“እኛን የራበን ፍቅር ነው!”

ማሰላሰያ፤

“እህልማ ሞልቷል ሆዴ መች ጎደለ፣

ፍቅራችን ብቻ ነው ያልተደላደለ።”

ይህ ዜማ በተወዳጁ ድምጻዊ ከተቀነቀነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል። “እህል መች ጠፋ ፍቅር እንጂ!” የሚለው የዜማው ማዕከላዊ መልዕክት የብዙዎችን ጆሮ ማርኮ እንደነበር ዕድሜውን ያደለን የዚያ ዘመን ምሥክሮች ያለ መሃላ እውነቱን አረጋግጡ ቢሉን ለምሥክርነት ዓይናችንን አናሽም። ዜመኛው ሊያመላክት የፈለገው መልዕክት ምናልባትም የሚከተሉትን የወቅቱን የሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ በውክልና ለማሳየት አስቦ ሳይሆን አይቀርም።

አንድ ኩንታል ጤፍ በብር አሥራ አምስት መገዛቱን፣ በአምስት ሣንቲም ሁለት ጥምዝ ዳቦ መሸመቱን፣ ሽሮና በርበሬ በገፍ እየተቀመመ በየደጃፉ ላይ መሰጣቱን፣ አማርጠው የሚመገቡት የሆቴል ቤት ራትና ምሣ ከአንድ ብር ያነሰ ዋጋ ይቆረጥለት እንደነበር፣ በወሎ ፈረስና በማሞ ካቻ ዝነኛ አውቶቡሶች “ቦለለለለ” በሚል ዜማ እየተደሰቱ በነፃነትና በፍቅር በስድስት ብር ክፍያ ክፍለ ሀገራት የሚካለሉበት፣ በሃያ አምስት ሣንቲም የደርሶ መልስ ቲኬት አንበሳ አውቶቡስን የሚጋልቡበት ያ ዘመን “የሞኝ ትዝታ” ሳይሆን በርግጥም “እህልማ ሞልቷል” ቢዜምበት ትክክለኛ መገለጫ ስለመሆኑ አያከራክርም።

“አንተ ማነህ? ብሔርህስ ከወዴት ነው? የፖለቲካ አቋምህስ ወደየትኛው ያጋድላል? ወዘተ.” እየተባለ እጅግም በማይጠየቅበት በዚያ ዘመን “ከጾታዊና የአፍላ ወጣቶች መናቆር እና ከአንዳንድ አልፎ ሂያጅ የጎረምሶች ግጭት በስተቀር” እርስ በእርስ መፋቀር፣ ተሳስቦ አብሮ መኖር፣ መረዳዳትና መደጋገፍ ብርቅም ድንቅም አልነበረም። ዜመኛው እንዳለውም ቢያንስ ለዕለት እንጀራ እርካታ እንደዛሬው ብዙ እንባና ብሶት የሚፈስበት ዘመን አልነበረም።

ድምጻዊው “እህልማ ሞልቷል” እያለ ከፍቅረኛው ጋር የተፈጠረውን ግጭት አምርሮ በመግለጽ “ኑሯችን ሊደላደል አልቻለም” ብሎ ማማረሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገር ደረጃ ግን “የፍቅር ርሃብ” እጅግም ጠንቶብን እንደዛሬው መያዥያ መጨበጫ የጠፋበት ዘመን አልነበረም። ዛሬያችንን ከትናንታችን ጋር ስናነጻጽር ግን የተራብነው “በፍቅር ብቻ ሳይሆን በእንጀራ ጉርሻ” ጭምር መሆኑ ምሥክሩ ጀማው ሕዝብ ሳይሆን አገር ራሷ ነች። የእህል ርሃቡም ሆነ የፍቅር ድህነቱን ደርበን የታመምነው ብልሃቱና መፍትሔው በእጃችን እያለ መሆኑ የእንቆቅልሻችንን ክብደት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

ለዚህ ጸሐፊ ትርጉማቸው ከማይገቡት የአገራዊ ብሂሎች መካከል “በዱሮ በሬ ያረሰ የለም” የሚለው ከብዙዎቹ መካከል አንዱ ነው። ዛሬ በጣርና በጭንቅ ብንንፈራገጥም አልሞላ እያለን ነፍሳችን እንዳይወጣ ብቻ ከየትም ተንደፋድፈን እየተሸማን የምንሸምተው የእለት ቀለባችን በዱሮ በሬ ታርሶ ዘሩ ከእኛ ዘንድ ተላልፎ ስለደረሰ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። በትናንት በሬና ገበሬ ታርሶ የዘር እህሉ ከእኛ ዘንድ ባይደርስ ኖሮ ማሳችንም ሆነ ማዕዳችን ጦም ውሎ ጦም ማደር ብቻ ሳይሆን ለህልውናችን ጭምር ፈታኝ በሆነ ነበር። ስለዚህም በዱሮ በሬ አርሰው ለዛሬ ህልውናችን የእህል ዘር ላሸጋገሩልን በሬና ገበሬ ምሥጋናችን ይትረፍረፍላቸው!

“የዱሮን ዘመን ናፋቂ” የሚለው “ትችትም” እንዲሁ የትዝታን ጉልበት የሚያብረከርክ አባባል ነው። በተፈጥሮ የታደልነውን “የትዝታ ፀጋ” በሚያንቋሽሽ መልኩም “ለዘለፋ” ካልሆነ በስተቀር ብዙዎች አባባሉን “በደግነት” አዘውትረው ሲጠቅሱት አይስተዋልም። እርግጥ ነው አንዳንዶች ድብቅ “የዛሬ አፍቃሬነት” አቋማቸውን ለማጉላት ሲፈልጉ ብቻ ለንግግራቸው ማጎልበቻነት ይህንን ብሂል እንደሚጠቀሙበት አይጠፋንም። ድሮ የሚታወሰው “በሚተቹ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን” ወርቃማ የሆኑ ተናፋቂ ትዝታዎች በተሸሸገቡት “ሰም” መሆኑም በፍጹም ሊዘነጋ አይገባም። “ሰምና ወርቅ” እንዲሉ መሆኑን ልብ ይሏል።

ይህንን እውነታ ጥቂት እናፍታታው፡- “ድሮ” የትዝታና የታሪክ ጎታ ነው። “ዛሬ” ደግሞ እየኖርንበት ያለውን የዘመን ዐሻራ የምናሳርፍበት ሰሌዳችን ነው። “ነገም” እንዲሁ የምንጠባበቀውና የምንጓጓለት ተስፋ ነው። ስለዚህ ዛሬን የምናንቆለጳጵሰውን ያህል ትናንትንም እንዲሁ “የጥንቱ ትዝ አለኝ” እያልን ብንቆዝም ሊያስተቸንም ሆነ ሊያስነቅፈን አይገባም። የትናንቱ ከሌለ ዛሬያችን “አቅመ ስንኩል” መሆኑ አይቀርም። በዛሬያችን መነጽር ነገን መናፈቅና ስለ ነገ ማቀድ ካልቻልንም “ኑሯችን ጣዕም አልባ፤ ተስፋችንም መኮስመኑ” አይቀሬ ይሆናል።

“Old songs revive the memories of the good days just like you’re living them again” እንዲሉ የጥላሁን ገሠሠን “ሸበቶ” የዜማ ግጥም ለቁዘማችን መነሻ አድርገን ለመጠቀም የፈለግነው የትናንትን መልካም ትውስታ በሚገባ ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳየን በማመን ነው። ለማንኛውም ለትናንታችን ትንሣኤ አጎናጽፈን ይህንን ያህል በንባብ ከተጓጓዝን ዘንድ ወደ ዛሬው አሀገራዊ እውነታ መለስ ብለን “ያልታደልሽ እንዴት አደርሽ” በማለት ራሮታችንን ለኢትዮጵያችን እንገልጽላታለን።

“ኀዘንሽ ቅጥ አጣ…”

የትናንቶቹም ሆኑ የዛሬዎቹ እናቶችና ነፍስ አወቅ እማወራ እህቶቻችን አልባሳቶቻቸውን መድበው የሚያስቀምጡት ለአዘቦት ቀናት የሚለበሱ፣ ለተለዩ በዓላት (Occasions) የሚያቆነጁና ለልቅሶና ለኀዘን የሚያገለግሉ በሚል ከፋፍለው ነው። እርግጥ ነው የዘመናይ እንስቶች የአለባበስ ፕሮቶኮል ገደብና ዳርቻው ጠፍቶበት የተመሰቃቀለ ይምሰል እንጂ “ኀዘን” ሲያጋጥማቸው ግን “ጥቁር በጥቁር” የመልበሱን ባህል ዛሬም ድረስ ወደ ጎን አልገፉትም።

ይህ ጸሐፊ እውነታውን ለማረጋገጥ ባለቤቱንና ከአንድም ሁለት እናቶችን ስለ ጥቁሩ የኀዘን ልብስ ጉዳይ ጠይቋቸው የሰጡት መልስ “ለኀዘን የሚለበሱ አልባሳትን አዘጋጅታ ከቤቷ የማታኖር ሴት ምኗ ሴት ይባላል።” የሚል አጭር መልስ ሰጥተውታል። የጅምላ ፍረጃው ለጊዜው ባይበረታታም (የሃይማኖትና የባህል ልዩነቶች ስላሉ) ብዙ እህቶቻችንና እናቶቻችን እንደ ትናንቱ ዛሬም በዚህ ጉዳይ ጥንቁቅ መሆናቸውን ግን መካድ ተገቢ አይሆንም።

የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ሊወክሉ ከሚችሉ ተጠቃሽ አባባሎች መካከል “ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ፤ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ” ከሚለው የተሻለ ገላጭ ብሂል ይኖራል ለማለት አያስደፍርም። ከላይ እንደገለጽናቸው እናቶችና እህቶቻችን ሳይሆን አገሬ የኀዘን ጨርቋን (ማቋን) አጣጥፋ ለክፉ ቀን ብላ አላስቀመጠችም። ይልቁንስ አብዛኞቹ ታሪኮቿና ዛሬዎቿ የኀዘን፣ የመከራ፣ የጦርነትና በእርስ በእርስ ሽኩቻ የተሞሉ ስለሆኑ “ማቋን” አውልቃ “የክት ልብስ” የለበሰችባቸው ዘመናት ቢፈተሹ እጅግም እንደሆኑ ለመረዳት አይከብድም።

የምናከብራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራችን የነበሩት ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ በዚያው ባስተማሩን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት በ1959 ዓ.ም “በኀዘን ጨርቅ ተቆራምዳ” ለነበረችው አገራቸው በብዕራቸው ካሰናኙላት ግጥም መካከል ጥቂት አንጓዎች እንዲህ ይነበባሉ። ይህ ጸሐፊ ግጥሙን ካነበበ ወደ አራት አሠርት ዓመታት የተቆጠረ በመሆኑ ሙሉውን ሃሳብ እንዳለ ለማስታወስ መቸገሩ አልቀረም። ትዝ የሚሉትን ብቻ እንዲህ ያስታውሳል።

“ይኸው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣

ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ።

እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣

የእናት ሞት የአባት ሞት የልጅ ሞት ያጠቃት፣

…ጥቁር ያስለበሳት፣

ለካ እርሷ ኖራለች ዘመን የሞተባት።

ይህ ጸሐፊ በአንድ ወቅት በአገራችን አንደኛው የገጠር ክፍል በርከት ያሉ ቀናት ለመቆየት ዕድል አጋጥሞት ነበር። የዚያ አካባቢ በርካታ እናቶች ፀጉራቸውን ተላጭተው፣ ጥቁር ሻሽ እንደነገሩ ሸብ አድርገውና ለእግራቸው ጫማ ተጠይፈው አስተውሎ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በቅርቡ የነበሩትን “ምሁራን” ሲጠይቅ ያገኘው መልስ “ከታሪካዊ ኀዘን ስላልተላቀቁ ነው” የሚል ነበር። መልሱ ትንሽ ጎምዘዝና ጠነን ያለ ቢለስልም “ዘመን የሞተባት” ከሚለው የገጣሚው ሃሳብ ጋር የሚገጥም ይመስላል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

እስከ መቼ ፍቅር ተርበን፣ ሰላም ርቆን፣ እርስ በእርስ መግባባት ተስኖን ለመጠፋፋት እንደጀገንን በዘመን ላይ ዘመን እየካብን ለመኖር እንፈቅዳለን? የእኛ “በላ” ያነሰ ይመስል እስከ መቼስ የፍቅር ርሃብተኛ ተተኪ ትወልድ ለማፍራት እንጨክናለን? በታሪካዊ ኀዘን የተልኮሰኮሰው የኢትዮጵያ የማቅ ልብስ ያነሰ ይመስል ከትናንት ይልቅ በከፋ ሁኔታ ዛሬም በልጆቿ ንፁህ ደም እንዲጠለሽስ ስለምን እንፈቅዳለን? እውነትም “ኀዘንሽ ቅጥ አጣ…” ይሏል እንዲህ ነው።”

