ሀገር የሚያቀኑ የሰላም ሃሳቦች

እንደ ሶቅራጠስ ያሉ ታላላቅ አሳቢያን የዘመናዊነትን መነሻ የላቀ ሀሳብ ያደርጉታል። እንዲህ አይነቱ ምልከታ ከክርስቶስ ልደት በፊት ላለው አእምሮና ልብ ብቻ ሳይሆን አሁን ላለው ትውልድም የሚሰራ ነው። የሰው ልጅ በሀሳብ ተሟግቶ ካልተሸናነፈ በሌላ በምንም ቢሸናነፍ ልክ አይሆንም። ሀገር የሚያቀና፣ ነውር የሚመልስ የሀሳብ ሙግት ነው።

ሰላም የሚመጣው በሀሳብ ነው። በምን አይነት ሀሳብ ካለን ውይይትና ምክክርን ባስቀደመ መድረሻውን እርቅና አንድነትን ባደረገ ሀሳብ ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ የጦርነት መነሻም ሀሳብ ነው። ምን አይነት ሀሳብ የሚለውን ለማወቅ ጠቢብ መሆን አይጠበቅብንም።

የጦርነት ሀሳቦች ሁልጊዜም የራስወዳድነት ሀሳቦች ናቸው። እኔነትን አስቀድመው በጥፋት የሚያበቁ ናቸው። የእኛም ሀገር የጦርነት አስተሳሰቦች ከዚህ መሰሉ የራስወዳድነትን ከዛም እልፍ ሲል ከጽንፈኛ አስተሳሰቦች የሚመዘዙ ናቸው።

ዓለም የተራመደችው እና እየተራመደች ያለችው ሀሳብ በሚሉት የለውጥ እና የስኬት ሰረገላ ላይ ነው። ዓለም ከትናንት ዛሬ ሌላ ናት። እኛ ግን ከትናንት ስህተቶቻችን መማር ስላልቻልን ትናንቶች ላይ ነን። ትናንትን በገደሉብን ባበላሹብን ታሪኮቻችን ዛሬም እየሞትን ነው።

በይዋጣልን ውስጥ የምትቆም ሀገር፣ የሚበረታ ትውልድ የለም። የዛሬ እንከኖቻችን ይዋጣልን የወለዳቸው ነውሮች ናቸው። እኚህን ትናንትናዊም ሆኑ አሁናዊ ጉድፎች የሚያጠራ የሀሳብ ሙግት ያስፈልገናል። ጦርነት የቀለለንን ያክል ተነጋግሮ መግባባት ቢቀለን ዛሬ ላይ ባለማዕረግ ነበርን። እልኸኝነት የቀለለንን ያክል አብሮነት ቢቀለን ዛሬ ላይ በትናንሽ ነገሮች ዋጋ ባልከፈልን ነበር።

ይዋጣልን አሸናፊ የለውም። የወንድማማቾች ጥል በታሪክ ገጽ ላይ ነውር ከመጻፍ ባለፈ ማንንም አያስከብርም። የትላንት ታሪኮቻችን በእርስ በርስ ጦርነት አዳፋ ታሪክ የጻፍንባቸው ናቸው። የእኚህ ገጾች መቀየር ኢትዮጵያን ለመቀየር፣ ትውልዱን ለማነጽ ቀዳማይ መስፈርት ነው። ይሄ የሚሆነው ደግሞ በሀሳብ መሸናነፍን ስንለምድ ነው።

የጠመንጃ ዘመን ላይ አይደለንም። ዓለም ተቀይራ በሀሳብ ማሸነፍ ላይ ደርሰናል። ሀሳብ እናንሳ። ጠመንጃዎቻችንን ጥለን እስኪ እጅ እናንሳ። እስኪ እጅ እንሳ። እስኪ ሀሳብ እንቀባበል። ታሪኮቻችንን በሀሳብ ካላደስናቸው በጠመንጃ አናድሳቸውም። ችግሮቻችንን በውይይት ካልፈታናቸው በመገዳደል አናስተካክላቸውም።

ሞት ለምንም ነገር መፍትሄ ሆኖ አያውቅም። ሞት ሞትን እየወለደ ሀገርን ለስጋት፣ ትውልዱን ለጥርጣሬ የሚጥል ነው። የእኛ መገዳደል ለኢትዮጵያ ‹የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ› አይነት ተረት ነው። የሚጠቅመው ማንም የለውም። የሚያዋጣን ትርፋችንን በሰላም ውስጥ መፈለግ ነው።

ሀገር የሚያቀኑ የሰላም ሀሳቦች ናቸው ። የሰላም ሀሳቦች እንደ ወይን ናቸው፤ እለት እለት የሚጣፍጡ። ሞት መራራ ነው። ተከባብረን በመኖር እንጂ ገለንና ሞተን ለሀገራችን የምንጨምርላት የለም። ሰው በሀሳብ መሸናነፍ ካልቻለ ለምንም ነገር ነውጥን የሚመርጥ ነው። በነውጥ ውስጥ ደግሞ መከራና ስብራት እንጂ ለውጥ እና ከፍታ የሉም። በጥላቻ እሳቤ የከፍታዎቻችንን ማማ በጦርነት ያፈረስን ህዝቦች ነን። ጀግንነትን ጦርነት ውስጥ በመፈለግ አባዜ የበረከታችንን ምኩራብ ያፈረስን ነን።

በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የተሰወረችው ጀምበር እንድትወጣ፣ ጭጋጉ ጠርቶ ብርሀናችን እንዲታይ የሰላም ድምጾች፣ የእርቅ አንደበቶች መብዛት አለባው። አእምሮ የሰጠንውን ነው የሚቀበለው። እስከዛሬ ጦርነትንና ጥንፈኝነትን ሰጥተንው በዛ አውድ ውስጥ ብዙ ዋጋ ሲያስከፍለን ቆይቷል። እስኪ ሰላምን እንስጠው። እስኪ ተነጋግሮ መግባባትን እናውርሰው።

አንዳንድ የጦርነት ሊቅሀን ጦርነት አእምሮ ውስጥ ነው የሚፈጠረው ይላሉ። እውነት ነው ጦርነት አእምሮ ውስጥ ነው የሚፈጠረው። አእምሮ ጥላቻን ሲያረግዝ፣ እኔነትን ሲያስቀድም፣ እልኸኝነትን ሲመርጥ ጦርነት ቀስቃሽ ወደሆኑ ርምጃዎች ይሄዳል። በዛው ልክ ሰላምም የሚፈጠረው አእምሮ ውስጥ ነው። ያ ማለት አእምሮ የጦርነትና የሰላም ቦታ ነው ማለት ነው። ዋጋ እያስከፈለን ያለው የተለማመድነው የጦርነት ልምምድ ነው። ከዚህ አውድ ለመውጣት የሰላም ልምምድ ያስፈልገና። የሰላም ልምምድ ከሰላማዊ ሀሳብ፣ ከእኛነትና ከእርቅ ከተግባቦትም የሚነሱ ናቸው።

አእምሮን መግራት የለውጥ እና የስኬት ትልቁ ቀመር ነው። ሀገራችን ተለውጣና ህዝቧም በራሱን ችሎ እንዲኖር ጦርነትን የተለማመደ አእምሯችን በሰላም ሀሳቦች መገራት አለበት። ያለፈው ይበቃናል ስንል ለሰላም በሮቻችንን እንክፈት። ያልተገራ አእምሮ እንዳልተገራ ፈረስ ነው። ዝም ብሎ የሚፈረጥጥ። በነፈሰበት የሚነፍስ። ያልተገራ አእምሮ ምክንያት አያምንም። በመነጋገር ለሚፈቱ ትናንሽ ችግሮች ጦርነትን የሚመርጥ፣ ሀይለኝነትን የሚያስቀድም ነው።

ፖለቲካ የአእምሮ ውጤት ነው። ፖለቲካ ምንም አይደለም ስም ነው። እንዳሻው የሚሆነው አእምሮ ባላቸው ፖለቲከኞች ነው። ፖለቲካችን እንዲያምር ከምንም በፊት ፖለቲከኞቻችን አእምሯቸውን መግራት አለባቸው። የእነሱ አስተሳሰብ፣ የእነሱ ሥርዓት ነው ወደ ሀገርና ህዝብ ላይ የሚያርፈው። ያለፖለቲከኛ ፖለቲካ ብቻውን ኃይል የለውም። ፖለቲካችን ነውጥ ፈጣሪ፣ የጦርነት እሳቤዎችን አራማጅ የሆነው ባልተገራ አእምሮና ልብ ነው።

ስለሀገራችን ባለ አእምሮ እንሁን። ባለ አእምሮነት መዳረሻው ሰላማዊነት እና የሀገር ፍቅር ነው። ባለ አእምሮነታችን ከሰላም ካልጀመረ፣ ስልጣኔአችን አንድነታችንን ካልታከከ የተሰወረችብንን የሰላም ጀንበር አንደርስባትም። እርግጥ ነው ሰላም ፈላጊዎች ነን። ስለ ሰላም ብዙ ዋጋ ከፍለናል።

የሰላም ሀሳቦች በምንም አይነት በደል ውስጥ እርቅና አንድነት የሚያምጡ ናቸው። በምንም ያክል አለመግባባት ውስጥ ብንቆም እንኳን የጦርነትን እሳቤ ሽረው ወደመተቃቀፍ የሚያደርሱ ናቸው። የዚህ ዓለም ታላቁ እውቀት የሰላም እውቀት ነው። የሰላም እውቀት ሀገር የሚማግር ጥበብ ነው። እንዴትም ሀገርን ለውድቀት፣ ህዝብን ለሞት አይሰጥም። በመሸነፍ ውስጥ የሚያሸንፍ፣ በስክነት ውስጥ የሚበረታ ነው።

የኒልሰን ማንዴላ እውቀት የይቅርታ እውቀት ነበር። የማህተመ ጋንዲ፣ የማርቲን ሉተር እውቀት የፍቅር እውቀት ነበር። ፖለቲካችንን በፍቅር እና በይቅርታ እስካላደስን ድረስ ታጥቦ ጭቃ ነን። ታጥቦ ጭቃ መሆን ሳይሆን ታጥቦ መጥራት ነው የምንፈልገው። የእስካሁኑ መንገዳችን ታጥቦ ጭቃን፣ ድጥና ማጥን፣ እንቅርትና ጆሮ ደግፍን፣ በሀና ቆረቆርን የሚያስታውስ ነው።

ሰረገላችን በጠራ እውቀት ካልሆነ ከራቀ ነገ አንደርስም። ሰረገላችን ሰላምና አንድነት ካልሆነ ራሳችንን ከራሳችን መታደግ አንችልም። ጠላቶቻችን ሌሎች ቢሆኑ ይሄን ያክል ባልተቸገርን ነበር። ጠላቶቻችን ራሳችን ሆነን ነው የተቸገርነው። ራሳችን በፈጠርነው ችግር ራሳችንን እያጠቃን፣ ታሪካችንን እያበላሸን፣ ትውልዱን እየመረዝን ከራቀ ትናንት መጥተናል። የሚያሽረን ሀሳብ፣ ሀገር የሚያቀና የምክክር መድረክ ያስፈልገናል።

የምክክር መድረክ አንድነት የሚመጣበት፣ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበት ነው። የምክክር መድረክ ሀሳብ የሚዋጣበት፣ አቅጣጫ የሚተለምበት የፍቅርና የአብሮነት መዐድ ነው። ችግሮቻችን ምን እንደሆኑ፣ እንዴት እና በማን፣ መቼ እንደመጡ እንኳን ተጨባጭ እውነታ ላይ የምንደርሰው አብረን ስንቀመጥ ነው። አብረን ባልተቀመጥንበትና ለመነጋገር ፍቃደኞች ባልሆንበት ሁኔታ የሚመጣ መፍትሄም ሆነ አንድነት የለም።

ፍቅርን በማያምጥ አእምሮ ውስጥ ጦርነት የለም። ልቦቻችን ፍቅርን እንዲያመጡ፣ አንድነትን እንዲወልዱ በኢትዮጵያ ባህልና ወግ እንካድማቸው። በፍቅር የታረሰ ልብ ለወዳጁ ክፉ አይሆንም። ያቃተን ፍቅርን ማማጥ ነው..አንድነትን መውለድ ነው። ለዚህም ነው በወንድሞቻችን ላይ አፈሙዝ የምናዞረው።

ጦርነት በልዩነት ተጀምሮ በጥላቻ የሚያበቃ የሀገርን ኢኮኖሚ፣ የትውልዱን ተስፋ የሚነጥቅ የስህተት ቦታ ነው። ጦርነት መፍትሄ የሌለው ለባሰና በባሰ ጥላቻ ውስጥ የሚያኖር፣ የብዙ ትውልዶችን ነገ የሚያፈርስ የቁርሹ መነሻ ነው። አብዛኞቹ የዓለም ጦርነቶች ከብዙ ሞትና ሰብአዊ ጉስቁልናዎች በኋላ በመጨባበጥ የተጠናቀቁ ናቸው። የቅርብ ጊዜውን የሰሜኑን ጦርነት ብናስታውስ እንኳን ከብዙ ሞትና ኪሳራ በኋላ በመተቃቀፍ የተጠናቀቀ ነው።

ለመማር ከተሰናዳን ብዙ የሚያስተምሩ ያለፉ ታሪኮች አሉን። ጦርነትን በተመለከተ እንደ እኛ አስተማሪ ታሪክ ያለው ሀገር የለም። እየገደልንና እየሞትን የመጣን ህዝቦች ነን። በተለይ ያለፉት ስልሳ ዓመታት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆነው መቅረብ የሚችሉ ናቸው። ሞተንና ገለን በመጨባበጥ ውስጥ ሳይሆን ሳንሞትና ሳንገድል በመጨባበጥ ውስጥ ነው ፍቅር ዋጋ ያለው።

ዘመናዊ አእምሮ ለጦርነት በር አይከፍትም። ዘመናዊ አእምሮ ጥላቻና መለያየትን በእርቅና በፍቅር የሚቋጭ ነው። ዘመናዊ አእምሮ ለትውልዱ የጥላቻ ቤት አይሰራም። ትውልዱን በፍቅር ምንጣፍ ላይ ያራምዳል እንጂ። በአንድነት የምንቆምበት፣ በአንድነት የምንራመድበት በሀሳብ የተሸመነ፣ ብዙ ኢትዮጵያዊ እጆች አንድ ላይ ሆነው የፈተሉት የፍቅር ምንጣፍ ያስፈልገናል። የእኔ የአንተ የማንባባልበት፣ የማንሞትበትን፣ የማንጎሳቆልበት የይቅርታ ድብዳብ ያስፈልገናል።

ሰላም ሉአላዊነት የሚጀምርበት፣ ስልጣኔ የሚረጋገጥበት አውድ ነው። በሰላም ምንጣፍ ላይ እስካልተራመድን ድረስ ለምንፈልገው ለየትኛውም ነገር ሩቅ ነን። ሰላም አሁን ላለው ትውልድ ሁነኛ መመዘኛው ነው። በሰላም ካልተመዘንን በምንም ብንመዘን ልክ አንሆንም። በፖለቲካችን ውስጥ፣ በማህበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ ለሰላም የሚሆን እውቀት ካለን በየትኛውም መመዘኛ ብንለካ ዘመናዊ ነን።

ይሄ እውነት ለእኛ ሲሆን የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም። ዓለምን በውበት የቀለሙ አእምሮዎች፣ ትውልድን በጥበብ ያሳመሩ ልቦች ዛሬ ላይ የተግባቦት ሀሳብ አጡ ቢባል ለሰሚው ግራ ነው። ያጣነው ሀሳብ አይደለም። ያጣነው እልኸኝነትን አውልቆ የሚጥል እውቀት ነው። ወደፈለግንበት ወዴትም ለመሄድ ፍቅር የቀደመበት፣ አንድነት የተከተለበት እውቀት ያስፈልገናል። በእውቀት እና በስክነት ካልሆነ ነባርና አሁናዊ ችግሮቻችንን መርታት አንችልም።

የጦርነት ነጋሪትን የሚጎስሙ ሀሳቦች፣ ጥላቻዎች አዋርደውን እንጂ ጠቅመውን አያውቁም። እነኚህ የመገፋፋት ነጋሪቶች እንዲቆሙ በጋራ ቁጭ ብለን በጋራ መምከር ይኖርብናል። እንደ ሀገር የጋራ አጀንዳ ያስፈልገናል። ከጦርነት የሚመልሰን እርቅና ምክክር ያለበት የጋራ አጀንዳ ነው።

ሀሳቦቻችን ሀገራችንን እንዲያጸኑልን የሰላም ሀሳቦች ያስፈልጉናል። ከወንድማማች ሞት የሚታደገን መፍትሄው ይሄ ብቻ ነው። የሰላም ሀሳቦች እንደ ሰላም ርግቦች ናቸው። ማረፊያቸው በጎ ዛፍ ላይ ነው። በጎ ዛፍ ደግሞ በጎ ፍሬ የሚሰጥ ነው። እናም በሀሳብ መሰልጠንን፣ በተግባቦት ሀገር ማቅናትን የእርምጃችን መነሻ እናድርግ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 5/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *