ዓለም የዘነጋው የሱዳን ዘግናኝ ጦርነት

የሱዳን ጦር አመራሮች ከተቀየሩ በ72 ሰዓት ውስጥ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ ነን። ሃሜቲ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ መሪ ለቀጠለው ግጭት የሱዳን ህዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል ። ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሱዳን ጦር ለሦስት አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ ከነበሩ ገዥዎች ትዕዛዝ ሲቀበል ነው የኖረ ሲሉም ከሰዋል ።”ጦር ኃይሎች ላሉ ወንድሞቻችን አፋጣኝ መፍትሄ ከፈለጋችሁ ፤ አመራራችሁን በ72 ሰዓት ውስጥ ስምምነት ላይ እንደርሳለን” ብለዋል ። ይሄን ይበሉ እንጂ ውጊያው ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሉዓላዊ ጽ/ቤቶችን ለመቆጣጠር እየተዋጉ ነው።

ሃሜቲ በሰራዊታቸው ተከበው ባስተላለፉት 5 ደቂቃ በሚረዝመው የቪዲዮ መልእክታቸው ፤ በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ዝርፊያ እየፈጸሙ ነው መባሉን አስተባብለዋል። የሱዳን ቀውስ ዛሬ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም 119ኛ ቀኑን ይዟል። የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በካርቱም ጎዳናዎች ላይ እየተፋለሙ ነው። ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቆም ጫናውና ግፊቱ ቢቀጥልም ፤ በመዲናይቱ የሚገኙትን ወታደራዊ እና ስልታዊ አካባቢዎች ለመቆጣጠር በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ከባድ ውጊያ ተባብሷል።

የአይን እማኞች ለአል አይን ኒውስ እንደተናገሩት፤ ጦሩ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ለማስመለስ እና በመሀል ከተማ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት “ጠቅላይ ዕዝ” ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል የአየር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ። ሰራዊቱ በኦምዱርማን የሚገኘውን ብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት ለመያዝም እየተዋጋ ነው ብለዋል። እንደ እማኞች ገለጻ ፤ ሰራዊቱ በመድፍ ተኩስ ከካርቱም በስተደቡብ በሚገኘውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ስብስብን ኢላማ አድርጓል ። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ደግሞ ከከተማዋ በስተደቡብ የሚገኘውን የጦሩ ክፍል እየከበቡ ነው ። ምንጮች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በባህሪ ከተማ የሚገኘውን “ሲግናል ኮርፕስ”፣ ከካርቱም በስተሰሜን የሚገኘውን “ዋዲ ሰይድና” ወታደራዊ ካምፕን እና በኤል-ኦቤይድ የሚገኘውን “ሼይካን” የአየር ማረፊያ ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳለው “ግጭቱ በካርቱም ፣ ባህሪ እና ኦምዱርማን ከተሞች ቀጥሏል” ሲል በዳርፉር (ምዕራብ) እና በኮርዶፋን ግዛቶች (ደቡብ) ጦርነቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ። ድርጅቱ በሚያዝያ 7 ቀን በጦር ሰራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን መፈናቀላቸውን እና መሰደዳቸውን አስታውቋል ። ለዩክሬናውያን እንደ ጉድ የሚጎርፈው የገንዘብና የዕለት ደራሽ እርዳታ በቻድ ፣ በኢትዮጵያና በሌሎች ጎረቤት ሀገራት ለተጠለሉ ሱዳናዊ ግን ብርቅ ሆኖባቸዋል።

ጦርነቱ እየተባባሰ ፣ ጎረቤት ሀገራትንና መላ ቀጣናውን ስቦ እንዳያስገባ እየተሰጋ ነው። የሰላም ጭላጭል የማይታይበት ፤ ተፋላሚ ኃይላት ከድርድር ይልቅ እንደ ጎረምሳ ይዋጣልንን፤ መሳሪያ መወልወልንና ትጥቅ ማሳመርን የመረጡበት ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በጥርጣሬ የሚታዩበት ፤ ራሽያና አሜሪካ የየራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚራኮቱበት ፤ ኢትዮጵያ በፈጥኖ ደራሽ ፤ ግብጽና ኬንያ በሱዳን ጦር ድጋፍ የሚታሙበት ፤ እነ ኢጋድና የአፍሪካ ሕብረት በተፋላሚዎች ዘንድ ለአሸማጋይነትና ለአደራዳሪነት በአይን ያልሞሉ ሞገስ ያጡ ፤ የአረብ ኤምሬቶችና ሳውዲ አረቢያ ደግሞ ተፋላሚዎችን በፔትሮ ዶላርና በጦር መሳሪያ ጎራ ለይተው በመደገፍ ክስ እየቀረበባቸው ነው።

ጄኔራሎቹ ለጊዜው በትጥቃቸውና በጦራቸው የተማመኑ ቢመስሉም ወደ ድርድር መምጣታቸው አይቀርም ። ወታደሮቻቸው ይጨራረሳሉ ፣ የሀገር ኢኮኖሚ ይደማል ፣ ሰላማዊ ዜጎች ይፈናቀላሉ፣ ይሞታሉ እንጂ የማታ ማታ ሁሉም ጦርነት በሰላም ድርድር መቋጨቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። የአልጀዚራ ዘጋቢ ሸርጂኒያ ፔትሮማርቺ 100 ቀናት ያለፈው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በንጹሃን ላይ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃ መፈጸሙን፤ ጎሳን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንደገና እያገረሹ ሲሆን ጦርነቱም እየተባባሰ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዳይስፋፋ መሰጋቱን ዘግባለች። በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ መካከል ሚያዚያ መጀመሪያ በመዲናዋ ካርቱም የተቀሰቀሰው ግጭት ወደለየለት ደም አፋሳሽ ጦርነት ተባብሶ ወደ ዳርፉር ፣ ኮርዶፋንና ብሉ ናይል ክልሎች እየተስፋፋ ይገኛል።

ጦርነቱን ለማስቆም የተደረጉ ተከታታይ ጥረቶች የሚጨበጥ ውጤት ሳያመጡ የተኮላሹ ሲሆን ተፋላሚ ኃይሎችም ወታደራዊ የበላይነትን ለመቀዳጀትና ገዥ ስትራቴጂካዊ መሬቶችን ለመቆጣጠርና ቁልፍ ወታደራዊና ሲቭላዊ ተቋማትን ለመያዝ ዘግናኝ ደም አፋሳሽ ጦርነት እያካሄዱ ነው ። ሁሉቱም ጄነራሎች ጦርነቱን ድል እናደርጋለን ብለው ስለታበዩ ከየአቅጣጫው የተዘረጉላቸውን የሰላም እጆች መግፋታቸውን የቀጣናው ተንታኞች ለአልጀዚራ ይናገራሉ።

ባለፈው ግንቦት ሁለቱ ተፋላሚዎች ተደራዳሪ ልኡካቸውን ሳውዲ አረቢያና አሜሪካ ወደ ሚያሸማግሉት ጅዳ የላኩ ቢሆንም ድርድሩ ያለ ውጤት ተበትኗል ። ወደ 20 የሚጠጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቀለማቸው ሳይደርቅ ወዲያው ተጥሰዋል ። ለጥሰቱ ተፋላሚዎች እርስበርስ እየተካሰሱ ነው ። በጄነራል አልቡርሀን የሚመራው የሱዳን መንግሥት በጄነራል ሀሜቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ የተኩስ አቁሞቹን በተደጋጋሚ ስለሚጥስ ለአንድ ወር ያህል ከድርድሩ ራሳቸውን አግልለው የነበር ሲሆን ፤ ከ10 ቀናት በፊት የጦሩ ልዑካን ወደ ጅዳ መመለስ እንደተሰማ ድርድሩ ይጀመራል የሚል ተስፋ አጭሮ የነበር ቢሆንም እስካሁን የተሰማ ነገር አለመኖሩን የአልጀዚራ ዘጋቢ ቨርጅንያ ታስታውሳለች ።

ከጅዳው ድርድር ክሽፈት በኋላ የአፍሪካ ሕብረት የማደራደር ፍላጎቱንና ዕቅዱን አቅርቦ የተወሰነ ርቀት መሔድ ቢችልም እንደ ቀደሙት ድርድሮች ሳይሳካለት ቀርቷል ። ድርድሩ ቢሳካለት ኖሮ የተፋላሚ ኃይላትን ተኩስ ከማስቆም ባሻገር በሱዳን ያሉ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ፣ ተቃዋሚዎችንና ጄነራሎችን ያሳተፈ ፖለቲካዊ ንግግር በማድረግ ሁሉንም ያሳተፈ የሲቭል የሽግግር መንግስት ማቆምና በመጨረሻም በምርጫ ላሸነፈ ስልጣኑን ለማስረከብ ያለመ ነበር ይለናል አልጀዚራ።

በአፍሪካ ሕብረቱ ድርድር ከእነ ጄነራል አብድል ፈታህ አልቡርሀንና ጄነራል ሞሐመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሚቲ ጋር ስልጣን ተጋርቶ የነበረውና በመፈንቅለ መንግስት ገለል ያደረጉት የሲቭሉ ጥምረት ተካቶ ነበር ። በጅዳው ውይይት ላይ የሲቭል ጥምረቱ አለመጋበዙ እስከዛሬ ድረስ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል ።በግንቦት መጨረሻ አካባቢ ተፋላሚዎችን ለማደራደር የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ሲቀር ፤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ወይም ኢጋድ እንዲሁ በአዲስ አበባ ያልሰመረ የማደራደር ሙከራ አደረገ ። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካይ ሲገኙ የሱዳን ጦር ኬንያ ገለልተኛ ስላልሆነች አልሳተፍም አለ።

ከሶስት ቀን በኋላ በግብጽ ካይሮ በፕሬዚዳንት ኤልሲሲ የሚመራውን ውይይት ጄነራል አልቡርሃን ድጋፍ የሰጡት ሲሆን ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት የጎረቤት ሀገራት ፤ የአረብ ሊግ ዋና ጸሐፊና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ተሳትፈዋል። የግብጹ ፕሬዝዳንት ዘላቂ የተኩስ አቁም ስለሚደረግበትና ሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ ስለሚመቻችበት እንዲሁም የሱዳን ፖለቲካ

 ፓርቲዎችን ያሳተፈ አካታች ውይይት ስለሚካሄድበት አግባብ ዕቅዳቸውን አቀረቡ። ሀሳቡ ተቀባይነት በማግኘቱ ለተግባራዊነቱ የሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተካተቱበት መድረክ ተመሠረተ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉቱ ተፋላሚዎች መድረኩን ደግፈው መግለጫ አወጡ።

የሱዳንን ደም አፋሳሽ ጦርነት በቅርበት የሚከታተሉት የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ አስተባባሪ አለን ቦስዌል ፤ በዚህ ጦርነት ትብብርና ዲፕሎማሲ ኮስምኖ ለተጽዕኖ የሚደረግ ፉክክር ገኖ ወጥቷል ይላሉ ። በዚህ ዘግናኝ ጦርነት ዲፕሎማሲ ተገቢውን ቦታ ሳያገኝ የቀረው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ ለአሜሪካ የሱዳን የእርስ በርስ ዕልቂት ቀዳሚ አጀንዳዋ ስላልሆነ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ይህን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ እዚህ ግባ የሚባል ጥረት አላደረገችም ይሉናል ቦስዌል።

