ሊታረም የሚገባው የበጀት አጠቃቀም  -በባለበጀት መሥሪያ ቤቶች

መነሻ ሃሳብ

የፋይናንስ በጀት ለአንድ ሀገር መንግሥት መንግሥታዊ ሥራዎችን ለማከናወን ቀዳሚውን ሚና የሚጫወት፤ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚያስችሉት አቅሞች አንዱ ነው፡፡ ይሄ የፋይናንስ ሃብት ደግሞ አንድም በግብር የሚሰበሰብ ነው፤ አለፍ ሲልም ከውጪ ወይም ከውስጥ ፋይናንስ ተቋማት በብድር የሚገኝ ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ደግሞ ከውጭ መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኝ ብድር እና ርዳታ በእጅጉ ተጠባቂ ነው፡፡

በኢትዮጵያም ከዓመት ዓመት እያደገ የመጣው የፋይናንስ ፍላጎት እና ይሄንኑ ተከትሎ እየጨመረ የሄደው ዓመታዊ በጀት እነዚህን የገቢ ምንጮች በአንድም በሌላም መልኩ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የዘንድሮውን (የ2016 በጀት) እንኳን መመልከት ቢቻል፤ እንደ ሀገር ያስፈልጋል ተብሎ ከተያዘው 801 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ የውጭ ርዳታን ጨምሮ ከግብርና ታክስ ይሰበሰባል ተብሎ የታሰበው (ያውም በበጀት ሰነዱ መሠረት ነው) 520 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነው፡፡

እንደ አጠቃላይ የበጀቱ የፋይናንስ ምንጭ ተብሎ የተቀመጠው (የ2016 በጀት ጠቅላላ ገቢ) የውጭ እርዳታን ጨምሮ 520 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ነው፡፡ ይሄም ቢሆን ግን የ281 ነጥብ 05 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት አጋጥሟል። በመሆኑም ይህንን ጉድለት በብድር ለመሸፈን እና የበጀት ፍላጎቱን ለማሟላት ነው የታቀደው፡፡

የበጀት ድልድሉን ለመመልከት ያህል ደግሞ፣ 203 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብሩ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን፤ 369 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪዎች፣ እንዲሁም 214 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብሩ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ፤ እና 14 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ተደርጎ የተመደበ ነው፡፡

የመንግሥትን መንግሥታዊ ኃላፊነት ለማሳ ለጥ የተቋቋሙ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችም እንደየተልዕኳቸው ክብደትና ሥፋት አንጻር እየተመዘነ ከመደበኛውም፣ ከካፒታሉም፣ ከዘላቂ ልማት ግቡም የሚደለደልላቸው እንደመሆኑ፤ ይሄንኑ ለበጀት ዓመቱ የተመደበላቸውን በጀት በተገቢው ሁኔታ ለታቀደለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ የመጠቀም ኃላፊነትም፣ ግዴታም እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡

ምክንያቱም በጉድለት የታጀበን ሀገራዊ በጀት፣ ለብድር እና ርዳታ ደጅ ተጠንቶ የሚገኝን ሃብት፣ ያላቸው ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የሌላቸውም ከሌላቸውም ላይ ቀንሰው ከሚከፍሉት ግብር የተሰበሰበን ገንዘብ በቁጠባ እና ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ በመጠቀም ሀገርም ሕዝብም ከሃብቱ የሚያተርፉበትን እድል መፍጠር ከእነዚህ ተቋማት እና ተቋማቱ ከሚመሩ አካላት የሚጠበቅ ነው፡፡

እንደ እኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን በዚህ አግባብ የሚገለጹ ተቋማት ምን ያህል ናቸው ቢባል ከ50 እና 60 በመቶ የሚሻገሩ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ከፊሉ የተበጀተለትን በጀት 25 በመቶ ያህሉን እንኳን ጥቅም ላይ ሳያውል የበጀት ዓመቱ ይጠናቀቅበታል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የበጀት ዓመቱ ግማሽ ላይ ሆኖ በጀት ጨረስኩ ይልና ተጨማሪ በጀት ሊጠቀም ይዘጋጃል፤ ሳያስፈቅድ ከአንዱ የበጀት ርዕስ ወስዶ ለሌላኛው የበጀት ርዕስ ተጠቅሞ የሚገኘውም እጅጉን የበዛ ነው፡፡

በዚህ መልኩ ሥራን እና ኃላፊነትን ማዕከል አድርጎ የተመደበን በጀት ደግሞ አለመጠቀምም ሆነ ከተበጀተለት በላይ መጠቀም የየራሳቸው ችግሮች አሏቸው፡፡ ምክንያቱም የበጀት አጠቃቀም አንድም የተሰጠን ሥራ በልኩ ተገንዝቦ ከመከወን አለመከወን ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ምናልባት ከሃብት ብክነት እና ምዝበራ ጋር ሊያያዝ የሚችልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡

ከዚህ አኳያ መንግሥት በአንድ የበጀት ዓመት ለሚያከናውናቸው የአስተዳደር እና የጠቅላላ አገልግሎት፣ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎቶች እና የልማት ሥራዎች የሚያስፈልገውን ወጪ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መልኩ የበጀት ድልድል ለማድረግ፣ የበጀት አፈጻጸሙን ለመከታተልና ለማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓትን ለመዘርጋት ሲል፤ የፌዴራል መንግሥት የበጀት አስተዳደር መመሪያ አውጥቶ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡

ምክንያቱም እንደ ሀገር ከተያዘው በጀት አኳያ ለተቋማት (ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች) የሚደለደል በጀት ተቋማቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር በሚተላለፍላቸው የበጀት ድልድል ማስታወቂያ መሠረት የበጀት ድልድላቸውን አዘጋጅተው በሚያቀርቡት ጥያቄ ላይ፤ እንዲሁም የተቋማቱ ተልዕኮ ላይ ይመሠረታል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚቀርበው በጀትም ትክክለኝነት እና ተገቢነት ተመዝኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅቡልነትን ሲያገኝም ነው ፀድቆ ተፈጻሚ የሚሆነው።

በዚህ መልኩ የጸደቀው በጀት ታዲያ መሥሪያ ቤቶቹ በእቅዳቸው መሠረት ስለመጠቀም አለመጠቀማቸው የራሱ የሆነ የመከታተያ ሂደት ወይም የበጀት መቆጣጠሪያ መዝገብ (የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ሥርዓት) ሊኖረው የተገባ ነው፡፡ ይሄንን እንዲከታተል እና እንዲቆጣጠርም የተሰየመ የራሱ ተቆጣጣሪ አካል አለው፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ደግሞ ለዚህ ቀዳሚው ተቋም ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት የምሞክረውም የሀገራችን ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ለበጀት ዓመት ከሚመደብላቸው በጀት አኳያ ያላቸው የአጠቃቀም እና ከዚህ ጋር አብረው የሚገለጹ ጉዳዮችን ነው፡፡ ለዚህም መመሪያውን፣ የዋና ኦዲተር የሦስትና አራት ዓመታት (ከ2003 እስከ የ2014 በጀት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተወሰኑትን በመውሰድ) የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችን ናሙና በመውሰድ፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችን ምልከታ እንደ ማጣቀሻነት በመጠቀም ይሆናል፡፡

ከበጀት በላይ መጠቀም

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2003 በጀት ዓመት ሂሳብ ዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው፤ በበጀት ዓመቱ በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና ደንብ መሠረት ተቋማት የተፈቀደላቸውን በጀት ሥራ ላይ ማዋላቸውን ለማጣራት ኦዲት ተደርጓል። በዚህም መሠረት 29 መሥሪያ ቤቶች ለልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱ ሥራ ላይ አውለዋል፡፡

በዚህ መልኩ ከበጀት በላይ ወጪ የተደረገ ገንዘብ ከ288 ሚሊዮን 580 ሺህ ብር በላይ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የፋይናንስ እና ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤቶች ከሦስት ነጥብ 49 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቅም ግንባታ መሥሪያ ቤቶች ከ206 ሚሊዮን 646 ሺህ ብር በላይ፣ የልማትና ማኅበራዊ መሥሪያ ቤቶች ከሰባት ነጥብ 66 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም የንግድ እና አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ከ776 ሺህ ብር በላይ ድርሻ አላቸው፡፡

በተቋም ደረጃ ሲታይም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ገቢዎች ሚኒስቴር 67ነጥብ40 ሚሊዮን ብር ድርሻ ሲወስድ፤ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እና ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ከእነዚህ ተቋማት መካከል ናቸው፡፡

የ2006 በጀት ዓመት የበጀት አጠቃቀም ላይ የተደረገ የበጀት አጠቃቀም ኦዲት እንደሚያሳየው  ደግሞ፣ 37 መሥሪያ ቤቶች ለልዩ ልዩ ሂሳብ መደቦች ከተደለደለ በጀት በላይ የተጠቀሙ ሲሆን፤ በዚህም በድምሩ 235 ሚሊዮን 311 ሺህ 900 ብር ከተመደበ በጀት በላይ ወጪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይሄን ካደረጉ ተቋማት መካከል ደግሞ፣ ውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይገኛሉ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በ2010 በጀት ዓመት ላይ በተሠራ የበጀት አጠቃቀም ኦዲት መሠረት፣ 53 መሥሪያ ቤቶች እና አራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ 531 ሚሊዮን 366 ሺህ 928 ብር ተጠቅመው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከተገኙ ተቋማት ደግሞ አብዛኞቹ የትምህርት ተቋማት ሲሆኑ፤ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኢንስቲትዩት፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የ2012 በጀት ዓመት የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተም፣ 20 መሥሪያ ቤቶች እና 2 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ 846 ሚሊዮን 434 ሺህ 820 ብር ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ አድርገው ተገኝቷል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከልም ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በ2014 በጀት ላይ በተደረገ የበጀት አጠቃቀም ኦዲት ደግሞ፣ 35 መሥሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱ አንድ ቢሊዮን 567 ሚሊዮን 991 ሺህ 485 ብር ከተመደበላቸው በጀት በላይ ወጪ አድርገዋል። ከእነዚህ ተቋማት ውስጥም ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ክርስቲያን ታደለ ዋቢ አድርጎ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለኅትመት ባበቃው ዘገባ እንዳመለከተው፤ የፌደራል ባለበጀት ተቋማት በ2014/15 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ተጠቅመዋል።

በመረጃው እንደተመላከተው፣ ተቋማት ከዚህ ቀደም ከበጀት በላይ የተጠቀሙት ገንዘብ ቢሊዮን ብር ገብቶ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ያልተፈቀደላቸውን በመጠቀም ወደ ቢሊዮን አድገዋል፡፡ እዚህ ላይ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ ደግሞ ተቋማቱ ከበጀት በላይ የተጠቀሙት ገንዘብ መብዛትና ማነስ ሳይሆን፤ ተቋማት በሕግ የተቋቋሙ እንደ መሆናቸው ያልፀደቀን በጀት መጠቀም ነውርም፤ ወንጀልም መሆኑ ነው።

ያልተሠራበት በጀት

ቀደም ሲል እንዳነሳሁት የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና ደንብ መሠረት በጀታቸውን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋላቸውን ለማጣራት ባከናወነው ኦዲት፤ በ2003 በጀት ዓመት በ92 መሥሪያ ቤቶች ሦስት ቢሊዮን 54 ሚሊዮን 108 ሺህ 752 ብር ሥራ ላይ ያላዋሉት በጀት ተገኝቷል፡፡

በዚህ መልኩ የተመደበላቸውን በጀት ሥራ ላይ ካላዋሉት መካከል በሂሳብ ዘርፍ ተጠቃልሎ ሲገለጽ ደግሞ፤ የፋይናንስና ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤቶች ከ188 ሚሊዮን 221 ሺህ ብር በላይ፣ የንግድና አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የልማትና ማኅበራዊ መሥሪያ ቤቶች ከአንድ ቢሊዮን 18 ሚሊዮን 358 ሺህ ብር በላይ፣ እንዲሁም የአቅም ግንባታ መሥሪያ ቤቶች ከአንድ ቢሊዮን 774 ሚሊዮን 523 ሺህ ብር በላይ ድርሻ ይዘዋል፡፡

እንደ 2003ቱ በጀት ዓመት ሁሉ በ2006 በጀት ዓመት የበጀት አጠቃቀም ላይ በተከናወነ ኦዲት፣ 99 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 2 ቢሊዮን 576 ሚሊዮን 657 ሺህ 705 ብር ሥራ ላይ ያላዋሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ በተጨማሪ ሁለት መሥሪያ ቤቶች ከተፈቀደላቸው ከውስጥ ገቢ ሥራ ላይ ያልዋለ 24 ሚሊዮን 693 ሺህ 679 ብር ተገኝቷል፡፡

በጀታቸውን ሥራ ላይ ካላዋሉ ተቋማት መካከልም፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል።

በ2014 በተካሄደ የበጀት አጠቃቀም ሪፖርትም፣ 136 መሥሪያ ቤቶች በየሂሳብ ኮዶቹ ከተደለደለላቸው በጀት ከ10 በመቶ በላይ ያልተጠቀሙ ሲሆን፤ በዚህም በድምሩ 35 ቢሊዮን 75 ሚሊዮን 968 ሺህ 852 ብር ሥራ ላይ ሳያውሉት ቀርተዋል፡፡

ከእነዚህ ተቋማት መካከል ደግሞ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከ8 ቢሊዮን 958 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ከ3 ቢሊዮን 106 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከ1 ቢሊዮን 202 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከ1 ቢሊዮን 95 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ከ915 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር 599 ሚሊዮን ብር በላይ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ያቀረብኩት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በወጣው መረጃ መሠረትም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ዓመቱ ሀገሪቱ ለወጠነቻቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት እንዲውል ካፀደቀው በጀት ውስጥም 35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ አልዋለም።

የመውጫ መልዕክት

ቀደም ሲል ለናሙናነት በተጠቀሱት ሦስቱ የበጀት ዓመታት የወጡ መረጃዎች የሚያሳዩት፤ ተቋማት ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በ2003 በጀት ዓመት 29 መሥሪያ ቤቶች ከ288 ሚሊዮን 580 ሺህ ብር በላይ ከበጀት በላይ ሲጠቀሙ፤ 92 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ከ3 ነጥብ 54 ቢሊዮን ብር በላይ ሥራ ላይ ያላዋሉት በጀት ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ በ2006 በጀት ዓመት 37 መሥሪያ ቤቶች ከ235 ሚሊዮን 311 ሺህ ብር በላይ ከበጀት በላይ ሲጠቀሙ፤ 99 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ከ2 ቢሊዮን 576 ሚሊዮን ብር በላይ ሥራ ላይ አላዋሉም፡፡ እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመት 35 መሥሪያ ቤቶች 567 ሚሊዮን 991 ሺህ 485 ብር ከበጀት በላይ የተጠቀሙ ሲሆን፤ 136 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 35 ቢሊዮን 75 ሚሊዮን 968 ሺህ 852 ብር በጀታቸውን ሥራ ላይ አላዋሉትም፡፡

በዚህ መልኩ በጀት ሳይፈቀድ ወጪ ማድረግ ደግሞ በፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ የተከለከለ ከመሆኑም በላይ፤ የመንግሥት ገንዘብ ያለ አግባብ እንዲባክን፤ በጀት ለማጽደቅ ሥልጣን የተሰጠው አካል ሳይፈቅድ የመንግሥት ገንዘብ ሥራ ላይ እንዲውልም ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ተቋማት የበጀት ዝግጅታቸውን በበቂ ጥናት ማዘጋጀት እና አፈጻጸሙንም የበጀት አዋጁን ተከትለው ሊያደርጉ ይገባል፣ የሚለው ደግሞ የዋና ኦዲተርም ምክር ነው፡፡

በተመሳሳይ የተፈቀደ በጀትን አለመጠቀም የታቀዱ ሥራዎች ሳይከናወኑ እንዲቀሩ እና መሥሪያ ቤቱ ዓላማውን እንዳያሳካ ከማድረጉም በላይ፤ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በመንግሥት ተፈቅዶላቸው ሊጠቀሙበት የሚችሉትን በጀት እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የተቋማቱን የብቃት ማነስ የሚያመለክት ሲሆን፤ ተቋማቱ በጀቱን ተጠቅመው እንዲያከናውኑ እና ሀገርና ሕዝብ ከሥራው እንዲጠቀሙ የሚጠበቀው ውጤት እንዳይገኝ ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ይሄን አይነት አካሄድ ለቀጣይ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባው ስለመሆኑ መገንዘብ የተገባ ነው፡፡

ምክንያቱም ከበጀት አጠቃቀም ጋር በተገናኘ የተያዘ በጀትን ሥራ ላይ ባለማዋልም ሆነ ከተበጀተ ገንዘብ በላይ የመጠቀም አዝማሚያ ከዓመት ዓመት ያልታረመ ጉዳይ ስለመሆኑ ባለፉት አስርተ ዓመታት በተወሰዱ ናሙናዎች (ከ2003፣ 2006፣ 2010 እና 2014 በጀት ዓመት ላይ) መመልከት ይቻላል፡፡

ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል ልማት ላይ መዋል የነበረበት ሃብት ለልማት ተግባር እንዳይውል ያደርጋል፡፡ ለዚህ ዓቢይ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በየቦታው የተወጠኑ እና ከፍ ያለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መሠረተ ልማቶች በበጀት እጥረት ጊዜ እየቆጠሩ (አንዳንዶቹም ተቋርጠው) ያሉበትን ሐቅ መመልከቱ ነው፡፡ በመሆኑም ለብድርና ርዳታ ደጅ ተጠንቶ ጭምር ከተገኘ ሃብት ላይ በጀት ተመድቦላቸው ሳይጠቀሙበት የሚያሳድሩ እና ለልማት መዋል ሲገባው እንዳይውል ምክንያት የሚሆኑ ተቋማት ይሄ ተግባራቸው ከ2016 በጀት ዓመት እንዳይደገም ከወዲሁ ራሳቸውን ማረም ይኖርባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ታስቦ የተመደበ ሃብት ለግለሰቦችና ቡድኖች መበልጸጊያ ሆኖ ብዙኃኑ የበዪ ተመልካች እንዲሆን እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያውም ከእለት እለት መልኩን እየቀያየረ የመጣው የሙስናና ሌብነት ጉዳይ ሲሆን፤ በተለይ ይሄን አይነት አካሄድ ሹማምንትና ተባባሪዎቻቸው ሊበላበት የማያስችልን የበጀት ርዕስ ገንዘብ ሊበላበት ወደሚያስችል የበጀት ርዕስ በማ ዛወር ሊጠቀሙበት የሚችሉበትን እድል የሚያሰፋላቸው ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑ ይሄን ሊታረም፣ መሰል አካሄድም በ2016 በጀት ዓመት እንዳይገለጥ በትኩረት ሊሠራበትና ከተከሰተም ተገቢው እርምት ሊወሰድ የሚገባው ዐቢይ ሥራ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከተቋም በፊት ሀገር፤ ከሹመኛ በላይ ሕዝብ በእጅጉ ዋጋ አላቸው፡፡

ከድሃው ሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ፤ የሃገር አንጡራ ሃብት ተይዞ በብድርና ርዳታ የሚገኝ ምንዛሪ ለአገርና ሕዝብ በሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ላይ ሊውል እንጂ፤ ለተቋማት መፈንጫ፣ ለሹማምንትና ተባባሪዎቻቸው ጮማና ውስኪ መራጫ እንዳይሆን፤ ለግለሰቦች መንደላቀቂያም እንዳይውል ተገቢው ክትትል፣ እርምትና ርምጃ መውሰድም ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ የሞራልም፣ የሕግም ግዴታ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት ይገባል፡፡

ማሙሻ ከአቡርሻ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

 አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *