ውስጧን አንባቢ- በሥራ ተርጓሚ

ሕይወቷን ሙሉ ለዲዛይኒንግ ሙያ ሰጥታለች። ወደ ሙያው ከገባች 30 ዓመታት ተቆጥረዋል። ዲዛይኒንግ በኢትዮጵያ እምብዛም ሳይታወቅ ጀምሮ ሙያው ላይ ነበረች። ሥራውን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጋለች። ዘርፉን ማሳደግ ቀላልና በእሷ ጥረት ብቻ የሚሳካ እንዳልሆነ የገባት ግን ዘግይቶ ነበር። በጊዜው ሞራሏ ተነክቶ ችላ ብላ ብትተወውም ‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው ›› እንዲሉት ሆኖ እንደገና ወደ ሥራው እንድትመለስ አጋጣሚዎች ምክንያት ሆኖታል።

የእጅግ ጥበብ መስራችና ባለቤት ዲዛይነር እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ፤ የዲዛይኒንግ ሙያን እውቀትና ክሂል በሚገባ ጠንቅቃ የተማረችው ባህር ማዶ በግሪክ ሀገር ነው። ይሁን እንጂ ሙያውን ከእናቷ የወረሰች ነው። እናቷ የእጅ ሥራ፣ ፈትል እና መሰል ጥበባዊ ሥራዎች ባለሙያ ናቸው። አዘውትረው ሀገር ልብስ ይለብሱ ነበር ።

በልጅነቷ ይህንን እያየች በማድጓ ሙያ በውስጧ እንዲቀረጽ ሆኗል። ዲዛይነር የሚለውን ሙያ አትረዳውም እንጂ የምታየውም የምትስራው ነገር ሁሉ ከዲዛይን ጋር የተያያዘ እንደነበር ታስታውሳለች። ልብሶቿ ሳይቀር ቀዳ በምትፈልገው መልኩ ታሰፋ እንደነበርም አትረሳውም።

ተማሪ ሳለች የልብስ ስፌት ማሽን ገዝታ ዝም ብላ አስቀምጣም ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ስለዲዛይኒንግ ሙያ ምንም፣ አይነት እውቀት አልነበራትም። ወደፊት ዲዛይነር እሆናለሁ ብላም አስባም አልማም አይደለም። እንዲሁ ሳታወቀው ግን በሙያው ፍቅር ተንድፋ ነበር።

የእጅጋየሁ የትውልድ ቦታ አዲስ አበባ ከተማ ቢሆን አባቷ ወታደር ስለነበሩ በሕጻንነት እድሜዋ ወደ ሐረር ይዘዋት ስለሄዱ እድገቷን ወይም የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው ሐረር ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም እዚያው ሐረር ተከታተላለች። ከዚያም በቤተሰቦቿ ሥራ አማካኝነት ወደ ሀገር ግሪክ አቅንታለች።

የቀለም ትምህርቷን በግሪክ ‹‹ኢሮፒያን›› ኮሌጅ ተብሎ በሚጠራ ትምህርት ቤት ገብታ ለመማር በቅታለች። በዚህ ጊዜ ነበር ለጥበብ እንደተጠራች ያወቀችው። ምንም ሳታውቀው በውስጧ ተዳፈኖ የነበረው ውስጣዊ ፍላጎት ከአቅሟ በላይ ሆኖ ገንፍሉ እንዲታይ የሆነ። በአጋጣሚ በግሪክ ላገኘቻቸው ኢትዮጵያዊት ሴት ይህንን ውስጣዊ ስሜቷን፣ ለአርት ያላትን ፍቅርና ፍላጎቷን ተነፈሰች። ሴትዬዋ ፍላጎቷን በመረዳት ወደ ዲዛይን ትምህርት ቤት ይዘዋት ሄዱ። የዲዛይኒንግ ሙያ መግቢያ በሩንም ጠረጉላት።

የሄደችበት ትምህርት ቤት ቀደም ሲል የአሜሪካ ሴቶች የዲዛይኒንግ ትምህርት ቤት የነበረ። በወቅቱ ግን አሜሪካዊያን ለቀው በመሄዳቸው ወደ ግሪክ ሴቶች ትምህርት ቤት ተቀይሯል። ትምህርቱ የሚሰጠው ‹በሄሌኒካ› ወይም በግሪክ ቋንቋ ነበር። እጅጋየሁ ወደ ሀገር ግሪክ ከሄደች ስድስት ወር ብቻ ያስቆጠረች በመሆኑ ቋንቋውን አትችለውም። ትምህርቱን የመማር ፈተና የገጠማት ያኔ ነበር።

ቋንቋውን ካላወቀች መማር እንደማትችል ቢገለጽላትም እጅጋየሁ ግን ውስጣዊ ፍላጎቷ አይሎ ስለነበረ ቋንቋውንም ባላውቀው እማራለሁ ብላ ድርቅ አለች። ከዚያም ጎን ለጎን ቋንቋውን የሚያስተምራት አስተማሪ ተቀጥሮላት ትምህርቷን ቀጠለች። ፍላጎቷን የተረዳቻት አንዲት መምህርት ትምህርቱን እንድትማር ረዳቻት።

የዲዛይን ትምህርቱ ረጅም ጊዜ የሚወስድና ረጅም ሂደት ያለው ቢሆንም ለእጅጋየሁ ግን ከሦስት ወራት በኋላ ቋንቋም አላስፈለጋትም። የተግባር ትምህርቱን በሚገባ መወጣት ቻለች። ትምህርቱንም ለሦስት ዓመት ያህል ተምራ አጠናቀቀች።

ውስጣዊ ፍላጎቷን ለማሳካት ይህንን ሁሉ ዋጋ ከፋላ ያገኘችውን እውቀት እና ክህሎት ይዛ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው እጅጋየሁ፤ ዋና ትኩረቷን ያደረገችው ወደ ሀገሯ መመለስን እና በሙያዋ መሥራት ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስም ሥራዎቿን ለመሥራት የሚረዷትን ለዲዛይኒንግ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ የስፌት ማሽን፣ ኦቨር ሎክ ማሽን እና ጨርቃ ጨርቅ ይዛ ነበር።

እጅጋየሁ፤ በግሪክ ሀገር ያገኘችውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅማ የዲዛይኒንግ ሙያን በማስፋፋት ለበርካቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ ስለነበራት ልክ እንደተመለሰች በቀጥታ ወደ ሥራው ገባች። ‹‹እጅግ ጥበብ›› የሚለውን ድርጅቷን በመመስረት የተለያዩ ዲዛይን ያላቸውን አልበሳት በመሥራት ሥራዋን በትጋት ቀን ከሌሊት መሥራት ቀጠለች።

ወቅቱ በ1987 ዓ.ም ነበር። ያን ጊዜ የነበረው አቤክስ ሆቴል የፋሽን ትርዒት በማዘጋጀት ዲዛይን ያደረገቻቸውን አልባሳት (ሥራዎቿን) ለእይታ ማብቃት ችላለች። ይሁንና በጊዜው ለፋሽን ትርዒት የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ የጠበቀችውን ያህል ውጤት ማግኘት አልቻለችም። እንዲያውም ለሥራው ያላትን ፍቅርና ሞራል የሚጎዳ ሁኔታ ገጠሟት ነበር። እጅጋየሁ የነበረውን ሁኔታ ስታስረዳም ‹‹እኔ እዚያ አይቼ የመጣሁትን፣ ማድረግ የፈለኩትና የነበረው ተቀባይነት አይገናኝም። ይልቁንም ሞራልን የሚገድል ነበር›› ትላለች።

ሥራው ብዙ ተግዳሮት ያለውና ፈታኝ እንደነበር የገባት እጅጋየሁ፤ ሙያውን ትታ ማንኛውንም አይነት ልብስ ዲዛይን እስከ መሥራት ደርሳለች። ነገር ግን ጊዜ የማይፈታው ነገር የለምና ወደ ሥራ እንድትመለስ የሚያደርጋት አጋጣሚ ተፈጠረላት። ይህም የ2003 ዓ.ም ‹‹ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ›› የቆንጅና ውድድር ነበር። በዚህ ውድድር የቁንጅና ተወዳዳሪዎቹን ልብስ ዲዛይን በማድረግ እንደገና ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪው ተመልሳ እንድትገባ ሆናለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሙያዋ በሥራዋ አድጎ ሥራዋቿን በትጋትና በጥራት መሥራት ቀጥላለች።

‹‹የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎችን ሀገር ልብስ ዲዛይን ካደረጉ በኋላ ወደ ሽመና ሥራ ገባሁ›› የምትለው እጅጋየሁ፤ በወቅቱ ያጋጠማት ተግዳሮቶች ወደ ልዩ ፍላጎቷና ህልሟ እንዳስገባት ትናገራለች። በቁንጅና ውድድር ላይ የሚሳተፉት 26ቱም ተወዳዳሪዎች አንድ አይነት ዲዛይን ያለው እና አንድ አይነት ጥበብ መልበስ ስለነበረባቸው እነዚህን አልባሳት ዲዛይን አድርጎ ለማሰራት ትልቅ ተግዳሮት ገጠማት እንደነበር ታስታወሳለች።

ልብሱን የሚሰራ ሸማኔ ማግኘት እና ሸማኔው ተገኝቶ እንኳን ልብሱ ቢሰራ በቀለም ወይም በሚፈልገው መጠን አንድ አይነት ነገር ማግኘት በወቅቱ የገጠማት ፈተናም እንደነበር ታወሳለች። ይህ ደግሞ ከፍተኛ በእልህና ቁጭት ሥራዋን እንድትጀምር ያስቻላት ነው። ስለዚህም መኖሪያ ግቢዋ ውስጥ ቤት ሠርታ ከሁለት ሸማኔ ጋር በመሆን ሥራዎቿን መሥራት ቀጠለች።

የሽመና ሥራውን በውስጣዊ ደስታ ተሞልታ ትሰራ ስለነበረ ይህም የምትፈልገው ሥራ እንድትሰራ በእጅጉ እንዳገዛት ታነሳለች። ‹‹ይሄ ሥራ ብዙ ነገር ጠቅሞኛል። ያስጀመርኩት ሥራ ቀለሙ ካላማረኝ ሥራውን እንዲቋረጥ አድርጋለሁ። የሚበላሸው የእኔ ክር ነው፤ ለጉልበታቸው እከፍላቸዋለሁ። በዚህም ውስጤ የሚፈልገውን ነገር መሥራት ጀመርኩ። ይሄ ሥራ ውስጤን አረካኝ፤ እስከ እኩለ ሌሊቱ ድረስ ቆይቼ እስራ ነበር›› ትላለች።

ከሸማኔዎቹ ጋር የምታደርገው የሥራ ቅርርብ ደግሞ የሽመና ሙያን ጠንቅቃ እንድታወቅ ረድቷታል። አሁን ላይ በደንብ ተግባብታ የምትሰራው ሥራ እንደሆነም ትናገራለች።

በትንሽ የቀበሌ ቤት የሀበሻ ልብስ ትስራ የነበረችው እጅጋየሁ፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ልብስ ለመሥራት ጨረታ አሸንፋ ሥራውን ስትጀምር ማምረቻ ቦታዋ በጣም ጠባብ ነበር። በዚህም ማምረቻ ቦታ ለማግኘት ያላንኳኳችው የመንግሥት በር አልነበረም። ከብዙ ጥረትና ልፋት በኋላ ግን ማለትም ከአራት ዓመታት ምልልስ በኋላ አሁን እየሰራችበት ያለውን የማምረቻ ቦታ(ሼድ) አግኝታለች።

ሥራዎቿ ለማስፋት ግን የሽመና ሥራ የሚሰራበት ሌላ ተጨማሪ ቦታዎች ያስፈልጋት ነበር። በአጋጣሚ አርባ ምንጭ የመጎብኘት እድል አግኝታ ስለነበር አርባ ምንጭ የሚገኙ 33 ሸማኔዎች በማደራጀት ባሉበት ቦታ ሆነው ሥራ እንዲጀመሩ አድርጋለች። ሸማኔዎቹም ከአዲስ አበባ በየሳምንቱ እና በየአስራ አምስት ቀናት ጥሬ እቃ ይላክላቸዋል፤ ይሸምናሉም። በዚህ ሁኔታም ችግሯን ፈታለች።

እዚህ በሚገኘው የማምረቻ ቦታ ሌሎቹን ሥራዎቿን ታከናውናለች። በዚህም ዲዛይን የሚያወጡ ሦስት ሸማኔዎች እንዳሏት ትናገራለች። ለሥራዎቿ የምትጠቀምባቸው ማሽኖች ከልማት ባንክ በብድር ያገኘቻቸው ቢሆንም አሁን እዳውን ከፍላ በማጠናቀቋ የራሷ አድርጋቸዋለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ልብስ ዲዛይን በማድረግ ለሰባት ዓመታት ያህል የሰራችውና አሁንም እየሰራች የምትገኘው እጅጋየሁ፤ ልብሶቹን ዲዛይን ከማድረጓ በላይ ክር በመምረጥ ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ በጣም በጥንቃቄና በጥረት እንደምትሰራ ትናገራለች። አሁን ላይ የምትፈልገውን አይነት ሽመና ለመሥራት ባህር ዳር ‹‹ጣና ዌቪንግ›› ከሚባሉ የሽመና ሥራን ከሚሰሩት ሸማኔዎች ጨርቅ በማምጣት፤ እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ደግሞ ‹‹ጃኖ የሽመና ሥራ›› የተለያዩ ጨርቆችን በፈለገችው መጠንና ቀለም ሰርተው እንዲያቀርቡላት በማድረግ ሥራዎቿን ትከውናለች።

እጅጋየሁ ማንኛውም ሰው የሚለብሳቸውን ጃኬት፣ እስካርፖች፣ የዘወትር ልብስ፣ ጫማ እና የመሳሳሉትን በራሷ ዲዛይንና ቀለም ትሰራለች። ባህላዊ የሆኑ አልባሳትንም እንዲሁ ባህላዊነታቸውን ሳይለቁ በመሥራት ታቀርባለች። ‹‹ልብስን በማሸመን የዘወትር ልብስ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ የእኛ ልብሶች አብዛኛውን ጊዜ የሚለበሱት በበዓላት ወቅት ነው፤ አሁን ላይ ይሄንን ለውጪዋለሁ። ሽመናውን በመለወጥ ማንም ሰው ዘወትር የሚለብሰው ልብስ አድርጌዋለሁ›› ትላለች።

እጅጋየሁ በአርባ ምንጭ ለ45 ሸማኔዎችና ለአምስት ጥጥ ፈታይ ሴቶች የሥራ እድል የፈጠረች ሲሆን፤ በአዲስ አበባ በሚገኘው ማምረቻው ደግሞ 30 ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥራ እያስራች ትገኛለች።

‹‹ምርቶች ወደ ውጭ መላክ (ኤክስፖርት) ከባድ ነገር ነው፤ እኔ ዘው ብዬ መግባት አልፈልግም፤›› የምትለው እጅጋየሁ፤ አሁን ላይ ግንኙነት በመፍጠር ወደ ውጭ ሀገር የምትልካቸው ልብሶች እንዳሉና እነዚህም በትዕዛዝ እንደማንኛውም ደንበኛ የሚወሰዱ ልብሶች እንደሆኑ ትናገራለች።

‹‹በኤክስፖርት ደረጃ ለመድረስ በቅድሚያ ጥራት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ጥራት ላይ ለመድረስ ቀጣይነት ያለው የጥሬ እቃ አቅርቦት ትዕዛዝን በጊዜና በሰዓቱ ማድረስን ይጠይቃል። ጥራት ላይ ለሁለት ዓመት ሰርተናል፤ ድጋፍ ተደርጎልን በመሥራታቸው በዚህ ዓመት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የአይ ኤስ ኦ (ISO) ሰርተፊኬሽን ወሰደዋል። ስለዚህ ምርቶቻችን ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል፤ በቅርቡ ወደ ኤክስፖርት ሥራ እንገባለን ›› ትላለች።

አሁን ላይ የምታመርታቸውን ልብሶች መነሻዋ የሆነች የቀበሌ ቤትን ጨምሮ ሦስት የመሸጫ ሱቆችን ከፍታ ምርቶቿን እያቀረበች ትገኛለች። በኦንላይን ገበያ በመጠቀምም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርቶቿን እንዲሽጡ እያደረገች ነው።

‹‹የዲዛይንግ ሙያ አድካሚ ብዙ ጥረትና ልፋት የሚጠይቅ ስለሆነ ካልወደድሽው አትሰሪውም›› የምትለው እጅጋየሁ፤ ለሥራ ፍቅር ካለና ሥራውን ከወደዱት መቼም ድካሙ ሳይሰማ መሥራት እንደሚቻል ታምናለች። በተለይ የዘርፉ ተግዳሮች የሚባሉት የጥሬ እቃ አቅርቦት ከተፈታ ብዙ መሥራት እንደሚቻልም ታነሳለች። ችግሮቹ ተፈትተው ሀገር ውስጥ የሚመረትበት ሁኔታ ቢኖር ለባሹ አይቸግርም ነበርም ትላለች። የሀገሩ ልብስ ገዝቶ የመልበስ አቅምና በሀገሩ ምርቶች የሚኮራ ዜጋም መፈጠሩ እንደማይቀር ትናገራለች።

በቅርቡ በህንድ ሀገር የተካሄደው የንግድ ኤክስፖ ላይ ተሳትፋ እንደነበር የምትናገረው እጅጋየሁ፤ ‹‹ህንድ ውስጥ ከውጭ የሚገባ ምንም ነገር የለም። ልብሳቸው ሁሉም በራሳቸው የተሰራ ነው። ሁሉም ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን መሳሪያዎች እዚያው ይገኛሉ። የሽመና ሥራቸውን እንዲሁ አዘመነውታል። እኛ ምርት የተወሰነ ለማሳየት ይዘን ሄደን ነበር። የእኛ ምርቶች በዋጋ በጣም ውድ ናቸው። የእነሱ ግን በጣም ርካሽ ነበር። እኔ መድረስ የምፈልገው እዚያ ደረጃ ላይ ነው፤ ከውጭ ምንም ነገር ባይገባ ሰው የእኛን ልብስ ብቻ ቢለብስ ብዬ እመኛለሁ፤ ከሌሎች ጋር በዘርፉ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር በመሆኑ በህንድ ያየነው ዘመናዊ የሽመና ማሽን በማስመጣት የሀገራችን ሽመና ለማዘመን እቅድ ይዘናል›› ትላለች።

‹‹ቀደም ሲል ያሉ ዲዛይነሮች ትምህርት ቤት ሳይገቡ ወርቅ የመሳሳሉ ልብሶች ይሰራሉ›› የምትለው እጅጋየሁ፤ የፋሽን ትምህርት ቤቶች በተስፋፉበት በዚህ ወቅት ዲዛይኒንግ ሙያ ያላቸው ወጣቶች እድለኞች ናቸው። ሙያው እንዲያድግ ተግተው ሊሰሩ ይገባል ስትል ትመክራለች።

እጅጋየሁ ወደፊት ባለሙያ የማፍራት ሌላ ግዴታዋ መሆኑን ስለምታምን የዲዛይኒንግ ትምህርት ቤት የመክፈት እቅድ አላት። ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ሥራን ለመስራት ጥረት እንደምታደርግም ትገልጻለች። ይህንን ሙያ ለሌሎች ለማስተላላፍ ጥረት እያደረገችም እንደሆነ ታስባለች። ጅምሯን ከዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በግላቸው የተግባር ልምምድ በሚያደርጉ ተማሪዎች ጀምራለች። ማምረቻዋን ለእነርሱ ክፍት በማድረግ ሙያውን እንዲለምዱ እያደረገች ትገኛለች።

‹‹ይህ ሙያ ተረካቢ ይፈልጋል። ለዚህም አሁን ላይ ውጭ ሀገር የሚኖረው አንደኛው ልጄ ይህንን ሙያ በማሳደግ ወደ ፋብሪካ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አስቧል። ኤክስፖርት ውስጥ ለመግባት እንዲሁም ትምህርት ቤት መክፈት ትልቅ ፍላጎት አለውም›› ብላለች።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *