በአገር ደረጃ ከተረጅነት ለመላቀቅና በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል በተለይ በስንዴ ምርት ላይ በተሠራው ጠንካራ ሥራ ከስንዴ ተረጅነት በመላቀቅ ወደ ውጭ ምርት መላክ ተጀምሯል። በተመሳሳይ በሩዝ ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ፤ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ሀገር አቀፍ የሩዝ ሰብል ልማት ፕሮግራም ይፋ ሆኗል። ይህንን እንደ አገር የተያዘውን እቅድ ክልሎች በተግባር ወደ መሬት እያወረዱት ይገኛሉ። ለአብነት ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በቡኖ በደሌ ዞን በበደሌ ወረዳ የሩዝ “ኢንሼቲቭ” ልማትን በክልሉ በይፋ አስጀምረዋል።
በሩዝ ምርት ራስን ከመቻል አልፎ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በተያዘው እቅድ በክልሉ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ለመሸፈን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ700 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሩዝ መሸፈኑን ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ አስታውቀዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ክልል የሩዝ “ኢንሼቲቭ” ልማቱ እየተጧጧፈ ይገኛል። በአገር በሩዝ “ኢንሼቲቭ” ልማት ውጤታማና ምርታማ ለመሆን ምን አስቻይ ሁኔታዎች አሉ? በአንጻሩ ደግሞ በዘርፉ ምን ተግዳሮቶች አሉ? ችግሮቹን ለመፍታት ቀጣይ የቤት ሥራዎች ምንድን ናቸው? በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግሯል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ እንዳብራሩት፤ በአፍሪካ ወደ 32 አገሮች የአህጉሪቱን የሩዝ ልማት ትስስር ለማሳደግ (correlation for African rice development) በአግራና በጃይካ በኩል የሚደገፍ አገራዊ የጋራ ፎረም አላቸው። ኢትዮጵያ የእዚህ ፎረም አባል ነች። በዚህ የጋራ ፎረም አገሮች የ10 ዓመት የሩዝ ሰብል ልማት ዕቅዳቸውን ያቀርባሉ። ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ያቀደችው የሩዝ ምርቷን በእጥፍ ማሳደግ ነበር። ይህንን ግቧን አሳክታለች። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ሩዝ እንደ አገር ዋነኛ ስትራቴጂክ ሰብል አልነበረም። ነገር ግን አሁን ላይ በአገሪቱ ትልቅ የአመጋገብ ለውጥ መጥቷል። ይህንን ተከትሎ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ የሚጠቀም የማህበረሰብ ክፍል እጅግ ብዙ ነው።
በሌላ በኩል ዓለም ላይ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ሰብሎች ተብለው በግንባር ቀደምትነት ከተቀመጡ ሶስት (ስንዴ፣ ሩዝና በቆሎ) ሰብሎች አንዱ ሩዝ ነው። አሁን ላይ እንደ አገር ሩዝ ዋነኛ ሰብል ነው። በአገር ደረጃ ከህዝብ ቁጥር እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ለመሸፈን አንዱ አይነተኛ ሰብል ነው። እንዲሁም ደግሞ ከተሜነት እየተስፋፋ በመምጣቱ የሸማቾች ምርጫ እየጨመረ ይገኛል። በዚህም ሩዝ በሸማቾች ዘንድ በስፋት ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል። በተጨማሪ በሩዝ ምርት ራስን ከመቻል ባለፈ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።
በ10 ዓመቱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር መሰረት ግብርና ሚኒስቴር በልዩ ሁኔታ በ10 ዓመት ውስጥ ሊያሳካቸው ከያዛቸው 10 ፕሮግራሞች “10 in 10” ውስጥ አንዱ የሩዝ ሰብል ልማት ነው። በመርሃ ግብሩ መሰረት በቀጣይ አምስት ዓመት አገሪቱ ከውጭ ከምታስገባው 70 በመቶ ምርት 40 በመቶውን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ወደ 30 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። በ10 ዓመት ውስጥ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ፍጆታዋን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ ምርቷን ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ይህን እቅድ ለማሳካት ለሩዝ ምርት በጣም ተስማሚ የሆኑ ሰባት ማዕከሎች/አካባቢዎች ተለይተው በአማራ ክልል ፎገራ፣ በኦሮሚያ ክልል ጨዋቃ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና አቦቦ፣ በሱማሌ ክልል ጎዴ፣ በጋምቤላ ክልል ፓዌ እንዲሁም ማይጸብሪ በስፋት የሩዝ ሰብል ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው። እነዚህ ማዕከሎች ለሩዝ ሰብል ልማት አየር ንብረታቸው ተስማሚ፣ በቂ የውሃ አቅርቦት ያላቸው እንዲሁም በአንዳንዶቹ አካባቢ ቀደም ሲል የሩዝ ሰብል ልማት ሲካሄድባቸው ስለነበር፤ በቂ ልምድ ያለባቸው በመሆናቸው ሩዝን ለማምረት ምቹ ቦታዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
“የሩዝ ሰብል ልማት ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት እራሱን የቻለ የግብርና መካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል” የሚሉት አቶ ኢሳያስ፤ በዋናነት በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር እንደ አገር ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችሉ የመውቂያ፣ የማጨጃ፣ የማቀነባበሪያ (መፈተጊያ፣ መቦረሻ/polish) … ወዘተ የመሳሰሉ የግብርና ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ የሉም። ይህ ባለመኖሩ በአገሪቱ የሚመረተው የሩዝ ምርት ጥራቱ የወረደ፣ የተሰባበረ፣ በቂ ምርት የማያገኝበት፣ የድህረ ምርት ብክነቱም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ፤ ምርቱም ገበያ ላይ በህብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ አይደለም። በሀገር ውስጥ የሚመረተው ሩዝ ጥራቱ የወረደ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከሌላ ሰብል ጋር (ከጤፍ ወዘተ) ቀላቅሎ ለምግብነት ከማዋል ባለፈ ልክ ከውጪ እንደሚገባው ሩዝ ብቻውን ለምግብነት አያውለውም። በዚህም ከራሷ አልፋ ለሌሎች መትረፍ የምትችል አገር ጥራት ያለው ምርት በስፋት ማምረት ባለመቻሏ ከፍጆታዋ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማውጣት ከውጪ ማስገቧቷ እንደባለሙያም፤ እንደ ዜጋም የሚያስቆጭ ነው።
በፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል የሩዝ ተመራማሪ ዶክተር ባዩ በላይ በበኩላቸው፤ በስንዴ የተጀመረው “ኢንሼቲቨ” በሩዝ ሰብል ልማት ላይ መቀጠሉ ይበልጥ አገሪቱን ውጤታማ ያደርጋታል። ምክንያቱም አገሪቱ ሩዝን በስፋት ለማምረት ተስማሚ የእርሻ መሬት፣ አፈር፣ አየር ንብረት እና በቂ የውሃ ሀብት አላት። እንደ አገር ስድስት ሚሊዮን ሄክታር በዝናብ ብቻ የሩዝ ሰብልን ማልማት የሚቻልበት ተስማሚ የእርሻ ቦታ አለ። ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ የአፍሪካ የውሃ ማማ እንደመሆኗ መጠን ያሏትን የወንዝ ተፋሰሶቿ፤ ጠልፎ በመስኖ የሩዝ ሰብል ለማልማት የሚያስችል በትንሹ 3 ነጥብ 7 ሄክታር ተስማሚ መሬት አላት ይላሉ።
በድምሩ በዝናብና በመስኖ በ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሩዝን በስፋት ማምረት ከተቻለ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎች አገሮች መትረፍ የሚቻልበት እድል መኖሩን የሚናገሩት ዶክተር ባዩ፤ ነገር ግን አገሪቱ ባላት አቅም ልክ እንዳትለማ የሚያደርጋት የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ። አንደኛው ሩዝ አገር በቀል ሰብል ባለመሆኑ፤ በየደረጃው በአርሶ አደሩ፣ በባለሙያው፣ በተመራማሪው …ወዘተ የሩዝ ሰብል ልማት የዕውቀት ውስንነት መሆኑን ያስረዳሉ።
ሌላው በቅድመ እና ድሕረ ምርት የሚታዩ ማነቆዎች አሉ። በማለት እነዚህን ማነቆዎች ሲያብራሩ፤ ሩዝ በሚመረትባቸው አካባቢዎች በቂ የሆነ የመስኖ መሰረተ ልማት አለመዘርጋት፤ በሩዝ ማምረቻ ማዕከሎች ተገቢ ያልሆነ የመሬት ዝግጅት እና የውሃ አያያዝ መኖር፤ እንደሌሎች አገሮች ለአገሪቱ አየር ንብረት ተስማሚ የሩዝ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩም ሆነ በዘርፉ ለሚሰማሩ አልሚዎች በስፋት አማራጭ አለመቅረብ እና የዘር እጥረት መኖር በቅድመ ምርት ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ይናገራሉ።
በአንጻሩ በድህረ ምርት ላይ በተለይ በማቀነባበር ሂደት ላይ የተሻሻሉ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ጥራት ያለው ምርት እንደ አገር እየተመረተ አይደለም። ምርቱም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ አልወጣም። ስለዚህ በቅድመ እና ድሕረ ምርት ባለው ሰንሰለት የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሱን ኃላፊነት በሚገባ ከተወጡ፤ ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት የሚያስፈልጉ የተሻሻሉ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂዎችን በተለይ መንግሥትና በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች ማሟላት ከቻሉ፤ ጥራት ያለውና እሴት የተጨመረበት ምርት በስፋት በአገር ደረጃ ማምረት ይቻላል። በዚህም አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን ፍጆታዋን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ማስቀረት ትችላለች ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አገሪ ቱ ባላት አቅም ልክ ማምረት ከቻለች ከራሷ አልፋ ምርቷን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበት አንድ ዘርፍ ነው። ምክንያቱም አብዛኞቹ ጎረቤት አገሮቻችን በስፋት ሩዝ ተመጋቢዎች ናቸው። በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ በቅርቡ ምርቷን ለጎረቤት አገሮች በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበት የገበያ እድል እንዳላት ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ተመራማሪው “የኢትዮጵያ የሩዝ ሰብል ምርታማነቷ በሄክታር ሶስት ቶን” መሆኑን ጠቁመው፤ የዳበረ የሩዝ ሰብል ምርት ልምድ ያላቸውና በሩዝ ምርት ታዋቂ የሆኑ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ታንዛኒያ፣ ማዳጋስ ካር፣ ዩጋንዳ እና የመሳሰሉት ብዙ ግብዓት ተጠቅመውና መዋለነዋይ አፍሰው የኢትዮጵያን ያህል ምርት አያገኙም። አብዛኞቹ አገሮች በሄክታር የሚያመርቱት ከ 1 ነጥብ 5 እስከ 2 ነጥብ 5 ቶን ብቻ ነው። ስለዚህ ሌሎች አገሮች የሰጡትን ትኩረት ያህል ሰጥተን ግብዓትና መዋለነዋይ ማፍሰስ ከተቻለ ከእነርሱ በእጥፍ ማምረት የሚያስችል አቅሙም፣ ተፈጥሮውም፣ ምርታማነቱ አለ ይላሉ።
አገሪቱ በአማካይ ከባህር ወለል በላይ 2000 ጫማ ከፍታ ላይ ትገኛለች። ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሚሆነው ከዚህ ጫማ ከፍታ በታች ባሉ አካባቢዎች ነው። ስለዚህ ከባህር ወለል በላይ ከ1000 እስከ 1500 ባለው የጫማ ከፍታ ላይ የሚገኙ ጎዴ፣ ጨዋቃ፣ ፓዌ ወዘተ የመሳሰሉ ቆላማ አካባቢዎች ላይ በስፋት ቢሠራ ይበልጥ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተመራማሪው ያስረዳሉ።
በሩዝ ሰብል ምርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አቶ ኢሳያስ ጠቁመው፤ በተለይ ከውጭ ከሚገባው ምርት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችና ሜካናይዜሽን ለማሟላት እንደ አገር ትልቅ ግብ ተቀምጧል። ከዚህ አኳያ ሩዝን በማምረትና በማቀነባበር ሂደት የሚፈጠረውን የምርት ጥራት መጓደል እና ብክነት ለመቅረፍ ከጃፓን መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ይላሉ።
የተሻሉ ማሽኖችን እና ቴክኖሎጂዎችን ከጃፓን በማምጣት ሩዝን በመፈተግና በሞበረሽ ሥራ ላይ በቀጣይ ብዙ አልሚዎች ይሠማራሉ። ሌላው ሼህ ሙሀመድ አላሙዲን በሜድሮክ ኢቨስትመንት ግሩፕ ኩባንያቸው አማካኝነት ደብረ ዘይት አካባቢ ትልቅ የሩዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ገንብተዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሩዝ ማቀነባበሪያ ካምፓኒ የአገሪቱን የሩዝ ምርት ጥራት ለማሳደግ ትልቅ አቅም አለው። ሆኖም ፋብሪካው ካለው የማቀነባበር አቅም አንጻር በቂ የሩዝ ግብዓት በአቅራቢያው እያገኝ አይደለም። ምክንያቱም ሩዝ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ከፋብሪካው በጣም ይርቃሉ። በዚህ የተነሳ ለአገሪቱ የሩዝ ምርት ጥራት የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ አለመሆኑንም ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለፃ፤ በጥናትና ምርምር ተደግፎ በሳይንሳዊ ዘዴ የአገሪቱን የሩዝ ሰብል ልማት ለማሳደግ ፎገራ አካባቢ በጃይካ (Japan international corporation) ድጋፈ ብሔራዊ የሩዝ የጥናትና ሥልጠና ማዕከል ተቋቁሟል። ይህ ትልቅ ዕምርታ ነው። ምክንያቱም ከምንም ተነስተው ዛሬ ላይ በሩዝ ምርት የታወቁት እንደ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች ውጤታማ ሊሆኑ የቻሉት አንዱ የጥናትና ሥልጠና ማዕከል በማቋቋማቸው ነው። እንደ አገር ይህ ማዕከል መቋቋሙ የተለያዩ ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂዎችን ውጤታማነታቸውን ማዕከሉ ላይ ለመፈተሽ ይረዳል። በተለይ የአካባቢው ማህበረሰብ ከማዕከሉ የዕውቀት፣ ግብዓትና ቴክኖሎጂ ያገኛል።
የህብረተሰቡን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ያስችላል። በጥቅሉ ማዕከሉ ከማሳ መረጣ ጀምሮ በአስተራረስ፣ በአዘራር፣ በአጨዳ፣ በመፈተግና በመቦረሽ ወዘተ ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት የሚስተዋሉ የእውቀት ክፍተቶችን በመሙላት ሳይንሳዊና አዋጭ በሆነ ዘዴ በመከወን የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
ከዚህ ባሻገር ከአመጋገብ አንጻር ያለውን ክፍተት ለመሙላት ህብረተሰቡ ሩዝን ከምን ከምን ጋር አቀላቅሎ እንዴት ለምግብነት ማዋል እንደሚችል በአማራ ክልል የአመጋገብ ሥልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኝ አንድ ፕሮጀክት አለ። በዚህም በክልሉ ሩዝን ለምግብነት ከማዋል አኳያ ብዙ እምርታዎች ታይተዋል። እንዲሁም በክልሉ ጥራት ያለውና ገበያ ላይ ተመራጭ የሆነውን “ፐርፖሬትድ” የተሰኘውን የሩዝ ዝርያ ማምረት የሚቻልበት ሥልጠና ተሰጥቷል። ይህ የሩዝ ዝርያ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል። ይህንን ጥራት ያለው የሩዝ ዝርያ በማምረት ሂደት የተለያዩ ማህበራት መሠማራታቸውን አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች እምነት፤ ለሩዝ ሰብል ልማቱ ከእርሻ እስከ ማቀነባበር ባለው ሂደት እራሱን የቻለ የግብርና ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ በማሟላት ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ምርት በስፋት ማምረት ከተቻለ በተለይ ሩዝ በሚበቅልበት አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ከተረጅነት ማላቀቅና እራሳቸውን ችለው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ይቻላል። እንዲሁም የተጀመረውን የሩዝ ልማት “ኢንሼቲቪ” በተመረጡ የሩዝ እርሻ ቦታዎች ላይ በስፋት አጠናክሮ በማስቀጠል፤ አገሪቱ ከራሷ አልፋ ምርቷን ለውጭ ገበያ በማቅረብ፤ ስታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ወጪ በማስቀረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበት ዘርፍ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተዘዋዋሪ የኤዥያ አገሮች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አላቸው። ይህንን ሰፊ ህዝብ መግቦ የሚያሳድርና የምግብ ፍላጎታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እያሟላ ያለው ሩዝ ነው። በተመሳሳይ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ እንደ ስንዴና ሩዝ የመሳሰሉ ሰብሎች ላይ ዘመኑ በደረሰበት ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ተደግፎ የአገርን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ካልተወጣ፤ በፍጥነት እያደገ ከመጣው የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር አኳያ በቀን ሶስቴ ይቅርና አንድ ጊዜ ተመግቦ ማደር ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም