አገር ለማኖር ሕግ ማስከበር የህልውና ጉዳይ

ሰሞኑን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተለይም በአማራ ክልል የሚስተዋለው ነገር በእኔ አረዳድ እንኳንስ መሆን ቀርቶ መታሰብም የሌለበት ነው። ኢትዮጵያ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ያለፈችበትን ፈታኝ ሁኔታ ከሚገነዘብና በሁኔታው ቀዳሚው ፍዳ ቀማሽ ከሆነ አካል ይህ የሚጠበቅም የሚታሰብም አይደለም። ስትደማ የከረመች አገር መልሶ ማድማት በእጅጉ መራር ኀዘን ነው።

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህ አካሄድ ጉልበት ከማባከን ያለፈ ተቀባይነት የሌለው ነው። ጦርነት ፍትህና ርትዕ የሚያስገኝ አካሄድ አይመስለኝም። የአገር ህልውና ለውጭ ጠላት እያጋለጡ የህልውና ጦርነት የሚባል ነገርም ተቀባይነት አይኖረውም፤ በአመክንዮም አይሰራም። ጥያቄዎችን በሕጋዊ አግባብ በመጠየቅ እንጂ በጉልበት ለማስፈጸም መሞከርም በእጅጉ አደገኛና ውጤቱም የከፋ ነው።

በአንድ ወቅት ከአንድ ጀነራል ጋር የነበረኝን ቆይታ አስታውሳለሁ፤ እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹በዚህ ዘመን ጫካ ውስጥ ጠመንጃ ይዞ መቀመጥ አያስፈልግም። ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ይመልሳታል እንጂ አይጠቅማትም። ጫካ ውስጥ የሚገባው አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖር ተገዶ ነው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ የሚገፋፋ ነገር የለም። ምህዳሩ የተመቻቸ ይመስለኛል። ዱሮ በአገራችን ምርጫ የለም። አሁን ግን ህዝቡ የሚፈልገውን ይመርጣል የማይበጀውን ይጥላል። በዚህ መሄድ ነው የሚጠቅመው ሁሉም የየራሱ ሃሳብ አለው። ይህ ባህል ጥሩ ነው። ከዚህ ውጭ የእኔ ሃሳብ ብቻ መሆን አለበት ማለት አይጠቅምም፤ አይሆንም። ሌላውም ሃሳብ አለው። የሚበጀውን ደግሞ ህዝቡ ያውቃል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመቻቸ ይመስለኛል›› ነበር ያሉት።

እኔም ይህን ሃሳብ ቃል በቃል ለመውሰድ የተገደድኩበት በምክንያት ነው። በዚህ ዘመን መሪዎችን ለመቅጣት ሁነኛ መፍትሄ በእጃችን ላይ አለ። አንድ ሃቅ መካድ የለብንም። በአማራ ክልል በህዝብ ለዚያውም በአብላጫ ድምጽ የተመረጠ መሪ እና ፓርቲ አለ። ይህ አመራር በአግባቡ ኃላፊነቱን ካልተወጣ የሚቀጣበት መንገድ አለ። የሚፈለገው አካል ወደ ሥልጣን፤ የማይፈለገው ደግሞ ከሥልጣን የሚቀነስበት አመቺ ዕድል አለ።

የምርጫ ወቅት ጠብቆ ያልፈለጉትን አካል በድምጽ መቅጣት በቂ ነው። ትናንት ሕጋዊ እውቅና ያገኘን አካል ዛሬ በጠመንጃ አፈሙዝ ና! ሥልጣንህ ልቀቅ፤ ና! ውረድ! ይዋጣልን! የሚለው አካሄድ አደገኛ ነው። ይህ ልምምድ ኢትዮጵያን ሌት ተቀን ለማተራመስ ለሚያስቡ ታሪካዊ ጠላቶች እጅግ ፈንጠዝያን የሚፈጥር ነው። ይህ ልምምድ የጎረቤት አገር ሶማሊያን ታሪክ የሚያስከትል ነው።

አሁን የሚስተዋለው አካሄድ በፍጥነት ካልተቀጨ በየሰፈሩ ‹‹የሚፈበረኩ›› የጎበዝ አለቆች እንዳሻቸው ፈላጭ ቆራጭ የመሆን ዕድል ይሰጣቸዋል። ሕግና ሥርዓት አይከበርም። በጎበዝ አለቆች የምትተዳደር አገር ደግሞ የውጭ ጠላቶች በፈለጉት መንገድ እኩይ ተግባራቸውን የሚነግዱባት፤ የሚዘውሯትና አስተማማኝ ሕልውና የሌላት ትሆናለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምትገኝን አገር ማንም የጦር መሳሪያ መሸቀጫና ማራገፊያ ያደርጋታል።

ሕግ አልባ የሆነች አገር የጦር መሳሪያ አምራች አገራት ጥይታቸውን የመግደል ብቃት የሚፈትሹባት ምድር ትሆናለች። እንግዲህ በቅርበት ያለችውን ሞቃዲሾ እያየን አዲስ አበባ ዳግማዊ ሞቃዲሾ ትሁን የሚል አስተሳሰብ ያለው አካል አንድም አገሩን የማይወድ፤ አንድም ደግሞ የህሊና መቃወስ ያለበት አካል ሊሆን ይገባል። በመሆኑም አገር አውራ ዶሮ እንደሚበትነው ስጥ መሆን የለበትም። አገር የራበው ጅብ ሞትርፎት የሚሄድ፤ ግሪሳ ብድግ ብሎ የሚከበው ሊሆን አይገባም፤ ለዚያውም በጀግና ሠራዊቷና ህዝቧ ተከብራ የኖረችዋን- ኢትዮጵያ።

በአንድ ወቅት የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ የሚከተለውን ሃሳብ አስፍሮ ነበር። ቀደም ሲል በአጎራባች ክልሎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ተደጋጋሚ ጥቃት ይደርስባቸው እንደነበር በሰፊው ያትታል። ለአብነትም ከቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ማስታወስ በቂ ነው። ለዚህም የአገር መከላከያ ሠራዊት በከፈለው ዋጋ ይህ በአሁኑ ወቅት መስመር ይዟል። በዚያ ክልል አማራ ማፈናቀል የሚባለው ነገር ከተሰማ ቢያንስ አንድ ዓመት አልፏል።

አማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በተሰራ ሥራም በርካታ ሕገ ወጥ ኃይሎችን በመቆጣጠርና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ጠላት በከፈተው አጀንዳ ሳይሆን በልማትና ህዝባዊ ትስስሮች አጀንዳውን ማክሸፍ ተችሏል። ከቀያቸው የተፈናቀሉትም ወደቦታቸው ተመልሰዋል። የጉሙዝ የህብረተሰብ ክፍሎችም ‹‹የአማራ ኢ-መደበኛ ኃይል ሊያጠቃህ›› ነው በሚል ወደጫካ የወሰዱትን የህብረተሰብ ክፍልም ወደስፍራቸው መልሰዋል። ከአፋር ክልል ጋርም የተካሄዱ በርካታ መድረኮች የፀጥታ ስጋት በነበረባቸው አካባቢዎች ላይ የአመራር ለአመራርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ በመቀጠሉ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን በመጠቆም መሻሻሎች እንደነበሩ አብራርተው ነበር።

እኔም ጭምር በአሁኑ ወቅት አንድ የምረዳው ሃቅ አለ። ኦሮሚያ ክልልም በብዛት ሲፈናቀሉ የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በአሁኑ ወቅት እንደ ቀድሞ ተፈናቀሉ የሚለው ዜና ብዙም የሚሰማ አይደለም። ይህ የሚያሳየው በየጊዜው መሻሻሎች መኖራቸውን ነው። ዳሩ ግን በአሁኑ ወቅት እንደ ምክንያት እየተነሱ ከሚገኙ ገፊ ምክንያቶች ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ነገር ግን በአሁኑ ወቅት መፍትሄ እየተበጀላቸው ያሉ ነገሮች ናቸው።

እንግዲህ ከዚህ መረዳት የሚቻለው በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚቃረን ነው። ይህ አካሄድ አደገኛ ነው። በቀላል አረዳድ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ‹‹ኢ-መደበኛ›› ኃይሎች፣ ኦነግ ሸኔ ሌሎች ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመናበብ የሚንቀሳቀሱ ስለመሆናቸው መገመት አይከብድም።

ይህ ካልሆነ ሌላ ተዓምር ሊኖር አይችልም። የመንግሥትን መዋቅር በኃይል በመናድ ሥልጣን የተቆናጠጠ ኃይል ማንኛውንም ነውር ከመፈፀም አይመለስም። ሃይማኖት አይገዛውም፤ ሕግ ድንበር አያበጅለትም፤ ባህልና ይሉኝታ አይገደውም ሥልጣንንም ጠገብሁ አይልም።

በርካታ አገራት መሪ አልባ የሚሆኑት በመሰል ልምምዶች መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ይህን ችግር ከወዲሁ መቅጨት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊሳተፍበትና ይመለከተኛል ማለት አለበት። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየትና በመደራደር ሃሳብን ማስረጽ ይቻላል።

የተለየ ርዕዮተ ዓለም ያለው አካል ሃሳቡን በመሸጥ ተከታዮችን ማፍራትና በፖለቲካ ገበያ ወይንም በምርጫ አሸንፎ መንበረ ሥልጣኑን ሊቆናጠጥ ይችላል። ነገር ግን የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለዚያውም የኢትዮጵያ ህልውና የመጨረሻውን ምሽግ ሥም በማጠልሸት ብሎም በሠራዊቱ ላይ ቃታ በመሳብ አንበረክካለሁ ማለት አንድም ውርደት አንድም እውቀት አልባ መሆን ነው።

በመሆኑም አገር ለማኖር ሕግ ማስከበር የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማወቅ የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን እንደአገር ለማስቀጠልና የሠላም መንገድን የሚያጠለሹትን አደብ ማስገዛት የመንግሥት ግዴታ ነው። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ተባባሪ መሆን ይጠበቅብናል።

ከሰለሞን መክብብ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *