የተማረው ትውልድ የሥነ ምግባር እሴቶች ህጸጽ ሊታረም ይገባል !

ዘመንን በሚዋጅ እውቀት እና በሥነ ምግባር አስተምህሮ ያልተገራ አእምሮ መቼም ቢሆን አትራፊ ሊሆን የሚችልበት እድልም ሆነ አቅም አይኖረውም። ይኖረዋል ብሎ በዚህ አእምሮ መተማመን ጥፋትን በራስ ላይ እንደ መጥራት የሚቆጠር ነው። ይህን እውነታ ከፍ ባለ ደረጃ ሀገር እና ህዝብን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መመልከት ከተቻለ የችግሩ አሳሳቢነት ከግምት ያለፈ፤ጥፋቱም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

አንድ ማህበረሰብ/የአንድ ሀገር ሕዝብ ዛሬም በስኬት ለመሻገር ከሁሉም በላይ ያለበትን ዘመን የሚዋጅ እውቀት ባለቤት መሆን ይጠበቅበታል። ይህ እውቀት በተጨባጭ የማህበረሰቡን ስኬታማ ትናንቶች መፍጠር የቻለ ፤ ከትናንት ስህተቶች የታረመ እና ነገዎችን ተስፋ ማድረግ የሚያስችል ፤ ከሁሉም በላይ ለማህበረሰቡ እሴቶች የተገዛና እነሱን አጎልብቶ ማስቀጠል የሚችል እንዲሆንም ይጠበቃል።

የዓለም ታሪክ እንደሚያመለክተው ፤ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተፈጠረ ስልጣኔ መሰረቱ እውቀት ነው። እውቀት የተሻሉ ነገዎች ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ከመሆን ጀምሮ ፤ ለዛሬ ማስተማመኛ በመሆን አንድ ማህበረሰብ ከትናንት ወደ ዛሬ በተሻለ ህይወት እና የህይወት መርህ በተስፋ ማሸጋገር የሚያስችለውን ሁለንተናዊ ዝግጁነት የሚያላብሰው ነው ።

ይህ እውቀት በሥነ ምግባር የመገራቱ እውነታ ፤በተለይም የሴራ ፖለቲካ እና የገነገነ እራስ ወዳድነት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እየተላበሰ በመጣበት በዚህ ዘመን እውቀትን እራሱን ከጥፋት የመታደግ ያህል የሚቆጠር፤ ያለ በቂ እውቀት የሚነዱ አጥፊ መንገዶችን በመቀነስ፤ የአንድን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ቀጣይ እጣ ፈንታውን ብሩህ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

በኛ ሀገር ፊደል መቁጠር /መማር/ ከፍ ያለ ግለሰባዊ፣ቤተሰባዊ፣ ማህበራዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው በስፋት ይታመናል ፤ ይህንን ተከትሎም በማህበረሰቡ ውስጥ ለእውቀት /ለትምህርት ያለው መነቃቃት ከፍ ያለ ነው ። በየዘመኑም እንደ ሀገር የደረስንበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረጉ አስተምህሮዎችና እነሱን የሚሸከሙ የትምህርት ሥርዓቶች ቀርጸን ተንቀሳቅሰናል።

በቤተ- ክህነት ከሚጀምረው የቄስ ትምህርት ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመናዊው ትምህርት ፣ ብዛት ያላቸው ዜጎች ፊደል ከመቁጠር እስከ ፕሮፈሰርነት ደረጃ ደርሰው በብዙ መልኩ ለሀገር ተስፋ የሆኑበት ሀገራዊ እውነታ ተፈጥሯል፤ አሁንም እየተፈጠረ ነው። ለዚህም በየዘመኑ የነበረ ትውልድ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። የዛሬውም ትውልድ እየከፈለ ነው።

በተለይም ዘመናዊ ትምህርት ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ መንግሥት ለትምህርት ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት ተንቀሳቅሷል፤ ወላጆችም ቢሆኑ ከጉሮሯቸው እየቆጠቡ ፣ጾማቸውን እያደሩና እየዋሉ ሳይቀር ልጆቻቸው ተምረው ለራሳቸው ፣ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው ተስፋ የሚሆኑበትን እድል ለመፍጠር ረጅም መንገድ ተጉዘዋል።

ይህ ሁሉ በሆነበት ሀገራዊ እውነታ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ የሆነውና እየሆነ ያለው ግን እንደታሰበውና ተስፋ እንደተደረገው አልሆነም፡፡ ከዛ ይልቅ ተማርኩ የሚለው ኃይል ማህበረሰቡ ለረጅም ዘመናት የገነባቸው የሥነ ምግባር እሴቶችን በመሸርሸር ሀገር እያለፈችበት ላለው የግጭትና የሁከት ፣ የጦርነትና የትርምስ ትርክት ዋነኝ ተዋናይ ሆኖ ተገኝቷል ። በዚህም በብዙ ተስፋ ሲጠብቀው ለነበረው ማህበረሰብ የችግርና የመከራ መፍትሄ አመላካች ሳይሆን የስቃይ ምንጭ ሆኗል።

የተማረው ኃይል በትምህርት ያገኘው እውቀት በሥነ ምግባር እሴቶች ያልተገራ እና በህጸጾች የተሞላ በመሆኑ ፤ለመከባበር ከዚህ ለሚመነጭ መደማመጥ የተገዛ ሳይሆን ቀርቷል ፡፡በመናናቅ ከዚህ በሚመነጭ ጥላቻ ለመገዳደልና ለመጠፋፋት የሚተጋ ሆኖ ተገኝቷል። የራስ ወዳድነቱም ደረጃ ሀገርን አደጋ ውስጥ እስከ መክተት የደረሰ ሆኖ በተጨባጭ ተስተውሏል።

ይህ የጥፋት መንገዱ የመማርን ትርጉም ጎደሎ ከማድረግ ባለፈ ፤ ማህበረሰቡ በተማረው ትውልድ ላይ የነበረውን ተስፋና እምነት አሳጥቶታል፤ የመማር ትርጉም ምንድነው ብሎ እንዲጠይቅ አድርጎታል። በሀገሩ ነገዎች ላይ ያለውንና የነበረውን ተስፋ በማቀጨጭ እንዲቆዝም አስችሎታል ፤ በግራ መጋባት ውስጥ ሆኖ የሚይዘውና የሚጨብጠው ነገር እስኪፈልግ አድርሶታል።

ይህ ትናንትና እና ዛሬ በተማረው ትውልድ ላይ የታየውና የሚታየው የሥነ ምግባር እሴቶች ህጸጽ ሊታረም የሚችልበት እድል ካልተፈጠረ ፤ እራሱ የተማረው ትውልድ ሆነ በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ወደ አሰባቸው ብሩህ ነገዎች መድረስ አይችሉም። እንደ ሀገር ከግጭት አዙሪት ወጥተን ዛሬን አጣጥመን መኖር የምንችልበትን ሀገር መፍጠርም አንችልም ።

አዲስ ዘመን ነሃሴ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *