ተፈጥሮን በተፈጥሮ ለማከም አስፈላጊውን ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል

ተፈጥሮ አንድ ትርጉም ያለው አይደለም። ብዙ ቋንቋና ትርጉም የሚሰጠው ነው። በዚህም ምክንያት አንዱን ነክተን አንዱን አለመንካት አይታሰብም። ክፍልፋይ ክፍሉን ካልተመለከትነው በስተቀር ለመተንተንም ይቸግረናል። ስለምንነቱ ለማውራትም ይከብደናል። ምክንያቱም እርሱ ውበት ነው፤ ሕይወት ነው። እርሱ ፈውስ ነው፤ አዲስ ነገር መፍጠሪያም ነው። በቃ ብዙ ነገር ነው።

ተፈጥሮ የአመጋገብ ሥርዓትን ይወስናል፤ የአኗኗርንም ሁኔታ እንዲሁ። ለአብነት ለዛሬ አንድ ጉዳይን ብቻ አንስተን እንመልከት። ይህም የማዳበሪያ ጉዳይ ነው። ትንናንት አርሶአደሩ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ሲጠቀም ምን ምን መልካም አጋጣሚዎች እንደነበሩት ማንም የሚያውቀው ነው። ዛሬስ ሲባል መልሱ በተለየ መልክ አለው፤ ስቃይ ነው።

አርሶአደሩ ትናንት ለተፈጥሮ ማዳበሪያ መሥሪያ ምንም የሚያወጣው ነገር አልነበረውም። ይልቁንም አትራፊ ሆኖ ሌሎች የግብርና ሥራዎችን ጭምር እንዲሠራበት ዕድል ተፈጥሮለታል። ለአብነት ከብት እያረባ እበቱን ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ይጠቀመዋል።

የጓሮ አትክልቶችን በግቢው እየተከለ ብስባሹን የሚጥልበት አጋጣሚ የለም። በብዙ መልኩ አቅጣጫዎችን እየቀያየረ በባለሙያ እየተረዳ ተፈጥሮን በተፈጥሮ እያከመ ምርቱን በብዛትም በጥራት አምርቶ ለገበያ ያቀርባል። ሸማቹም ቢሆን ደስተኛ ሆኖ በጥሩ ዋጋ እየገዛ ይመገባል። ጣዕሙ ጭምር ምን እንደነበር ማስታወስ ለብዙዎች ከባድ አይደለም።

ዛሬስ ከተባለ ነገሩ ተቃራኒ ሆኗል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምን ይሠራል የሚል እሳቤን አርሶአደሩ በመያዙና የአፈር ማዳበሪያውን ማለትም የኬሚካል ማዳበሪያውን ከመሬቱ ጋር አጋብቶ ከዚያ ውጪ እንዳያስብ ሆኗል። በእርግጥ ይህንን ማዳበሪያ መጠቀሙ ጥፋት አልነበረውም። ጥሩ ምርትም እየተገኘበት እንደቆየ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሆኖም የአጠቃቀሙ ጉዳይ ብዙ ችግሮችን እንደፈጠረ በማሳያ ማንሳት ይቻላል። የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ዓለሙ መብራቱ እንደሚሉት፤ አርሶ አደሩ ምርቱን ለማሳደግ ማዳበሪያ ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀሙ ከዓለም አቀፉ የማዳበሪያ አጠቃቀም ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አለው። ለምሳሌ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በአንድ ሄክታር 10 ኪሎ ግራም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን ያለው የአጠቃቀም ምጣኔ ለአንድ ሄክታር 12 ኪሎ ግራም ነው። ይህ ደግሞ በአፈሩ ለምነት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም አርሶአደሩን እየፈተነው ያለው። የአፈር ማዳበሪያን በዚህ መጠን ልዩነትም መጠቀም እንዳይችል የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መሬታቸው ማዳበሪያውን አዘውትሮ መጠቀም የለመደ በመሆኑ በተከሰተው የዋጋ ንረት ምክንያት የመንግሥትን በር ከማንኳኳት አልፈው አደባባይ እስከ መውጣት አድርሷቸዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንዳሉት፤ ከፍተኛውን የአፈር ማዳበሪያ የምታቀርበው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባቷ የዓለም የአፈር ማዳበሪያ መሸጫ ዋጋን እንዲያሻቅብ አድርጎታል። በዚህም እንደ ሀገር ያለው የመግዛት አቅም በፍላጎት ልክ ሊሆን አልቻለም።

ፍላጎት 20 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ሲሆን፤ አሁን መቅረብ የቻለው የአደረውን ጨምሮ 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው። ከዚህ የተነሳም ለአርሶአደሩ የሚመከረው የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች እንዲጠቀም ነው። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። በዚህም 153 ሚሊዮን ሜትር

 ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ተችሏል።

ከዚሁ ከማዳበሪያ አጠቃቀም ጉዳይ ጋር በተያያዘ አንድ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ እንዳለ ይነገራል። ይህም የኬሚካል የአፈር ማዳበሪያን አዘውትሮ መጠቀም ለአፈር አሲዳማነት መንስኤ መሆኑ ነው። በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁም በአፈር ላይ ሰፊ ምርምር ያደረጉ ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ለአፈር አሲዳማነት መፈጠር ምክንያቱ ልዩ ልዩ ቢሆንም አንዱ ግን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት አርሶአደሮች አብዛኛው በሚባል ደረጃ ከተፈጥሮ ማዳበሪያ ይልቅ የኬሚካል ማዳበሪያው ላይ ጥገኛ ሆነዋል። ይህ ደግሞ የአፈር አሲዳማነት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ አሁን ላይ እንደሀገር ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት ተሸፍኗል። 3ነጥብ2 ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ «ጠንካራ» በሚባል ደረጃ የተጎዳ ነው።

ይህም አጠቃላይ ከሚታረሰው መሬት 3ነጥብ7 ሚሊዮን ሄክታር ማምረት ወደማይችልበት ደረጃ አድርሶታል። ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ይህን መሬት (አሲዳማ መሬት) ማከም ካልተቻለ እንደሀገር ስጋቱ ሙሉ መሬቱን ሊሸፍን የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

በማስረጃነት በ1989 ዓ.ም በሀገሪቱ ጠንካራ በሆነ አሲዳማነት የተጠቃው መሬት 13 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን፤ በ2014 ይህ አሀዝ ወደ 28ነጥብ1 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ማለት አሲዳማነቱ በ25 ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል። ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ መሬቱን አክሞ ለመጠቀም እጅግ አዳጋች ይሆናል። የችግሩን አሳሳቢነት በጊዜ በመረዳት ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የአፈርን ጤናማነት ማከም ካልተቻለ በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል እያደረግነው ያለው ጥረት ስኬታማ ሆኖ ማየት የሚታሰብ አይሆንም።

ክብረ መንግስት

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 30/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *