በጃንጥላው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር ካሉት ተቋማትና ከአብዝተውም ተጠቃሾቹ አንዱ ነው- ዩኔስኮ። በመሆኑም ውሳኔዎቹ ገዢ ናቸው፤ ምክረ ሀሳቡም እንደዛው። በመሆኑም፣ በቅርቡ ባስተላለፈው ያልተጠበቀ ውሳኔ ብዙዎች ተደናግጠዋል፤ በርካቶች እንደ ገበቴ ውሃ በመዋለል ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ የደገፉት ሲሆን ጥቂቶች “ወግድ” አይሉት ነገር ሆኖባቸው እንጂ ቢያስወግዱት በወደዱ ነበር።
ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንሳዊ እና ባሕል ድርጅት) እንደ ስሙ በርካታና የገዘፉ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፤ በተለይ በዓለም አቀፍ ትብብር በትምህርታዊ፣ ሳይንስ እና ባሕላዊ መርሐ ግብሮች አማካኝነት ሰላምን፣ ማኅበራዊ ፍትህን፣ የሰብዓዊ መብትን እና የዓለም አቀፍ ደህንነትን ለማበረታታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኝ ድርጅት ነው። የተቋሙ ጽሕፈት ቤት በፓሪስ (ፈረንሣይ) ውስጥ የተገነባ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ከ50 በላይ የመስክ ቢሮዎች ያሉት በመሆኑ በብዙዎች ይታወቃል። በብዙዎች ይጠቀሳል። ለብዙዎችም እንግዳ አይደለምን።
ይህ ድርጅት (UNESCO) ሁሌም በሚሠራው ሥራ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተለይም የባሕል ቅርስ ዝርዝር ተጨባጭ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ምዝገባ ሥራው ሁሌም ሲጠቀስ ይሰማል። በእሱ በኩል እውቅናን ለማግኘትም ብዙዎች ሲታትሩም ነው የሚታዩት። የባሕላዊ ቅርሶች እና ንብረቶች የባለቤትነት መብት ድንጋጌዎችን ሲያፀድቅ (ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ (በሥነጽሑፉ ዘርፍም እንደዛው) ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ናት) … ይታያል። በዛው ልክም፣ ድርጅቱ ከምሥረታው ጀምሮ በትምህርት በኩልም በከፍተኛ ደረጃ በመንቀሳቀስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን፣ ውሳኔዎችን ሲወስን ሲያስተላልፍ ነው የኖረው።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የዛሬው አነጋጋሪ ውሳኔ ነውና እንደሚከተለው እንመለከተዋል። ሰሞኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያወዛገበና እያነታረከ ያለ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ቢኖር ዩኔስኮ የጣለው እገዳ፣ ያወጣው ደንብና ሁሉም የትምህርት ተቋማት ይተገብሩት ዘንድ ያስተላለፈው ዓለም አቀፍ ጥሪ ነው።
ዩኔስኩ የትምህርት ጉዳይ ጉዳዩ እንደ መሆኑ መጠን በጉዳዩ ላይ ሳንካ የሚፈጥሩ ነገሮች ሁሉ እንደሚመለከቱት፤ መፍትሔ ማፈላለግም የሱ ሥራ መሆኑ፤ በዚህም “ለምን ይህንን አደረገ?” የሚል ወቀሳ ሊነሳበት እንደማይችል የታወቀ ነው። በመሆኑም ሰሞኑን ተማሪዎች በትምህርት ተቋሟት ውስጥ (በመማር-ማስተማሩ ሂደት) ምንም አይነት ዘመናዊ የእጅ ስልኮችን (ስማርትፎን) እንዳይጠቀሙ መታገድ ያለባቸው መሆኑን ከውሳኔ ላይ ደርሶ ለተግባራዊነቱ ለየሀገራት የትምህርት ተቋማት ማሳወቁ ነው።
ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በጉዳዩ ላይ በርካታና ሰፋፊ ጥናቶችን ማድረጉን የገለፀ ሲሆን ግኝቶቹም ስማርትፎኖች በልጆቹ (ተማሪዎቹ) ላይ ከጤና ጀምሮ በርካታ ጠንቆችን እንደሚያስከትሉና ለትምህርት ጥራት ወሳኝ የሆነውን የትምህርት ሂደት እጅጉን እንደሚጎዱት፤ ሰው ተኮር የሆነውን የመምህሩን አቀራረብ ሰው ተኮር ያልሆነው ስማርትፎን እንደሚያሰናክለው … ደርሶበታል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ከ200 በላይ የትምህርት ሥርዓቶችን (ኢዱኬሽን ሲስተምስ) መርምሬያለሁ፤ አንዳቸውም የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተማሪዎችና መማር-ማስተማሩ ሂደት ላይ ስለሚያስከትሉት ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ ተገቢውን ሽፋን አይሰጡም፤ በቂ የጥናትና ምርምር ሥራዎችም አልተሠሩበትም … በማለት የሚወቅሰው ድርጅቱ ከሥነልቦና ጀምሮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነትምህርታዊ፣ ግለሰባዊ … ጉዳዮችን “በጥልቀት ተመልክቻለሁ” ያለ ሲሆን፣ በሁሉም መስክ ስማርትፎኖች ጉዳት እንዳላቸውና መታገድ ያለባቸው መሆኑ ላይ ያሰመረበት ሆኖ ይገኛል። ለዚህም ከፖሊሲ አውጪዎች ጀምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲልም ያሳስባል።
ጥናቱ እንደደረሰበት ከሆነ ተማሪዎች ማኅበራ ዊነትን እንጂ ግለኝነትን ከማያበረታታው ትምህርት በማፈንገጥ ግላዊ አስተሳሰብን (“Those urging increasing individualisation may be missing the point of what education is about” ይለዋል ጥናቱ)፣ መነጠልና ከመጠን ያለፈ ሞባይል ስልክ መጠቀምን እያዝወተሩ ሲሆን፣ ከመምህራቸው ጋር እንኳን የገጽ-ለገጽ ግንኙነት እስከማቆምና ለሁሉም ነገር በሞባይል ስልካቸው መተማመን ላይ ሁሉ ደርሰዋል። ትምህርት ቤት ብቻም አይደለም፤ ቤታቸውም ሲሄዱ ይህንን ነው የሚያደርጉት። ይህ ከጤናቸው ጀምሮ በማንኛውም መልኩ የሚደገፍ አይደለም። በመሆኑም፣ ጉዳዩ የመምህራን ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነውና ሁሉም በመተባበር መምህራንን ሊያግዛቸው ይገባል።
እንደ ድርጅቱ ጥናት ስማርትፎኖች ተማሪዎች መረጃዎቻቸውን እርስ በርስ ይዘራረፉ ዘንድ ሁሉ የሚያገለግሉ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገው ጥናት 16 በመቶ ያህሉ ናቸው ለርዳታቸው ጥንቃቄ አድርገው የተገኙት። በመሆኑም፣ አብዛኞቹ ተማሪዎች በወንጀለኞች የሚጠቁ ከመሆኑ አንፃር ስማርትፎኖች በትምህርት ቤቶች ውስጥ መከልከል፤ ወይም በአስፈላጊ ደንብና መመሪያ፣ በጥብቅ ቁጥጥር ሊተዳደሩ ይገባል።
እርግጥ ነው፣ ይህ በ2025 ሙሉ ለሙሉ የበላይነቱን ይይዛል የተባለለት ቴክኖሎጂ (digital revolution እንደ መሆኑ መጠን) ትልቅ አቅም ነው ይዞ የመጣው፤ ይህ የሚካድ አይደለም የሚሉት የዩኔስኮ ዳይሬክተር-ጀነራል አውድሬይ አዞላይ ሲሆኑ፤ ይህ እንደ ማንኛውም ዘርፍ የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ያስፈልገዋል። ካልሆነ ይህ ተገቢ ያልሆነ የተማሪዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም (Excessive or inappropriate student use of technology in the classroom and at home ይሉታል) የትምህርት ጥራትን ያወርደዋል ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንቅፋት ከመሆኑም ባለፈ አውዳሚ ነው፤ የትምህርቱን ክፍለ ጊዜ ሙት ያደርገዋል። የተማሪዎች ተሳትፎ እንዳይኖር ያደርጋል፤ አያዳምጡም፤ አይጽፉም፣ አያነቡምም።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት እንደ ተረጋገጠው የተማሪዎች እና ቴክኖሎጂ ግንኙነት አሉታዊ (negative link) ነው። በሚያስተምር፣ ሰብዕናን በሚገነባ … ደረጃ አይደለም እየተጠቀሙበት ያለው። በመሆኑም ተማሪዎች ስማርትፎኖችን ቢያንስ ትምህርት ቤት ይዘው ሊመጡ አይገባም። ሊታገድ ይገባዋል። ወይም፣ ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት እያደረጉት እንዳለው ራሱን በቻለ ሕግ ሊተዳደር ይገባል። እንደ አንድ ማኅበራዊ ችግር ታይቶ ልጓም ሊበጅለት የግድ ነው።
ሌላው በዚሁ ጥናት (በGlobal Education Monitoring Report Team አማካኝነት የተጠናው “Global education monitoring report, 2023: technology in education: a tool on whose terms?”, 2023) የተነሳው መሠረታዊ ጉዳይ ስማርትፎኖች የእጅ ስልኮች በቀጥታ ከኢኮኖሚ አቅም ጋር የተገናኙና ባለውና በሌለው መካከል ትልቅ ልዩነት መፍጠራቸው ነው።
በጥናቱ እንደ ተረጋገጠው ስማርትፎን ተጠቃሚዎች የፈለጉትን በፈለጉት ጊዜ የሚያገኙ ሲሆን የሌላቸው ደግሞ ምንም ማግኘት አለመቻላቸው፤ ከናካቴውም ክፍል ጥለው ሁሉ በመውጣት ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው፤ ይህም ይበልጥ በኮቪድ-19 ጊዜ “በየቤታችሁ ሆናችሁ ትምህርታችሁን ተከታተሉ (online learning)” በተባለ ጊዜ ከ500 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች (በዓለም አቀፍ ደረጃ) ከትምህርቱ ውጪ እንደሆኑ በግልጽ የተስተዋለ ጉዳይ ነው። አይደለም ስማርትፎን የኤሌክትሪክ ኃይል (መብራት) ያላቸው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከአራቱ አንዱ ብቻ ነው።
በመሆኑም ለሁሉም ተማሪዎች እኩል እድልን መፍጠር ካስፈለገ መፍትሔው ስማርትፎኖችን ከትምህርት ቤቶች ማገድ፤ አለበለዚያም ጥብቅ የአጠቃቀም ሕግ (መመሪያ) ማውጣት ያስፈልጋል። ካልሆነ የትምህርት ኢ-ፍትሐዊነትንና ኢ-እኩልነትን . . . ሁሉ ያስከትላል። አርተፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)ም እንደዛው ሲሆን ለዚህ አይነቱ የቴክኖሎጂ ውጤትና አተገባበር ሥርዓተ ትምህርት ያላቸው (ያዘጋጁ) ሀገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በመሆኑም ሁሉም ሀገራት በዚህም ጉዳይ ላይ አብዝተው ሊያስቡበት እንደሚገባም በጥናቱ ተመልክቷል።
ይህ ትምህርትን እቤት ሆኖ መከታተልን በተመለከተና ተማሪዎች ከገጽ-ለገጽ ይልቅ በተናጠል እንዲማሩ፤ ቴክኖሎጂን (ስማርትፎኖችንና ሌሎችንም) በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠቀሙ በማድረግ በኩል የግል የትምህርት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ስለሚይዙ እነሱም፣ ከማኅበራዊ ፋይዳና ሰብዓዊነት አኳያ አይተውት፣ በጉዳዩ ላይ አጥብቀው እንዲያስቡበት ሲልም የዩኔስኮ ጥናት አስተያየቱን አስፍሯል።
ኦንላየን ትምህርት የራሱ የሆነ ስፍራ ቢኖረውም ክፍል ውስጥ በአካል ተገኝቶ፣ ከመምህር ጋር ገጽ ለገጽ ተገናኝቶና ከብጤ (ፒር) ጋር ሆኖ ትምህርትን መከታተልን ሊተካው እንደይችልም “online learning had its place, but was no substitution for the physical classroom.” በማለት ይሄው ጥናት አስፍሯል።
“ስማርትፎኖችን መጠቀም የተማሪዎች መብት ነው ከሚለው ጀምሮ”፣ ጉዳዩ በተማሪዎች ቤተሰቦች በኩልም ተቃውሞ የቀረበበት ሲሆን፣ የተቃውሞው መንስኤም “ልጆቻችንን በምን እናገኛቸዋለን፣ የትራንስፖርትና የመሳሰሉትን ክፍያዎች የሚከፍሉት በሞባይል ስለሆነ ያ እንዴት ሊደረግ ነው?” ወዘተ የሚሉ ምክንያቶች ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች ይቅረቡ እንጂ ለጥያቄዎቹ መፍትሔዎችም ስላሉ “ስማርትፎኖች ከትምህርት ቤቶች ይታገዱ” የሚለውን ወደ “አይታገዱ” ሊቀይረው አይችልም የሚል ምላሽን ነው ያገኘው።
እገዳ – ከዩኔስኮ ውሳኔ በፊት
ከዩኔስኮ በፊት ቀድመው ስማርትፎን (ሴልፎን) በትምህርት ላይ እያደረሰ ያለውን የከፋ አደጋ በመገንዘብ፤ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን የኢንተርኔት ጥቃት (cyber bullying) በመረዳት እገዳን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት አሉ። ጥናቱ ይህንንም ያካተተ ሲሆን ባደረገው ዓለም አቀፍ ዳሰሳ ከአራት ሀገራት አንዱ በትምህርት ተቋማት የስማርትፎን ስልኮችን አግዷል፤ ወይም በሕግም ይሁን በየተቋማቱ የውስጥ መመሪያ እንዲተዳደሩ ተደርጓል። ከእነዚህ ሀገራት መካከልም ማሳያ ይሆኑ ዘንድ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ደች፣ ጣሊያን … ከነአሠራራቸውና የወሰዷቸው እርምጃዎች ተጠቅሰዋል። በአሜሪካ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 76 በመቶ የሚሆኑት በእጅ ስልኮች ላይ እገዳን ከጣሉ መሰንበታቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ስጋት ከሀገራት ቁርጠኝነት አኳያ
ከላይ በተነጋገርንበት ጥናትም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው ዘንድ እንደ አንድ ትልቅ ስጋት ሆኖ የቀረበው “ይህንን የድርጅቱን ጥናት ወደ መሬት ለማውረድ ሀገራት ምን ያህል ቁርጠኛ ይሆናሉ?” የሚለው ሲሆን፤ ሚዛን የደፋው አስተያየት መጪው ትውልድ የተሻለና የበለጠ ዲሞክራት፣ የበለጠ የምርምር ሰው፣ የበለጠ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች … ይሆን ዘንድ የሚመኙ፤ ከቴክኖሎጂ ተኮር ሳይሆን ሰው ተኮር ራዕይ ያላቸው ሀገራት ጥናቱን ወደ ተግባር እንደሚለውጡት ምንም ጥርጥር የለም የሚለው ነው። ከተማሪዎች መብት አኳያ የሚነሱ ጥያቄዎችም ወሳኝ በሆነ መልኩ ደጋፊ ሊያገኙና ስማርትፎኖችን ዳግም ወደ ትምህርት ተቋማት የሚጋብዙ ሆነው ሊገኙ አልቻሉም።
አጠቃላይ መረጃ
ምናልባት ስማርትፎን ላይ ይህንን ያህል ማተኮሩ ለምን ተ(አስ)ፈለገ? የሚል ገራገር አስተያየት ሊነሳ ይችል ይሆናል። ከሆነ፣ የሚከተለው ጥቅል መረጃ የራሱ መልስ ይኖረዋልና እንመልከተው።
ሜይ 7, 2023 ዳግም የታደሰ (አፕዴት የተደረገ) እና “How Many People Have Smartphones in 2023? (KEY Statistics)” በሚል ርዕስ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳመለከተው በዓለም ላይ 6.925 ቢሊዮን የሚሆነው ሕዝብ የስማርትፎን ተጠቃሚ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 85% አሜሪካውያን፣ 55% እስያውያን (ከዓለም 60% የሚሆነው ሕዝብ ያለው እዚህ አህጉር ነው)፣ 60.5% እንግሊዛውያን… ናቸው። ከ6.925 ቢሊዮን ስማርትፎኖች ውስጥ 98% የሚሆነው በወጣቱ (በተለይም GenZ በሚባለውና እድሜው ከ18-29 ያለው) እጅ መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል። በ2020 ብቻ $50 ቢሊዮን በስማርትፎኖች አማካኝነት ተንቀሳቅሷል። ከ10 የእጅ ስልክ ብራንዶች 7ቱ የስማርትፎን መተግበሪያ (app) ያላቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 89.5% የሚሆነው ማኅበራዊ ሚዳያዎች (ፌስቡክ እና የመሳሰሉት) ላይ የተጫኑ (install የተደረጉ) ናቸው።
94% ደቡብ ኮሪያውያን ስማርትፎን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 6% የሚሆኑት ስማርትፎን ያልሆኑ የእጅ ስልኮች (featured phones) ተጠቃሚዎች ሲሆን፤ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከሚገኙ ሕዝቦች 45% የሚሆኑት ስማርትፎን ተጠቃሚዎች መሆናቸውም ተመልክቷል።
በዚሁ ጥናት ላይ እንደ ሰፈረው፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ የስማርትፎን ተጠቃሚ ቻይና ስትሆን፣ 911.92 ሚሊዮን ቻይናውያን የምርቱ (ቴክኖሎጂው) ተጠቃሚዎች ናቸው (ሕንድ በ439.42 ሚሊዮን ትከተላለች)። ከላይ በተመለከትነው የዩኔስኮ ጥናት መሠረት ቻይና ትምህርት ቤቶች ስማርትፎኖችን የሚያስተዳድሩበት የራሳቸው ሕግና ደንብ ያላቸው ሲሆን፣ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ስማርትፎኖችን መጠቀም የሚቻለው 30 በመቶ ብቻ ነው። ይህም ለቻይና በዩኔስኮ በኩል ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቷል።
በጣም ፈጣንና ውስብስብ ሥራዎችን በማቀላጠፍ የሚታወቀውና ለአሁኑ ዘመን የሰዎች የሥራ ላይ ስንፍና ምክንያት የሆነውን፤ አዝናኝ በመሆኑ ምክንያትም ሠራተኞች በሥራቸው ምርታማ እንዳይሆኑ (ጊዜያቸውን በመሻማት) ያደረገውን ስማርትፎን፤ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ5 ሰዓት በላይ በእሱ ላይ ማሳለፍ ለከፍተኛ የጤና ችግር እንደሚያደርስም በዚሁ ጥናት ላይ ተመልክቷል።
ልክ ከላይ እንደ ተመለከትነው የዩኔስኮ ውሳኔ ሁሉ፣ በርካታ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች ሰዓት ወደ ሥራ ቦታዎች ስማርትፎን ይዘው እንዳይገቡ ማገዳቸውም በጥናቱ ተካትቷል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም