አረንጓዴ አሻራ ለካ ስልጣኔንም እየታደገ ነው…!?

በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ህጻናት በ1ኛ ደረጃ የሕብረተሰብ ሳይንስ ወይም የታሪክ ትምህርት ስለ የሰው ልጅ ስልጣኔ መነሻ “ሜሶፓታሚያ”ወይም የባቢሎን ገነት አልያም የኤደን ገነት ወይም “ለሙ መሬት ማጭዴ ጨረቃ”/the fertile crescent/ተምረዋል። በግሪክ “ሜሶፓታሚያ” ማለት በሁለት ወንዞች መካከል የሚገኝ ለም መሬት ነው። በጢግሪስ እና ዮፍሬጢስ ወንዞች መሐል። ዛሬ ይሄ የፍጥረታትና የስልጣኔ ምንጭ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ እየጠፋ ወደ ምድረ በዳ አቧራነትና አሽዋነት ተቀይሯል።

የዮፍሬጢስ ወንዝ ተፋሰስን ተከትለው በግብር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ወንዙ እየደረቀ ውሃው እጅግ እየቀነሰ፤ ያ ለም መሬትም ተራቁቶ እህል ማብቀል ስላልቻለ የቤታቸውን የጭቃ ጡብ አንድ በአንድ እያነሱ፤ በር፣ መስኮትና ጣራ እየነቀሉ እየተሰደዱ ነው። የመጀመሪያው ተሽከርካሪ/wheel/፣ የመስኖ አውታርና የእጅ ፅሑፍ የተጀመረበት፤ የስልጣኔ መነሻ የተባለው በሰው ልጆች ታሪክ ከጥንታዊ ስልጣኔዎች አንዱ ስለሆነ ነው። የሱመር፣ የአካዲ፣ የባቢሎንና የአሦር ጥንታዊ ባህሎች መገኛም ነበር።

የሜሶፓታሚያ ስልጣኔ ከ10,000 ዓመት ዓለም ጀምሮ በአካባቢው የግብርና ማህበረሰብ የተፈጠረበት፤ በመቀጠልም ከተሞች መቆርቆርና መስፋፋት የጀመሩበት ዘመን ነው። ዜሮን በቁጥርነት መጠቀምን ጨምሮ ሒሳብ የተጀመረው በዚሁ ስልጣኔ ነው። በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ስልጣኔ መነሻ የነበረው ይህ አካባቢ በአየር ንብረት ለውጥ ዳፋ የተነሳ ወደ በርሀማነትና ምድረ በዳነት እየተቀየረ የስልጣኔ አሻራው በሒደት እየጠፋ ነው።

የሶስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ማለትም የክርስትና፣ የእስልምናና የይሁዲ መነሻ ጭምር የሆነው ይህ አካባቢ ዛሬ በአካባቢ አየር ሙቀት የተነሳ በድርቅ እየተመታ ይገኛል። የዛሬን አያድርገውና በ20ኛው መክዘ የኢራቋ ባስራ በውሃ ቦዮቿና በጀልባዎቿ የምስራቋ ቬነስ በመባል ነበር የምትታወቀው። ለሙ ማጭዴ ጨረቃ በመባል የሚታወቀው አካባቢ የዛሬዋን ኢራቅ፣ እስራኤል፣ ሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ቱርክና ኢራን ያካትታል። እነዚህ አካባቢዎች ባለ ለም መሬትና በውሃ የታደሉ ነበሩ። ከፍተኛ ውሃ በመጠቀም የሚታወቀውን ሩዝ ለ2000 ዓመታት ሲያመርት የኖረ አካባቢ ዛሬ በውሃ እጥረት ጉሮሮው ደርቋል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ ላይ ግን የኢራቅ መሬት 40 በመቶ ወደ በርሀማነትና ምድረበዳነት ተቀይሯል። የአየር ንብረት ለውጥና በርሀማነት፤ የውሃ አጠቃቀምና አስተዳደር ችግር፣ ውሃን የሚያባክኑ የመስኖ አውታሮች፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች አለመከናወን፣ የደኖች መመናመንና ችግኝ በወቅቱ አለመተከሉ የስልጣኔ መነሻና ለም የነበረው ሜሶፓታሚያ ከምድረ ገፅ እየጠፋ ነው።

በዚያ ሰሞን ይህን መርዶ እንደነ The New York Times እና BBC ያሉ አለማቀፍ ብዙኃን መገናኛዎች ሲቀባበሉት ስመለከት፤ “አረንጓዴ አሻራ” የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የተራቆተው መሬት እንዲያገግምና የደን ሽፋኑ እንዲመለስና ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባሻገር ለካ ስልጣኔን ከጥፋት ይታደጋል እላለሁ። ለዛውም ከዓለማችን ታላላቅ ስልጣኔዎች አንዱ የሆነውን የናይል ስልጣኔ ወይም የግብጽ ስልጣኔ።

የናይል ወይም የግብጽ ስልጣኔ በታላቁ አሌክሳንደር በ332 ዓ.ም እስከተደመሰሰ ድረስ በዓለማችን ቀደምትና ነባር ስልጣኔ ሲሆን፤ ከ3150 እስከ 3000 ዓመት ዓለም ድረስ የሰሜን ምስራቅ የናይልን ተፋሰስ ተከትሎ የተስፋፋ ገናና ስልጣኔ ነበር። የናይል ወንዝ ለግብጽ ስልጣኔ የደም ስር ነበር። ለግብርናው በጣም አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ለም አፈር በተለይ በክረምት ወቅት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች በደለል መልክ ይዞ ይመጣል። በዚህ ደግሞ ከፍተኛ ምርት ስለሚገኝ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የእደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ቄሶች፣ ጸሐፊዎችና ገበሬዎች ሊፈጠሩ ችለዋል።

በመጓጓዣነትም ያገለግላል። የላይኛውና የታችኛው ግብጽ እየተባለ ይከፈል የነበረውን ፈርኦን ናርመር አንድ አድርጓታል። የግብጽ ስልጣኔ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ እጹብ ድንቅ ኪነ ሕንጻዎች፣ ፒራሚዶችና ቤተመቅደሶች ይታወቃል። ለዓለማችን አዳዲስ የጹሑፍ ጥበቦችን፣ ህክምናን፣ ስነ ሕንጻን፣ የአስተዳደር ጥበቦች፣ ጂኦሜትሪንና ሒሳብን አስተዋውቋል። እንደ ሜሶፓታሚያ ስልጣኔ ሁሉ የአየር ንብረት ለውጥ የግብጽን ስልጣኔ አሻራንም እንደ ትቢያ ሊጠርገው አንድ ሀሙስ ቀርቶት እያለ አረንጓዴ አሻራ በነፍሱ ደርሶለታል።

በኢትዮጵያ ለበርካታና ተከታታይ ዓመታት እየተሰሩ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችና አረንጓዴ አሻራ በመጀመሪያ የአባይን ከዚያ የናይልን ተፋሰስ ከተደቀነበት አደጋ በመታደግ የናይል ስልጣኔንም የዛሬዋን ግብጽም ለማቆየት ያግዛል። እያገዘም ይገኛል። የሜሶፓታምያ እጣ እንዳይደርሰው አድርጓል። ግብጽ ግን ይሄን ዘላቂ ገጸ በረከትና ትሩፋት ማየት ተስኗት ስለ ውሃ ክፍፍልና የጎላ ጉዳት ስለማያደርስባት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፊቷን ትነጫለች። ከጥንት እስከዛሬ ሀገራችንን ለማዳከም ሌት ተቀን ትሰራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ግብጽ ሲሆን ሀገራችንን ብታግዝ በብዙ ታተርፋለች። ሀገራችን ባለፉት 20ና ከዚያ በላይ ዓመታት የሰራችው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች፤ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ የተከለቻቸው እየተከለቻቸው ያሉ ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለግብጽ ስልጣኔ ህልውና እስትንፋስ ናቸው። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት እንመልከት።

ባለፉት 50 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ያደረሳቸውን ጉዳቶች አስመልክቶ ያስጠናውን ጥናት ይፋ ሲያደርግ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ባለፉት 50 ዓመታት ከ4 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ ሲያደርስ 2 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል። የሚያሳዝነው የበለጸጉ ሀገራት ባመጡት ጦስ ዋጋ እየከፈሉ ያሉት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቢሆኑም እነሱም በአየር ንብረት ፍዳቸውን መብላታቸው አልቀረም።

ሰሞነኛውን የአሜሪካና የአውሮፓ ከፍተኛ ሙቀትንና ሰደድ እሳትን ልብ ይሏል። ሆኖም የከፋውን ዋጋ እየከፈሉ ያሉት በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ህይወታቸውን ከሚያጡ 10 ሰዎች ውስጥ ዘጠኙ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ናቸው። ከፈረንጆቹ 1970 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስተዋል። በምስራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል።

አስከፊ ድርቅ፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ ሰደድ እሳት፣ ሱናሚ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሎ ነፋስ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የደረሱ የአየር ንብረት አደጋዎች ናቸው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በአኅጉራችን 1800 አስከፊ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተከስተው 755 ሺህ ህዝብ ሲሞት ከ185 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሷል። አሜሪካ ብቻዋን በዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የ1 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት ጎብኝቷታል። ዛሬም በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ሙቀት እየተሰቃየች ነው።

የእስያ አህጉር ከሁሉም አህጉራት በበለጠ በአየር ንብረት ለውጥ የተጠቃ ሲሆን በነዚህ አደጋዎች ምክንያት የ1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ጉዳት ደርሶበታል። ሌላ የዓለም ባንክ ጥናት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ እስከ 2050 ድረስ ከ38 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችል ይተነብያል። የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ሆነው የሚፈናቀሉት፤ በድርቅ ሳቢያ ሌላ የእርሻ መሬት አሊያም ለየት ያለ ስራ ለመፈለግ ወደ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚፈልሱ አርሶአደሮች እንዲሁም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ይገኙበታል።

በእንቅርት ላይ እንዲሉ የበለጸጉ ሀገራት ለአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ቃል የገቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ድጋፍ አለመፈጸማቸው አኅጉሩ አካባቢ ጥበቃ ላይ ሊሰራቸው ያቀዳቸውን ተግባራት ማስተጓጎሉን የአፍሪካ ህብረት መግለጹ አይረሳም። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባይደን የአየር ንብረት ልዩ መልዕክተኛ ጆን ኬሪ ሰሞኑን አሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምንም አይነት ካሳ እንደማትከፍል መናገራቸው ዓለምን እያስገረመ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 5 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማለትም ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ እና ብሩንዲ በአየር ንብረት ለውጥ ከፉኛ እየተጎዱ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል። በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ፐሬዚዳንት ሃፌዝ ግሃኔም፤ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መጠነ ሰፊ እርምጃ በአፋጣኝ ካልተወሰደ እስከ 2050 ድረስ በርካታ ሚሊየኖች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብለዋል። የካርቦን ልቀት መቀነስን ጨምሮ ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚረዱ እርምጃዎችን በአፋጣኝ መውሰድ ከተቻለ የተፈናቃዮችን ቁጥር በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም አስታውቀዋል።

ሀገራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ካልተስማሙ ከየኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ የከባቢ አየር ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይጨምር ይሆናል ሲል ስጋቱን ያጋራው የTIME ዘገባ በበኩሉ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ዓ.ም 350 ሚሊዮን ሕዝብ ለድርቅ፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ድህነት ሊጋለጥ ይችላል ሲል አበክሮ ያስጠነቅቃል። የዓለም ሙቀት በሽርፍራፊ ሴንትግሬዶች በጨመረ ቁጥር የአየር ንብረት ለውጡ እየተባባሰ ይሄዳል። ይህ ፍርሀትን ለማንገስ ሳይሆን በሳይንቲስቶች የተረጋገጠ ጥሬ ሀቅ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች ላለፉት አስርት ዓመታት ፖለቲከኞች ለአሳሳቢው የአየር ንብረት መዛባት ትኩረት እንዲሰጡት ነጋ ጠባ ቢወተውቱም ሰሚ ሳያገኙ በመቅረታቸው ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የዓለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ርሀብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሀ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት፣ ስራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትንና የጸጥታና የደህንነት ችግርን ከማቃለል ባሻገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል።

