የሚሠራ ይደገፋል፤የወደቀ ይረዳል!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት ነገር ነበር:: አንድ ሰው ሱፍ ለብሶ፣ ጽድት ብሎ ‹‹ታክሲ ውስጥ ቦርሳ ተዘረፍኩ›› ቢል 10 ብር ያለው ሰው አምስቱን ይሰጠዋል፤ ምክንያቱም የአቻነት ስሜት ይሰማዋል::

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው የምርም ተቸግሮ መሆኑ ያስታውቃል:: የሆነ ጎስቋላ ሰው እንደዚያ ቢል ግን ጎስቋላ መስሎ እየለመነ ነው በሚል ማንም ልብ አይለውም:: ምንም እንኳን አሁን አሁን በየትኛውም መንገድ ማጭበርበር ያለ ቢሆንም የሰውየውን ተክለሰውነት አይቶ መገመት ግን የተለመደ ነው:: እንዲህ ዓይነት ተክለሰውነትና አለባበስ ያለው ሰው ድንገተኛ ነገር ካላጋጠመው አይለምንም ነው የሚባለው::

ይህን የሚያረጋግጥ የአንዲት የግል ድርጅት ሠራተኛ ገጠመኝ አውቃለሁ:: ልጅቷ ቦርሳ ስትቀይር ገንዘብ መያዝን ረስታለች:: ታክሲ ውስጥ ከገባች በኋላ ልትከፍል ስትገባ ነው እንዳልያዘች ትዝ ያላት:: በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆና ረዳቱን እንደረሳች ስትነግረው ‹‹ምንም ችግር የለውም›› አላት:: ታክሲ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለቀጣይ ጉዞዋ ለታክሲ ብለው የሰጧት ‹‹ራይድ ያስይዛል›› እያለች ስትቀልድ ነበር::

ያቺ ሰው ተክለሰውነቷ የተጎሳቆለ፣ አለባበሷና ነገረ ሥራዋ ሁሉ የቦዘኔ ቢመስል ኖሮ ረዳቱም ዝም አይላትም፣ ለቀጣይ ታክሲ የሚሆን በሚል ማንም ሰባራ ሳንቲም አይሰጣትም፤ ምክንያቱም ይህ በየዕለቱ በየመንገዱ የምናየው ነው::

አንድ የአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴን አስተያየት ልጨምርና ወደ ዕለቱ አጀንዳ ልሂድ:: ኃይሌ ‹‹ሰይፉ በኢ ቢ ኤስ›› የተባለው የቴሌቪዥን ሾው ላይ ቀርቦ ነበር:: ሰይፉ በቀልድ መልክ አስመስሎ ኃይሌን ገንዘብ ላይ ቆንቋና (ስስታም ነገር) እየተባለ እንደሚታማ ነገረው:: ኃይሌም በቁም ነገር ሲመልስ፤ ‹‹ለሚሠራ ሰው ነው ድጋፍ የማደርግ›› ነበር ያለው:: ምንም ለማይንቀሳቀሱ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ሰዎችን ሰነፍ ማድረግ ነው:: ድንገተኛ አደጋ የደረሰባቸው ወይም መሠረታዊ ችግር ያለባቸው ካልሆኑ በስተቀር ‹‹ቁጭ ብላችሁ ብሉ›› የሚል እርዳታ ማድረግ ሰዎችን ማበለሸት ነው:: ሥራ ለሚፍጨረጨሩ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ግን ዘላቂ መፍትሔ ነው::

እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያስታወሰኝ የዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝት ነው:: የዓለም ባንክ ማለት ማን ማለት እንደሆነ እና ምን ማለት እንደሆነ ማብራሪያ አያስፈልገውም::

ፕሬዚዳንቱን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተለያዩ አካባቢዎችን አስጎብኝተዋቸዋል:: የዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት የአረንጓዴ ቦታዎችን ጎብኝተዋል፣ የማምረቻ ቦታዎችን ጎብኝተዋል:: እንዲያውም የማምረቻ ቦታዎችን ከጎበኙ በኋላ የሠራተኞቹን ትጋት አድንቀዋል:: የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ራዕይ አድንቀዋል::

እኚህ ሰው የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው:: የዓለም ባንክ ምን እንደሚሠራ ደግሞ ግልጽ ነው:: በተለይም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው:: እየሠሩ ላሉ ሀገራት ማለት ነው:: ይህ ተቋም ገንዘቤን ለእነዚህ ሰዎች ብሰጣቸው ምን ያደርጉበታል ብሎ ያስባል:: እንኳን ዓለም አቀፍ ተቋም ይቅርና ግለሰቦች እንኳን ለሰዎች ብር የሚሰጡት የአስፈላጊነቱን ሁኔታ አይተው ነው:: አረቄ ለሚጠጣበት ሰው እና ዳቦ

 ለሚገዛበት ሰው እኩል አይሰጥም:: ልጆች ሲለምኑ ‹‹ምን ልታደርግበት ነው?›› ብለው ይጠይቃሉ:: ልጁ የተናገረውን ነገር አይተው ነው አዋቂዎች ብር የሚሰጡት::

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በተመለከቷቸው ነገሮች ኢትዮጵያ እየተጋች መሆኑን አይተዋል:: የዓለም ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመጠበቅ እያደረገች ያለውን ትጋት፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና የዜጎች ሥራ ፈጠራ አስተውለዋል:: እነዚህ ነገሮች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጡት ቦታ ትልቅ ነው::

ዓለም አቀፍ እንግዳ ሲመጣ ሀገሪቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ ሊጎበኝ አይችልም:: ይህን እንኳን እንግዳ፣ ነዋሪዎችም አላደረግነውም:: የሚመጣን እንግዳ ስናስጎበኝ ደግሞ ምን ምን ቦታዎች መጎብኘት እንዳለባቸው ማሰብ አለብን:: ስለዚህ ለእንዲህ ዓይነት እንግዶች የሚጎበኙ ነገሮች መኖራቸው ትልቅ ለውጥ ነው:: ለመጣው እንግዳ ሁሉ የሺህ ዘመናት ታሪክ ያላቸውን እነ አክሱምና ላሊበላን ብቻ ማስጎብኘት ‹‹የዛሬው ትውልድ ተኝቷል እንዴ?›› ያሰኛል:: ስለዚህ ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት የዚህ ትውልድ ዐሻራዎች መታየታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው::

አንዳንድ ወገኖች ‹‹ሕዝብ እየተቸገረ የቅንጦት ነገሮች ለምን ይሠራሉ?›› ይላሉ:: እርግጥ ነው የፀጥታ ጉዳይ ላይ መንግሥትን አምርረን ልንጠይቅ ይገባል፤ የልማትና የገጽታ ግንባታ ላይ ለምን ይሄ ተሠራ ማለት ግን የሀገርን ኋላቀርነት መመኘት ነው:: ይህቺ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማት ማረፊያ የሆነች ከተማ የዓይን ማረፊያ ሊኖራት ይገባል፤ የዓለም አቀፍ ከተሞች ተወዳዳሪ መሆን አለባት:: ይህቺ ታሪካዊ ሀገር የዛሬውን ትውልድ ዐሻራ ማሳየት አለባት:: አለበለዚያ ይህ ትውልድ የሚወከልበት ነገር የለውም ማለት ነው::

ሲሠሩ የነበሩ ፕሮጀክቶች ያላቸውን ዓለም አቀፍ ጠቀሜታ እነሆ በዓለም ባንኩ ፕሬዚዳንት ዓይነት እንግዶች አየነው:: እኚህ ሰው ወደ አፍሪካ ሲመጡ እንደዚያ ዓይነት ነገር አይጠበቅም:: ስለዚህ የተራቆቱ አካባቢዎችንና የቆሸሹ ሰፈሮችን እየመረጥን ማሳየት ነበረብን? የዓለም የዲፕሎማሲ ብልጠት ራሱ እንደዚህ ነው:: በጎ በጎ ነገራቸውን ብቻ ነው እየመረጡ የሚያሳዩት::

ከዚህ ይልቅ ማድረግ ያለብን ለወደፊቱ ሁሉም አካባቢዎች ጽዱ እና አረንጓዴ እንዲሆኑ ነው:: የመጣ እንግዳ በየትኛውም የአዲስ አበባ አካባቢ ወይም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ቢያርፍ ለዓይኑ ማራኪ የሆነ ነገር አይቶ እንድሄድ ማድረግ ነው:: ያንን እስከምናደርግ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሠሩ ፕሮጀክቶችን ማሳየት የግድ ይለናል:: ምክንያቱም አድናቆትም ሆነ ድጋፍ የሚያደርጉት እየሠራ ላለ ሀገር እንጂ እጁን አጣጥፎ ለሚቀመጥ አይደለም:: የፋይናንስ ተቋማት በባህሪያቸው ድጋፍ አድራጊ እንጂ እርዳታ ሰጪዎች አይደሉም:: ለሥራ መሥሪያ ነው ድጋፍ የሚያደርጉት፣ የሚሠራ ሀገር ነው ድጋፍ የሚያደርጉት:: ድጋፍና እርዳታ ይለያያል፤ ድጋፍ እየሄደ ያለ አካል ነው ድጋፍ የሚደረግ፤ እርዳታ ግን የወደቀውን ለማንሳት ነው:: ስለዚህ ለመደገፍ መሄድ አለብን::

እየሠሩ መለመን ሳይሰሩ ከመለመን በብዙ እጥፍ የተሻለ ነው:: የሚታይ ፕሮጀክት ሲኖር ነው ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች እምነት የሚኖራቸው:: ድጋፍ ቢደረግላቸው መሥራት የሚችሉ ናቸው ብለው ያምናሉ:: ይህ እንኳን እንደ ሀገር እንደ ግለሰብ እንኳን የሚደረግ ነው:: ስለዚህ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ቀልብ ለመሳብ እንሥራ!

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 5/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *