የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
መንግስት የህዝብን ሰላም፣ የሀገር ደህንነትን፣ እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ፤
ይህ እንቅስቃሴ የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፤
የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም ህግ እና ስርዓት ለማስከበር የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል::
ክፍል አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌ
1. አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የሕዝብን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6 /2015″ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል::
2.ትርጓሜ
ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም ሲባል፦
1) የሕግ አስከባሪ አካል ማለት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ የሚያሰማራቸው ሌሎች የፀጥታ አካላት ማለት ነው፤
2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ማለት ይህን አዋጅ ለማስፈፀም በዚህ አዋጅ አንቀፅ 5 መሰረት የተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አደረጃጀት ማለት ነው፤
3) ህግ ማለት የፌዴራል ሕገ- መንግስት፣ እንደ አግባብነቱ በፌዴራል ወይም በክልል መንግስታት ህግ አውጪ ወይም ስልጣን ባለው ህግ አስፈፃሚ አካል የወጣ የክልል ሕገመንግስት፣ አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ ማለት ነው፤
4) ሰው ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ማለት ነው፡፡
5) በዚህ አዋጅ በወንድ አነጋገር የተገለጸው ሴ ትንም ይጨምራል፡፡
3 የተፈፃሚነት ወሰን
ይህ አዋጅ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር እንዲሁም በክልሉ አስተዳደር የሕዝብን ሠላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚወሰድ እርምጃን፣ በክልሉ ወይም በሃገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ችግር የሚያባብስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ወይም ሁኔታን በሚመለከት እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡
ክፍል ሁለት
ስለ አስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ
4 የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መም ሪያ እዝ መቋቋም እና ኃላፊነት
1 ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መም ሪያ ዕዝ ተቋቁሟል ።
2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ አባላት፣ መዋቅር እና አደረጃጀት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወሰን ይሆናል።
3) የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ጠቅላይ ዕዙ ተጠሪ ነት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ ኒስትር ይሆናል።
4) አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ፤
ሀ) አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት ወስደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈፃሚ የሚያደርጉ ግብረ ኃይሎችን ወይም ኮሚቴዎችን ሊያቋቁም ይችላል፤
ለ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 የተመለከቱ እርምጃዎችን በተመለከተ አስፈላጊውን ውሳኔ ያስተላልፋል፣ ያስፈጽማል፣
ሐ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ 6 የተመለከቱ የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎችን ያስከብራል፣
መ) በአማራ ብሄራዊ ከልላዊ መንግስት የሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላትን በአንድ ዕዝ ሥር አድርጎ በበላይነት ያስተባብራል፣ ይመራል፣
ሠ) ኃላፊነቱን ለመወጣት ሌሎች አስፈላጊ እና አግባብ የሆኑ ስልጣኖች ይኖሩታል።
ክፍል ሶስት
በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተከለከሉ ተግባራት
5. አስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መም ሪያ ዕዙ የዚህን አዋጅ ዓላ ማ ለማሳካት አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያም ን፦
1) የአደባባይ ስብሰባና ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን የመከልከል፣
2) የሰዓት እላፊ የማወጅ፤ ለተወሰነ ጊዜ አንድ መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም መጓጓዣ ዘዴ እንዲዘጋ እና እንዲቋረጥ ማዘዝ፣
3) ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ለማዘዝ፣
4) የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስን ለመከልከል፣
5) በሀገረ መንግስቱ እና በህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣስ እና አፈፃፀሙን የማደናቀፍ ወንጀልን መፈጸሙ፣ መሞከሩ ወይም ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ማናቸውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር በማድረግ ለማቆየት፣
6) ወንጀል እንደተፈፀመባቸው ወይም ሊፈፀምባቸው እንደሚችል የተጠረጠሩ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በየትኛውም ጊዜ ማናቸውንም ስፍራ እና መጓጓዣ ለመበርበር፣
7) መንግስታዊ እና ህዝባዊ ተቋማትና የመሰረተ ልማቶች ጥበቃ ሁኔታን ለመወሰን፣
8) ማናቸውም ከዚህ አዋጅ ዓላማ በተፃረረ መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የተጠረጠሩ የመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ሌሎች አካላት እንዲዘጉ፣ እንዲቋረጡ፣ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ወይም እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ ለማዘዝ፣
9) ማንኛውም አገልግሎት መስጫ ተቋም እንዳይዘጋ እና ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማዘዝ፣
10) ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪዎች እና ማጓጓዣ እቃዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማዘዝ፣
11) የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅሮችን መልሶ ማቋቋም፣ ማደራጀት ወይም የአስተዳደር እና የፀጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች እርምጃዎችን የመውሰድ፣
12) የህዝብን ሰላም፣ የሃገር ደህንነትን አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን የመውሰድ፣ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ትእዛዝ የመስጠት ስልጣን አለው፤
6, የተከለከሉ ተግባራት እና ግዴታዎች
1) ማንኛውም ሰው ይህንን አዋጅ፣ በአዋጁ መሰረት የሚወጡ መመሪያዎችን፣ የሚሰጡ ትዕዛዞች እና የሚተላለፉ ውሳኔዎችን የመተግበር እና የማክበር ግዴታ አለበት።
2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና በክልሉ የአመጽ እንቅስቃሴን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር፤እንዲሁም የጸጥታ መደፍረሱን የሚያባብስ ንግግር፣ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ቅስቀሳ በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨት የተከለከለ ነው።
3) በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የቁሳቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው።
4) ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው ።
5) ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ፈቃድ ውጪ ማናቸውንም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
6) ማንኛውንም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የስራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከከለ ነው።
7) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
7. ተመጣጣኝ ኃይል ስለመጠቀም እና የማይታገዱ መብቶች
1) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መም ሪያ ዕዝ በዚህ አዋጅ የተመለ ከቱ የአስቸኳይ ጊዜ እርም ጃዎችን ለማስፈፀም
አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሕግ አስከባሪ አካላት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲጠቀሙ መመሪያ ለመስጠት ይችላል።
2) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎችም፣ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 93 (4) (ሐ) መሰረት ሊታገዱ የማይችሉ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን እና መብቶችን፣ እንዲሁም የተመጣጣኝነትን እና የአስፈላጊነት መርሆዎችን ማክበር ይኖርበታል።
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
8. ተፈፃሚነታቸው የታገዱ ሕጎች
1) በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚህ አዋጅ ንዑስ አንቀጽ 9 ከተገለፀው አግባብ ውጪ የትኛውም የዳኝነት አካል ስልጣን አይኖረውም፡፡
2) በቪዬና ኮንቬንሽን፣ በሌሎች የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ደንቦች እውቅና የተሰጣቸው የዲፕሎማቲክ መብቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጎች ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ ተፈፃሚነታቸው ታግዶ ይቆያል::
9. የወንጀል ተጠያቂነት
1) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እንደ ጥፋቱ ክብደት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።
2) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የተፈፀመው ወንጀል በሌሎች ሕጎች ከዚህ ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ የከበደው ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል።
3) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተፈፀሙ የአዋጁ እና በአዋጁ ማዕቀፍ የሚወጡ ደንብ እና መመሪያ ጥሰቶች የሚያስከትሉት የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ የአዋጁ ተፈጻሚነት ጊዜ ቢያበቃም በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 9(2) መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብ ይችላል።
4) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በአዋጁ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ የሚመጣ የወንጀል ተጠያቂነትን አስመልክቶ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ መደበኛ የወንጀል ስነ ሥርዓት ድንጋጌዎችም ተፈፃሚነት አይኖራቸውም።
5) የፀጥታ ሁኔታው የመደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማያስችልበት ሁኔታ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች ከዚህ አዋጅ ጥሰት ጋር ተያያዥ የሆኑ የወንጀል ጉዳዮችን አስመልክቶ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች እና የፍትህ አካላት መደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ አካላትን ተክተው እንዲሰሩ የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መም ሪያ ዕዝ ሊወስ ን ይችላል።
10. ደንብ እና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
1)የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሃገርን ሰላምና ህልውና፣ የህዝብን ደህንነት፣ ህግ እና ሥርዓትን ለማስከበር በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 (4) (ሀ) መሰረት ደንብ የማውጣት ስልጣን ይኖረዋል።
2) የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ በአዋጁ ወይም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት በሚወጡ ደንቦች የተሰጠውን ስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ እና ኃላፊነቱን ለመወጣት አስፈላጊ መመሪያዎችን ያወጣል።
3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሚወጡ መመሪያዎች ተፈፃሚ ከመደረጋቸው በፊት ለህዝብ በስፋት ተደራሽ በሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ እንዲተዋወቁ መደረግ ይኖርበታል።
11. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
1) ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የፀና ይሆናል።
2) የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል።
አዲስ አበባ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ/ም
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2015