የግጭት ነጋዴዎች ሰለባ እንዳንሆን

በአሁን ወቅት በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች በኩል መልካም እና ገንቢ እሳቤዎች የሚንሸራሸሩትን ያህል በብዙ መልኩ የሥነ ሥርዓትና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ጎልቶና ተደጋግሞ ይታያል። በዮቲዮብ፣ በፌስቡክ፣ በቲክቶክ፣ በቴሌግራም ወዘተ በርካቶች ጥላቻንና ስሜታዊነትን ይሰብካሉ። ጦርነት ይቀሰቅሳሉ። ግለሰብን፣ ሕዝብና ሀገርን የሚያኳስሱና የሚያፈርሱ መልእክቶችን ያስተላልፋሉ።

መንደሩ «ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት» በሚል የሕግ ሽፋን ድብቅ አላማ ባነገቡና በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደር ግለሰቦች አስፈሪ በሆነ መልኩ ተወሯል። በተለይ ለአንዳንዶች ሀገር የማፍረሻ ጥይትና ቦምብ ሆኖ እያገለገለም ይገኛል።

የእነዚህ በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደር ግለሰቦች መገለጫም ብዙ ነው። ጥላቻ እንጂ ፍቅር አያውቁም። ሞት እንጂ ሕይወትን አይመርጡም። ጥፋት እንጂ ልማት ዓላማቸው አይደለም። ከማዳን ለመቅበር ይቸኩላል። አእምሯቸው በመንደር ማንነት የታጠረ ነው።

አያስቡም። አይጨነቁም። አበጥሮ ከማጣራት በሩቁና በግርድፉ መፈረጅ ይቀላቸዋል። አንድን ክስተት በርዝውና ከልሰው እንዳልሆነ ያሰፍራሉ። የድብቅብቆሽ ዓለምን እየፈጠሩ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የፀዳውን ካደፈው ይደባለቃሉ።

በስሜተኛነትና በወገንተኛነት የተበከሉ በመሆናቸው የጠራውንና የነጣውን እውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብተው ያቀርቡታል። እውነትን በውሸት ይለውሳሉ። ያታልላሉ። ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠር ማጣራትን አያውቁም። የሚዘሩት ጥላቻ፣ የሚያቆሙት ሐውልት፣ የሚያፈርሱት ምልክት፣ የሚጽፉት ክታብ፣ የሚያበጁት ገደብ፣ የሚቆፍሩት ጉድጓድ እጅጉን አስፈሪ ነው።

አብዛኞቹ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ምቾትና እንቅልፍ ማሳጣት ዓላማቸው ያደረጉ የጥፋት ጥቅመኞች ናቸው። በኢትዮጵያ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና ፍትህ እንዲሰፍን ፍላጎት የላቸውም። በሀገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ቀጣይ እንዳይሆን የሚችሉትን ሁሉ ያዋጣሉ።

በሕዝብ ስቃይ የሚፈነድቁ እነዚህ በማህበራዊ መገናኛ አውታር አርበኞች የጥፋት ተግባር መነሾ የሚቀዳውም ጥልቅ ከሆነው የግል ጠብና ቂማቸው ነው። በዚህ የተስፋ ቢስነት ጥላቻና ቂም የተዋቀሩ እንደመሆናቸውም በመርዛማ ብዕራቸው የሚረጩትን መርዝ አደገኛነት አይረዱትም።

ከሁሉ በላይ እንድ የሚያደርግ መገለጫው የተቃራኒ ምኞት ሰለባ መሆናቸው ነው። እነዚህ በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደር ግለሰቦች ከየራሳቸው ምኞት ውጭ የሚያዩት የለም። ከአስደሳቹ ይልቅ የሚያስለቅስውን መራጮች ናቸው። አምጠው የወለዱት ክፋት ለማሳደግ የሚሞክሩ፤ ክፋታቸው ተመልሶ እነሱን እንደሚያቃጥል እንኳን በቅጡ የማይገነዘቡ ድኩማን ናቸው።

የሆነውንም፤ ያልሆነውም፤ ቢያውቁትም ሆነ ባያውቁት የመጣላቸውን ሁሉ መዘርገፍ ምርጫቸው ነው። የማሳወቅ እንጂ የማወቅ አምሮት የላቸውም። ለማስተማር መማር እንደሚያስፈልግ የዘነጉ፤ ለማሳወቅ ማወቅ ግድ እንደሚል የማይረዱ ናቸው።

ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ ይቀናቸዋል። ከመፍጠር ይልቅ አቃቂር መውጣት ምርጫቸው ነው። የተሻለ ካስተዋሉም ለማኮሰስ ወይም ለማሳነስ ይጣጣራሉ። በጎሳ ምሽጉ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አንድነት ውስጥ ልዩነትን ለማጉላት ይሟሟታሉ። አእምሯቸው ውስጥ ባስቀመጡት ምስል በጅምላ ይጣላል። ይንቃል። ይሰድባል።ያዋርዳል።

ከመንቀፍም ባለፈ ለወደፊት የሚሻሻልበትን ምክር መስጠት ምርጫቸው አይደለም። በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ወይም አጀንዳ ላይ ማጠቃለያ ለመስጠት ይቸኩላሉ። ማጠቃለያቸውም ከስሜት የመነጨ እንጂ ትክክለኛ አመክኒዮን መሰረት አድርጎ የሚቀመር አይደለም።

ሊኖራቸው ቢገባም ራሳቸውን የመውቀስ ባህል የላቸውም። ሁልጊዜ ትክክል መሆን ስለሚፈልጉ ስህተትን መቀበል እሬት እሬት ይላቸዋል። ስህተትን መቀበል ቀርቶ ከነአካቴው ስህተቱ አይታያቸውም። ስህተትን ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌሎች ለማላከክ የሚሽቀዳደሙ ናቸው።

ሕዝብ ተረጋግቶ እንዳይኖር የተሳሳተ ዓላማቸውን በሰው አእምሮ ውስጥ የሚያሰርፁት እነዚህ የማህበራዊ መገናኛ አውታር ግጭት ነጋዴዎች ሌላ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር አብዛኞቹ ማንነታቸውን በፎቶ አለመግለፃቸው ነው። እነ ስሙ ሌላ ፤ መልኩ ሌላ ናቸው።

ምንም እንኳን ትክክለኛ ፎቶአቸውን በማስቀመጥ ማንነታቸውን ሳይድበቁ መርዝ የሚረጩትን ቁጥር በርካታ ቢሆን አብዛኞቹ ግን ማንነታቸውን አያሳውቁም። ፎቶአቸውን አያስቀምጡም። አንዳንዶችም የግለሰቦችንና የድርጅቶችን ተመሳሳይ ስም ይጠቀማሉ። ይህ መሆኑም ያሻቸውን በፈለጉት መንገድ ለማስተላለፍ ከለላን ሰጥቷቸዋል። የሚያከብሩት ሕግ፣ የሚፈሩት ኃይል እንዳይኖር አድርጓቸዋል።

ማንነታቸውን ደብቀው ራሳቸውን በተለያየ ማንነት የሚያስተዋውቁ እነዚህ ስመ ብዙ መርዛም ፀሃፍት፤ በዚህ ጭንብል ተሸፍነው ወተቱን አጥቁረው፤ ማሩን አምርረው ይቀርባሉ። ሰዎችን ከሰዋዊ ክብራቸው ዝቅ ያደርጋሉ፤ ያዋርዳሉ።

«ትንሽ ምላጭ ሀገር ትላጭ» እንደሚባለው በመሰል የወረደ ተግባር በርካቶችን መርዘዋል፣ እየመረዙም ናቸው። ከሰሞኑ እንኳን በአማራ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ሕግ ማስከበር ላይ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ስም ለማጠልሸት የሄዱበት ርቀት እጅጉን የሚያሳዝን ሆኖ ታይቷል።

መሰል የማስመሰል ሥራዎች ሠራዊቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እንዲፈጥር ታስቦው የሚሰሩ ሴራዎች ከመሆናቸውም በላይ ሠራዊቱ የተሰለፈበትን አላማ እና ተልእኮ ወደ ጎን በመተው በሥነ ልቦና ተጠቂ እንዲሆንና ሕገ መንግስታዊ ግዳጁን እንዳይፈፅም ታስበው የሚቀመሩ አፍራሽ ቀሽም ፕሮፖጋንዳ አካል ናቸው።

አብዛኞቹ በማህበራዊ የመገናኛ አውታር በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደር ግለሰቦች መኖሪያቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ነው። ይህ በመሆኑም አንድ ክፍል ውስጥ በመቀመጥ በሚረጩት መርዝ የሚጎዳው የእነርሱ ቤተሰብ አይደለም። የግጭት ነጋዴዎቹ ሰለባ የሚሆነው ምስኪኑ የሀገሬው ሰው ነው።

በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ተጥደው፤ በተለኮሰው የዘረኝነትና የጥፋት እሳት ላይ ነዳጅ የሚያርከፈክፋም ብዙዎች ናቸው። በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ደግሞ ፀሃፍቶቹ በርካታ መርዝ አከፋፋይ ማለትም ሼር አድራጊዎች አሏቸው።

ለወሬአቸው የሚሠጡት ርዕስ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ቢሆንም ከመከታተልና ከራሱ አልፎ ሌሎቹም ቢጤዎቹም ማካፈሉን አያቆምም። ከመንቀፍ ይልቅ ጎበዝ! በርታ! የሚሏቸውና መርዙን መውደዳቸውን ‹‹ላይክ››እና ‹‹ሼር›› በማድረግ የሚገልፁ ተከታዮቻቸው ቁጥርም በርካታ ነው።

ይሁንና በእነዚህ መርዛም ብዕር የጨበጡ ፀሃፍትና አከፋፋዮቻቸው በርካታ ንፁሃን እየተጉዱ ነው። ብሔር፣ ፆታና ቦታ በመቀየር የግጭት ድግስ የሚደግሱ ግጭት በመቀስቀስና ብጥብጥ በማንገስ የሕዝብ መፈናቀልና ስቃይን እያባባሱት ይገኛሉ።

በተለይ የፀሃፍቶቹን ድብቅ ዓላማ ያልተረዱ ንፁሃን ወገኖች ሳያጣሩ በሚሰጡት አፀፋ ሕዝቦች ወደ ግጭት ሲያመሩና ሲተናኮሱ እያስተዋልንም እንገኛለን። በአሁን ወቅትም መርዝ የሚያሰራጩ ፀሃፍቶቹ ቁጥርም ሆነ በእነርሱ ተግባር የሚደርሱ ጥፋቶች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። ይህ እስከሆነም ጠንሳሾቹ ሳይውል ሳያድር ከመንደሩ ሊሸሹ የሚችሉበት መፍትሔ መቀየስ የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባር ሊሆን የግድ እንደሚል ማሰብ ይኖርብናል።

በርግጥ የሰው ልጅ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እንዲሁም መረጃን የማግኘት መብቱ እንዳለው አያከርክርም። በዲሞክራሲያዊ ሀገር መሰል መብቶች መገደብ እንደሌለባቸውም ሁላችንንም ያስማማል። በሀገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊና ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚሰጡ ገንቢ ሃሳቦችና በመንግሥት አሰራር ላይ በሚታዩ ድክመቶች ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶችንና ትችቶች መበራከታቸውም የሚጠላ አይደለም። አስተማሪና ለለውጥ መነሾ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጥርጥር የለውም።

ይሁንና በሰንካላ አስተሳሰብና በተንኮል በሕዝቦች መካከል ግጭት መዝራትና መርዝ መርጨትን እንደመብት ወይም ሃሳብን በነፃነት እንደመግለፅ መመለከት ነገ እንባና ደም ወለዱን ጨምሮ እንደሚያስከፍል መገንዘብ የግድ ነው። መሰል አካሄድም ሳይውል ሳያድርም በቃ ሊባል እንደሚገባው በእጅጉ መተማመን ይኖርብናል።

የፌስቡኩን መንደር የወረሩትን መርዝ የሚረጩት ብዕረኞች ዓላማ ለማክሸፍ ደግሞ ቀዳሚው የተጠቃሚው ኃላፊነት ነው። ከሁሉ ቀድሞም ለፀሃፍቶቹ ድጋፍ መቸር የአእምሮንና የኅሊናን መዳከም ወይም ጭራሹኑ አለመኖር እንደሚያመላክት መረዳት ይገባል።

እንደ ፀሃፍቶቹ ላለመጥበብና በራስ የአስተሳሰብ ሳጥን ብቻ ላለመታጠርም ጥበብ ያለው ማንበብ እንዲሁም ጥሩ እና መጥፎውን አበጥሮ በመለየት መመልከትን መልመድ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ጥበብ የሌለው ማንበብ እይታ ትክክለኛና የተመጣጠነ አስተሳሰብ እንዲሁም አስተዋይ አዕምሮን አይገነባምና ነው።

ከሁሉ በላይ በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደሮች ዓላማ ሕዝብንና ሀገርን ምቾት እንቅልፍ ማሳጣት መሆኑን ከመገንዝብ ስህተታቸውን አይቶ ከማለፍ ይልቅም «ስህተቱን ነው ፣ ቀጣፊ ናችሁ» ማለትና በተጨባጭ ምክንያት ብሎም ማስረጃ መሟጋትን ልምድ ማድረግም ያስፈልጋል።

በተለይ በዚህ ፈታኝ ወቅት የግጭት ነጋዴዎች ሰለባ ከመሆን ልንጠነቀቅና እንደ ዜጋ ወገናቸውንና ሀገራቸውን ለመታደግ ያላቸውን አቅምና ችሎታ ሁሉ አሰባስበው የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። በተለይ ሀገር ገደል አፋፍ ላይ ባለችበትና ጠላቶቿ መውጫና መግቢያ ባሳጧት ወቅት፣ ከምንግዜውም በተለየ የስከነ፣ እውነትነት ያለውን ሀገርን እና ሕዝብን አደጋ ላይ የማይጥል፣ ገንቢ ሃሳቦችን መለዋወጥ ላይ ስለማተኮር ማሰብ መልካም ነው።

በሕዝብ ደም የሚገበያዩ ግጭት ነጋዴ ሆድ አደሮችም ቢሆን አንድን ክስተት በመመረዝና ከልሶ የጠራውን ከደፈረሰው፣ የፀዳውን ከአደፈው መደባለቅ እንዲሁም መርዛም መልዕክታቸው በብዙ ሰዎች ስለተደገፈ እውነት አይሆንምና ሁልጊዜም ቢሆን ምክንያትን ማስቀደም፣ መረጃዎችን እየመረጡ ስለመጠቀምና መመርመር ሊያሰቡ ይገባል።

ከሁሉ በላይ በሕዝብ ደም ገንዘብ ለማግኘት እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና በሀገርና ሕዝብ ሰላምና አንድነትን በማያመጣ “የበሬ ወለደ” ተረት ተረት የሚደርሰው ሁሉ አቀፍ ጥፋት ሊሰቀጥጣቸው ይገባል። ዛሬ ላይ ከሰው ፍርድ ማምለጥ ቢቻልም ፤ ነገ ከነገ ወዲያ ከራስ የህሊና ፍርድ ማምለጥ እንደማይችሉ ጠንቅቀው ሊረዱት ይገባል።

ማህበራዊ መገናኛ አውታሮችን መንደር የወረሩትን ግለሰቦች ዓላማ ለማክሸፍ መንግሥትም ቢሆን ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ግድ ይለዋል። በርካታ ሀገራት በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ አውጥተዋል። ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ የቀውሱ ገፈጥ ቀማሽ በመሆኗ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ሊኖራት የግድ ይላል።

በአጠቃላይ ለአንድ ሀገር ሕዝብና ሰላም ብሎም ብልፅግና ሁላችንም ማህበራዊ መገናኛን ለሀገርና ለወገን መድህን፤ ብሎም ለሁሉም ለሰው ልጅ ለሚጠቅም ምግባር እንጠቀምበት። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እንታደግበት። የግጭት ነጋዴዎች ሰለባ ከመሆን በመጠንቀቅም ምንጊዜም ከልዩነት ይልቅ ለአብሮነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከመናናቅ ይልቅ መከባበርን፤ ከማፍረስ ይልቅ መገንባትን፣ ከእኩይነት ይልቅ ሰናይነትን፣ በአጠቃላይ ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ሥራ እንስራበት።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *