ውጤት እያስመዘገበ ያለው ህብረት ሥራ ኤጀንሲ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በ2015 በጀት ዓመት አቅዶ ያከናወናቸውን ወደኋላ የቀረባቸውን ተግባራት ከሰሞኑ ገምግሟል። በግምገማውም ውጤታማ የሆነባቸውንና ቀሪ የቤት ሥራዎቹን በመለየት በቀጣዩ በጀት ዓመት ለሚሠራቸው ሥራዎች መነሻ ዕቅድ በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ባከናወናቸው በርካታ ተግባራትም በአብዛኛው ከፍ ያለ ውጤት ማስመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አስገንዝቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ አከናወንኩ ያላቸውንና ውጤት ማስመዝገብ ቻልኩ ባላቸው ተግባራት ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ዓሊን አነጋግረናል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ኤጀንሲው የተለያዩ ተግባራትን መፈጸም ችሏል። በመደበኛውና በማደራጃ እንዲሁም በግብይት ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ሰርቷል። በተለይም ከኑሮ ውድነት ጋር በተገናኘ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድቦ ገበያውን ለማረጋጋት ባደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

ከአራት መቶ ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማ መግባት የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ ተችሏል። በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ዝውውር ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ይህ መሆኑ ደግሞ በተለይም በእሁድ ገበያ የአዲስ አበባ ከተማ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ እድል የሰጣቸው እንደነበርና ገበያውን ማረጋጋት የተቻለበት እንደሆነም አንስተዋል።

ኤጀንሲው ከግብይት ባለፈ ህግ የማስከበር ሥራን አጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በኦዲት ተግባር ከፍ ያለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በቁጥጥርና ክትትል ዘርፍም እንዲሁ በርካታ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ያብራራሉ። በተለይም ህግ በማስከበር ሥራ ላይ የህግ ድጋፍ በማድረግ ኤጀንሲው ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሸነፍ አቅሙን አድጓል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት ማለትም በመሰረታዊ የሸቀጦች ስርጭትና በሌሎች ምርቶች ልውውጥ ህገወጥ ተግባር የፈጸሙ 362 የሚደርሱ የአመራር አካላትና የቅጥር ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን ያብራራሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ኤጀንሲው ብድር ወስደው ብድራቸውን ለረጅም ዓመት ያልከፈሉ አካላትን ወደ ህግ በማምጣት ሃብቱን እንዲመልሱና መስመር ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በማበደርና በመበደር እንዲሁም በመቆጠብ ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ ተችሏልም።

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፤ አንደኛው ኦዲትና ቁጥጥር የሚያደርግ ክፍል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ማደራጃ የሚባለው ነው›› የሚሉት አቶ ግዛቸው፤ እነዚህ ሁለት ትላልቅ ክንፎች ሥራውን አስተባብረው ብድርና ቁጠባ ማህበራትንና ግብይቱን ጨምረው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ አለ። በዚህም የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበራት በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠት ችለዋል። በዚህም 6ሺ 562 ለሚደርሱ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በማደራጃው የሥራ ክፍልም እንዲሁ ወጣቱንና ሴቶችን በማደራጀት በቋሚ ቅጥርና በጊዜያዊ ቅጥር አጠቃላይ ከ9ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ያነሳሉ።

የህብረት ሥራ ማህበራቱ ጤናማ አሰራር እንዲኖራቸው ለማድረግ የኦዲትና የህግ ሥራ መሠራቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማዕከልና በክፍለ ከተሞች ቀርበው ክርክር ከተደረገባቸው 107 ኬዞች መካከል ኤጀንሲው 103 ኬዞችን ማሸነፍ ተችሏል። እነዚህ ኬዞቹም ጉድለት ያስመዘገቡ የህብረት ሥራ ማህበራት፣ ብድር ወስደው ያልመለሱ አካላትና ሌሎችም ጉዳዮችን የያዙ መሆናቸውንም ነው ያመላከቱት።

ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት ህብረተሰቡን እያንገላታው ያለውን የኑሮ ውድነት ለመታደግ የህብረት ሥራ ማህበራት ያስፈልጋሉ። እነርሱም በንግዱ ውስጥ ባላቸው አቅም ልክ እየሠሩ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አንስተው፤ ማህበራቱ በተወሰነ መንገድ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሥራት እንደቻሉ ይገልጻሉ። ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድቦ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ገንዘቡ ከተመደበበት ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ከ422ሺህ በላይ ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርቶች ወደ ገበያው መግባት ችለዋል። ከተማ አስተዳደሩ ይህን ሃብት መድቦ ህብረት ሥራ ማህበራቶች ምርቱን ማቅረብ ባይችሉ የኑሮ ውድነቱ ከዚህም በላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጥር ይችል ነበር። እናም በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በጤፍ ምርት ላይ ተፈጥሮ የነበረውን እጥረት ጨምሮ ብዙ ችግሮች በከተማ አስተዳደሩ መልካም ፈቃድና በኤጀንሲው ስራ አማካኝነት ነገሮች እንዲቀሉ ሆነዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጤፍ ላይ የተፈጠረውን እጥረት ለመቅረፍ ከኦሮሚያ፣ ከአማራና ከሌሎችም ክልሎች ጋር በመተባበር ምርትን ለማስገባት በተደረገው ጥረት ከ162 ሺህ ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት ወደ ከተማዋ መግባቱን ጠቁመው፤ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችና መሰረታዊ ሸቀጦች እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን በማህበራቱ አማካኝነት ወደ ከተማ ገብተው ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራም መሰራቱን ያብራራሉ። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ያደረገው ድጎማ እጅግ እንዳገዘም ያነሳሉ።

መንግስት ድጎማውን ያደረገው በጤፍ፣ በስንዴና በቆሎ ምርቶች ላይ ሲሆን፤ በሌሎች የኢንዱስትሪ ምርት በሆኑ እንደ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ ኤጀንሲው አቅዶ የሰራባቸው እንደሆነም ነው የጠቀሱት። ለዚህም 13 ቢሊዮን ብር ለማንቀሳቀስ አቅደው 11 ቢሊዮን ብር ዝውውር ማድረግ እንደቻሉም ያስረዳሉ።

አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በተገቢው መንገድ ለማረጋጋት ከዚህ በበለጠ ምርት ወደ ከተማ መግባት እንዳለበትና ህብረት ሥራ ማህበራቱም ከዚህ በበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ያነሱት አቶ ግዛቸው፤ ማህበራቱ ይህንኑ መሰረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ይላሉ። ለዚህም በአብነት የሚያነሱት የከተማው ነዋሪ ከሚያነሳቸው ችግሮች መካከል ማህበራቱ የሚያቀርቧቸው ምርቶች ከሌሎች የገበያ ቦታዎች ጋር ሲነጻጸር በዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነው።

‹‹ከዚህ ቀደም የምርት ዝውውሩ ችግር ያልነበረበት በመሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ራቅ ብለው በመጓጓዝ ምርቱ ካለበት ቦታ ያመጡ ነበር። ነገር ግን በአሁን ወቅት ያለው የሰላም ሁኔታ ራቅ ብለው ማምጣትን እየገደበ መጥቷል። ይህም ቢሆን ግን የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ከመደበኛው ገበያ ሰፊ ልዩነት ባይኖራቸውም መጠነኛ ቅናሽ አላቸው ››ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለአብነትም ጤፍ ከ1ሺህ500 እስከ 2ሺህ ብር ድረስ ልዩነት አለው፤ ይህ ደግሞ ሊበረታታ የሚገባም ነው ሲሉ ሥራቸው ምን እንደሚመስል ያብራራሉ።

ብዙም ልዩነት አይታይም የሚባለው በፋብሪካ ምርቶች ላይ መሆኑን ያነሱት አቶ ግዛቸው፤ እንደ ፓስታ፣ መኮሮኒና የመሳሰሉት ላይ ነው። ያም ቢሆን እስከ አምስት ብር ድረስ እንደ የአይነቱ ልዩነት ያለው እንደሆነና ህብረተሰቡ ሰፊ ልዩነት ጠብቆ የሚመጣ በመሆኑ እርካታን ማግኘት እንዳልቻለ ያስረዳሉ።

ወደ ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የሚመጣው ህብረተሰብ ትልቅ ልዩነት ይኖራል ብሎ በማመን እንደሆነ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማህበራቱ ምርቶችን ሰፊ በሆነ የዋጋ ልዩነት ማቅረብ እንዳይችሉ ያደረጋቸው የአቅርቦት እጥረቱ እንደሆነ ይናገራሉ። ምርቱ በተለያየ መንገድ ዋጋው ጨምሮ ስለሚመጣ ከተማ ውስጥ ደርሶ ለሸማቹ በሚቀርብበት ጊዜ ዋጋው ከፍ ይላል። ይህ ደግሞ በፍላጎትና አቅርቦት ላይ ባለው ክፍተት ምክንያት ሸማቹ እንዳይረካ ያደርገዋል ይላሉ።

እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ዋናውና ዘላቂው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው። መንግሥት ስንዴ ላይ እየሰራው ያለው ሰፊ ሥራ ለአብነት የሚጠቀስ ሲሆን፤ መሰል ሥራዎችን በተለያዩ ዘርፎች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በከተማ ግብርና እየተመረቱ ያሉ የከተማ ግብርና ምርቶች በእሁድ ገበያ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ እንዲመጣ መስራት ይገባል። ለአብነትም የእንቁላል ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ እየጨመረ ነው። ሌሎች ምርቶችም እንዲሁ በተለይም በየአካባቢውና በየጓሮው የሚመረቱ ምርቶች መጠን ከፍ እያለ ሄዷል። ስለዚህም ከተማ ግብርና ላይ ከተሰራ ከተማ ላይ ዋጋ የማይቀንስበት ምክንያት አይኖርም።

‹‹ዋናው ነገር የኑሮ ውድነቱንና የሸቀጦች ዋጋ ንረትን ለመሸከም የሥራ እድል ያገኘ የህብረተሰብ ክፍል ያስፈልጋል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከተማ አስተዳደሩ በዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና በዚህም ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ብቻ ከ9ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ አንድ ውጤት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የህብረት ሥራ ማህበራቱ ድርሻቸው ውስን ቢሆንም በጥራትና ምቹ በሆነ መንገድ ምርቶችን ለሸማቹ ከማድረስ አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች ስለመኖራቸው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት ወራት የክረምቱ ሁኔታ ጠንከር በማለቱ በተለይም በሽንኩርት ምርት ላይ የመበስበስ ሁኔታ እንዳጋጠመና ውሃ እንደተኛበት ያነሳሉ። ይህም ቢሆን ይላሉ አቶ ግዛቸው ይህም ቢሆን በተቻለ መጠን ጸሐይ ብልጭ ሲል እየተሰበሰበ ወደ ከተማ የሚመጣበትን አማራጭ ተፈጥሯል። ለሸማቹ እየቀረበም ይገኛል በማለት የከተማቸውን ችግርና የፈቱበትን መንገድ ያብራራሉ።

የጥራት ችግር ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪም በጤፍ ምርት ላይም እንዲሁ ያጋጠመ ችግር መሆኑን በማስታወስ፤ በከተማዋ የጤፍ እጥረት በተከሰተ ጊዜ ምርቱን በዘመቻ ወደ ከተማ ማስገባት የተቻለ ቢሆንም የጥራት ችግር ስለመኖሩ ህብረተሰቡ ያቀረበውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ የጤፍ ምርቱን በመሰብሰብ እንዲቀይሩ የማድረግ ሥራ እንደሰሩም ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

በአጠቃላይ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ለሸማቹ የሚያቀርባቸው ምርቶች ጥራታቸው የተጠበቀ፣ በዋጋ ተመጣጣኝና ተደራሽነታቸው ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ የሆነ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። አሁንም ይህንን ሥራውን አጠናክሮ መጓዝ አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ግዛቸው፤ በዋናነት ከክልሎች ጋር ቅንጅት ፈጥሮ መሥራት ይገባል። በክልሎች ካሉ ዩኒየኖችና ከፌዴራል ህብረት ሥራ ኮሚሽን ጋር በጋራ መሥራት ያስፈልጋልም ይላሉ።

አቶ ግዛቸው እንደሚሉት፤ በቀጣይነት ወደ ኮንትራት ግብርና በመግባት ከገበሬው ጋር ውል በማሰር የተለያዩ ምርቶችን እንዲያቀርብና አስቀድሞ እንዲሸጥ በማድረግ ይሠራል። አስፈላጊ የሆነውን ምርት ገበሬው እንዲያመርት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ታስቦና ታቅዶ የሚሠራ ሲሆን፤ ይህም የሚፈለገውን ምርትና የምርት መጠን አስቀድሞ ማወቅ ያስችላል። ለተግባራዊነቱም በክልል ከሚገኙ የግብርና ቢሮዎች፣ የህብረት ሥራ ኮሚሽንና ከክልል ከተማ አስተዳደሮች ጋራ በጋራ መሥራት ይገባል። በዚህም የአቅርቦት፣ የጥራትና የተደራሽነት ችግር ቀስ በቀስ ይፈታል።

ከመሰረታዊ ሸቀጥ ጋር በተያያዘ ሸማቹ ምርቶቹን ሳያገኝ የሚያልቅበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ ከሸማቹ በተደጋጋሚ በሚቀርብ ቅሬታ መመልከታቸውን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ኤጀንሲው የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ እየተጠቀመ ይገኛል። ለአብነትም ከንግድ ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ቴከኖሎጂን በመጠቀም እየሠራ ነው። በዚህም አንድ ሰው አድራሻውና የሚወስደው መጠን ስለሚታወቅ መሰረታዊ ሸቀጦቹን እንዲያገኝ ያደርጋል። ሸማቹ በሚወጣለት ተራ መሰረት መውሰድ የሚችልበት አሰራርም ነው። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት በተወሰነ መልኩ በኮልፌ ቀራንዮና በአዲስ ከተማ ክፍለከተሞች ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል። በሌሎችም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚሰራበት ነው የገለጹት።

ኤጀንሲው ከቋሚ ሥራው ባሻገር የበጎ ሥራ አገልግሎቶችን የሰጠ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ካከናወናቸው በጎ ተግባራት መካከል መቀንጨርና መቀጨጭ ላይ የተሰራው ሥራ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። 9ሺህ500 የሚደርሱ ነብሰጡር እናቶችንና ህጻናትን በመለየት ከህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን እናቶችና ህጻናቱ በየወሩ ሰባት አይነት ምግብ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም 32 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ ከ286 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደረገበት እንደሆነም አቶ ግዛቸው ያነሳሉ።

ሥራው የተጀመረው በተያዘው በጀት ዓመት እንደሆነና በተከታታይ ለ12 ወራት ያለማቋረጥ መዝለቅ ቻለም እንደሆነ ይናገራሉ። በዚህ ደግሞ በርካታ እናቶች ጤናማ ልጅ መውለድ ችለዋል፤ ህጻናቱም የነገ አገር ተረካቢ ሆነው እንዲያድጉ እድል አግኝተዋል። ስለዚህም ይኸው ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆንም አመላክተዋል።

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *