ሰሞኑን ሰፈራችን ለተከታታይ አምስት ቀናት ያህል መብራት ጠፋ። በመሃል ለትንሽ ደቂቃዎች፣ ቢበዛ ለሰዓታት ይመጣና ድጋሚ ይጠፋል። መብራት የጠፋባቸው ቤቶች በጣም ጥቂት ናቸው። ያው የተለመደው የመብራት መቆራረጥ ነው በሚል ከዛሬ ነገ ይመጣል እያልን ጠበቅን። አብዛኞቻችን ሥራ ውለን ማታ ስለሆነ የምንገባው ‹‹ምንድን ነው?›› ብሎ ለመጠየቅ ዕድሉ የለም።
አንድ ዕለት ማታ ገና ከሥራ እንደገባሁ የውጭው በር ተንኳኳ። ለበሩ ቅርብ የእኔ ቤት ስለሆነ በሩን ከፈትኩ። ያንኳኩት የጎረቤት ሰዎች ነበሩ። ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ናቸው፤ የቤቱን ባለቤት እንድጠራላቸው ጠየቁኝ። በዚያ ሰዓት እንደማይገባ ነገርኳቸውና ‹‹በሰላም ነው ወይ?›› ስልም ጉዳዩን ጠየቅኳቸው። የመጡበት ጉዳይ የአካባቢው መብራት የሚስተካከለው ገንዘብ ተከፍሎ ስለሆነ ማዋጣት እንዳለብን ነገሩኝ።
እኔም ቆጣ ብዬ ‹‹ለካ ከአቅም በላይ ባልሆነ ችግር ነው እንዴ እስከዛሬ የቆየው?›› በማለት ማስተካከል ግዴታቸው እንደሆነ ተናገርኩ። የመጡት ሰዎች ‹‹ግዴታቸው ነው›› የሚለው እንደማያዋጣ ነገሩኝ። ንግድ ቤቶች ያሉባቸው የአካባቢያችን ቤቶች ብር ከፍለው እንደመጣላቸውም አስረዱኝ። የምርም ደግሞ ንግድ ቤቶች ያሉበት ሰፈር አልጠፋም። እኔም ያስለመዱት ልማድ ዛሬ አይቀረፍ እንግዲህ በሚል ስንት ብር እንደሚያስፈልግ ጠየቅኳቸው። በዚህ የሚስተካከል ከሆነ ችግር የለውም ብየ የጠየቁኝን ብር ከኪሴ አውጥቼ ከፈልኩ፤ የሙስና ተባባሪ ሆንኩ ማለት ነው።
ከቆይታ በኋላ ድጋሚ በሬ ተንኳኳ፤ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል እየገመትኩ ከፈትኩት። ከመጡት ውስጥ አንደኛዋ ናት። የመጣችው ብሩን ለመመለስ ነው። ‹‹ምነው?›› ብዬ ስጠይቃት አንደኛዋ ሴትዮ ‹‹አልከፍልም!›› ብላ ነው። አልከፍልም ብቻ ሳይሆን የሚከፍሉትን ሁሉ አጥብቃ ስለተቃወመችና ስለከለከለች ነው። ምንም እንኳን የመብራቱ አለመስተካከል ቢያናድደኝም በሴትየዋ መከልከል ግን አልተናደድኩም፤ ምክንያቱም ትክክል ናት።
ብሩን ተቀብየ ገባሁ። እንደተለመደው በጨለማ አደርን። በነጋታው ጠዋት አቅራቢያችን ካለ ሱቅ ጎራ ብዬ ‹‹የእናንተ መብራት መጣላችሁ እንዴ?›› ብዬ ስጠይቅ የተሰጠኝ መልስ ገንዘብ ከፍለው የተስተካከለላቸው ስለመሆኑ ነው። በድጋሚ መብራት ያልመጣላቸው ሰዎች ጋ ሄድኩ። እንዲህ ጉዳዩን እንድከታተለው ያደረገኝ የመብራት ፍላጎቴ ሳይሆን ልዩነቱ እንዴት እንደመጣ አስገርሞኝ ነው። የአንደኛውን ቤት ባለቤት ስጠይቃት በንዴት የሰጠችኝ መልስ፤ በአቅራቢያ ከሚገኘው የመብራት አገልግሎት ተቋም በተደጋጋሚ ሄደው ምንም መፍትሔ እንዳልተገኘ ነው። ‹‹ስንሄድ፤ ‹አሁን ይስተካከላል ሂዱ› ይሉናል። ግን እስከ ሁለት ቀን አይመጣም፤ በድጋሚ ስንሄድም ያንኑ ነው የሚሉን›› ነበር ያለችኝ። እንግዲህ እንደሚታማው ሌላ የተለመደ ነገር አለ ማለት ነው።
እንዲህ አይነት ትንንሽ ብልሹ አሰራሮች በግለሰቦች ጥረት አይስተካከሉም። አንድና ሁለት ሰው ‹‹ግዴታችሁ ነው ስሩት!›› ቢል ተሰሚነቱ ያን ያህልም ነው፤ እንዲያውም እልህ ነው የሚያዝበት። ሌላ ተጨማሪ ጥፋት ነው የሚጨመርበት። ለአንድ ብልሹ አሰራር ከበላይ አካል ፈጣን ምላሽ አለመሰጠት ሕዝቡንም ተስፋ ቢስ ያደርገዋል። ‹‹እኔ ተናግሬ ለውጥ ላላመጣ›› የሚል ግዴለሽነትን ያለማምዳል። ሰዎች ዕለታዊ አገልግሎትን ለማግኘት ሲሉ ልክ እንዳልሆነ እያወቁት ይከፍላሉ። ምክንያቱም ‹‹አልከፍልም›› ቢሉ አገልግሎቱን ያጣሉ እንጂ ብልሹ አሰራሩ አይቀረፍም።
ለእንዲህ አይነት የዘቀጠ አሰራር መፍትሔው መንግሥት ቆራጥ ውሳኔ ቢወስን ነበር። ለምሳሌ፡- ይህን የሚያደርጉ አካላት ላይ ፈጣንና ግልጽ እርምጃ ቢወሰድ ዳግም ይህን የሚያደርግ አይኖርም። ዜጎችም ‹‹እኔ ተናግሬ ለውጥ ላላመጣ›› ከሚል ተስፋ አስቆራጭ አመለካከት ይላቀቁና ይደፋፈራሉ። በየአገልግሎት መስጫ ቦታው የእጅ መንሻ እየተባለ የሚሰጠው ሰጪዎች ገንዘብ ረክሶባቸው ሳይሆን ከዚያ ውጭ አገልግሎቱን የሚያገኙበት መንገድ ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበ ስለሆነ ነው።
አሁን አሁን ሕጋዊ እስከሚመስል ድረስ በብዙ አገልግሎት ማግኛ ቦታዎች ላይ ‹‹ቶሎ እንዲሰራልህ…›› የሚባል ነገር እየተለመደ ነው። ቶሎ መሰራትም ሆነ መዘግየት ያለበት በአሰራሩ መመሪያ፣ ባለው የወረፋ ብዛት መጠን እንጂ በሰዎች የኑሮ ደረጃ መሆን የለበትም። አንድ ድሃ አገልግሎት ለማግኘት መደበኛውን የወረፋ ሕግ ሲጠብቅ ገንዘብ ያለው ግን በአቋራጭ ከአሰራሩ ውጭ አገልግሎቱ ሊሰጠው ነው ማለት ነው።
አንዳንድ ጊዜ በመንግሥት ደረጃ የሚነገር መረጃ በዜጎች ዘንድ አመኔታ የሚያጣው በእንዲህ አይነት ልክስክስ ሰራተኞችና አመራሮች ነው። ለምሳሌ፤ በመንግሥት ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር የለም ሊባል ይችላል፤ መብራት የጠፋበት ዜጋ ግን ይህን አያምንም። ‹‹ታዲያ አቅርቦት ካለ ለምን ጠፋ?›› ሊል ይችላል። በመሃል ያለውን ብልሹ አሰራር አይረዳም። በግብርና ግብዓቶች ዘንድ (እንደ ማዳበሪያ አይነቶች) ገበሬው ይማረራል፤ በመሃል ያለውን ደላላ አያውቅም። ከላይ ያለውን መንግሥት ያማርራል።
በእርግጥ በመሃል ያሉ ደላሎችንና ልክስክስ ሰራተኞችን መመንጠር የመንግሥት ኃላፊነት ነው። በዚህ ሊወቀስ ይገባዋል። ያም ሆኖ ግን እንዲህ አይነት ነገሮችን መቆጣጠር ከዜጋውም ይጠበቃል። እርስ በእርስ መማማር ያስፈልጋል።
የሰለጠነ ሰራተኛ የሚፈጠረው የሰለጠነ ዜጋ ሲኖር ነው። የሰለጠነ ዜጋን የሚፈጥረውም የሰለጠነ የመንግሥት አመራር ነው። ተደጋጋፊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። አንዳንድ ተቆርቋሪዎች እንዳሉ ሁሉ አንዳንድ ደንታ ቢስ፤ ይባስ ብሎ የአገር ገጽታ የሚያበላሹ ሰራተኞች ደግሞ አሉ።
ከፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት የአንድ አገር ወዳድ ዜጋ ጥረት ትዝ አለኝ። የብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ይሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙዚዬም ሲቋቋም መሰለኝ። የተበታተኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች እየተፈለጉ ነው። በአንዳንድ ግዴለሽ ሰራተኞች (ሆን ብለውም ሊሆን ይችላል) ብዙ አገራዊ ታሪክ የያዙ ሰነዶች ሜዳ ላይ ተጥለዋል። ሰዎች ከየተጣሉበት እየሰበሰቡ ለተለያዩ ነገሮች መጠቅለያ አደረጓቸው። ሙዚየሙን የማቋቋም ኃላፊነት ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ ግን ያገኘውን ሰነድ ብቻ መሰብሰብ አልበቃውም። በየሱቁ እየዞረ ከኪሱ እያወጣ በራሱ ሳንቲም ገዛቸው።
ልብ በሉ እንግዲህ ልዩነት፤ አንዳንዱ ለማፍረስ ይሰራል፤ አንዳንዱ ደግሞ ራሱ ተጎድቶ ለአገር የሚጠቅም ነገር ይሰራል። ያ ሰውየ እነዚያን ሰነዶች ከየሱቁ የገዛበትን ገንዘብ መንግሥት አያወራርድለትም። ከግልህ ካልገዛህ ተብሎም አይጠየቅም። ከፊቱ ያገኘውን ብቻ መሰነድ ይችላል። ዳሩ ግን የአገሩን ገጽታ የሚሰራው ለተሰጠው ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ከልቡ ነው። ለህሊናው እርካታ ነው።
ብልሹ አሰራርን የሚደጋግሙ የሕዝብና መንግሥት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰራተኞችም ሆኑ አመራሮች ሕዝብና መንግሥት መተማመን እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ። ዜጋው በራሱ ሀገር የሚማረር፣ የራሱን ሀገር የሚጠላ፣ የራሱን መንግሥት የሚራገም እንዲሆን ያደርጋሉ። ከአቅም በላይ ባልሆነ ችግር ለረጅም ቀናት አገልግሎት የተቋረጠበት ዜጋ መማረሩ አይቀርም። ያጋጠመው ችግር በግልጽ ተነግሮት፣ ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ የአካባቢውን ሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢነገር ሕዝቡም ቅር አይለውም። ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲህ አይነት ልክስክስ አሰራሮች ሲለመዱ ግን መማረር ይበዛል። ራሱ ኢትዮጵያዊው ዜጋ ‹‹አይ ኢትዮጵያ!›› ማለት ያበዛል።
ይህ እንዳይሆን፤ መንግሥት በጥቂት ምግባረ ብልሹ ሰራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች የሚደረገውን ብልሹ አሰራር ሊቆጣጠር ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015