ተፋላሚ ኃይሎች ላይ ተጽዕኖ በማሳዳር ሰላም ማምጣት የሚችሉ የቀጣናው ሀገራት እርስ በርስ የማይግባቡ መሆናቸው ሌላው ችግር ነው። የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ወይም ዩኤኢ እና ሳውዲ አረቢያ የገቡበት ፉክክርና እልህ እንቅፋት ሆኗል። ካይሮ ከአዲስ አበባና አቡዳቢ ጋር ባላት ወቅታዊ ግንኙነት ንፋስ የገባ መሆኑ ፤ በዴሞክራቶች የሚመራው የባይደን አስተዳደር ከሳውዲም ሆነ ከዩኤኢ ጋር ያለው ግንኙነት የተቀዛቀዘ ስለሆነ፤ በዚህ ውጥረት ላይ ሆነው በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ስለተቸገሩ ፤ ጉዳዩ ባለቤት ያጣ ይመስላል ይላሉ ቦስዌል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ቢያንስ 3000 ሰዎች ተገድለዋል። ሚሊዮኖች ቤት ንብረታቸውንና ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል ። በቢሊዮን ዶላሮች የሚሰላ የኢኮኖሚ ጉዳትም ደርሷል ።የኮንፍሉየንስ አድቫይዘሪ ዳይሬክተርና የሱዳን ጉዳይ ተንታኝ ኮሎድ ኬር በበኩላቸው ግጭቱ ከተቀሰቀሰ አንስቶ በርካታ የማሸማገል ጥረቶች ቢደረጉም ተፈላሚ ኃይሎች አሻፈረኝ በማለታቸው ሱዳናውያን ሰላም ርቋቸዋል ። ጄነራሎቹ የማደራደር ጥረቶችን እንደ ጊዜ መግዣ እንጂ እንደሰላም መንገድ አድርገው አያዩዋቸውም ይላሉ።

ጄነራሎች ራሳቸውን እስከአፍንጫቸው እያስታጠቁና ጦር እያደራጁ ሲሆን አንዱ ሌላውን ለማንበርከክ እየፎከሩ እንጂ ለሀቀኛ ድርድር ዝግጁ አለመሆናቸውን ኬር ይናገራሉ። 2.6 ሚሊዮን ሱዳናውያን የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሲሆኑ ፤ 750ሺህ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል። ሴቶች 12 አመት ያልሞላቸውን ህጻናት ጨምሮ በገፍ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እየተፈጸመባቸው መሆኑንም ሴቭ ዘ ችልድረን ይፋ አድርጓል ። በዳርፉር የአረብ ታጣቂዎች ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር በመተባበር የማሳሊት ጎሳ አባላትን እየጨፈጨፉና የጎሳ ማጽደት ወንጀል እየፈጸሙ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው ይለናል አልጀዚራ።

በምዕራብ ሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት በ2003 ዓም ከ300ሺህ በላይ ሱዳናውያንን እንዳስጨረሰው ሁሉ አሁንም ተመሳሳይ ዕልቂት እንዳይከሰተ ስጋት ፈጥሯል። የምዕራብ ዳርፉር ከተማ በሆነችው ኤል- ጄኔይና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተገድለው በጅምላ የተቀበሩ የ87 ሰዎችን አስከሬን ማግኘቱን በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ገልጿል። ውጊያ በሚካሄድባቸው የካርቱምና የዳርፉር አካባቢዎች ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወታደራዊ የበላይነት ስላለው ወታደሮቹ ይዘርፋሉ ፣ መንደሮችን ወደ ፍርስራሽነት ይቀይራሉ ፣ አስገድደው ይደፍራሉ። በዚህ የተነሳ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተቀባይነት እያጣ ነው።

በጄነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር በቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽር ደጋፊዎች ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን አይደለም ማሸነፍ መገዳደር እየተሳነው ነው። ምንም እንኳ ጦሩም ሆነ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን ሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ባይኖራቸውም በቀላሉ ገሸሽ የሚደረጉ አይደሉም ይሉናል ቦስዌል። ስለሆነም ድርድሩን በማስቀደም ሰላም ማውረድ ከዚያ ደግሞ ሁሉን ያሳተፈ ፖለቲካዊ ምክክር ማድረግ ያሻል። የጦርነቱን ዳራ መለስ ብለን በወፍ በረር እንቃኝ።

በሱዳን መዲና ካርቱምም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚያዚያ 7 ፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ፤ በሀገሪቱ ጦር አዛዦች የስልጣን ሽኩቻ ለወራት ነግሶ የነበረው ውጥረት ጡዘት ውጤት ነው ትለናለች የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ ዘጋቢ ቤቨርሊ ኦቺንግ ። የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች ሲቪል መንግሥት ለማቋቋም ተስማምተው የነበር ቢሆንም በሌተናል ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም በቅጽል ስማቸው”ሔሚቲ”የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል ወይም Rapid Support Forces (RSF) ፤ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት አልቀላቀልም በማለቱ ጦርነቱ ሊቀሰቀስ ችሏል።

ለመሆኑ ጎረቤታችንን ሱዳን እናውቃታለን ። ሱዳን በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ ሲሆን በአኅጉሩ 3ኛ ትልቅ ሀገር ናት ። ስፋቷ ወደ 2 ሚሊየን ስኩየር ኪሎ ሜትር ይጠጋል ። የሕዝብ ብዛቷ 46 ሚሊየን ደርሷል። በዓለማችን ካሉ ጎስቋላና ድሀ ሀገራት አንዷ ናት ። የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 750 ዶላር ይገመታል ።የሱዳን ሕዝብ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን፤ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋም አረበኛና እንግሊዘኛ ነው ። ከ2021 ዓም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሱዳን በጄነራሎች መማክርት የምትመራ ሲሆን፤ የሀገሪቱ ጦር አዛዥና ምክትላቸው የዚህ መማክርት አስኳል ቢሆኑም በመሀላቸው በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ወደለየለት ጦርነት ገብተዋል።

በጦር አዛዡና በሚገርም ሁኔታ በመፈንቅለ መንግሥት ላይ መፈንቅለ መንግሥት አካሂደው ራሳቸውን ፕሬዚዳንት አድርገው በሾሙት አልቡርሀን እና በምክትላቸውና በቀድሞው የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ የዛሬው የRSF አዛዥ ጄነራል ሔሜቲ መካከል ለበላይነት በሚደረግ ሽኩቻ ሱዳን ቁም ስቅሏን እያየች ነው ። ወደ ጦርነት ያስገባቸው ስልጣን በመጠቅለል የሀገሪቱን ሀብትና ጦር ያለአዛዥ ናዛዥ መቆጣጠር መሆኑ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ቢሆንም ፤ ሀገሪቱ በምትመራበት ፍኖተ ካርታና ወደ ሲቭል አስተዳደር ለማምራት ባሰበችው መንገድ ላይም መግባባት አለመቻላቸው እንደምክንያት ይጠቀሳል።

ዋናው ጦር ያማዘዘው ጉዳይ ግን 100,000 የፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል ወይም Rapid Support Forces (RSF) ከሀገሪቱ ጦር ከተዋሀደ በኋላ ማን ይምራው የሚለው ጥያቄ ላይ ሁለቱ ጄነራሎች መግባባት አለመቻላቸው ነው ጦርነቱን የጫረው። ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ጥቂት ሳምንታት በፊት የፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል ባልተለመደ ሁኔታ በመላ ሀገሪቱ እንደ አዲስ መሰማራትና መስፈር መጀመሩ የሀገሪቱን ጦር ስጋት ላይ ስለጣለው ውጥረት መፍጠሩ ይነገራል።

ሆኖም መጀመሪያ አካባቢ በሁለቱ ጄነራሎች ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ በውይይት ይፈታል የሚል ምኞት ነበር ይሉናል። ሚያዚያ 7 ቀን 2015 ዓም የመጀመሪያዋ ጥይት ከተተኮሰች ጀምሮ ቢያንስ ወደ 3000 የሚጠጉ ሲሞቱ ወደ 25000 የሚጠጉ ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ የዶክተሮች ሕብረት ይገልጻል። ጦርነቱ በመዲናዋ ካርቱም የሚገኙ ዋና ዋና የመንግሥት ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚካሄድ ቢሆንም ሰላማዊ ዜጎች ሰለባ እየሆኑና እየተፈናቀሉ ነው። የፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል ሰራዊት ሕዝብ በብዛት ወደ ሚኖርባቸው የከተማዋ ክፍል በመግባታቸው ጦርነቱን አዳጋች አድርጎታል ይላሉ ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ።

የሱዳን አየር ኃይል 6 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ካርቱም የአየር ድብደባ እያካሄደ መሆኑ ከተዘገበው በላይ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሳይሞቱና ሳይቆስሉ እንዳልቀረ እየተሰጋ ነው። የፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል ወይም Rapid Support Forces (RSF) በ2013 ዓም የተመሠረተ ሲሆን ፤ ከዚያ በፊት የዳርፉር አማጽያንን ለመዋጋት በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አልበሽር ይሁንታ የተቋቋመና የጃንጃዊድ ሚሊሽያ በመባል ይታወቅ ነበር። ይህ ቡድን በዳርፉር በዘር ማጽዳት መከሰሱ ይታወሳል ።

በሌተናል ጄነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም”ሔሚቲ”የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ በየመንና በሊቢያ ጦርነት የተሳተፈ ሲሆን ፤ የRSF መሪ ጄነራል ደጋሎ የሀገሪቱን የወርቅ ማዕድን ልማትና ንግድ በበላይነት መቆጣጠራቸውና የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤት መሆናቸው ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደርግ ጭምር መሆኑን ይገለጻል። ፈጥኖ ደራሽ አጋዥ ኃይሉ/RSF/ተደጋግሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ፣ በዘር ማጥፋትና ማጽዳት ይከሰሳል። በ2019 ዓም ለተቃውሞ የወጡ 120 ሰላማዊ ሰልፈኞችን በመግደል ፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን በማቁሰልና በጅምላ በማሰር ተደጋግሞ ስሙ ይነሳል።

በሀገሪቱ ጦር ውስጥ ሌላ ከ100,000 በላይ ሰራዊት ያለው ጦር መኖሩ ውሉ አድሮ የደህንነትና የጸጥታ ስጋት መሆኑ እንደማይቀር ሳይታለም የተፈታ ነው ። ይህ ጦርነት በመፈንቅለ መንግስት ወደ አገዛዝ መጥተው ሱዳንን ለተከታታይ 30 አመታት ቀጥቅጠው የገዙት ኦማር አልበሽር ከአራት አመት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ከተወገዱ በኋላ በሀገሪቱ የረበበው ውጥረት ውጤት ነው ይላሉ ። ፕሬዚዳንት አልበሽር ከአገዛዛቸው እንዲወርዱ የሚጠይቁ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ከተካሄዱ በኋላ መፈንቅለ መንግሥት ብርቁ ያልሆነው የሱዳን ጦር በመፈንቅለ አወረዳቸው ። ሆኖም ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን አጠናክረው በመቀጠል ጦሩ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጥርጊያውን እንዲያመቻች ጫና መፍጠር ጀመሩ ።

ብዙም ሳይቆይ ጦሩንና ሲቭሉን ያካተተ ጊዜያዊ መንግሥት ቢመሰረትም በ2021 ዓም በጄነራል ቡርሀን የተመራ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄደ ። ከዚህ በኋላ ነው የሁለቱ ጄነራሎች የስልጣን ትንቅንቅ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ ይሉናል የሱዳንን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ባለፈው ታህሳስ ወር ስልጣንን ወደ ሲቭሉ ለማስተላለፍ ቢስማሙም በሒደቱ ላይ መግባባት ባለመቻላቸው ከሸፈ ።

ጄነራል ደጋሎ የ2021 ዓም መፈንቅለ መንግሥት ስህተት እንደነበረና ፈጥኖ ደራሹ ጦራቸውም ሆነ እሳቸው ከዚህ በኋላ ከካርቱም ሊሒቃን ጋር እንደማያብሩና ከሕዝቡ ጎን እንደሚቆሙ ቃል ቢገቡም ያመናቸው አልነበረም ። ጄነራል ቡርሀን ጦሩ በምርጫ ላሸነፈ ሲቭላዊ አካል ስልጣን እንደሚያስረክብ ቃል ቢገቡም በተግባር ሲያውሉት አልታየም ። እሳቸውም ሆኑ ሔሜቴና ደጋፊዎቻቸው ስልጣን ብናስረክብ ነገ በሀብታችንና በምንፈጥረው ተጽዕኖ ላይ ሊመጡብን ይችላሉ ብለው ይሰጋሉ።

የእርስ በርስ ጦርነቱ ሀገሪቱን ሊበታትናትና ለማያባራ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊዳርጋት ፤ አጎራባች ሀገራትን ስቦ በማስገባት ቀጣናውንም አኅጉሩንም እንዳያመሰቃቅለው ይፈራሉ ። ሁለቱን ጄነራሎች ለማነጋገር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም እስካሁን የተጨበጠ ነገር የለም ይሉናል የዴፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ወይም ኢጋድ የኬንያን ፣ የደቡብ ሱዳንና የጅቡቲን ፕሬዚዳንቶች ወደ ካርቱም ልኮ ለማሸማገል አቅዶ የነበር ቢሆንም አልተሳካም ። ዩናይትድ ኪንግደም ፣ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ሕብረት እስከ ዛሬ ድረስ ተኩስ ቆሞ ድርድር እንዲጀመር እየወተወቱ ቢሆንም ሰሚ አላገኙም።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ካለፈው ሚያዚያ 7 ፣ 2015 ዓ.ም አንስቶ በተዋጊ ጄትና ሔሊኮፕተር ወይም በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጦርነት እየተካሄደ ከባድ ጉዳትም እየደረሰ ነው ። በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ላይ ሌላ መፈንቅለ መንግሥት በማስተናገዷ ዓለም ተገርሞ ሳያበቃ ፤ አሁን ደግሞ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ገብታለች ። የወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣና ሕዝባዊ አመፅ በማይለያት ሱዳን በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር በ1989 ዓ.ም ፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የተቆናጠጡትን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር የ30 ዓመት አገዛዝ ፤ በ2019 ዓም በሰፊ ሕዝባዊ አመፅ ከተወገደ በኋላ በወታደራዊ ጀኔራሎች እጅ ወድቃ ጦርነት ውስጥ ገብታለች ፡፡

በርካታ ተዋናዮችና እጆች በበዙበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በሱዳን በሁለት ጀኔራሎች በሚመሩ ተዋጊ ኃይሎች መካካከል የተፈጠረው ሰሞነኛ ጦርነት ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በርካቶች ቆስለዋል፡፡ የኦማር አልበሽር ከሥልጣን መወገድን ተከትሎ በሁለቱ የጦር ጄኔራሎች ማለትም የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ፤ ምክትላቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ደጋሎ ስትመራ የቆየችው ሱዳን ፤ በሁለቱ ጄነራሎች መካከል በተፈጠረ “የሥልጣን ሽኩቻ”በዋና ከተማዋ ካርቱም የጀመረው ግጭት ወደ በርካታ ከተሞች መስፋፋቱን ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ ፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች ከአራት አመት በፊት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ያስወገደው ሕዝባዊ አመፅ የሚመኘውን ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ከማቆም ይልቅ፣ እርስ በርስ መወነጃጀልንና ለማይጠረቃው የስልጣን ምሳቸው መሻኮትን መርጠዋል፡፡

የሳምንት ሰው ይበለን !

ሻሎም !

አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *