ሕገ ወጥ ስደትን እና የሚያስከትለውን አደጋ ለመግታት

ከዛሬ ይልቅ ነገን ተስፋ በማድረግ፣ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ብዙዎች የወላጆቻቸውን ጥሪት አሟጠው የሌላቸው ደግሞ ከዘመድ አዝማድ በመበደር ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ እንደውም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ልጁን ወደ ውጭ ሀገር ያልላከ ዜጋ እንደ ደሃ ወይም ኋላቀር ስለሚታይ ‹‹እኔስ ከማን አንሼ›› ብሎ መማርና መሥራት የሚችለውን ልጁን ያውም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለስደት መርቆ ይሸኛል፡፡

ሰዎች ስለምን ሕገ ወጡን መንገድ ይመርጡታል? ከተባለ በዋነኛነት በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህም ሕግ በሌለበት ሁኔታ የሕገ ወጥ ደላላዎች ሚና ከፍ ያለ ነው፤ በአማላይ እና በሚያፈዝ ማደናገሪያው ቃላቸው ብዙዎችን የበርሃ ሲሳይ አድርገዋል፡፡

በሀገር ውስጥ በቂ የሥራ ዕድል አለመኖርም ብዙዎች ስደትን እንዲናፍቁ ወይም እንዲመርጡ ያደርጋቸዋል ተብሎ ታመናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀገር ውስጥ ከመሥራት ይልቅ በቀላሉ ወደ ውጭ ሀገር ሄጄ የእራሴን፣ የቤተሰቤን እና የዘመዶቼን ሕይወት መቀየር እችላለሁ ብሎ በማመን በርካቶች ምርጫቸው ያደርጉታል፡፡

ለወትሮም ቢሆን ምርጫው ትክክል ያልነበረው እና በሀገሬ ‹‹አያልፍልኝም ›› ብሎ ያመነው፣ ከዛም ባለፈ በሕገ ወጥ መንገድ የተሰደደ ዜጋ ብዙ ውጣ ውረዶች ብዙ ናቸው፡፡ ዳግም የሀገሩን መሬት ሳይረግጥ የበረሀ ሲሳይ ሆኖ ሊያልፍ የሚችልበት ክስተት ብዙ ነው፡፡

ከዚህ ሲሳይ የተረፉት ደግሞ ባህር ላይ ባሉ ወንበዴዎች የሰውነት አካላቸው ዋጋ ተቆርጦለት ለሽያጭ ከመቅረብ ባሻገር አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው ለከፋ የጤና ችግር መዳረጉ የተለመደ ነው ፡፡ አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ስደተኛ ልጆቻቸው በሕይወት ይኖሩ ወይም ይሙቱ ባለማወቃቸው በተስፋ ዘወትር ደጅ ደጃቸውን እንዲያማትሩ ግድ ብሏቸዋል፡፡

በሀገራቸው ተከብረውና በፍቅር ይኖሩ የነበሩ ወንድም እህቶቻችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በሕገ ወጥ መንገድ ተሰደው የሰውነት ክብራቸውን አጥተው ብዙ መከራና ግፍ ደርሶባቸዋል ፡፡ በተለይም ወደ አረብ ሀገር የሚሄዱ ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች በአሰሪዎች መደብደብ፣ መደፈር፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ ክፍያ መከልከል ያጋጥማቸዋል።

ከፎቅ ላይ መወርወር፣ ‹‹ሕገ ወጥ ናችሁ ›› ተብለው በፖሊስ የተያዙት በተጣበበ እንዲሁም በተፋፈገ ቤት ውስጥ አጉሮ በማሰር አስከፊ ስቃዮችን የማሳለፍ ክስተት በስፋት ያጋጥማቸዋል ፡፡ ምናልባትም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እስካሁን ባለመቆሙ ምክንያት ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች ዛሬም ድረስ የሚደርስባቸው ሰዎች አሉ ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

አሁንም የተለያዩ አደናጋሪ ሃሳቦችን በማህበራዊ ሚዲያ በመልቀቅ ዜጎች ሕጋዊ በሚመስል ነገር ግን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አውሮፓ በትምህርት ዕድል ስም ፣ ሀገራቱ በብዙ የሥራ ዘርፎች ሰዎች ይፈልጋሉ በሚል የብዙ ቤቶች ጥሪት ተሟጧል፡፡ በለስ ቀንቷቸው ወደ ሀገራቱ የደረሱት ደግሞ የተባለው የትምህርት ወይም የሥራ ዕድል ቀርቶ የጎዳና ተዳዳሪ፣የአእምሮ ታማሚ እንዲሁም ተመጽዋች ሆነው ታይተዋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ሕጋዊ መንገዶችን በመከተል ነገን የተሻለ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ መንገድ የሄዱት ዜጎች ከቤተሰባቸው ጋር እስከወዲያኛው ሳይቆራረጡ፣ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት በመቀየር ምሳሌ መሆን ችለዋል፡፡

ሕይወት ብዙ መንገዶች እንዳሏት ያመኑት እና የተረዱት ደግሞ ሀገራቸውን ሳይለቁ እንዴት መሥራት እንደሚቻል ምሳሌ መሆን የቻሉ ብርቱዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንደ አማራጭም ሕጋዊን መንገድ በመከተል ወደ አረብም ይሁን ወደሌሎች ሀገራት በማቅናት በተሻለ ክፍያ፣ ግፍ እና እንግልት ሳይደርስባቸው እንዲሁም አካላቸው ላይ ጉዳት ሳይደርስ፣ ሕይወታቸውም ሳያልፍ ወገናቸውን እና ሀገራቸውን መጥቀም ችለዋል፡፡

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስብስብነት እና በድርጊቱ ላይ ሰፊ የሚባል ሰንሰለት ያለው መሆኑን በመረዳት በመንግሥት በኩል ብዙ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለአብነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተጓዙባቸው ሀገራት በችግር እንዲሁም በእስር ላይ ያሉ ዜጎችን ለሀገራቸው መሬት ለማብቃት ያደረጉት ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣በግል ድርጅቶችና ግለሰቦች አማካኝነት ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው የተደረጉ ሰፊ ንቅናቄዎች የሚታወሱ ናቸው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ፈራሚ ስትሆን፤በዚህም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም በሰዎች መነገድ ከባድ ወንጀል እንደሆነ አምና የተቀበለች ሀገር ናት፡፡ድርጊቱን ለማስቆም የሚወጡ ሕጎችን ፣ፖሊሲዎችን መመሪያዎች በመፈተሽ ብሎም ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ ሀገር ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳይ መቀነስ ይገባል፡፡ ለዚህም በሕገ ወጥ ደላሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር የተሻለ ቅንጅታዊ አሠራር እንዲኖር በማድረግ ለተጎጂዎች (ከስደት ተመላሾች) የሚሰጡ አገልግሎቶች በተሻለ አግባብ ሊቀርቡ የሚችሉበትን አሰራር መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረግ ማንኛውም ዝውውር ገንዘብን፣ ጉልበትን፣ጊዜን እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት የሚነጥቅ ድርጊት መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ድርጊት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እጃቸው ያለበት ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ድርጊቱ አስከፊ መሆኑን እንዲያውቁ፤ሕጋዊውን መንገድ እንዲከተሉ የግንዛቤ ሥራዎች መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው፡፡

በሀገር ውስጥ የሥራ እድሎችን በስፋት መፍጠር፣ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ለስደት ያለውን የተዛባ አመለካከት ማቅናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ችግሩን ለዘለቄታው ለመከላከል ዋነኛው አቅም ነው። ከዚህ ውጪ ዜጎች ለሥራም ይሁን ለትምህርት ወደ ባህር ማዶ የሚያደርጉት ጉዞ ሕጋዊ መንገድን ብቻ የተከተለ እንዲሆን መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡

በምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *