ብሔራዊ ውይይት፤ መሠረታዊ ፋይዳውና የሀገራት ተሞክሮ

ሀገራዊ ውይይት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ውይይት የሚለውን እስከ ተረዳን ድረስ የተሸከመው ሀሳብ ግልፅ ነው። በመሆኑም፣ ወደ አስፈላጊነቱ እንሂድ።

ሀገራዊ ውይይት የሚያስፈልገው ለምንም ነገር ሳይሆን የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው። የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ማለት ደግሞ በጋራ ለመቆም፣ በጋራ ለመስራት፣ በጋራ ለመኖር ወዘተ መስማማት፤ መሰረታዊ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ቅራኔዎችን ከስራቸው መንግሎ ለመጣል እንጂ ፍፁም አንድና አንድ መሆን ማለት አይደለም። በመሆኑም የጋራ ወይይት የሚደገፍ፣ የሚበተረታታ፤ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ የመጣ ፅንሰ ሀሳብ … እንጂ የሚሸሽ፣ የሚነቀፍ፣ የሚያስበረግግ ጉዳይ አይደለም። ይህንን ስንል ደግሞ ከምንም ተነስተን ሳይሆን ከፅንሰ ሀሳቡ መሰረታዊ ብያኔና የሀገራት ልምድ ነው።

የሀገራዊ ወይም ብሄራዊ ውይይት (“ውይይቶች” የሚሉም አሉ) ፋይዳው ግጭቶችን ከማስቀረት፣ አላስፈላጊ ጦርነቶችን ከማስወገድ፣ ሰላምን ከማስፈን፣ ጉርብትናን ከማፅናት፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ከማድረግ … አኳያ ፍቱን መድኃኒት መሆኑ ምስክርነትን ካገኘ ሰንብቷል። ይህንንም ጥናቶች (ለምሳሌ ኦክቶበር 2015 ለአደባባይ የበቃው የሱዛን ስቲጋንት እና ኤልዛቤጥ ሙሬይ ጥናት) “conflict resolution and political transformation” በማለት በይነውት እናገኘዋለን። በመሆኑም፣ በአግባቡ ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት ያለ ምንም ማቅማማት ተግባራዊ ሲያደርጉትና ተጠቃሚ ሲሆኑ ስንመለከት ኖረናል፤ እየተመለከትንም እንገኛለን።

ምንም እንኳን ውይይት ለሀገራችንና ለእኛ፣ ለዜጎቿ ባይተዋር ባይሆንና ከማህበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን አንዱ ቢሆንም፤ የሀገራትን ልምድ በመውሰድ መመልከቱ ይህንን እሴታችንን የበለጠ እናጠናክረው፣ ተግባራዊም እናደርገውና ከፋይዳውም እንጠቀም፤ ካላስፈላጊ ውዝግቦች፣ ግጭቶች፣ ጦርነቶች እንታቀብ ዘንድ ያግዘናልና ወደ’ዛው እናዝግም።

ከላይ የጠቀስነው ጥናት የጥናቱ ማጠቃለያ አድርጎ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከአራቱ አበይት ነጥቦች የምንረዳው አቢይ ጉዳይ ቢኖር ብሄራዊ ውይይቶች (National dialogues) በጣም እየተለመዱና በስፋትን ስራ ላይ እየዋሉ መምጣታቸውን፣ አገራትንም ከከፋ የእርስ በእርስ መፋጀት ያወጡና አያወጡ ያሉ ሲሆን፤ በተለይም ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ወዘተ ውይይቶችን ከማካሄድም ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና አገራዊ ደህንነት፤ ለጋራ አጀንዳ መኖር ያላቸው አስተዋፅኦ ከዚህ በመለስ የማይባል መሆኑን ነው።

ከዚሁ፣ National Dialogues: A Tool for Conflict Transformation? በሚል ርእስ ከቀረበ ጥናት መረዳት እንደሚቻለው ብሄራዊ ውይይቶች አንድ ወጥ የሆነ አቀራረብ ወይም የውይይት መንገድ (one-size-fits-all model) የላቸውም። ነገሩ ወፍ እንዳገሯ ትጮሀለች እንደሚባለው ነውና ከላይ ለእኛ፣ ለኢትዮጵያዊያን “ውይይት ከማህበረ-ባህላዊ እሴቶቻችን አንዱና ዋናው ነው” እንዳልነው ሁሉ የመወያያ መንገዳችንም ሆነ የውይይት ስልታችን ፍፁም ኢትዮጵያዊ መሆኑ ላይ በመስማማት ለብሄራዊ ወይም አገራዊ ውይይት እጅ መስጠት የግድ የሚጠበቅብን ይሆናል ማለት ነው።

ይሄው የቅርብ ጥናት ብሄራዊ ውይይቶች መርህ ያላቸው መሆኑንና ለመርህም መገዛት እንዳለባቸው፤ በመርህም መመራት ያለባቸው መሆኑን የሚያብራራ ሲሆን፣ መርሆቹንም (inclusion, transparency and public participation, a far-reaching agenda, a credible convener, appropriate and clear rules of procedure, and an implementation plan) በማለት (አካታችነት፣ ግልፅነትና ህዝባዊ ተሳትፎ፣ አስፈላጊና ችግሩን መሰረት ያደረገ የጋራ አጀንዳ፣ ተአማኒነት ያላቸው ተወያዮች ወይም ተቋማት፣ ተገቢነት ያለው አሰራር፣ ሊተገበር የሚችል እቅድ) ይዘረዝራቸዋል። እነዚህ “መርሆች” ተብለው የተዘረዘሩት፣ እንደ አጥኚዎቹ ድምዳሜ ማለት ነው፣ ለሁሉም የሚሰሩ ሲሆን፤ አፈፃፀማቸው ግን እንደየሀገራቱ ማህበራዊ – ባህላዊ አሰራር፣ ዘይቤና የዴሞክራሲ ባህል ሊሆን እንደሚገባ ያሰምሩበታል።

ከዚሁ አኳያ የሀገራትን ልምድ ስንመለከት ሀገራዊ ወይም ብሄራዊ ውይይቶች በተለያየ መልኩ ተከናውነው ወይም ሲከናወኑ እንመለከታለን። ያ ማለት ግን ስለ ተከናወኑ ብቻ ውጤታማ ወይም ስኬታማ ሆነዋል ማለት አይደለም። ከላይ የተዘረዘሩት መርሆችን ያላከበሩ በመሆናቸውም ይሁን ወይም የሀገራቱን ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች ባለመጠበቃቸው ምክንያት የከሸፉና የተፈለገውን ውጤት ያላመጡ ብሄራዊ ውይይቶች እንዳሉም መገንዘብ ይገባል። ያ ማለት ብሄራዊ ውይይት በራሱ ግብ አይደለም ማለት ነው።

በርካታ ጥናቶች ብሄራዊ ውይይቶች የሚያስፈልጉት በተለይ ለአፍሪካ አህጉር ነው የሚሉ አስተያየቶችን አስፍረው ነው የምናገኛቸው። ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ግጭቶች፣ በተለይም የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ከፍ ሲልም ጦርነቶች፣ መፈንቅለ መንግሥት ወዘተ በአብዛኛው የሚስተዋሉት በዚሁ አህጉር ስለ ሆነ የሚል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር ባይቻልም፤ ብሄራዊ ውይይቶች ለማንም ቢሆን አስፈላጊዎች መሆናቸው ላይም መከራከር አይቻልም።

በብዛት ብሄራዊ ውይይቶች ተካሂደው የከሸፉባቸው ሀገራት መኖራቸው ሲነገር ይሰማል። ከሚነገርባቸው ሀገራት መካከልም ቱኒዚያ፣ የመን … (2013 – 14) እና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል። እንዲሁም በ2015 በየመን የነበረው ግጭት ብሄራዊ የውይይት ኮንፈረንስ (NDC)ን የግድ አስፈላጊ አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ “ያለቀለት ነው” ባይባልም እስካሁን በእነዚህ ሀገራት ብሄራዊ ውይይቶች የተፈለገውን ወይም ይጠበቅ የነበረውን ውጤት አላስገኙም። በመሆኑም፣ ሀገራት ከእነዚህ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ በብሄራዊ ውይይቶቻቸው ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን መንገዶች ሊቀይሱ እንደሚገባ የብዙዎች ምክር ነው።

የአሜሪካው የሰላም ኢንስቲቲዩት (USIP) ጥናት እንደሚለው ደግሞ ብሄራዊ ውይይቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ሊተኮርባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ሲሆን፤ እነሱም ውይይቱ ሰፋና ጠለቅ ባለ እንጂ አንድ ነጠላ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር የለበትም፣ በመንግሥት ከሚመሩ ተቋማት ውጪ መከናወን፣ መመራት … አለበት፤ ብሄራዊ ውይይቱን የሚመራው አካል ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን ብቻ ሳይሆን የራሱ መተዳደሪያ ደንብና ህግ ሊኖረውና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ሊጋብዝ ግድ ነው፤ ለውይይቱ ሙሉ ፍቃደኛ መሆንን፣ ቁልፍ የሆኑ ባለ ድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ማካተት፣ ተሳታፊዎችን ወደ ግጭት ከሚገፋፉ ሀሳቦች መራቅ (conflict-fueling themes) አለባቸው፤ ሊፈፀሙ የታቀዱ ተግባራት በሙሉ በባለ ድርሻ አካላት የጋራ ስምምነት የተደረሰባቸውና የሁሉንም ይሁንታ ያገኙ መሆን አለባቸው፤ መሰረታዊ የሰው ልጆችን መብቶች ሊያከብሩ፤ ወይም፣ የሰዎች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ አስፈገላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ሊደረግ ይገባል።

በብሄራዊ ውይይቶች ወቅት ያልተገደበና ያልተሸራረፈ የህዝቦች ተሳትፎ ከሚገመተው በላይ ወሳኝ መሆኑ የሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ ሊያገኝ እንደሚገባ በቃኘናቸውም ሆነ ሌሎች፣ በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ካልሆነ የውይይቱ ውጤት የተገላቢጦሽ ሆኖ ሀገርንና ህዝብን ወደ አልተፈለገ አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተመልክቷልና እነዚህ ሁሉ ወደ ብሄራዊ ውይይት ትግበራ ከመገባቱ በፊት ሊታሰብባቸው የሚገቡ አንኳር ነጥቦች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት የእነ የመን ብሄራዊ ውይይቶች (2013–14 NDC) በስኬት ያለመጠናቀቅ ዋነኛ ችግሮች የእነዚህ መርሆች፣ በተለይም አካታች አለመሆናቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማልና ለሌሎች ሀገራት ትምህርት ሰጪነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም የሚል እምነት አለ። በተለይ በ“ፌዴራሊዝም” ፅንሰሀሳብ ላይ አለመስማማታቸው የፈጠረው ቀውስ ቀላል አልነበረም። ጉዳዩን የአሜሪካው የሰላም ኢንስቲትዩት Continuing disagreement over the financial and political mechanisms for federalism are a principal grievance fueling the current civil conflict in Yemen that erupted less than fifteen months after the NDC’s conclusion. በማለት ነበር የገለፀው።

የቱኒዚያውም “በስኬት ተጠናቀቀ” ተብሎ ይታወጅ እንጂ በባለሙያዎች እይታ አካታች አልነበረም። እንደውም ፖለቲካዊ ስልጣንን ለመቆጣጠር የተደረገ እንቅስቃሴ እንጂ የብሄራዊ ውይይት መልክም አልነበረውም ተብሎ ነበር ሲተች የነበረው።

የሴኔጋል (2008–09) ብሄራዊ ውይይት (Assises Nationales) በተለያዩ ሀገራት (ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ …) የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላትን እስከ ማሳተፍ ድረስ በመሄዱ የብዙዎችን አድናቆት አግኝቶ የነበረ ሲሆን፤ የተገኙ ውጤቶችንም በባለሙያዎች ሲያስተነትን የነበረ መሆኑም እንደዚሁ አድናቆትን አትርፎለታል – ሌሎች ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።

በማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ (CAR) የተካሄደውና Bangui Forum በመባል የሚታወቀው፣ በሜይ 2015 የተከናወነው ውይይት በሹማምንቱ “በጥሩ ሁኔታ የተካሄደ” ለማስመሰል በርካታ ጥረቶች ተደርገው የነበረ ቢሆንም፤ “የህዝቡን ድምፅ ያላካተተ” ተብሎ ከመተቸት ያመለጠ ሊሆን አለመቻሉ ብቻም ሳይሆን ፎረሙን “ህጋዊ ሰውነት የሌለው ፎረም” እስከ መባል አድርሶት እንደ ነበር ይነገራል። አስፈፃሚ ኮሚቴውንም (The Bangui Forum Implementation Committee) እንደዛው።

ከላይ የጠቀስነው እና ስድስት ሀገራትን (ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኬኒያ፣ ሌባኖስን፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ እንዲሁም የመን) ብሄራዊ ውይይቶችና ፎረሞች የዳሰሰው የአሜሪካው የሰላም ኢንስቲትዩት ጥናቱን ያላጠናቀቀ ሲሆን፣ ለዚህ እየሰጠ ያለው ምክንያት ደግሞ ብሄራዊ ውይይቶችን የተመለከቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠንተው የሚያልቁ ሳይሆኑ ሁሌም እየተጠኑ የሚሄዱ፤ አዳዲስ አሰራሮች እየታከሉባቸው የሚሻሻሉ፤ ስህተቶች እየታረሙ የሚሄዱበት ሂደት መኖር ያለበት የሚል ነው።

ከእስከ ዛሬ ክንውኖች መረዳት እንደሚቻለው ብሄራዊ ውይይቶች በከፍተኛ ደረጃ ሀብትን (ሪሶርስን) እንደሚፈልጉ (እንደሚጨርሱ)፣ በቂ ጊዜ ተወስዶባቸው ሊሰራባቸው እንደሚገባ፣ ያለ የሌለ የፖለቲካ ኃይልን (political energy) አሟጦ መጠቀም (ትእግስትን ጨምሮ) እንደሚያስፈልግ … ነው መገንዘብ የተቻለው።

በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ውይይት ለማድረግ በአዋጅ ተቋም (የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን) መስርታ እየሰራች ትገኛለች። ለተቋሙ መቋቋምም ቁልፍ ምክንያት የሆነው “በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ እና በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ”፤ “አካታች ሀገራዊ ውይይቶች በሀገራዊ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት እና ከጦርነት በኋላ ባሉ ሁኔታዎች ለዘላቂ መፍትሔ አስፈላጊ በመሆናቸው”፤… እንደ ሆነ በአዋጁ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

ተቋሙም (“የሚቋቋመው ኮሚሽን መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያቶችን ይለያል፣ ብቃት ባለውና በገለልተኛ አካል ውይይት እንዲካሄድባቸው ያደርጋል። በዚህም መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ይሰራል” ተብሎ በአዋጁ ላይ እንደ ሰፈረው) በዚሁ መሰረትም፣ በየጊዜው ምን እየሰራ እንዳለ፣ ምን እንዳቀደ ሲናገር ይሰማል። ወደ ውይይቱ እየተቃረበ መሆኑም እየተነገረ ነው። በመሆኑም፣ እዚህ ያልናቸውም ሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ተካትተው ከውይይቱ የተሻለ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ መንፈሳዊ … ውጤትና ስኬት ይገኛል ብለን እንጠብቃለን።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *