሔር ከእድሜያቸው አንጻር የግብርና ሥራው ፈታኝ ቢሆንባቸውም ዓመት ያህል ግን ጠንክረው ሠሩ። እንደ እድልም እርሳቸው ባረሱት መሬት ላይ ከፍ ያለ ምርት ለመሰብሰብ ተቻለ። በዚህም መላው ቤተሰብ ተደሰተ። ከአመት የግብርና ሥራ በኋላ ግን፤ አባታቸው ያሰቡትን የጋብቻ ሃሳብ አቀረቡላቸው። አቶ ወልደሔር ግን በወቅቱ ትዳር መመስረት ሳይሆን ነጋዴ የመሆን ፍላጎት ነበራቸውና ህልማቸው አባታቸውን እያስተዛዘኑ ‹‹ነጋዴ መሆን እፈልጋለሁ እባክህ አሁን እንዳገባ አታድርገኝ›› ብለው ለመኑ። ያም ቢሆን ግን አባት ከአቋማቸው ፍንክች አልል አሉ። አቶ ወልደሔርም ‹‹ነጋዴ ከመሆን የሚያስቀረኝ የለም›› በማለታቸው በአባትና ልጅ መካከል አለመግባባት ተከሰተ።
አባት የልጃቸውን አቋም ሲያዩት ከመለሳለስ ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ተረዱ። ልጅም ‹‹አግባ ካልከኝ እጠፋልሀለሁ።›› ሲሉ ዛቻ ቢጤ ጣል ማድረግ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ አባት መለስ ብለው “ ለመሆኑ የምትነግደው ምንድን ነው?”
በማለት ለልጃቸው ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ። አቶ ወልደሔርም ‹‹ የምነግደው አንተ ባለችህ አንድ በቅሎ ነው።›› ብለው መልሳቸውን ሰጡ። አባት ልጃቸውን ለአደባባይ እንጂ ለነጋዴነት አያስቡምና በሁኔታም ቢከፉም ፤ ልጃቸውን ማስቆም ግን የማይቻል መሆኑን ሲረዱ፤ በግድ ተስማምተው በቅሏቸውን ሰጡ። ልጅም የተሰጣቸውን በቅሎ ይዘው ወደተመኙት የንግድ ሥራ ገቡ።
በአንድ ኮርቻ በቅሎም እህል እየሸመቱ ደጀን ድረስ እየሄዱ መሸጡን ተያያዙት ። “…የገጠሙኝን ችግሮች እየተቋቋምኩ በአንድ በቅሎ ጭነት ለብዙ ጊዜ ሰራሁ። አቅሜን እያዳበርኩ ስመጣ ግን ሁለት በቅሎ ቢኖረኝ የተሻለ መስራት እችላለሁ ብዬ በማሰብ አባቴ ገንዘብ እንዲበደርልኝና አንድ በቅሎ ልገዛ ማሰቤን ነገርኩት፤ እሱም ተበድሮልኝ በሁለት በቅሎ ደግሞ ስራዬን አጠናክሬ ቀጠልኩ” ይላሉ።
አቶ ወልደሔር የንግድ ሥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጣ። እርሳቸውም በሙሉ ኃይላቸው በጥሩ መንፈስ ሥራቸውን ቀጠሉ። ከሥራቸው ውጪ ሌላ የሚያዩት የሚሰሙትም ነገር አልነበረም። ከትውልድ ቀያቸው በእግራቸው የስድስት ቀን ጉዞ እያደረጉ እህል ጭነው በመምጣት መሸጥ ቀጠሉ። ሲመለሱ ደግሞ ለአካባቢው የሚያስፈልገውን ሸቀጣ ሸቀጦች ይዞ በመሄድ መነገድ የሥራቸው ባህርይ ነበር።
በዚህ መካከል ግን አባታቸው ያን ቀድመው ያስቡላቸው የነበረውን ትዳር እንዲመሰርቱ አደረጉ። ቤተዘመድ ተሰብስቦ ድል ባለ ሰርግ አቶ ወልደሔር ትዳር መሰረቱ። ይህም ቢሆን ግን ትዳሩ መክረም አልቻለም። አቶ ወልደሔር የንግድ ስራቸውን ወደአዲስ አበባ የማስፋት ውጥን ያዙ። በዚህም 150 ኪሎግራም ማር በመያዝ አዲስ አበባ አምጥተው ለመሸጥ ወሰኑ ። አዲስ አበባ ማር በረንዳ ገብቶ በመሸጥ ገንዘብ ሰብስበው ሀገራቸው ገቡ።
“…ስራው እየተጠናከረ ሲሄድ፤ ከአባቴ ልጅ ወንድሜ ጋር ሽርክና ገባን። በዚህም ጤፍ፣ ማር ፣ቆርቆሮና ሌሎችንም ነገሮች መሸጥ ጀመርን። የአዲስ አበባውን ሥራ የምሰራው እኔ ነኝ። እነርሱ ደግሞ ካሉበት ሆነው ይልካሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን በ1968 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ደርግ ከቢቸና ጀምሮ ችግሮች እየተፈጠሩ ሰዎች እየተገደሉ መምጣታቸው ሰማሁ።” ይላሉ።
አቶ ወልደሔር መጀመሪያ በአባታቸው ተጽዕኖ የመሰረቱት ትዳር ውጤታማ ባይሆንም አባታቸው ግን አሁንም ለልጃቸው የምትስማማ ሚስት ፍለጋቸውን አላቋረጡም ነበር። በዘመድ አዝማድ ፈልጉ በማለት ይናገሩ ነበር፤ ፍለጋው ተሳካ ። አቶ ወልደሔርም ስለልጅቷ ሁኔታ ሲነገራቸው ተስማሙ “ትሁን ” ሲሉም አጸደቁ። አቶ ወልደሔር በብዙ ነገር የምትመስላቸውን አጋዥ የትዳር ጓደኛቸውን አገኙ።
ከዚህ ትዳራቸው ልጆች ወለዱ። በወቅቱ እርሳቸው አዲስ አበባ ሆነው ወንድማቸውና አባታቸው ደግሞ ከሀገራቸው የሚልኩትን እህል እየሸጡ የጋራ ንግዳቸውን አጧጥፈው ነበር። የደርግ መንግሥት ግን ሀገራቸው ገብቶ ብዙ ንጹሀንን እየገደለ መሆኑንና ባለቤታቸውና ልጆቻቸውም ሸሽተው ወደ አባይ በረሃ መምጣታቸውን ሰሙ። ሳይውሉ ሳያድሩ በመካነ ሰላም አድርገው በሳይንት በኩል አባይ በመድረስ ቤተሰባቸውን አገኙ።
ቤተሰብና ልጆቻቸውን ይዘውም በ1968 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ገቡ። አዲስ አበባ ላይ በቂ ንብረት ለማፍራትም የቻሉ በመሆኑ ቤተሰባቸውን ምን ላድርግ ብለው አልተጨነቁም ።
‹‹… በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ እኔ ወንድሜና አባቴ በጋራ (በሽርክና ) እየሰራን ነው። ኋላም የታናሼ ታናሽ ወንድሜ ተጨምሮ ስራውን ለአራት እንሰራው ነበር ። በነገራችን ላይ እኔ በሰውም ሆነ በስራ አምናለሁ። ከሁኔታዎች ጋር ደግሞ እራሴን ለማዋሃድ ብዙም አልቸገርም። ስራው ላይ ትልቁም ድርሻ የእኔ ነው”።
አቶ ወልደሔር አዲስ አበባ ቤተሰባቸውን ካመጡ በኋላ፤ ልጆች ወደትምህርት ቤት ከመላክ በተጨማሪ እርሳቸውም ትምህርታቸውን ቀጠሉ። ጎን ለጎን ደግሞ ስራቸውንም መስራት ነበረባቸው፤ ኃላፊነቱም ስለበዛባቸው ሀገር ቤት ያለውን ሥራ ለወንድማቸውና ለአባታቸው በመተው አዲስ አበባ ሌላ ሥራ ለመጀመር አሰቡ።
“…አዲስ አበባ ከገባን በኋላ ልጆቼን ትምህርት ቤት አስገብቼ እኔም በቀጥታ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ተፈትኜ የአምስተኛ ክፍል ትምህርቴን ቀጠልኩ። ወደ ስድስተኛ በጥሩ ሁኔታ አለፍኩ፤ ከዛም ካቴድራል ትምህርተ ቤት ተፈትኜ በመግባት ከሰባተኛ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስ ያለውን ትምህርት ተማርኩ። በኋላም መደበኛውን ትምህርቴን አቋርጬ እዛው ካቴድራል የእንግሊዝኛ ቋንቋን ለሁለት ዓመት ተማርኩ ” በማለት የትምህርት ህይወታቸውን ይናገራሉ።
አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያ ሥራ ያደረጉት ድለላ ነበር። በዚህም የተለያዩ ነገሮችን በመደለልና በማገበያየት ኑሯቸውን ቀጠሉ። በደርግ ዘመን በመንግሥት ባለቤትነት ይተዳደር የነበረ አንድ የጣሊያን የሰም ፋብሪካ ለግለሰብ ለማከራየት ጨረታ ይወጣል። አንድ ሰው ተሳትፎ የጨረታው አሸናፊ ይሆናል። ሰውዬው ጨረታውን ካሸነፈ በኋላ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ስላልነበረው አቶ ወልደሔር በሽርክና ፋብሪካውን ማንቀሳቀስ ይጀምራሉ። ከመንግሥት ጋር የኪራይ ውል በስሙ የተፈራረመው ሸሪካቸው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ ባህሪ እያሳየ ይመጣል። አቶ ወልደሔር በሽርክና ተስማምተው ሥራ ሲጀምሩ ተማምነው እንጂ ምንም ፊርማ አልነበራቸውም። ሰውዬው ግን ይህንን ክፍተት እንደ ትልቅ ደካማ ጎን በመቁጠር በሥራ ላይ ተደጋጋሚ ችግር መፍጠር ይጀምራል።
ሁኔታዎች በዚህ ላይ እንዳሉ ድርቅ ተከሰተ፤ ንቦቹም የሚሰጡት የማር ምርት እየተዳከመ መጣ። ይህም ሁኔታ የሰም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ። በዚህም የተነሳ ፋብሪካው ተዳከመ። አቶ ወልደሔር ግን መርካቶ አካባቢ አንድ ሱቅ በመግዛት የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች መሸጫ ይከፍታሉ። ከዚህም ጐን ለጐን ሌላ ነገር መፍጠር ግድ ሆነባቸውና “በፖራፊን ዋክስ” ጧፍ ማምረት ጀመሩ።
በመካከሉ ኢሕአዴግ መላ ሀገሪቱን መቆጣጠርና መምራት ጀመረ። በማዕከላዊነት ይመራ የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ ለነፃ ገበያ ቦታውን ለቀቀ። በገበያ ሕግጋት የሚመራ ኢኮኖሚ ተደነገገ። ስለሆነም የቤተሰባቸው አባላት የአክሲዮን ባለድርሻ የሆኑበትን አምስት ኩባንያዎችን አቋቁመዋል። ኩባንያዎቹ ግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ግዮን ኢንዱስትሪያል ኬሚካል፣ ግዮን ጋዝ፣ ኮምፓልሳቶ፣ ምሥራቅ ዳቦ፣ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካዎች ናቸው።
በግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮሜርሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር የሰም ፋብሪካ ፣የቡና ማዘጋጃና ላኪ ድርጅት፣ አጋሮ የቡና ማበጠሪያ ድርጅት ፣ደረቅና ፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ፣ ጊዮን ኢንዱስትሪያል ኬሚካልና ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ ጊዮን ጋዝና ካርቶን፣ የኢትዮጵያ ኮምፐልሳቶ ፋብሪካ፣ ምስራቅ ዱቄት ዳቦና ብስኩት ፋብሪካ ፣ ባህር ዳር ሆቴል ከሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ጥቂቶቹ ናቸው። በአሁኑ ወቅትም በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ከ 2 ሺ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች እየሰሩ በስራቸውም በርካታ ቤተሰብን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
“…..ለእኔ ከፍተኛ እርካታን የሚሰጠኝ ይህ ነው። በአንዲት የገጠር መንደር ተወልጄ፣ ጥብቆ ለብሼ፣ ያለ ጫማ በባዶ እግሬ ተጉዤ፣ ከብት ጠብቄ አድጌ፤ በአንዲት የኮርቻ በቅሎ የጀመርኩት ንግድ ዛሬ የብዙ ድርጅቶች ባለቤት አድርጎኛል። በዚህም ብዙ ሰራተኞች ተቀጥረው እንጀራ ሲበሉ ሳይ ደስ ይለኛል።” ይላሉ።
ተወልደው ባደጉበትም አካባቢ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ (መሰናዶ) ትምህርት ቤት አቋቁመዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ የተወሰኑ ዓይነ ሥውራን ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍም ያደርጋሉ። በጊዜ ብዛት አርጅታ ልትፈራርስ የተቃረበችውንና በዩኔስኮ የተመዘገበችውን የመርጦ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ቆርቆሮ በማልበስና ተጠብቃ እንድትቆይ በማድረግ ትልቅ ቅርስ የማዳን ሥራም አከናውነዋል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ኩዌት፣ ኮሪያ፣ ጃፓንና ጣሊያንን ሲጐበኙ ካስከተሏቸው አሥር ቀዳሚ ላኪዎች መካከል አቶ ወልደሔር ይገኙበታል። በዚህ ዓይነቱ ጉብኝት ላይ በየሀገሮቹ ካሉት ገዥዎችና ላኪዎች ጋር የፊት ለፊትና የጋራ ውይይት በማድረግ ጥሩ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና ጠቃሚ ዕውቀትም ለመቅሰም እንደቻሉ ይናገራሉ።
የቤተሰብ ሁኔታ
የሰባት ልጆቼ እናትና የስኬቴ ሁሉ አጋር ይሏቸዋል ባለቤታቸውን ወይዘሮ ለምለም ዋለልኝን። ባለቤታቸው በጣም ታታሪ ሥራ ወዳድ በልጆች አስተዳደግም የተዋጣላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር በስራቸውም ላይ ከገቡ በኋላ ውጤታማ ሰራተኛ እንደሆኑ ይመሰክራሉ። ልጆቼ ካምፓኒዎቹን በማኔጀርነት እየመሩ ይገኛሉ ይላሉ።
የበጎ አድራጎት ድርጅት
በትውልድ ቦታቸው ላይ የአብነት ትምህርት ቤትን በመደገፍና እንዳይጠፋ በማድረግ የጀመሩት የበጎ አድራጎት ሥራ ከዛም በኋላ ቀጥሎ በተናጠል የሚመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የመደገፍና ከበጎ አድራጎት ጋር የተያያዙ ሌሎች ስራዎችንም ያከናውናሉ። ይህ ሥራ ግን በተናጠል ከሚሆን ለምን በተደራጀ መልኩ አይሆንም? በማለት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ችግረኛ የሆኑ ሴት ተማሪዎችን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እንዳይቸገሩ በማድረግ ቀጠሉ። ይህ ጅምር ወደ ባህርዳርና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎችም አድጎ እየተሰራበት ነው።
ነገር ግን ይህ የተናጠል ድጋፍ የትም አያደርስም በማለት፤ በእርሳቸውና በባለቤታቸው ስም የበጎ አድራጎት ድርጅትን በማቋቋም እርሳቸው የአቅማቸውን እያደረጉ ሌሎች ፍቃደኞችም እየተሳተፉበት ስራውን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
ፍኖተ ህይወት
አቶ ወልደሔር ከልጅነት እስከ አሁን ያለፉበትን የተጓዙበትን የሰሩትን የወጡትን የወረዱትን የህይወት ውጣ ውረድ የሚያሳይ የራሳቸውን ግለ ታሪክ በመጻፍ በ2010ዓ.ም ለንባብ አብቅተዋል።
“…ግለ ታሪኩ የእኔ ቢሆንም እዛ ላይ የሰፈሩት ነገሮች በሙሉ ግን በተለይም ለወጣቱ አቅም የሚጨምሩ ስኬት ከመሬት ተነስቶ የሚመጣ አለመሆኑን የሚያሳዩ ብዙ የሚያስተምሩ ቁም ነገሮችን የያዘ ስለመሆኑ መናገር እችላለሁ” ይላሉ።
አቶ ወልደሔር ይህንን የራሳቸውን ግለ ታሪክ ለትውልድ ለማቆየት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ቤተ መጽሐፍት ያላቸው ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች መጽሐፉን አንብቤ እጠቀማለሁ ለሚሉ ሁሉ ለመስጠትም ፍቃደኛ ናቸው።
ስኬት ለአቶ ወልደሔር
ስኬት ውሳኔ ነው። ስኬት ለንግድ ሥራ ደግሞ ታማኝነትም ነው። አንድ ሰው ለቤተሰቡ፣ ለሚሰራው ሥራ፣ ለሀገሩ፣ ለአስተዳዳሪው መንግሥት ታማኝ ከሆነ ይሳካለታል። በአንድ ጀምበር ሀብታም ካልሆንኩ የሚል የዘመኑ ወጣት ግን ጉዞው የትም የማያደርስ ነው። ስኬቱ እንኳን ቢመጣ አጥፊው ሊሆን ስለሚችል ጊዜ ወስዶ ሰርቶ ጥሮ ማግኘት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015