ሀገራችንን ብንወስድ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደጋ የነበሩ ወይና ደጋ፣ ወይና ደጋ የነበሩ ቆላ፣ ቆላ የነበሩ በርሀ፣ በርሃ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ሳህራ እጅግ በርሃማ እየሆኑ ነው። ዓመት እስካመት ይገማሸሩ የነበሩ ወንዞች፣ በየገመገሙ፣ በየጋራና በየሸንተረሩ ይንፎለፎሉ የነበሩ ምንጮች ደርቀዋል። ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ የነበረው የደን ሽፋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሶስት በመቶ የማይበልጥ ነበር። አሁን በተደረገ ርብርብ የደን ሽፋኑን ወደ 17 በመቶ ከፍ ብሏል። በአየር ንብረት ለውጡ የተነሳ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ከመመላለሱ ባሻገር በበልግና በመኸረም መከሰት ጀምሯል። ለዚህ አሰቃቂው የቦረናና የሱማሌ ድርቅ ጥሩ አብነት ነው። ከዓመት ዓመት ይከሰት በነበረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የከርሰና የገፅ ምድር ውሃ እጥረት ተከስቷል።

እየተቆራረጠና እየተዛባ የሚጥለውን ዝናብ ቢሆንም ደኖች በመራቆታቸው የተነሳ አፈሩ ውሃ መያዝ ባለመቻሉ ጠብ ባለቁጥር ስለሚሸረሸር የአፈር መከላትን እያባባሰ ግብርናውን አደጋ ላይ ጥሎታል። በዚህ የተነሳ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ተመጣጣኝ ምርት ማምረት አልቻለችም። የግብርና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አይደለም አግሮ ኢንዱስትሪውን ዜጋውን መመገብ እንደተሳነው ከመንገድ ቀርቷል። በቅርብ የወጡ ጥናቶች 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ያትታሉ።

የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ጥሩ ዜና የለውም። እየታረሰ የነበረው መሬት ለምነቱን በማጣቱና በመራቆቱ የተነሳ እየቀነሰና እየተራቆተ ይገኛል። የከፋ የምግብ እህል እጥረት፣ ድህነትና የበዛ ስራ አጥ ባለበት ሀገር መታረስ የሚገባው አብዛኛው መሬት ዛሬም ጦም ያድራል። አበው የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ይቋጥራል፣ ባቄላ ያፈሳል እንዲሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገራችንን ጨምሮ በዓለማችን እያየናቸው ያሉ የደን ቃጠሎዎች፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ውሽንፍር፣ የበርሀ መስፋፋት፣ የወቅቶች መዛነፍ፣ ወዘተረፈ የዓለም ሙቀት መጨመር እነ ትራምፕ እንደ ሚሊቱ የደባ ኀልዮት ሳይሆን የእለት ተእለት የህይወት ገጠመኝ ከሆነ ውሎ አድሯል።

ሰሞኑን እንኳ 100 ሚሊየን አሜሪካውያን እስከ 120 ዲግሪ ፋራናይት ለሚደርስ ከፍተኛ የሙቀት አደጋ ተጋልጠዋል። የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ ድሀ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ባለው የኢንዱስትሪ አብዮት ባካበቱት ሀብት እየተቋቋሙት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ያለእዳቸው ውድ ዋጋ እየከፈሉ ነው። በግብርናችን ያለ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የዓለም ሙቀት መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል።

ዛሬም በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ አልቻልንም። ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኩታ ገጠም ግብርናን፣ በተወሰነ ደረጃ ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመስራት፣ በተለይ ዘንድሮ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ማስቀረት መቻሉ የአተያይ ለውጥ በማምጣቱ ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብር ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *