«በክልሉ በወተትና በዶሮ ሀብት ልማት የተጀመረው ሥራ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው»  – አቶ ተክሌ ጀንባ -የሲዳማ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ

የሲዳማ ሕዝብ ከብዙ ፈተና በኋላ በ2012 ዓ.ም ጥያቄው ተመልሶ፤ ክልል ሆኖ መመሥረቱ ይታወቃል። ከክልል ምሥረታ ማግስት ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በተለይ ክልሉ ውጤታማ የሚሆንበትን አካሄድ ሲያጠና እና ሲፈትሽ ከርሟል፡፡

በተካሔደው ጥናት ክልሉ የመሬት ጥበት ያለበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ባለው መሬት ላይ ውጤታማ መሆን የሚቻልበትን ስልት መቀየስ ተችሏል፡፡ ከዚህ አኳያ አነስተኛ የመሬት ይዞታ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በእንስሳት ሀብት ልማት ላይ እንዲሰማሩ መደረጉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህን በተመለከተ እና የእንስሳት ሀብት ልማቱ ላይ የተሠራው ሥራ ምን ይመስላል? የመኖ ሁኔታ እና የገበያ ትስስሩስ ላይ ምን ተሠርቷል? በሚሉ እና በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን የክልሉን የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጃንባ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በሚከተለው መልኩ አሰናድቶ አቅርቧል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ምን አቅዶ ምንስ ተሳካለት?

አቶ ተክሌ፡- ለክልላችን የ2015 በጀት ዓመት የተለየ ዓመት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።የዓመቱን እቅድ ከመጀመራችን በፊት የገጠር ልማታችንን በተመለከተ መሄድ የሚገባንን ያህል ርቀት ለመሔድ የተቻለንን ጥረት አድርገናል ብዬ መናገር እችላለሁ። በተለይ ከእንስሳት ሀብት ልማታችን አኳያ በምን አግባብ መተግበርና ወጤታማ መሆን ይቻላል የሚለውን ለመረዳት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተቋቋመ አንድ ቡድን በክልሉ ያለውን የመሬት ይዞታ በአግባቡ እንዲያጠና ተደረገ፡፡

የአጥኚው ቡድን ግኝት ያመላከተው አንደኛው በክልሉ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል 27 በመቶ የሚሆኑት በዜሮ ነጥብ ሁለት አምስት ሔክታር በታች በሆነ መሬት ላይ የሚኖሩ ናቸው።ሁለተኛው ደግሞ 46 በመቶ ያህሉ ከዜሮ ነጥብ አምስት ሔክታር በታች በሆነ መሬት ላይ የሚኖሩ መሆናቸው ታውቋል። በዚህ ጥናት አንድ የተረዳነው እውነት ክልላችን በእርሻ ላይ ብቻ በመመሥረት የሚሠራ ከሆነ ውጤት ማስመዝገብ እንደማይችል ነው። ስለዚህ በምግብ ራስን ለመቻል ስለሚከብድ የተለየ አማራጭ መውሰድ የግድ እንደሚልም ተገንዝበናል።

በተለይ 27 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ከሩብ ሔክታር በታች የመሬት ይዞታ ያለው አርሶ አደር ወደሥራ የገባው አማራጭ ገቢ የሚያገኝበት ፓኬጅ ተቀርጾ ነው። በተለይ ደግሞ የእንስሳት ሀብት ልማት ላይ ያተኮርን ሲሆን፣ በፓኬጁ ቅድሚያ እንዲይዝ ያደረግነው የወተት ሀብት ልማት ላይ ነው።በየደረጃው በዶሮ፣ ንብ፣ ዓሣ እና በጎች ሀብት ልማት በሚል ፓኬጆችን ተግባራዊ ወደ ማድረጉ ገብተናል። በተጨማሪ ሐር ልማት እና ከብት ማድለብ ላይ በፓኬጁ ውስጥ እንዲካተት አድርገናል። በዚህም መሠረት በክልላችን በሰባት ፓኬጆች ተመሥርተን ወደ ሥራ ገባን፡፡

ለምሳሌ በወተት ክላስተር ብቻ የለየነው 15 ወረዳ እና ሰባት ከተማ አስተዳድደር በጥቅሉ 22 መዋቅር አለ። በእነዚህ 22 መዋቅሮች ውስጥ ያሉ 104 ቀበሌዎችን ለይተን 312 መንደሮችን በማደራጀት ለአርሶ አደሮች ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ገባን። ይህን መነሻ በማድረግ በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 101 ሺ ዝርያ ለማሻሻል አቅደን በዓመቱ መጨረሻ 102 ሺ የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል 71 ሺ ጥጃዎችን ማግኘት ቻልን።

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ መኖ ወሳኝ በመሆኑ በዘርፉ ሥልጠና ከሰጠን በኋላ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ለማልማት አቅደን 13 ሺ 729 ሔክታር መሬት ላይ በማልማት ማሳካት ችለናል። በዚህ መነሻነት በዓመቱ መጨረሻ 3 ሺ 223 ቶን የወተት ምርት ለማምረት አቅደን ነበር። ከእቅዳችን በላይ ማለትም 3 ሺ 527 ቶን የወተት ምርት ማምረት ችለናል። ለምሳሌ በክልሉ ውስጥ የሚገኘው የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ የወተት ምርት እያቀነባበረ ለውጭ ሀገርና ለሀገር ውስጥ የሚያቀርብ ኩባንያ አለ፤ ለዚህ ኩባንያ 586 ሺ ሊትር ወተት አቅርበናል።ከዛ ውጭ የቀረውን ለአካባቢው ገበያና ለአዲስ አበባ ገበያ ማቅረብ ችለናል።

በዚህ ተግባራችን ከዚህ በፊት በወተት ምርት ገቢ ማግኘት ያልቻሉ አርሶ አደሮች በአሁኑ ሰዓት ፍላጎታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣት ችሏል። በከተማ አካባቢም እኛም በሠራነውና በፈጠርነው ግንዛቤ ከፍተኛ መነቃቃት ታይቷል። በዚህ መሠረት በዘርፉ በተደረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መሠረት በክልላችን ከዚህ ቀደም ቢበዛ ከአንዲት ላም እስከ 15 ሊትር ወተት ይገኝ የነበረው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እስከ 40 ሊትር ወተት ማግኘት ተችሏል። ይህ ውጤት ብዙዎቹን ዘርፉን እንዲቀላቀሉ በማነሳሳት ላይ ይገኛል፡፡

ወተት እንዲያመርቱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አርሶ አደሮችን በኅብረት ሥራ ማኅበራት በማደራጀት ወተት ከማምረት ወደ መሸጥ ገብተዋል። በዚህም መሠረት ከተሞች አካባቢ ምርታቸው የሚቀርብበትን ሥርዓት ዘርግተናል። ለምሳሌ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሁለት ወተት አቅራቢ ዩኒየኖች አዘጋጅተን በሃዋሳ ከተማ ወተት መሸጫ ቦታ ኖሯቸው የሚያመርቱትን ምርት ወደገበያ ያቀርባሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸው መሸጫ ማዕከል ውስጥ ንጹሕ ምርት እየሸጡ በተመጣጠነ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

በተለይ በአሁን ወቅት ከ400 እና 500 በላይ ሊትር ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች መሸጫ ቦታ የማዘጋጀት ሥራ እየሠራን ነው። በዚህ አግባብ ከማምረት እስከ መሸጥ ድረስ ያለውን ክንውን በቅንጅት በመሥራት ከፍተኛ መነሳሳት በመፍጠር ላይ እንገኛለን። በ2016 በጀት ዓመት 150 ሺ የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል 91 ሺ ጥጃዎችን ለማግኘት አቅደን እየሠራን ነው። እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2015 አካባቢ አጠቃላይ ‹‹ክልላዊ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ቀን›› ተብሎ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይፋ ተደርጎ የሚጀመርበት ቀን ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን በ2015 በጀት ዓመት በተሠራው ሥራ የተወለዱ ጥጃዎች አሉ።በዚያው ዕለት የጥጃዎች ኤግዚቢሽን በአንድ ቀበሌ ውስጥ ይካሄዳል። ይህ የሚሆነው በአቅራቢያው ያሉ አርሶ አደሮች እየተሠራ ያለውን ሥራ እንዲያዩና መነቃቃት እንዲፈጠር ለማስቻል ነው።

አዲስ ዘመን፡- የምግብ ዋስትናን ለማረ ጋገጥ በተጨማሪ የዶሮ ፓኬጅ ላይ መታቀዱም ይታወቃል።በዚህ ላይ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ተክሌ፡- በስፋት ሲሠራበት የቆየውና በተለይ የመሬት ጥበት ያለባቸው አርሶ አደሮች ገበያን ከማረጋጋት አኳያ ትልቅ ገቢ የሚያመነጭ ነው ተብሎ እየተሠራበት ያለው ዶሮ ላይ ነው።አርሶ አደሩን ከችግር የሚያስወጣ ከስድስት እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኝበታል ተብሎ የተያዘው የዶሮ ሀብት ልማት ሥራ ነው፡፡

በዚህ ዘርፍ በ2014 በጀት ላይ ያሰራጨነው የዶሮ ብዛት አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብቻ ነው። በ2015 በጀት ዓመት ደግሞ አቅደን የነበረው አራት ሚሊየን ዶሮ ነው።ይህን ስናቅድ እያንዳንዱ አርሶ አደር በቀን ከ50 ብር እስከ 200 ብር ማግኘት ይችላል በሚል መነሻ ነው። ይህ ሲሆን ለምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በምናደርገው ትግል መሠረት ማስቀመጥ እንችላለን። በዚህ መነሻ በአዲሱ በጀት ዓመት 375 ሺ የኅብረተሰብ ክፍል ከዶሮ ሀብት ልማት ተጠቃሚ እናደርጋለን ማለት ነው። ባቀድነው ልክ 4 ሚሊዮን 43 ሺ ዶሮ በማሰራጨት ከእቅድ በላይ ማሳካት ችለናል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክላስተር የተለዩት ሁሉም ወረዳ ማለት በሚያስችል ሁኔታ 30 ወረዳና ሰባት ከተማ አስተዳደር ናቸው። በ37ቱም መዋቅር ላይ 555 መንደር በማደራጀት 66 ሺ አርሶ አደሮች በዶሮ ሀብት ልማት ዘርፍ በቡድን ተደራጅተው የየቡድን መሪ በመምረጥ እና አስፈላጊውን ግብዓት በመውሰድ እንዲሁም በማሠልጠን ወደሥስራ መግባት ችለዋል፡፡

በዚህም የአንድ እንቁላል ዋጋ ሐዋሳ ከተማ አስር ብር ሲሆን፣ ይርጋለም ከተማ ደግሞ ስምንት ብር በመሸጥ ላይ ነው። ወደ ቦንሳ አካባቢ ደግሞ ሰባት ብር ነው። በአሁኑ ወቅት በአንድ አርሶ አደር እጅ እስከ 60 ሺ እንቁላል እስከማግኘት ደርሰናል። በአሁኑ ወቅት በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ ለ2016 በጀት ዓመት ስምንት ሚሊዮን ዶሮ ለማሰራጨት አቅደናል።በዚህም ሁሉም አርሶ አደር ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል ለመፍጠር ተዘጋጅተናል። ከሁለተኛው ከዶሮ ቀጥሎ በሶስተኛነት በሌማት ትሩፋት አሊያም በፓኬጁ የታቀፈው የንብ ማነብ ሥራ ነው፡፡

በክልላችን ቡና አምራች የሆኑ 15 ወረዳዎች አሉን። 15ቱም ወረዳዎች የታቀፉት በንብ ሀብት ልማት ስር ነው። በ15ቱ ወረዳ የሚገኙ 30 ቀበሌዎችን በመለየት እና በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ 30 መንደር በማደራጀት በእያንዳንዱ መንደር ውስጥ በኩታ ገጠም 20 20 አርሶ አደሮችን በመመልመል አሠልጥነናል። እንዲሁም የተሻሻሉ የንብ ቀፎዎችን በማቅረብ እና የንብ አያያዝ ሥልጠና በመስጠት ለመነሻ ዓመት በ15ቱ ቀበሌ የሚኖሩትን 600 አርሶ አደሮችን ማሠልጠን ችለናል።

ማሠልጠን ብቻ ሳይሆን ግብዓት በማቅረብና ዘጠኝ ሺ የንብ ቀፎ በማሰራጨት እያንዳንዱ አርሶ አደር በተለይ ለሚቀጥለው ዓመት ምርጥ ተሞክሮ መቀመር የሚቻልበትን ሥራ ጀመረናል።በተለይ ከቡና አበባ ከፍተኛ የማር ምርት መሰብሰብ የሚቻልበት እድል መኖሩን አይተን በሠራነው ሥራ፤ በማር ሀብት ልማት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበናል።

እያንዳንዱ አርሶ አደር 20 በመቶ ብቻ ከፍሎ የቀረውን 80 በመቶው በሦስት ዓመት ውስጥ እየሠራ የሚከፍልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በ2016 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ ዘጠኝ ሺ ቀፎ ለማሰራጨት ከክልሉ መንግሥት 20 ሚሊዮን ብር ተወስኖ ጸድቋል። በዚህ ዓመትም ወደ 2 ሺ 400 የሚሆኑ አርሶ አደሮችን በመያዝ የንብ ሀብት ልማት ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከዓሣ ሀብት ልማት አኳያስ ያስመዘገባችሁት ውጤት ምን ይመስላል?

አቶ ተክሌ፡- ለዓሣ ሀብት ልማት የተለዩ 12 ቀበሌዎች ናቸው።እነዚህም አካባቢዎች ወንዞች ያሉባቸው እና በቂ ውሃ ያላቸው ናቸው።12 ወረዳዎች በመንደር ተደራጅተው እያንዳንዱ መንደር ሃያ ሃያ አርሶ አደሮችን በማደራጀት ሥልጠና መስጠት ተችሏል። ለእያንዳንዱ አርሶ አደር በጓሮው ውሃ ለመያዝ የሚቆፈርበት አስር ሺ ብር ድጋፍ ተደርጎለት ኩሬ አዘጋጅቶ የክልሉ መንግሥት የዓሳ ጫጩት አቅርቧል።በዚህ መሠረትም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

አርሶ አደሩ በሁሉም የእንስሳት ልማት ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ትልቅ ሥራ ተሠርቷል። በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 240 የጓሮ የዓሣ ኩሬ ለማስቆፈር አቅደን 300 ኩሬ በማስቆፈር በአሁኑ ወቅት እየለማ ይገኛል። እነዚህም በመስከረም ወር ለአገልግሎት ብቁ የሚሆኑ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ለ2016 በጀት ዓመትም በዓሣ ልማት በ12ቱም ወረዳ ተጨማሪ መንደሮችን በመለየት እና ተጨማሪ አርሶ አደሮችንም በማሠልጠን ወደሥራ እንዲገቡ እናደርጋለን። በዚህም በከፍተኛ ደረጃ የዓሣ ልማት ሀብትን በማሳለጥ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ይሆናል።

ሌላው በ14 ቀበሌ ላይ እየተሠራ ያለው የበጎች ልማት ነው። ይህም ልማት እንደ አንድ ፓኬጅ የተወሰደ ነው። በተለይ ደጋማው አካባቢ በምርምር የታወቁ እና መንታ የሚወልዱ በጎች ናቸው። በተለይ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲወልዱ በማድረግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረግን እንገኛለን።በተመሳሳይ ለ2016ም እንዲሁ በተሻለ ለመሥራት ተዘጋጅተናል፡፡

በሌላ በኩል በሐር ልማት የታቀፉ አስር ወረዳ ናቸው፤ በእነዚህ አስሩ ወረዳዎች 310 ሴቶች ተደራጅተው ወደሥራ ገብተው እንዲያመርቱ ሁኔታዎችን አመቻችተንላቸዋል። በመሆኑም በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 897 ኪሎ ግራም የሐር ምርት ማግኘት ችለናል። አንድ ኪሎ አንድ ሺ 500 ብር በመሸጥ በትንሹ 4 ሺ 500 በትልቁ ደግሞ ስምንት ሺ ብር በማግኘት ላይ ይገኛሉ። ተጨማሪ 500 ሴቶችን በማደራጀት በ23 ሔክታር መሬት ላይ የጉሎ ምርት በማቅረብ አንድ ሚሊዮን 600 ሺ የሐር ትል በማቅረብ ተጠቃሚ እናደርጋቸዋለን ብለን አቅደናል።

የመጨረሻው የሥጋ ልማት ክላስተር ተብሎ የተለዩት ስድስት ወረዳዎች ናቸው።በተለይ ቆላማ አካባቢ በሥጋ ሀብት ልማት ዘርፍ ላይ የተለየ አካባቢ ነው። በስድስቱ ወረዳ ያሉ 12 ቀበሌዎችን ለይተን ከእዚህ ውስጥ ደግሞ በ24 መንደሮችን ለእያንዳንዱ መንደር 60 60 አርሶ አደሮችን ለይተን በ90 ቀን ውስጥ እንዴት ማድለብና ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ አሰልጥነናል፡፡

በዚህ አግባብም ወደ ሥራ አስገብተናቸው በ2015 በጀት ዓመት ከፍተኛ ሥራ መሥራት ችለናል። በዚህ በአዲሱ በ2016 በጀት ዓመትም በተመሳሳይ ወረዳዎች እና በተመረጡ ቀበሌዎች እንዲሁም መንደሮች ላይ 600 አርሶ አደር በሥጋ ሀብት ልማት ሥራ ውስጥ አስገብተን ለ2017 አብዛኛውን አርሶ አደር በዚህ ሥራ እናሰማራለን የሚል ርዕይ ሰንቀናል።

በአጠቃላይ በእንስሳት ሀብት ልማቱ ላይ በሰባት ፓኬጅ የሠራነው ሥራ እንደሀገር በግንባር ቀደምትነት የሚያስቀምጠን ነው።በክልል ደረጃ ደግሞ የአሠራር ሥርዓቱ ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ሥራ ነው ማለት ይቻላል።ሥራው በተለይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ እንዲሁም ለወጣቶችም ከፍተኛ የሥራ እድል የፈጠረ ለክልሉ ሕዝብና መንግሥትም ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት የቻለ እና ተስፋ የሚጣልበት ነው። በዚህ ሁኔታ መቀጠል ከተቻለ እንደ ሲዳማ ክልል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ድህነትን ታሪክ እናደርግበታለን።

በዚህ ዘርፍ በ2015 በጀት ዓመት ጅማሬ ላይ እንፈጥራለን ብለን የያዝነው እቅድ ለ20 ሺ የኅብረተሰብ ክፍል ነበር። ይሁንና ከታቀደው በላይ ለ23 ሺ የኅብረተሰብ ክፍል የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። ለምሳሌ በዶሮ ሀብት ልማት ብቻ የተፈጠረውን የሥራ እድል ማስተዋል ይቻላል። ይኸውም የአንድ ቀን ጫጩት እየተረከቡ ለ45 ቀን በማቆየት ለኅብረተሰቡ ከ45 ቀን በኋላ የሚያስረክቡ በወጣቶች ብቻ የተደራጁ 128 ኢንተርፕራይዞች ተፈጥረዋል።

እነዚህ ወጣቶች ከዩኒቨርስቲና ከኮሌጅ የወጡ ሲሆን፣ በመንግሥት ብድር ተመቻችቶላቸው እየሠሩ ነው። ለምሳሌ ከዚህ ጎን ለጎን 10ም 20ም ሺ ዶሮ አስገብተው ሌሎች ወጣቶችን ቀጥረው በማሠራታቸው የሥራ እድል የፈጠሩ አሉ። የሥራ እድሉ የተፈጠረላቸው አካላት በአሁኑ ወቅት ከ3 ሺ እስከ 10 ሺ ዶሮዎችን የሚይዙ ሲሆኑ፣ በዚያው ልክ ደግሞ እንቁላሉንም እያመረቱ የሚገኙ ናቸው። ይህን ዘርፍ ይበልጥ ለማጠናከር ለ2016 በጀት ዓመት በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የእንስሳት ተዋፅዖን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ በዘለለ ወደውጭ አገር ለመላክ የታቀደ ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ተክሌ፡- እኛ በእርግጥ እሱን ታሳቢ አላደረግንም። ዋናው ምክንያታችን አንደኛ በከፍተኛ ደረጃ የወተት ዋጋ ከጊዜ ወደጊዜ በሀገር ውስጥ እያሻቀበ መምጣቱ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የዶሮም ሆነ የእንቁላል ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ የገበያ ችግር ባለመኖሩም ጭምር ነው።ስለሆነም ያሰብነው በቅድሚያ ያለውን የሀገር ውስጥ የገበያ እድልን መጠቀም ነው። ይሁንና ለቀጣዩ ለ2016 በጀት ዓመት ግን እቅድ አለን፤ አንደኛ የሀገር ውስጥ ገበያን በተመለከተ ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ገበያን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት የገበያ ትስስር ላይ አንድ ቡድን ተቋቁሟል።

አዲስ ዘመን፡- የእንስሳቱ ምርታማነት ቀጣይነት እንዲኖረው ጤናቸውን ከመጠበቅ አኳያ የታሰበው እና የተሠራው ምንድን ነው?

አቶ ተክሌ፡- የመጀመሪያ ጉዳይ የዝርያ ማሻሻያ ያልተደረገባቸውን የነባሮቹን ዶሮዎች ቁጥር መቀነስ ነው። በተመሳሳይ የላሞችንም መጠን መቀነስ ነው። የጤና ጉዳይን በተመለከተ ላቦራቶሪ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ነው፤ በቅርቡም ሥራ ይጀምራል። በተጨማሪም በቂ ክትባትም እናዘጋጃለን።ይህ በተለይ ዶሮዎች እንዳይታመሙ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረጊያ ስልት ነው።ክትባት ብቻ ማዘጋጀት ሳይሆን በቂ ባለሙያዎችንም ማዘጋጀትን ይጠይቃል። ስለዚህ በየወረዳውና በየቀበሌው የጤና ባለሙያዎችን መመደብ የግድ ይላል፡፡

ከዚህ አኳያ የ2015 ተግባራትን የማጠናከሩን ሥራ እየሠራን ነው። በቂ የክትባት ግብዓትም ተሟልቷል። ባለሙያዎችንም አሠልጥነናል፤ በዚህም መሠረት ሁሉም ዶሮዎች ክትባት እንዲያገኙ ተደርጓል። ስለሆነም ምንም አይነት ችግር ሳያጋጥመንና ዶሮ ሳይሞትብን 2015 በጀት ዓመት ማጠናቀቅ ችሏል።

በቀጣዩ ዓመትም ልክ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በቂ ግብዓት ለማቅረብ በመሥራት ላይ ነን።በባለሙያ በኩልም በቂ ባለሙያዎችን አሠልጥነን ወደሥራ እንገባለን። ለዚህ በቂ ዝግጅት እያደረገን ነው።በአሁኑ ወቅት ወረዳና ክልል ላሉ በቂ ግብዓት ከወዲሁ ተዘጋጅቷል። በአርሶ አደሮች በኩልም አስቀድመው አያያዙን በአግባቡ በማወቃቸው ሥራው የበለጠ የተሳለጠ እየሆነ መጥቷል።

አዲስ ዘመን፡- ከዶሮ መኖ ጋር በተያያዘስ ምን ታቅዷል?

አቶ ተክሌ፡- በአሁኑ ወቅት ትልቁ ተግዳሮት የመኖ ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል።የዶሮ መኖ በአገር ውስጥ ብቻ በቀላሉ የሚመረት አይደለም፤ ከውጭ አገር በሚገቡ ግብዓቶች የሚዘጋጅም ጭምር ነው። በክልላችን አራት የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አሉ።እነዚህን አራት ፋብሪካዎች በማጠናከር በአካባቢው ከሚገኘው ግብዓት በመጠቀም የተመጣጠነ መኖ እንዲያዘጋጁ እና እያንዳንዱ ወረዳ ላይ ቅርንጫፍ ተከፍቶ አርሶ አደሩ የተመጣጠነ የዶሮ መኖ እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።

በዚህ ዓመት በዓለም ባንክ ድጋፍ ሁለት የዶሮ ማሳደጊያና የመኖ ማቀነባበሪያ ተቋማትን ‹‹የዶሮ መንደር›› በሚል ከወራት በፊት አስመርቀናል። ስለሆነም በቀጣይ ይህን ያስመረቅነውን ማዕከል ወደሥራ እናስገባለን።ይህ ተቋም ወደ ሥራ ሲገባ አንዱ ማዕከል ብቻ በዓመት ውስጥ ወደ 60 ሺ ዶሮዎችን በማሳደግ እና ወደ 500 ሺ ለሚሆኑ ዶሮዎች መኖ በማቀነባበር የሚያቀርብ ይሆናል።ይህ የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል በአካባቢው ከሚገኘው ግብዓት መኖ የሚያቀነባብር ስለሆነ ብዙም የዋጋ መጋነን አይኖረውም። በዚህ አግባብ በተመሳሳይ አይነት ሁኔታ ዘንድሮ የሚመረቅ የዶሮ ማሳደጊያና የመኖ ማቀነባበሪያ ማዕከል አለ። በመሆኑም በቀጣይም የተመጣጠነ መኖ ለማቅረብ እየሠራን ነው።በዚህ አይነት ሁኔታ በ2015 የታዩ የመኖ ችግሮችን በ2016 ለመፍታት እየሠራን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በእንስሳት ሀብት ልማቱ ላይ ባለው የሥራ እድል ወጣቱ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ምን ይመክራሉ?

አቶ ተክሌ፡- በተለይ ለወጣቱ ክፍል ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ቢኖር መማር በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ብቻ ለመቀጠር ሳይሆን ራስን በተለያየ መስክ በማየት ለተሻለ ነገር መነሳት እና መለወጥ ማለት ነው፤ በዋናነት መማር ማለት ራስን መለወጥ ነው። ራስን የተሻለ ለማድረግና ለመለወጥ ከተፈለገ ደግሞ ዝቅ ብሎ መሥራት ግድ እንደሚልና ይህም ለወደፊቱ ከፍታ ላይ የሚያስቀመጥ መሆኑን እገልጽላቸዋለሁ።ወደከፍታ ለመድረስ ደግሞ መሥራት ግድ ይላል።

በክልሉ በወተትና በዶሮ ሀብት ልማት የተጀመረው ሥራ እጅግ በጣም ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ነው።ከዚህ የተነሳ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ኑሮን በተሻለ መልኩ መቀየር የሚያስችል ሥራ ነው። ለምሳሌ አንዲት ላም 25 ሊትር ወተት የምትሰጥ ከሆነ በአንድ ሊትር የሚገኘው ደግሞ 55 ብር ነው። ይህ በ25 ሊትር ወተት ሲሰላ በቀን ከአንድ ላም ብቻ 1 ሺ 250 ብር ይገኛል፡፡

አንደኛ፣ ሁለተኛም ሆነ ሦስተኛ ዲግሪ ያለው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ግን የወር ደመወዙ አስር ሺ ከሆነ በቀን የሚያገኘው ገቢ ሲሰላ 333 ብር ብቻ ነው። ስለዚህ ሁለትና ሦስት ዲግሪ አለኝ የሚል የመንግሥት ሠራተኛ የሚያገኘው ገቢ ምን ያህል ዝቅ እንደሚል መረዳቱ አያዳግትም። ከዚህ የተነሳ የመንግሥት ሥራ ጠባቂ ከመሆን በተመቻቸው የእንስሳት ሀብት ልማት ላይ በመሳተፍ ኑሮን የተሻለ ማድረግ ብልሕነት ነው ባይ ነኝ። ስለሆነም ይህን እድል እንዲጠቀሙ እመክራለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፡፡

አቶ ተክሌ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *