ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ወር ላይ የ22 ዓመቷ የኢንጅነሪንግ ተማሪ አሊያ ሳላህ ሰልፍ በወጡ ሰዎች መካከል ሆና እየዘፈነች የተነሳችው ፎቶግራፍ ሴቶች በተቃውሞው ላይ ያላቸውን ተሳትፎ አጉልቶ በማሳየቱ የአለምን መገናኛ ብዙሀን ቀልብ ስቦ ከርሟል፡፡ የአለም መገናኛ ብዙሀን ከፎቶው በኋላ የሱዳን ተቃውሞ ላይ ትኩረታቸው ጨምሯል፡፡ አሊያ ወዲያው የተቃውሞው ምልክት ተደርጋ ተወሰደች፡፡ እሷ ያነሳችው ፎቱ ሙስሊም ሴቶች በፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ያሳየ ነበር፡፡ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በአሊያ ድርጊት ስርዓቱ እንዲወድቅ የሴቶች ተሳትፎ ያልተጠበቀና ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሱዳን ተቃውሞ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ሴቶች ቀደም ብሎ በአገሪቱ በነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው የሚታወስ ነው፡፡
በሱዳን ታሪክ ውስጥ ታዋቂ እና ተቀባይነት ያላቸው ሴቶች ያሉ ሲሆን ካናዳካ (የኑቢያ ንግስት) ስትሆን በወታደራዊ ስልት ታዋቂነት ያተረፈችው ከክርስቶስ ልደት በፊት 332 ላይ ታላቁ አሌክሳንደር የሰነዘረውን ጥቃት መመከት በመቻሏ ነው፡፡ ሌላዋ ደግሞ ዶክተር ካሃሊድያ ዛሂር በሱዳን የመጀመሪያዋ ዶክተር ስትሆን በእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ወቅት ተቃውሞ በማንሳቷ እአአ 1946 ላይ ታስራ ነበር፡፡ ፋጡማ ኢብራሂም ታዋቂ የኮሚኒስት አቀንቃኝ በመሆኗ የሱዳን የሴቶች ህብረት መሪ ተደረገች፡፡ ፋጡማ የሱዳን ሴቶች የመምረጥ፣ የእኩል ክፍያና የወሊድ ፈቃድ እንዲኖራቸው ሰፊ ትግል አድርጋለች፡፡
በጋዚራና በዳርፉር የሚገኙ ሴቶች በመካከለኛውና በሰሜን ሱዳን ታዋቂነታቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡ የሴቶቹ ዋነኛ ስራ የአምባገነን ስርዓት በመቃወም ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ ማድረግ ነው፡፡ በሱዳን ለአስርት ዓመታት ፖለቲካው በአንድ ወገን የተያዘና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተንሰራፋባት አገር ነች፡፡ በዚህ ሁኔታ አሊያ የታዋቂ ሴት ልጅ አደለችም፤ ነገር ግን አሁን ያለው ትውልድ አካልና በሱዳን አስተዳደር የተማረረች ሴት ነች፡፡ እሷና መሰሎቿ ለክብርና ለነፃነት ተቃውሞ ማሰማት ከጀመሩ በኋላ ቀስ በቀስ የአገሪቱን አስተዳደር ወደ መቃወም አመሩ፡፡
አብዛኛው መገናኛ ብዙሀን ስለ አሊያ የፃፈ ቢሆንም በተቃውሞ ወቅት የተናገረችውን ግን ማንም ትኩረት አልሰጠውም፡፡ በወቅቱ አሊያ ‹‹በሀይማኖት ስም እንታሰራለን፣ እንቀጣለን እንዲሁም እንገደላለን›› በማለት በመዝፈን እና የታዋቂውን ገጣሚ አዛሂር መሀመድን ግጥም በማነብነብ ድምጿን አሰምታለች። ‹‹ነገር ግን እስልምና ንፁህ ነው፡፡ እስልምና እምነት አምባገነኖችን መታገል እንደሚገባ ይናገራል፡፡ ጥይት ሳይሆን የህዝብ ዝምታ ነው የሚገድለው›› የሚሉ መፈክሮችንም ተናግራለች፡፡ አሊያስ ያደረገችው ድርጊት የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ እሷ ህዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ያደረገችው ድርጊት የሱዳን ሴቶች ተዋጊዎችና ተቀባይነት ያላቸው መሪዎች ሲሞቱ ሰዎቹን ለማሰብ ግጥም በማቅረብና በመዘመር የሚያደርጉት ባህላዊ ሁነት ነው፡፡
ሱዳናውያን የታዋቂዋን የኑቢያ ጊዜ ገጣሚ ሜሂራ ቢንት አቦዱ ግጥም የተጠቀሙበት ሲሆን፤ ግጥሙ ቀድሞ ብሎ የሱዳን ተዋጊዎች ከወራሪው የግብፅ መሪ ካዲፍ መሀመድ ፓሻ ነፃ ለመውጣት እንደማበረታቻ ተጠቅመውበታል፡፡ በተጨማሪም በሱዳን ነፃነት መባቻ አካባቢ ከኮርዶፋን አካባቢ ሃዋ አል ታግታጋ የተባለ ዘፋኝ የሱዳን ብሄርተኝነትን የሚደግፍና ቅዥ ግዛትን የሚቃወም ዘፈን በአትባራ በሚገኝ ትያትር ቤት በመዝፈኑ ታስሮ ነበር፡፡ በጣም አስፈላጊው ነገር የሚቀርቡት ግጥሞች ቀድም ባሉ ጊዜ የተሰሩ ሲሆን አሊያ እንደሌሎቹ የሱዳን ነፃነት ፈላጊዎችና አስተዳደሮቻቸውን እንደሚቃወሙ ሰዎች ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ህዝቡ ዝም እንዲልና እንዲፈራ ተደርጓል ብላ ታምናለች፡፡ እአአ 1992 ኦማር አልበሽር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አድርገው ስልጣን ከያዙ ሶስት ዓመት በኋላ የእስልምናን እምነት መሰረት በማድረግ ህዝባዊ ማዕቀብ በሁሉም ክልሎች አውጀዋል፡፡
ይህ አዋጅ የአገሪቱ ደህንነት አባላት ሱሪ የሚያደርጉ፣ ጸጉራቸውን ያልተሸፈኑ፤ የወጣ ዘፈን የሚዘፍኑ እንዲሁም ከወንድ ጓደኞቻቸው ጋር የሚዝናኑ ሴቶችን እንዲያስሩ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ በዚህም የደህንነት አባላቱ ሴቶችን በመተንኮስና ሴት ጋዜጠኞችን ያስሩ ነበር፡፡ እንዲሁም ዘፋኞችና አስተዳደሩን የሚቃወሙ ሁሉ በአዋጁ ሰበብ ታስረዋል፡፡ እአአ 2009 ላይ ጋዜጠኛ ሉብና አል ሀሰን በአስተዳደሩ ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘርዋ ሱሪ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ አድርጋ ተንቀሳቅሳለች በሚል አርባ ጅራፍ ግርፋት ተፈርዶባት ነበር፡፡ ነገር ግን በፍርድ ቤት ባደረገችው ክርክር አሸንፋለች፡፡ በዚሁ ዓመት ደቡብ ሱዳናዊቷ የክርስትና እምነት ተከታይዋ የ16 ዓመቷ ሶሊቫ ካሺፍ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ አጭር ቀሚስ አድርጋለች ተብሎ 50 ጊዜ እንድትገረፍ ተደርጓል፡፡
ይህ የህዝብ ተአቅቦ አዋጅ በዋናነት በስራ ላይ የሚገኙ ሴቶችን ለመቆጣጠርና የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው፡፡ እአአ 2017 በካርቱም ናይል መንገድ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ሻይ በመሸጥ የሚተዳደሩ 380 ሴቶች እንዲታገዱ ተደርጓል። ሴቶቹም የምግብና መጠጥ ማህበር በመመስረት ትግል አድርገው እገዳው እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ በአሁን ወቅት ተመሳሳይ የሆኑ ማህበራት የሱዳንን አስተዳደር ከፊት በመሆን እየተቃወሙ ይገኛሉ፡፡ ሀይማኖትና የአረብ ዝርያ በሱዳን ሁሉም አካባቢዎች አስተዳደሩ ህዝቡን ለመቆጣጠርና ለመጫን እየተጠቀመበት ያለ መሳሪያ ነው፡፡ አብዛኛው የሱዳን ባለስልጣናት ይህን አሰራር ለግል ፍላታቸው አውለውታል፡፡
የደቡብ ሱዳናዊቷ አክቲቪስት ሮሴልይን ኦይካ እንደምትናገረው፤ የሰሜናዊ ሱዳን መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በሀይማኖት የተገደበ ፖሊሲና በዋና ከተማውና በአካባቢ ብቻ ሀብት እንዲከማች በማድረግ ሌላው አካባቢ እድገት እንዳይኖር ይፈልጋሉ፡፡ እአአ 1980 ደቡባዊ ሱዳን አካባቢ ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ በአምባገነኑ ሱዳን መሪ ጋፋር ኒሜሪ ላይ ተነስቶ ነበር። ኒሜሪ የእስልምና ህጎችን ብዝሀ ሀይማኖት ባለበት አካባቢ ለመተግበር በመሞከሩ ተቃውሞ ስለገጠመው ነፁሀን ዜጎችን በማሰር፣ በማሰቃየት እንዲሁም በመግደል ፍላጎቱን ለማስረፅ ሞክሯል፡፡ አይካ እንደምትለው ከሆነ እአአ 1980 የአረብና የእስልምና ትምህርቶች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደ ግዴታ መወሰድ የለበትም የሚል ተቃውሞ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በወቅቱ እሷ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ የነበረች ሲሆን በተቃውሞ የነበሩት ዋነኛ ጥያቄዎች የነበሩት ማግለሎች እንዲቆሙ ነበር፡፡
ወቅቱን ስታስታውስ ‹‹የወታደራዊ ታንኮች ወደ ተቃዋሚዎቹ በማስጠጋትና መሳሪያ በመደገን ያስፈራሩ ነበር›› ትላለች፡፡ ወታደሮቹ ከሰሜናዊ ክፍል የመጡ ሲሆኑ ተቃውሞ ያሰሙ ተማሪዎች የወታደሮቹን ትዕዛዝ አንፈፅምም በማለታቸው ወደ ላይ ሲተኮስ ሁሉም የሞተ እንደመሰላትም ትናገራለች፡፡ አይካ በእሷ ወቅት የነበሩ ሴቶች አስፈላጊ የሆነ ሚናቸውን በመወጣታቸው ሰብዓዊ መብት ጥሰት መቀነሱንና በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲመጣ በማድረጋቸው ታመሰግናለች፡፡ በተመሳሳይ በዳርፉር የሴቶች ግጥም ታሪካዊ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሚናውን ጦርነትን በማበረታታትና በማብረድ ተወጥቷል፡፡ በቅርብ ዓመታት በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት በተደረገ ጥረት በግልፅ የአገሪቱን አስተዳደር አካላት ሲተቹ ነበር፡፡
በደቡብ ሱዳን ሴቶች በታጣቂ ቡድን ውስጥ አባል ሆነው የገቡ ሲሆን በተለይ በኑባ ተራራና በሌሎች አካባቢ በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ሴቶች በደቡባዊ ነፃነት እንቅስቃሴ ወይም ታጣቂ ቡድን ውስጥ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በተለይ በሁለተኛው የርስ በርስ ጦርነት ሚናቸው የጎላ ነበር፡፡
በካርቱም ሴቶች ለተቃውሞ ወደ አደባባይ ሲወጡ በሌሎች የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሴቶች ከወንዶች ጎን ቆመዋል፡፡ በዚህም በአልበሽር የደህንነት አባላት በጭካኔ ተደብድበዋል፡፡ ሴት ተቃውሞ አሰሚዎች ታስረዋል፣ ተሰቃይተዋል፤ እንዲሁም ተገድለዋል፡፡ ብዛት ያላቸው ሴት ታሳሪዎች በፀጥታ አስከባሪዎች የመደፈር አደጋ ገጥሟቸዋል። የአልበሽር መንግስት እንደዚህ አይነት ጭካኔ የተሞለበት አካሄድ በተቃዋሚዎች ላይ ሲወሰድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በደቡብና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ በሆነ ደረጃ ተቃውሞዎችን ሲያፍን ነበር። ለአስርት ዓመታት በአስቸኳይ አዋጅ ሽፋን የከፋ ጭፍጨፋ በንፁኀን ዜጎች ላይ ተደርጓል። በተጨማሪም በሲቪክ ማህበራት ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ተሰንዝሯል፡፡
በአሁን ወቅት ህዝባዊ ተቃውሞዎች የአለምን ቀለብ ስበዋል፡፡ በገጠር የሚገኙ ሴቶች ስለ አካባቢያቸው ባለስልጣናት በድፍረት መናገር ጀምረዋል፡፡ ከዋናው ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎችም ህዝቡ በነፃነት የተሰማውን በአደባባይ እያሰማ ይገኛል። አንዳንድ ሴቶች ከሚኖሩበት ገጠራማ ስፍራ ወደ ካርቱም በመጓዝ ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል። የፖለቲካና የፍትህ ጥያቄያቸው እስኪመለስ እስከመጨረሻው የሚታገሉ መሆናቸውንም በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
በተጨማሪም፤ በአገሪቱ መከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ከዳርፉር የመጡ ሴቶች ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፤ ከተቃዋሚዎቹ መካከል አንዷ እንደተናገረችው የሴቶች ህመም በተለይ የእናቶች ስቃይ ባለፉት አራት ወራት የበዛ ነበር፡፡ እአአ 2003 በደቡብ ዳርፉር በመንግስት ታጣቂዎች በተደረገ ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ መደፈር እና ሞት የተለመዱ የእለት ተእለት ተግባራት ነበሩ፡፡ በሴቶች ላይ የሚደረገው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ከልክ ያለፈ ሲሆን በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ አካላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ሴቶቹ በተቃውሟቸው ወቅት አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2011
መርድ ክፍሉ