“ፉንጋዎችን” ለመወከል ቲያትር የተማረው ጥበበኛ

“ችሎታ አለኝ የምትሉ አንድ አምስት ልጆች ከመጣቹህ ይበቃል፤ እኛ ጦር አይደለም የምናሰለጥነው። ደህና ደህና አንድ አምስት ልጆች ካሉ ይበቃል።” ይህ ንግግር የዛሬውን እንግዳችንና እውቅ ተዋናይ ወደ ጥበቡ ዓለም የጠራች ታሪካዊ ንግግር ናት።

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ (ስድስት ኪሎ) አዳራሽ በተማሪዎች ተሞልቷል። ከተማሪዎች በተጨማሪ ከየትምህርት ክፍሉ የተመረጡ መምህራን ስለትምህርት ክፍላቸው ማብራሪያ ሊሰጡ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል።

አብዛኛው ተማሪ ለይስሙላ ሊያዳምጥ ይዘጋጅ እንጂ በቤተሰብ ጫና፣ የተሻለ ገቢ ያስገኛል በሚል፤ እንዲሁም፣ በሚለብሱት ልብስና በአኳኋናቸው የማረኳቸውን ባለሙያዎች የትምህርት ዘርፍ ለመቀላቀል ወስነዋል። የተወሰኑት ተማሪዎች ግን ልክ እንደ ህጻናት ነጭ ወረቀት ሆነው ከሚሰሙት ዲስኩር ተነስተው የሙያ መስካቸውን ሊመርጡ በአዳራሽ ተገኝተዋል። የዛሬው ባለታሪክ ምን እንደሚማር አልወሰነም። የየትምህርት ክፍሉ ተወካዮች የራሳቸውን የትምህርት ክፍል ጎላ አድርገው ሲናገሩ ልቡ እየዋለለ ነበር የሚያዳምጠው።

አንድ ቀይ መልከመልካም ሰው ወደ መድረኩ ወጡ፤ ስለትምህርት ክፍላቸው ብዙ ይላሉ ብሎ ሲጠብቅ “ችሎታ አለኝ የምትሉ አንድ አምስት ልጆች ከመጣቹህ ይበቃል። እኛ ጦር አይደለም የምናሰለጥነው፤ ደህና ደህና አንድ አምስት ልጅ ካለ ይበቃል።” ብለው ከመድረክ ወረዱ። መልከመልካሙ ሰው የትያትር ክፍል መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ነበሩ። በዛን ወቅት ልክ እንደ አሁኑ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች በጋራ “ኮመን ኮርሶች”ን ይወስዱ ነበር። ሁለተኛ ዓመት ላይ የሚፈልጉትን የትምህርት ዓይነት ይመርጣሉ። ለዚህም ስለትምህርት አይነቶቹ ገለጻ ይደረጋል።

የትያትር ክፍለ-ትምህርት ተወካዩ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ገለጻቸውን እንደጨረሱ የትያትር ትምህርት ክፍልን ለመቀላቀል ወሰነ። መምህሩ ከመድረክ ሲወርዱ ጠብቆ የምስራች ይሆናል ብሎ የጠበቀውን የትያትር ትምህርት ክፍልን ለመቀላቀል መወሰኑን ነገራቸው። ከአስተማሪው ያገኘው መልስ ግን ያልጠበቀው ነበር፤ አይ አንተ አትሆንም የሚል አጭር መልስ ነበር። “ለምን?” የሚል ጥያቄ ሰነዘረ፤ “መልክህ አይሆንም ፉንጋ ቢጤ ነህ” የሚል መልስ ተሰጠው። “ታዲያ ምን ችግር አለ፤ እናንተ መልከ መልካሙን ሥሩ እኔ ፉንጋውን እሰራለሁ” ብሎ በአቋሙ ጸና።

የዛሬው የዝነኞች ገጽ ባለታሪክ ወላጆቹ ያወጡለት መጠሪያ ሚካኤል ታምሬ ይሰኛል። እንደ ጂጂ ዘፈን “ስመ ብዙ” ነው። በየጊዜው የሚጫወታቸውን ገጸ-ባህሪያት መስሎ ሳይሆን ሆኖ ስለሚሰራቸው የገጸ-ባህሪያቱ ሥም መጠሪያው ከመሆኑ ባሻገር የቅርቦቹ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለ በወጣለት ቅጽል “ቶኪዮ” እያሉ ይጠሩታል። በማቆላመጥ ”ሚኪ” የሚሉትም የትየለሌ ናቸው። በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ክፍልን ከመቀላቀሉ በፊት በነበረ ሕይወቱ “ጥበብ ጠራችኝ” ብሎ ጥሪውን ለማሳደግ አልጣረም። ጭራሽም መጠራቱን አያውቅም ነበር። ግን ከአባቱ ትያትር መውደድ ጋር ተያይዞ ከሰባት ዓመቱ አንስቶ ትያትር የማየት እድል ነበረው።

ያኔ ታዲያ ቅዳሜ ያየውን ትያትር በትምህርት ቤት መምህር የማይገባበት ክፍለ ጊዜ በኖረ ቁጥር ለክፍል ጓደኞቹ እያሳየ ቆይቷል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት በመከታተሉ እኩዮቹ በቀበሌ ኪነት በመሳተፍ ከትወና ጋር በፍቅር ሲወድቁ እሱ ርቆ ቆይቷል። እንደ አንድ ጥሩ የሀበሻ ልጅ ቤተሰቦቹን ለማስደሰት በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ደፋ ቀና ሲል ቆይቷል።

የፕሮፌሰር ተስፋዬን ጥሪ ተከትሎ ትያትር ለመቀላቀል የወሰነው ተዋናይ ሚካኤል “ሰኞ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ደስ ብሎኝ ለመማር ወደ ክፍል ስሄድ ትክክለኛ ውሳኔ መወሰኔን አረጋገጥኩ” ይላል። ለዚህም ከዚህ ቀደም ሰኞ ሰኞ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ይደብረው እንደነበር ያስታውሳል። በዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ክፍልን ከመቀላቀሉ በፊት የትወና ልምድ አልነበረውምና ለትንሽ ጊዜ ሁሉ አዲስ ሆኖበት ተቸግሮ ነበር።

ግን ለጥበብ የተፈጠረ ነውና በአጭር ጊዜ የትወና ዓለምን በልኩ ተዋወቃት። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሀምሳኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የተሰራውና ሚኪም የተሳተፈበት “በርባን” ቲያትርን የተመለከቱ ሰዎች ሀሪፍ ስለሆነ በቴሌቪዥን ቢቀርብ አሉ። ከጥበብ ጋር እንዲተዋወቅ እጁን ይዘው መንገድ የጠረጉትና የትያትር ትምህርት ክፍልን ሊቀላቀል መሆኑን ሲነግራቸው ምርጫውን ያከበሩለት፣ ዘመናዊ ናቸው የሚላቸው ወላጅ አባቱ አቶ ታምሬም ትያትሩን ካዩ መምህራን ጓደኞቻቸው ምስክርነት ተጨማሪ ትያትሩ ለፋሲካ በዓል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ የመመልከት እድል አገኙ።

አሁን እንዲህ በየቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለያዩ ገጸባህሪያት ሊናኝበት ያኔ በርባን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፋል የተባለ ቀን ከአባቱ ጋር ከጠዋት የጀመረ እስከማታ በጉጉት ጠብቀውታል። አባቱ ከሱ በላይ ጓጉተው ለሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ የልጃቸውን ሥራ እንዲመለከቱ ስልክ እየደወሉ ሲያሳስቡ ውለዋል። የያኔው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የአሁኑ እውቅ ተዋናይና ፕሮዲውሰር ሚካኤል ከሀምሳ በላይ ፊልሞችና አራት የመድረክ ቲትያትሮችን በብቃት ተውኗል። ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን መስኮት በተላለፉት “የእግር እሳት”፣ “ዳና” እና በ“ቅዳሜ ’ና’ እሁድ” በተሰኙ ተከታታይ ድራማዎች ላይ በብቃት ተውኗል።

በአሁኑ ሰዓት “ምን ልታዘዝ”፣ “ግራ ቀኝ” እና “በሕግ አምላክ” የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ላይ በብቃት እየተወነ ይገኛል። ሚዜዎቹ፣ ሂሮሺማ፣ ሀ እና ለ፣ የአርበኛው ልጅ፣ ነቄ ትውልድ፣ እሷና እሱ፣ መለኛው፣ ስንገናኝ፣ ወደ ራስ፣ ጥቁር እንግዳ፣ እናፋታለን፣ ሕጋዊ ጋብቻ፣ እኔና ቤቴ በብቃት ከተወነባቸው ፊልሞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። የሚስት ያለህ፣ ጓደኛሞቹ፣ መንታ መንገድና ከትዳር በላይ ሚኪ የተወነባቸው ተወዳጅ ትያትሮች ናቸው። ከፊልም አንጻር፣ ምንም እንኳን በትያትር የሚገኘው ብር ቢያንስም፤ በቁጥር ደረጃ የሰራው ፊልምና ትያትር ባይወዳደርም፣ በስሜት ግን የበለጠ ለትያትር ያደላል።

ትያትር ከስክሪፕት መናበብ፣ ከልምምድ ጀምሮ ያለው ሂደት ያስደስተኛል ይላል። ለበርካታ ጊዜ የሠራው ትያትር ቢሆንም ሁሌ ተራው ደርሶ መድረክ ላይ እስኪወጣ እንደ አዲስ ይጨነቃል። ትያትሩ ሲያልቅ ከተመልካች የሚሰጠው ምላሽም የተለየ ስሜት ይፈጥርበታል። ብሔራዊ ትያትር መድረክ ላይ እየሰራ ለስንት ነገር የታሰበችው አርቴፊሻል ሽጉጥ ላይ በመቀመጡ ተሰብሮ የተሰማው ድንጋጤን አይረሳውም። ግን እሱ ሚኪ ነውና በሽጉጥ መማረኩ ባይሆንለት በድምጽ ማርኳል።

ግልጽ ነው፣ ያልተፈተነውን መከራ ተፈተንኩ፤ ለጥበብ ስል ተሰቃየሁ ብሎ መታበይ እሱ ጋር ቦታ የለውም። በቃ ዩኒቨርሲቲ ተማረ፤ አብሮት የነበረና ብቃቱን የሚያቀው አብረሀም ገዛሀኝ “ሚዜዎቹ”ን ሲያዘጋጅ በፊልሙ አሳተፈው። ሚዜዎቹ ላይ ያየውና በትወናው የተማረከው ሰራዊት ፍቅሬ “ሂሮሺማ”ን ሲያዘጋጅ በስም ባያውቀውም ሚዜዎቹ ላይ የተወነውን፣ አይኑ ጎላ ጎላ ሰውነቱ ገዘፍ ያለውን ልጅ አምጡልኝ ብሎ አሰራው። ያኔ ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ባየው የቴዎድሮስ ትያትር ላይ ገብርዬን ሆኖ ከተወነው አበበ ባልቻ ጋር አብሮ የመስራት እድል አገኘ። እያለ ቀጥሎ ያለመዋዠቅ በትወና ዓለም ውስጥ ሥሙን ተክሏል።

የሚያውቁት አብረው የሰሩት የተሰጠውን ገጸባህሪ ለማወቅ የሚሄድበት ርቀት ይገርማቸዋል። እሱ በበኩሉ ለተሳካ ትወና የተሰጠውን ገጸ ባህሪ ገና ከጅምሩ ስለማንነቱና አስተሳሰቡ በፊልሙ ላይ ገጸባህሪው የወሰናቸውን ውሳኔዎች፣ የወሰነበትን ምክንያት ከዳይሬክተሩ ጋር በደንብ ያወራል። ሚኪ ሲሰራ ሰራ ለመባል አይደለምና የሚጫወተውን ገጸባህሪ ለመምሰል ሳይሆን ለመሆን እስከመጨረሻው ይተጋል። “ትወና ስሰራ ለኔ ወሳኙ ነገር የምጫወተውን ገጸባህሪ ማወቅ አለብኝ” የሚለው ተዋናዩ፤ የሚወክለውን ገጸ-ባሕሪ ለማወቅ ብዙ ርቀት ይጓዛል።

በዚህ ጉዞውም ገጸ-ባሕሪውን ከማንም በላይ አብጠርጥሮ ያውቃል። በዚህም ስክሪፕቱ ላይ ከተሰጠው በተጨማሪ ድምቀት የሚሆኑ ሀሳቦችን ይጨምራል። በዛው ልክ ገጸ-ባህሪው “ይህን አያደርግም” ብሎ የሚያምናቸውን ነገሮች ከስክሪፕቱ ውስጥ እንዲወጡ አዘጋጁን ያሳምናል። ገጸ-ባህሪውን በደንብ የተረዳ ተዋናይ ለገጸ-ባህሪው ታማኝ ሲሆን የተሳካ ትወና እንደሚወለድ ያምናል።

አብረውት የሰሩት ሁሉ ስለእሱ ያላቸው አተያይ ተመሳሳይ ነው። በአድናቆት በፊልም ቀረጻ ላይ የእሱ ዲሲፕሊን ይለያል፤ ገጸ-ባህሪውን በደንብ አጥንቶ ይገኛል። ሰዓት ማክበር መለያው ነው ይላሉ። እሱ ግን ይሄ ሙያውን የመውደዱ ማረጋገጫ አድርጎ ነው የሚያስበው። እሱ ቢያረፍድ አጠቃላይ የቀረጻ ቡድኑ ላይ መስተጓጎል ይፈጠራል ብሎ ስለሚያስብ ሰዓት አክብሮ ይገኛል።

የቀረጻ ቦታ ላይ የቀጠረው ሰው ሳይመጣ ብዙ ጊዜ እሱ ቀድሞ ይደርሳል። በተደጋጋሚ ቀድሞ እየተገኘ ሌሎችን በመጠበቅ ረዥም ጊዜ ሲያባክን ያስተዋሉ አዘጋጆችና የፕሮዳክሽን ባለሙያዎች እንደ አማራጭ እነሱም ሆኑ ሌሎች ተዋናይና ባለሙያዎች ተንጠባጥበው ይገኙበታል ብለው በሚያስቡበት ሰዓት ሲቀጥሩት፤ የተቀሩትን ቀደም ብሎ መቅጠር ይሻላል ብለው ስላሰቡ ይሄንኑ መተግበር ጀምረዋል።

ተውኜ ብር ሲከፈለኝ በጣም ግርም ይለኛል የሚለው ተዋናይ ሚካኤል፤ በጣም ደስተኛ የሚያደርገውን ሥራ እንደሚሰራና የፊልምም ሆነ የትያትር ስክሪፕት ቤቱ ሆኖ ሲለማመድ እራሱ ደስተኛ እንደሚሆንና ይሄ ደስታው ቤተሰቡ ድረስ እንደሚዘልቅ ይናገራል። ከፊልም ሂሮሺማ ላይ የተጫወተው የሻንበል ሸዋንግዛው ገጸ-ባህሪን በጣም ተረድቼውና ገብቶኝ የተጫወትኩት ገጸ-ባህሪ ነው ይላል። ሻምበል ሸዋንግዛው ለሀገሩ ብዙ የዋለ ግን ይሄ ውለታው ከምንም ሳይቆጠር የተበተነ የቀድሞ ወታደርና ኑሮውን ለመግፋት ምጣድ የሚጠግን ገጻ-ባህሪ ነው። ብዙ የዋለላት ሀገሩ ምንም ባትጠቅመውም ሀገር ተጎዳች ሲባል ለሀገሩ ቀድሞ የሚደርስ ሰው ነው።

በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውና የመጀመሪያ ፊልሙ አዘጋጅ በነበረው አብረሀም ገዛሀኝ በተዘጋጀው “የእግር እሳት” የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የተጫወተው የእስክንድር ገጸባህሪ እራሱን ፈትኖበታል። እስክንድር ከተለመደው ወጣ ያለ ገጸ-ባሪ ሲሆን መደሰቱም ሆነ መናደዱ መከፋቱ ፊቱ ላይ የማይታይ ነው። ፊቱ ላይ ስሜቱ እንዳይታይ አድርጎ መተወን ከባድ ቢሆንም ተዋናዩ ሚኪ ነውና ከጭካኔው እስከ አሟሟቱ ግሩም አድርጎ ተውኖት በሁሉም ልብ እንዲቀር አርጎታል።

አንድ ዳይሬክተር አምኖት ከዚህ በፊት ያልተጫወተውን ገጸ-ባህሪ እንዲጫወት እድል ሲሰጠው፤ ዳይሬክተሩ እንዳልተሳሳተና ምርጫው ልክ እንደነበር ለማረጋገጥ የማይወጣው ተራራ የማይቧጥጠው ገደል የለም። ከዚህ ቀደም የሰራውን ተመሳሳይ ገጸ-ባህሪ ከሚጫወት አዲስና ፈታኝ ገጸ-ባህሪ መጫወት ምርጫው ነው። ተተኪን ለማፍራት እውቀቱን የማይደብቀው ሚኪ በባላገሩ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው “ወጊሾ” የትወና ውድድር ላይ በዳኝነት በመሳተፍ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችን ያስደነቁትን አድንቆ የጎደላቸውን እንዲሞሉ የሚያደርግ ሀሳቡን አካፍሏል።

ትወና በሂደትና በልምድ እንደሚዳብር ያምናል። ለዚህም አብነት አድርጎ እራሱን ያነሳል። የመጀመሪያ ፊልሙ “ሚዜዎቹ” ላይ ሲተውን ዳይሬክተሩንና ፊልሙ አካባቢ ያሉ ባለሙያዎችን እንዲሁም ተመልካቾችን ማስደነቅና እንዴት ሀሪፍ ተዋናይ እንደሆንኩ ማሳየት እፈልግ ነበር። በዚህ የተነሳ ገጸባህሪውን ተረድቶ መተወን ላይ ያን ያህል ጥልቀት አልነበረኝም ይላል። ልምድ እየዳበረ ሲሄድ ገጸ ባህሪውን ለመረዳት ምን ማድረግ እንዳለበት፤ ምን አይነት ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዳለበት መረዳቱን ይናገራል።

ያም ቢሆን ለትወና ሁሌ አዲስ ነው። በተለይ ትያትር ላይ ከሁለት ዓመት በላይ ለሰራውም ትያትር ገብቶ እስኪተውን መጨነቅ፣ መጠበቡ አብሮት ነው። ግን ልክ የሱ ተራ ደርሶ መድረክ ላይ ሲወጣ ሚኪነቱ ቀርቶ ገጸ-ባህሪውን ስለሚላበስ የምን ፍርሀት። ተዋናይ ሰው አወቀኝ ብሎ መኮፈስ ከጀመረና ለገጸባህሪው መጨነቅ ካቆመ ያኔ የቁልቁለት ጉዞው ይጀምራል ብሎ ያስባል። ከሚወደውና ከጠፋበት የትያትር መድረክ ተመልሶ የምናይበት ቀን እንዲቀርብና ከጀመረው የከፍታ ጉዞ ላይ እንዲቀጥል ተመኘን።

 ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 30/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *