ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሳይቆራረጥ በህዝብ ንቅናቄ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን ያካተተ ነው። በተለይም ሁለተኛው ምእራፍ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 30 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንደሆነም ይፋ ሆኗል። እንዲህ ተጠናከሮ በመተግበር ላይ ያለው መርሃ ግብር የእስከ አሁን ሂደቱና ዘላቂነቱን በተመለከተ፤ በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዩኒት ክፍል አስተባባሪና የአረንጓዴ ዐሻራ አገራዊ መርሃግብር ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ከዶክተር አደፍርስ ወርቁ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ በቅድሚያ ስለቴክኒክ ኮሚቴው ኃላፊነትና ተግባር ቢገልጹልኝ?
ዶክተር አደፍርስ፦ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በማስጀመር በተነሳሽነትም በመምራትም ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስዱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። መርሃ ግብሩ በፌዴራል ሁለት አደረጃጀቶች ያሉት ሲሆን፤ አንዱ የተለያዩ አስፈጻሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተካተቱበት አብይ ኮሚቴ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአብይ ኮሚቴ ውስጥ የተቋቋመ የአረንጓዴ ዐሻራ ቴክኒካል ኮሚቴ ነው።
የቴክኒክ ኮሚቴው የሥራ ድርሻ ከክልሎች ጋር በመነጋገርና ከፌዴራልም ባለሙያዎችን በማሰማራት እንዲሁም መስክ በመሄድ መሬት ላይ ለሚሰራ ሥራ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር አስፈላጊ ድጋፍ በማድረግ፣ ከእቅድ እስከ ክንውን ያለውን ሥራ መከታተል ነው።
በተመሳሳይ የክልል ርእሰ መስተዳድሮች የሚያሰማሯቸው አብይ ኮሚቴና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል። ኮሚቴዎቹ እንደ የአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ ከመሬት፣ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማት ጋር የአደረጃጀት ሥርዓት በመፍጠር፤ እስከታችኛው የቀበሌ እርከን ድረስ በመውረድ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።
አዲስ ዘመን፦ በእነዚህ አደረጃጀቶች ያለው እንቅስቃሴ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር አደፍርስ፦ በእነዚህ አደረጃጀቶች እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ከፍና ዝቅ ያሉ የሥራ ውጤቶች ይኖራሉ። ነገር ግን በጥንካሬ በአርአያነት የሚጠቀሱ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ማለት ይቻላል። ከተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የተሰጣቸው አስፈጻሚ ተቋማት እንዳሉ ይታወቃል። ሆኖም የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት ከዘርፍ መሥሪያ ቤቶች አልፎ ከተቋማቱ ውጭ ያሉትን ሁሉ የሚያሳትፍ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል። መርሃግብሩ ሲጀመር አንድ መሥሪያ ቤት ወይንም ተቋም ብቻ እንዲመራው ሳይሆን፤ ዜጎች ሁሉ ዐሻራቸውን እንዲያኖሩበት ተደርጎ የተቀረፀ ነው።
ከዚህ ቀደም ባለው ተሞክሮ በተለይ በሚኒስቴር ደረጃ ያሉ መሥሪያ ቤቶች የጋራ መድረክ ፈጥረውና እቅድ አውጥተው የሚሰሩት ሥራ አናሳ ነበር። አንዱ ተቋም የሌላውን እቅድ መደገፍ፣ ጥቅምም ካለው የጋራ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ መገፋፋቶች ነበሩ። ለምሳሌ ግብርናው ደኑን በመግፋት የደን መሬቱን ለእርሻ ሥራ ሊያውለው ይችላል። በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የታየው የነበረውን የትብብር ማነስ ወደ ቅንጅታዊ አሠራር እንዲመጣ በማድረግ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መሻሻል ታይቷል።
አሁን ላይ በቅንጅት እየተሠራ ነው። ደኑ፣ የግጦሽ መሬት በየት በኩል ይሁን? ሰፈሩ፣ መንደሩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታው በምን መልኩ ይከናወን? የሚሉትን በጋራ መወያየት እየተቻለ ነው። ይህ ዛሬ ላይ በሚፈለገው ልክ ውጤት ባያስገኝም አሠራሩ በዚህ ከቀጠለ ነገ አንደኛው ልማት ሌላኛውን የማይገፋበት፣ ይልቁንም የአንዱ ልማት ለሌላኛው መሠረት የሚሆንበት ትምህርት ጭምር እየተማርንበት ነው። የአገር ልማትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው እንዲህ ያሉ ቅንጅታዊ ሥራዎች ሲሰሩ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቴክኒክ ኮሚቴ አደረጃጀት መመራቱ አግባብ አይደለም፤ ተቋማዊ መሆን አለበት የሚል ሃሳብ የሚያነሱ የዘርፉ ባለሙያዎች አሉ። እርስዎ ለአስተያየቱ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
ዶክተር አደፍርስ፦ በእርግጥ ይህ ጉዳይ በተለያየ የመድረክ አጋጣሚ ላይ ይነሳል። ሃሳቡ ለምን እንደሚነሳ እረዳለሁ። ጥያቄው የሚነሳው የሚያስተባብረው አንድ መሥሪያ ቤት መሆን አለበት፤ የሚለው አስተሳሰብ በመኖሩ ወይንም ይህ እሳቤም ባለመቀየሩ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ከሚተገብሩ ተቋማት አንዱ ግብርና ሚኒስቴር ነው። ችግኝ የሚያፈላው፣ ዘር የሚያቀርበው፣ መሬት የሚለየው ይኸው ተቋም ነው። ሌላው በአብይ ኮሚቴ ውስጥ ያለው ደንን እንዲያለማ፣ እንዲጠብቅና ጥቅም ላይ እንዲያውል በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ደን ልማት ተቋም ነው። እነዚህ ተቋማት ከፌዴራል እስከ ክልል አደረጃጀቶችን ዘርግተው ደን እንዲጠበቅ ያደርጋሉ። የአረንጓዴ ዐሻራ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ግብርና ሚኒስቴር ነው።
በአደረጃጀቶች ጥንካሬ ላይ መነጋገር ይቻላል። በተለይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አስተዳደር ላይ ያለው አደረጃጀት የዘላቂነት ችግር እንዳለበት በተለያየ ጊዜ ይነሳል። ተቋማት ወጥ የሆነ አሠራር ባለመከተላቸው አፈጻጸማቸውም ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ ያሳያል። አንድ ሥራ ሶስትና አራት ተቋማት ውስጥ የመገኘትና መበታተን ችግር ጥያቄ እያስነሳ ነው። ለምንድነው ወጥነት ያለው ተቋም ያልተመሰረተለት? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይገባዋል።
ጉዳዩ ከሚመለከተው ግብርና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ደን ልማት ተቋም ውጪ ያሉት አካላትም ተቀናጅተው የደን ልማት ሥራውን እንዲያስተባብሩ እና እንዲደግፉ ተደርጓል። ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር ተልእኮው መማር ማስተማር ቢሆንም፤ የአረንጓዴ ዐሻራ አካል እንዲሆን ተደርጓል፤ ምክንያቱ ደግሞ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ወይንም ዘላቂ የደን ልማት ሥራ የትምህርት አካል ከሆነና በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካትቶ ከታች መሠረት እንዲይዝ ከተደረገ ትውልዱ ስለደን፣ ስለመሬት መሸርሸር በአጠቃላይ ስለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኃላፊነት የሚሰማው ይሆናል።
ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናደርጋለን ስንል በገጠር ብቻ ሳይሆን፣ በከተማም ጭምር በመሥራት ሊገለጽ ስለሚገባ የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር አካል ሆኖ እንዲሰራ እየተደረገ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ሰው ቁጥር በመቀነስ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የመሬት መሸርሸርና ለምነት ማጣት በምርታማነት ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖ ምክንያት የገጠር ነዋሪው ወደ ከተማ ለመፍለስ ይገደዳል። ከተሞች የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ከፍ እንዲሉ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያስችላል።
መስኖና ቆላማ ሚኒስቴርም ዋና ሥራው ለመስኖ ልማት የሚውል የውሃ መሠረተ ልማት ማሟላት ከመሆኑ አንጻር ውሃ እንዲኖር አረንጓዴ ልማት ያስፈልጋል። ተቋሙ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ከሚያስተባብር አካል ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ያስፈለገው ለዚህ ነው ። እንደ ኢትዮጵያ በረሃማ የሆነ አገር ደን አልባ መሆን የለበትም። ዝናብ እንኳን ቢኖር ደን ከሌለ የሚዘንበው ዝናብ አሸዋ ጠርጎ ይሄዳል። ይህ ደግሞ በደለል የተሞሉ ወንዞችና ግድብ እንዲኖር በማድረግ ለ 20 ዓመትና ከዚያም በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባው የግድብ መሠረተ ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ በደለል ሊሞላ የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ቢሆን የመርሃ ግብሩ ተባባሪ መሆን ያለበት ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በግዥ ወደ አገር የሚገባውን የደን ውጤት በአገር ውስጥ መተካተት የሚቻለው ለአምራቾች የግብዓት አቅርቦት ምቹ ማድረግ ሲቻል ነው።
በአሁኑ ጊዜ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት ግማሽ ያህሉ ወይም 112 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ 54 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የመጎሳቆልና የለምነቱን ይዘት አጥቷል። የሚመነጠረው ደን መጨምርም ወንዞች መያዝ የሚገባቸውን ያህል ውሃ እንዳይዙ እያደረጋቸው ነው። በሂደትም ዝናብ እየጠፋ ምርት ማምረት የማንችልበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን።
እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች መፍታት የሚቻለው ሁሉም ተቋማት በትብብር ሲሰሩ በመሆኑ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ ማለት፤ በቂ መሬት አርሶ በቂ ምርት ማምረት፣ በቂ ዝናብ አግኝቶ በቂ ውሃ በግድብ ውስጥ በመያዝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና ለመስኖ ልማት ማዋል፣ በቂ የመጠጥ ውሃ ለገጠሩም ለከተማውም ማዳረስ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ የአረንጓዴ ልማት ዘመቻው እና የመርሃ ግብሩ ቀጣይነት ምን ያህል ነው?
ዶክተር አደፍርስ፦ የዘመቻ ሥራ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ብቻ የተጀመረ አይደለም። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አነስ ባለ እንቅስቃሴ በጊዜ ሂደት የደን ልማቱን ለማከናወን ጊዜ የለም። የተጎዳውን የአገሪቱን ግማሽ የቆዳ ሽፋን መልሶ እንዲያገግም አለማድረግ፤ ጉዳቱ እንዲጨምር ያደርጋል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከችግሩ ኋላ እንሄዳለን።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአካባቢ መራቆት ቀውስ ለተደጋጋሚ ድርቅ እያጋለጠ፤ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እና ተደራራቢ ችግር እንዲያጋጥማቸው አድርጓል። እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቋቋም በየአመቱ ሁለት ሚሊዮን የዛፍ ችግኞችን በመትከል በተወሰኑ አስፈጻሚ ተቋማት እንዲመራ ማድረግ ብቻ መሆን የለበትም። መወጣት የሚቻለው በዘመቻ ማህበረሰብን በማሳተፍ ነው።
ለተከታታይ አራት ዓመታት በተከናወነው የዛፍ ችግኝ ተከላ 25 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞች በመትከል ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል። ነገር ግን አሁንም ሽፋኑ ከአምስትና ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ አይሆንም። የተጎዳውን 54 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመሸፈን ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀናል። ይህን ችግር እስክናልፈው ድረስ የርብርብ ሥራ የግድ ይላል።
ዘመቻው እንዳይደበዝዝ ምን መሠራት አለበት? የሚለው ሃሳብ ያስማማል። እኛም እንደቴክኒክ ኮሚቴ ዘመቻው እንዳይቀዛቀዝ ምን መሠራት አለበት የሚለውን እናነሳለን። በዘመቻ ሥራ የተለያዩ ተግዳሮቾች ያጋጥማሉ። ይሄን መሸሸግ አይቻልም። የዘመቻ ሥራ በአንድ ጊዜ ስኬት የሚገኝበት ቢሆንም፤ በተከላ ወቅት የሚፈጠሩ ክፍተቶች በርካታ ናቸው። ችግኞችን በአግባቡ አለመትከል፣ የጉድጓድ አዘገጃጀት ፣አፈር ማልበስ፣ ከተከላ በኋላ ደግሞ እንክብካቤ ማድረግ ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ችግሮቹ እየቀነሱ ቢሆንም ተቀርፈዋል ማለት አይቻልም።
ሆኖም ግን አሁንም ዘመቻው ይደበዝዛል የሚል ስጋት የለንም። እስካሁን ባለው በየአመቱ መሪ ቃላት እየተመረጡ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም በየአመቱ የማስጀመሪያ መርሃግብር ያካሂዳሉ። እነዚህ የማነቃቂያ መንገዶች የመገናኛ ብዙሃንንም ትኩረት በመሳቡ በየጊዜው አጀንዳቸው በማድረግ፤ ለህዝቡ መልእክት በማስተላለፍና መረጃ በመስጠት ሽፋናቸውን መጨመር ችለዋል። በዜጎች በኩል ዐሻራን ለማሳረፍ ያለው ፍላጎት እያደገ ነው።
በአርሶ አደሩ በኩልም መርሃ ግብሩን ከመቀበል ባለፈ የሚተክለውን ችግኝም መምረጥ ተጀምሯል። ችግኝን በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ ወደ መጠቀምም ተሸጋግሯል። ይህን የህዝብ መነቃቃት በማስቀጠል ለችግሮች መፍትሄ መስጠት ከተቻለ በኋላ ዘመቻው በጊዜ ሂደት መስመር ይዞ ወደ በለጠ ተግባር ይሸጋገራል የሚል እምነት አለኝ ።
የዛፍ ችግኝ ተከላው ምድርን አረንጓዴ በማልበስ የተናጋው ሥነምህዳር እንዲመለስ ማድረግ ነው፤ ምርትና ምርታማነት እንዲጨመርም ያስችላል። በዚህ በአንድ ወቅት የመጣው ሃሳብ በጊዜ ሂደት ደግሞ ሰፍቶ ሌላ ሃሳብ ያመጣል። የተሰራውን ሥራ በማየት ተጨማሪ ነገሮችን መስራት ይጠበቃል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በውስጡ አገራዊ እሳቤ ይዞ ብዙ ነገሮችን በመነካካት እየሰፋ የመጣው ለዚህም ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የተገኘውን ተሞክሮ ቢገልጹልን?
ዶክተር አደፍርስ፦ አረንጓዴ ዐሻራ ያስገኘው ነገር አንዱ ማህበረሰቡ የተመናመነውን ደንና የተጎዳውን መሬት መልሶ መተካት እንዳለበት ግንዛቤ ይዟል። ልማቱ ለምርትና ምርታማነት እድገት እንዲሁም አኮኖሚውን በማሳደግ ያለውን አስተዋጽኦ መረዳት ችሏል። የተተከሉ ፍራፍሬዎች ደርሰው ውጤት ስላገኙባቸው ነገ የኢኮኖሚ ምንጭ ናቸው ማለት ጀምረዋል። የፍራፍሬ ችግኝ ብር የሚያስገኝ መሆኑን በደንብ እንደተረዱ አሳይተዋል። የአንድ አቮካዶ አትክልት ችግኝ ዋጋ ከአንድ መቶ ብር በላይ ነው። የደንም ሆነ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ፤ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። ቀደም ሲል በደን ታሪክ ውስጥ የማይታወቅ አሁን ላይ ግን እየተለመደ የመጣው በበልግ ወቅት ችግኝ መትከል ተጀምሯል።
የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የግብርና ሚኒስትሩ በየሳምነቱ አርብ ከአባላቱ ጋር በሥራው ላይ ይወያያሉ። ይገመግማሉ። አንድ ሚኒስትር የሚመራውና ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ስብሰባ የተለመደው የፓርቲ ወይንም የፖለቲካ ጉዳይ ላይ መነጋገር ነው። አረንጓዴ ዐሻራን ለየት የሚያደርገው እንዲህ አይነት መድረክ እንዲፈጠር ማስቻሉ ነው።
በፖለቲካ መሪዎችም ሆነ በተለያየ የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ቶሎ አጀንዳ መሆን መቻሉና ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በአንድ ያሳተፈ መሆኑ ሌላው መገለጫው ነው። በተቋማዊ አደረጃጀትና በአሠራር ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶች ላይ ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች ይኖራሉ። ከዚህ ውጪ አረንጓዴ ዐሻራ እንዳይተገበር የሚፈልግ አካል አለ ብዬ አላምንም።
በአረንጓዴ ዐሻራ በዓለምም ስም አትርፈናል። ኢትዮጵያን በበጎ የማያነሷት አንዳንድ አገራት እንኳን ሊክዱት የማይችሉት ሆኗል። በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በማህበራዊ ድረገጾች ላይ እንዲሁ በስፋት እየተነሳ ነው። እኛም ለጎረቤት አገሮች ጭምር በማቅረብ ተሳትፏችንን አስፍተን የተንቀሳቀስን ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በድክመት የሚነሱና መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
ዶክተር አደፍርስ፦ ጉዳዩ ግዙፍና ትልቅ ዓላማን የያዘ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። በጀትን ጨምሮ ለሥራው የሚያስፈልጉ ነገሮች አለመሟላት፣ ዘር ማዘጋጀት ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረግ የሚፈጠር የጥራት መጓደል፣ በማጓጓዝ ወቅትም በሚፈጠር ችግር በችግኞች ላይ ጉዳት መድረስ፣ ለችግኙ ተስማሚ የሆነ ጉድጓድ አለማዘጋጀትና ቀድሞ በመቆፈር ዝግጁ አለማድረግና ሌሎችም ተያያዥ ክፍተቶች አጋጥመዋል።
በችግኝ ጣቢያዎች የችግኝ ዝግጅት ዓመቱን ሙሉ የማይቋረጥ እንደሆነ ግንዛቤ ባለመኖሩ ፈጥኖ ችግኝ አለማዘጋጀት፣ አብዛኞቹን የችግኝ መደቦች በውስን የችግኝ ዝርያዎች የማስያዝ ፣ ከተከላ በኋላ የእንክብካቤ ማነስ፣ በተበታተነ ቦታ ተከላ ማከናወን ጥቂቶቹ ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው። ሆኖም ግን ክፍተቶቹ መርሃ ግብሩ 2011 ዓ.ም ሲጀመር በነበሩት ጊዜያቶች እንደነበሩት አይደሉም። መሻሻል እየታየ ነው። ችግሩን የበለጠ ለመቀነስ መስራት እንደሚጠበቅ የቤት ሥራ አድርጎ መውሰድ ይገባል።
ችግሮችን መነሻ በማድረግ በተበታተነ ቦታ እየተካሄደ ያለው ተከላ በኩታገጠም እንዲከናወን ምክረ ሃሳብ እየተሰጠ ነው። ለችግኝ ተከላ የሚሆን መሬት በመለየት ካርታ እንዲኖረው ማድረግ፣ ለአፈርና ጥበቃ እንዲሁም ለአትክልትና ፍራፍሬ የሚውለውን መሬትም እንዲሁ መለየት እንደሚያስፈልግ በተከላ ወቅትም የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ ግንዛቤ ከመፍጠር ሥራ ጎን ለጎን በማከናወን መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው።
ችግኞችንም እንዲሁ በመከፋፈል 40 በመቶ ለአገር በቀል ዛፎች፣ 30 በመቶ ደግሞ ፍራፍሬ፣ 30 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ለገበያ የሚውሉ የተለያዩ ችግኞች የመትከል አሠራር እንዲለመድም እንዲሁ ጥረት እየተደረገ ነው። በሁለተኛው ምእራፍም አረንጓዴ ዐሻራ በእውቀት መመራት አለበት የሚል አቅጣጫ ተይዟል።
አዲስ ዘመን፦ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወነው ችግኝ ተከላ በደን ሽፋኑ ላይ ሊኖረው ስለሚችለው አስተዋጽኦ ቢገልጹልን?
ዶክተር አደፍርስ፦ የደን ሳይንስ በሚያዘው መሠረት በተከናወነው ቆጠራ የጽድቀት መጠኑ 80 በመቶ ነው። ይሄ እንደአገር የተወሰደ ነው። ነገር ግን ለቆጠራ ናሙና ሲወሰድ በአንዳንድ አካባቢ የጽድቀት መጠኑ እጅግ በጣም ጥሩ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሊገኝ ይችላል። ይሄ ልዩነቱ የሚፈጠረው እንደ ሥነምህዳሩና እንደሚደረገው እንክብካቤ ነው።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ መስፈርት አንድ ዛፍ ደን ለመባል ሁለት ሜትርና ከዚያ በላይ ማደግ ይኖርበታል። የዓለም የምግብ ድርጅት ያስቀመጠው መስፈርት ደግሞ የዛፎቹ ቁመት ከአምስት ሜትር መብለጥ አለበት ይላል። አንድ መሬት የደን መሬት ነው ለማለት ደግሞ የመሬቱ ስፋት ግማሽ ሄክታር መሆን እንዳለበትና ፤ የዛፉ ጥላ መሬቱን ምን ያህል ሸፈነው የሚለውም በመስፈርት ተቀምጧል። በዚህ መስፈርት ከአራት ዓመት በፊት የተተከሉት ችግኞች ለደን የሚደርሱት ከስድስት ዓመት በኋላ ነው።
አሁን ላይ ጥረት እየተደረገ ያለው ግለሰቦች በየአካባቢያቸው ከሚተክሉት ውጭ በቆጠራ ውስጥ ያለው በየዓመቱ በአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተከላ ይከናወናል። በዚህ ስሌትም እስካሁን በተከናወነው ቢያንስ እስከ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ችግኝ ተተክሎበታል። በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ምን አተረፍን? ምን አጣን? ምንስ እናሻሽል? ሁለተኛውን ዙር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አንዴት እንምራው? በሚል ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል። ጥናቱ ብዙ መረጃ ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን አሁን ላይ ስላለው መረጃ ቢገልጹልን?
ዶክተር አደፍርስ፦ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት አሁን ያለው የደን ሽፋን 17 ነጥብ 2 በመቶ ነው። ይህ መረጃ በዓለም መስፈርት አነስተኛ ነው። በዓለም መስፈርት ከመሬት አጠቃላይ ሽፋን የደን ሽፋን 31 በመቶ መሆን አለበት። በተለይ ደግሞ እንደ አትዮጵያ ተራራማ የሆኑ አገሮች የደን ሽፋናቸው ከ 40 በመቶ በላይ መሆን ይጠበቅበታል። አለበለዚያ ለድርቅ፣ለጎርፍ፣ ለምርትና ምርታማነት መቀነስ ተጋላጭ ይሆናሉ። ኢትዮጵያ እንዲህ ያለው ችግር ውስጥ እንዳትገባ በአስር ዓመት አገራዊ መሪ እቅድ የደን ሽፋኗን ወደ 30 በመቶ ለማድረስ እየሰራች ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን
ዶክተር አደፍርስ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 4/2015