የሰላም ቋንቋ ርቆን፣ የውይይት ጠረጴዛ ተጠይፈን፣ ገድሎ መሞትን ምርጫ አድርገን “ይዋጣልን! ይለይልን!” የምንባባለው ፉከራና ቀረርቶ ከማጠፋፋት ውጭ ምን ፈየደልን? ምንስ የተሻለ ትሩፋት አስገኘልን? ሕዝብ ከሕዝብ፣ መንግሥት ከሕዝብ፣ ሕዝብ ከፖለቲከኞች፣ ፖለቲከኞች ከፖለቲከኞች እርስ በእርስ ተነጋግረንና ተመካክረን ኢትዮጵያ የኀዘን ጨርቋን እንድትጥል ከመትጋት ይልቅ ሻምላ ተማዞ ደም መቃባቱ ምን ይረባናል? በልዩነት አንድነትን መርጠን ተከባብረንና ተደጋግፈን እንዳንኖርስ ብሔራዊ አዚም ያደረገብን ከቶውን ምን ይሉት ክፉ መንፈስ ይሆን? “ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልስ ብትሰጡኝ…” አለ ድምጻዊው ቢቸግረው።

አንዱን አገራዊ ችግር ስንዘል ሌላ አርንቋ ፊታችን እየተደቀነ፣ አንዱን የመከራ ጅረት ስንሻገር ሌላ የከፋ ባህር ከፊታችን እየተዘረጋ እስከ መቼ “ለሙሴ በትር” እንደጸለይን እንኖራለን። ስለዚህም ነው “እኛን የራበን ፍቅር ነው!” በማለት ጮክ ብለን ለመናገር የምንዳፈረው።

ተስፋችን ከእለት ወደ እለት እየመነመነ ሲሄድ ሕዝብና መንግሥት ልብ ተቀልብ ሆነው እንደ ባህሉና እንደ ወጉ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ለመነጋገርና ለመወያየት ስለምን ተኳረፉ? ነብየ እግዚአብሔር ኢዮኤል ይህንን መሰል ችግር በዘመኑ አጋጥሞት ኖሮ ሕዝቡን የገሰጸው እንዲህ በማለት ነበር።

“ይህንን ለልጆቻችሁ ንገሩ፣ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ” በማለት ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ከመወያየትና ችግሮቻቸውን ከመፍታት ይልቅ እርስ በእርስ መጠፋፋትን በመምረጣቸው ተስፋቸው እንደምን እንደተሟጠጠ የገለጸው እንዲህ በሚል ጠንካራ ምሳሌያዊ አነጋገር ነበር። “ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፣ ከአንበጣ የተረፈውን ደጎብያ በላው፣ ከደጎብያ የቀረውን ኩብኩባ ፈጀው” (ትንቢተ ኢዮኤል 1፡3-4)።

“ሰማይ ቢቀደድ የአገር ሽማግሌ ይሰፋዋል” የሚለው የሽምግልና ጥበብ ስለምን ተሰወረብን? የመንፈሳዊ አባቶች ግሳጼና የምሁራን ምክረ ሃሳብስ ምነው አልደመጥ አለ?

ጎበዛዝት ሆይ!

“እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣

ወንድም እህት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣

ዘመድ ወዳጅ ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣

አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?”

ይህ ሕዝባዊ ግጥም ምንም እንኳን በዕድሜው “ያረጀና ያፈጀ” ይምሰል እንጂ ዘመን ተሻጋሪ መልእክቱ ግን ለዛሬው አገራዊ ፈተናችን “ትኩስና አስፈላጊ ማስታወሻ” ሊሆን ይችላል። ስለምን ቢሉ በፍቅርና በሰላም እጦት ምክንያት እየጣልንና እየወደቅን አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ ሳይኖር ጭራሺኑ ማርገጃም ሆነ መቀበሪያ እንዳናጣ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ስለሚሆነን ነው። ሰላም ለአገራችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *