በፈርኒቸር ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርቶ የተለያዩ የቤትና የቢሮ ቁሳቁሶችን ማምረትና በዘርፉ ስልጠና መስጠት ከጀመረ 12 ዓመታት አስቆጥሯል። ፈርኒቸሮች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ መመልከት የሁልጊዜ ቁጭቱ ነው። ይህን ቁጭት በሥራ ለማሸነፍ ከላይ ታች እያለ ይገኛል። ይሁንና ጉዳዩ ‹‹አንድ ሰው አስቦ በአንድ በሬ ስቦ›› አይሆንም እንዲሉ አበው፣ መንግሥትን ጨምሮ የበርካቶችን ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ባሰበውና በሚፈልገው ልክ ዘርፉን ማሳደግና ማሻሻል አልቻለም። ያም ቢሆን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በዘርፉ የድርሻውን ለማበርከት እየታተረ ይገኛል።
ከውጭ የሚገባውን ፈርኒቸር በሀገር ውስጥ ለማስቀረት በብርቱ እየተጋ ያለው የባምላክ እና የሳልማ ፈርኒቸር መስራችና ባለቤት አቶ አምላክቸር ሥዩም የፈርኒቸር ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው በስደት ከኖረበት እንግሊዝ ነው። ስደት አንገትን ቀና አድርጎ መሄድ ባያስችልም በስደቱ ጊዜ የቀሰመው ዕውቀትና ክሂል ግን ዛሬ ላይ ቀና ብሎ እንዲሄድና ለሌሎችም መትረፍ እንዲችል አድርጎታል። ምክንያቱም እንግሊዝ በፈርኒቸር ዘርፍ ሁሉንም የተባለውን ዕውቀት ሁሉ ሳትሰስት ለግሳዋለች። የማምረቻ ማሽኖችን ጭምር አስተዋውቃ ክሂል አስታጥቃዋለች።
በስደት ሕይወቱ ያገኘውን ዕውቀትና ክሂል ከነመሥሪያ ማሽኑ ጭምር ወደ ሀገሩ ይዞ የመምጣት ራዕይን ሰንቆ የነበረው አቶ አምላክቸር ድርጅቱን ከቤተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን ሲያቋቁም ፈርኒቸር ከማምረት ይልቅ በዘርፉ ወጣቱን ማሰልጠን ላይ ትኩረት በማድረግ ነው። ለስልጠናው ይረዳው ዘንድም በስደት ከቆየበት እንግሊዝ በርካታ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ችሏል።
ጂግጂጋ ከተማ ተወልዶ ሀረር እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ የማደግና የመማር አጋጣሚ የነበረው አቶ አምላክቸር፤ ከአዲስ አበባ እትብቱ ወደተቀበረበት ጅግጅጋ ተመልሶ ነው የ12ኛ ክፍል ፈተናን የተፈተነው። በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድል ገጥሞታል። ይሁንና የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንኳ ሳያጠናቅቅ፣ የሕይወትን ውጣ ውረድ ለመጋፈጥ ገና በጠዋቱ ነው ስደት የወጣው። የደርግ መንግሥት ወድቆ የኢህአዴግ መንግሥት በትረ ስልጣኑን በተቆጣጠረ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ሶማሊያ ተሰዷል።
ሀገር ወዳድነትን፣ ተቆርቋሪነትን፣ ወገንተኝነትንና ህዝባዊነትን ከወታደር ቤተሰቦቹ የተማረው አቶ አምላክቸር፤ ስደት የወጣው ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር እንደነበር ያስታውሳል። ከትውልድ ቦታው ጂግጂጋ ተነስቶ ሶማሊያ በገባበት ወቅት ሶማሊያ ጦርነት ውስጥ የነበረች ቢሆንም የወጣትነት ሙቅ ልቡን አዳምጦ ወደኋላ ሳይመለስ ከጓደኞቹ ጋር ህጻናትን ከማስተማር ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን በሶማሊያ ሠርቷል። ዋናው ዓላማ ከሀገር መውጣት በመሆኑ ከመርከበኞች ጋር ተቀራርቦ የመሥራት አጋጣሚም ተፈጥሮለታል። በዚህ ጊዜ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ የተባሉ ወቅቶችን አሳልፏል።
አቶ አምላክቸር፤ በነበረው የሥራ ትጋትና ቁርጠኝነት የተነሳ መርከብ ላይ ሥራ የማግኘት ዕድል አጋጥሞት መርከበኛ መሆን ችሏል። መርከብ ላይ ለሦስት ዓመታት እንደሰራ የካፒቴን ምክትል ኃላፊ እስከመሆን ደርሷል። ከስድስት ዓመታት የሶማሊያ ቆይታው በኋላ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ በኢትዮጵያ የቀድሞ ባህርና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በመርከበኝነት የመቀጠር ዕድል አግኝቷል። በወቅቱ የነበረው ውድድር በመርፌ ቀዳዳ የመሹለክ ያህል እጅግ ፈታኝ ቢሆንም እርሱ ግን ከተመረጡ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ መሆን ችሏል። ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ ሀገረ እንግሊዝ የተደረገውን የመርከብ ጉዞ ምክንያት በማድረግ እንግሊዝ መቅረት ችሏል።
እንግሊዝ ለመቅረት በወሰነበት ቅጽበት የአንድ ኢትዮጵያዊ ዕድልን ይዞ እንደገባ በማመን ዕድሉን በሚገባ ተጠቅሞ ወደ ሀገሩ ለመመለስ ለራሱ ቃል ገባ። እንግሊዝ ቀን ከሌሊት እየሠራ ራሱን ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሠርቶ ለመለወጥና ሀገሩ ላይ ቴክኖሎጂን በማምጣት የሥራ ዕድል መፍጠር የሁልጊዜ ህልምና ጉጉቱ ሆነ። እንግሊዝ በፈርኒቸር ዘርፍ የመሰማራት አጋጣሚ ተፈጥሮለት በዘርፉ ያለመታከት ሲሰራ የቆየው አቶ አምላክቸር፤ ሥራውን በሚሠራበት ወቅትም ዓላማ አድርጎ ይሠራ የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ይዞ ስለሚገባቸው ማሽኖች፣ ስለሚፈጥረው የሥራ ዕድል፣ ስለሚሰጠው ስልጠና ብሎም ዘርፉን እንዴትና ወዴት ማሳደግ እንደሚችል ነበር።
ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣት በብዛት ቢኖርም ማሽንን መሰረት ያደረገ ስልጠና ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ወጣቶችን በቀላሉ ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለ የተረዳው አቶ አምላክቸር፤ ወደ ሀገሩ ሲገባ ቀዳሚ ሥራው በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል መፍጠር ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሥራ የሚሠራው በማኑዋል እንደሆነና በማሽን ካለመሰራቱ ጋር ተያይዞ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እና ተወዳዳሪ መሆን እንዳልተቻለም መረዳት ችሏል።
በእንግሊዝ ሀገር በፈርኒቸር ኢንዱስትሪው 10 ዓመታት ካስቆጠረ በኋላ መለዋወጫ በቀላሉ የሚገኝላቸው፣ በቀላሉ የሚጠገኑና በርካታ ሰዎችን ማሳተፍ የሚችሉ የተለያዩ ማሽኖችን ለይቶ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ዓላማውን አሳክቷል። በመሆኑም ማሽኖቹን ተጠቅሞ በሀገር ውስጥ ያለውን ሰፊ የእንጨት ሀብት እንዲሁም የሰው ኃይል በመደመር በአሁኑ ወቅት የፈርኒቸር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ፣ ለማዘመንና ውጤታማ ለማድረግ ከላይ ታች እያለ ይገኛል።
በእንግሊዝ የነበረውን የ10 ዓመት ቆይታ ገታ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው አቶ አምላክቸር፤ የተማረውን ሊያስተምር፤ ያወቀውን ሊያሳውቅ የሰነቀውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ 300 ማሽኖችን ከእንግሊዝ ሀገር አስገብቷል። ማሽኖች በእንጨት ሥራ የሚሳተፈውን የሰው ኃይል ቁጥር በማሳደግ፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ያላቸው ድርሻ ትልቅ በመሆኑ ይህንኑ ትኩረት አድርጎ በመሥራት ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። ያም ቢሆን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው የሚናገረው አቶ አምላክቸር፤ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፈርኒቸር ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ የሁልጊዜ ቁጭቱ እንደሆነ ይናገራል።
አቶ አምላክቸር፤ በእንግሊዝ ያገኘው የፈርኒቸር ዕውቀትና ክህሎት አሁን ለሚገኝበት የፈርኒቸር ኢንዱስትሪው ትልቅ መሰረት ጥሎለት ያለፈ በመሆኑ ከማምረት በላይ ስልጠና ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ተገቢ እንደሆነ ያምናል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በማሽን መሥራት ብዙም የተለመደ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ የሚሰራው በማኑዋል አልያም በሁለትና ሦስት ማሽኖች በመሆኑ ነው። ይህም የኢትዮጵያ ምርቶች ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችሉ አድርጓል። ይህን መቀየር ደግሞ ቀላልና የሚቻል እንደሆነ ተናግሯል።
‹‹ፈርኒቸር ማኑፋክቸሪንግ ሮኬት ሳይንስ አይደለም›› የሚለው አቶ አምላክቸር፤ 90 በመቶ የሚሆነው ጥሬ ዕቃ በሀገር ውስጥ አለ። ስለዚህ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ማሽነሪ ተጠቅሞ ለውጥ ማምጣት እየተቻለ ፈርኒቸር ከውጭ ማስገባት በእጅጉ የሚቆጨው መሆኑን ሲያስረዳ፤ ፈርኒቸር በባህሪው ሰፊ ቦታን የሚይዝ በመሆኑ እንዳይገጫጭ በሚል ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል። በመርከብ ሰፊ ቦታ ይዞ በሚመጣበት ወቅት የሚጠይቀው ወጪ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት የፈርኒቸር ዋጋ የሚቀመስ አይደለም። ስለዚህ ፈርኒቸሩን ከማምጣት ይልቅ ማሽኑን አስመጥቶ ስልጠና መስጠት አዋጭና ተመራጭ ከመሆኑም በላይ ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እንደሆነ ይናገራል።
‹‹እያንዳንዱ ሰው አንድ ኮንቴነር ማሽነሪ አምጥቶ የማሽነሪ አጠቃቀም ስልጠና ቢሰጥ ሀገርን መቀየር ይቻላል›› የሚለው አቶ አምላክቸር፤ በሀገሪቱ በዘርፉ ስልጠና መስጠት የሚችሉ በቂ ተቋማት ያለመኖራቸው አንዱና ዋነኛው ችግር እንደሆነም ጠቅሷል። ብቁ የሆኑ ተቋማትን መፍጠር ከተቻለ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚቻልና ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማምረት እንደሚቻል በመግለጽ ይህም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ፈርኒቸር ለማስቀረት ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ያምናል።
በተለምዶ ‹‹የፈረንጅ ጽድ›› የሚባለውን እንጨት በስፋት በመጠቀም ፈርኒቸር የሚያመርተው ባምላክ ፈርኒቸር፣ ከቁርጥራጭ እንጨቶችና ተረፈ ምርት ተብለው የተጣሉ የተለያዩ እንጨቶችንም ይጠቀማል። በተለይም ከሚፈርሱ የድሮ ቤቶች በሚገኘው የማዕዘን እንጨትና ሌሎች እንጨቶች ጥራታቸው የተጠበቀ ፈርኒቸሮችን ያመርታል። በአብዛኛው የምግብ ጠረጴዛ፣ የተለያዩ ወንበሮችና በሮችን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ በማምረት ይታወቃል። ምርቶቹን በብዛት የሚጠቀሙት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ሲሆኑ፤ ለአብነትም አሜሪካ ኢምባሲ፣ ኦሮሚያ ባንክ፣ መሬት ባንክና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
የፈረንጅ ጽድ የሚባለው ደን በኦሮሚያና በአማራ ክልል በስፋት የሚገኝ እንደሆነ የጠቀሰው አቶ አምላክቸር፤ የፈርኒቸር ኢንዱስትሪው በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በጥራት ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ከደን ልማት ጀምሮ መሥራት እንደሚገባ ይናገራል። ለዚህም ወደ አርሶ አደሩ በመቅረብ መሥራትና ማገዝ ተገቢ እንደሆነ በማንሳት ዛፍ በመትከል ለደን ዋጋ መስጠት ተገቢ ነው። ለዚህም አርሶ አደሩ ዛፍ ተክሎ ተንከባክቦ በማቆየት ገቢ ማግኘት እንዲችል መሥራት አንዱና ዋነኛ ሥራው ሊሆን እንደሚገባም ነው ያስረዳው።
በውጭና በሀገር ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ በፈርኒቸር ዘርፍ ያሳለፈው አቶ አምላክቸር፤ ቢዝነስን ከፈርኒቸር ውጪ ማሰብ አይፈልግም። በዘርፉ የተጻፉ መጻሕፍትን በስፋት አንብቧል። ካነበባቸው መጻሕፍት መካከልም ወደ አማርኛ የመመለስ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ይህም ለዘርፉ መሰጠቱን የሚያሳብቅ ነው። በዘርፉ ስልጠና በመስጠት ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ዋነኛ ግቡ እንደመሆኑ 800 ለሚደርሱ ዜጎች የእንጨት ሥራ ስልጠና ሰጥቷል። በቀጣይም ይህንኑ የማስቀጠል ፍላጎት ያለው አቶ አምላክቸር፤ ሰልጣኞቹን የሚያገኛቸው በግል እንዲሁም በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው የሚሰሩና ያለባቸውን ክፍተት ለመሙላት የሚሰለጥኑ እንደሆኑ አጫውቶናል።
የፈርኒቸር ዘርፍ በተግባር የሚሰራ እንደመሆኑ ዲግሪ አይጠይቅም፤ በአብዛኛው የማሽን ክህሎት ያስፈልጋል። ለዚህም ከወረቀት ይልቅ ተግባር ላይ ትኩረት በማድረግ ለቴክኒክና ሙያ መምህራን ከ40 እስከ 100 ሰዓት የሚደርስ የስልጠና ቆይታ ይደረጋል። ሰፊ ጊዜ ወስዶ የሚሰለጥነው አንድ መምህር በርካታ ተማሪዎችን ማሰልጠን የሚችል በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ ውስጥ በርካታ ማሽነሪዎች በመኖራቸው በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ጭምር ባለሙያዎችን ልከው የሚያሰለጥኑበት አጋጣሚ ስለመኖሩም አስረድቷል።
ድርጅቱ በሚሰጠው ስልጠና እንዲሁም በምርት ሂደት ተሳታፊ ለሆኑ 116 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው አቶ አምላክቸር፤ በተለይም ስልጠና መስጠት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። ስልጠና ከሰጣቸው ተቋማት መካከል አየር ኃይል አንዱ ሲሆን፤ ይህ እድል የተፈጠረው ተቋሙ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወንበሮች በጨረታ ለመግዛት ያደረገውን ጥሪ ባምላክ ፈርኒቸር አሸንፎ በገባበት አጋጣሚ ነው። ባምላክ ፈርኒቸር አምርቶ ከመሸጥ ይልቅ አባላቱን አሰልጥኖ እዚያው አየር ኃይል ግቢ ውስጥ የሚፈልጉትን ወንበር ማምረት የሚያስችላቸውን የተግባር ስልጠና በመስጠት አባላቱ ግቢ ውስጥ ማምረት እንዲችሉ አድርጓል። ይህም እጅግ የሚያኮራው ሥራ እንደሆነ አቶ አምላክቸር ይናገራል።
ከዚህ በተጨማሪም 47 የቤተመንግሥት ሪፐብሊካን ጋርዶችን ጨምሮ 32 ከቤላ የመከላከያ የጦር ጉዳተኞችና 28 ከጎዳና የተነሱ ዜጎችን ማሰልጠን ችሏል። የጦር ጉዳተኞቹን ለማሰልጠንም ዊልቸርና የተለያዩ አጋዥ መሳሪያዎችን ከእንግሊዝ ሀገር በማምጣት ተመችቷቸው መሰልጠን እንዲችሉ አድርጓል። በድርጅቱ ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎች ማሽን ተጠቅመው በተግባር የሚሰለጥኑ በመሆናቸው ገበያው ላይ ተፈላጊ ናቸው።
የፈርኒቸር ዘርፍ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ መዶሻ፣ መሮና የተለያዩ መሳሪያዎችን የሚጠይቅ አይደለም። የሚጠይቀው ማሽኖችን ነው። ለዚህ ደግሞ ድርጅቱ በርካታ ማሽኖችን የያዘ በመሆኑ ማንኛውንም ሰው አሰልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት ይችላል። በአሁኑ ወቅትም 80 በመቶ ያህል ሴቶችና እናቶች ባምላክ ፈርኒቸር ውስጥ ተሳታፊ በመሆን በፈርኒቸር ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ሥራቸውን በጥንቃቄ የሚሠሩ እንደሆነና ለእያንዳንዱ ሥራም ዋጋ ሰጥተው የሚሠሩ እንደሆኑ ነው ያስረዳው።
‹‹ሰዎች በሚሰሩት ሥራ ገንዘብ ማግኘትን ብቻ ትኩረት ማድረግ የለባቸውም›› የሚል አመለካከት ያለው አቶ አምላክቸር፤ በሥራው ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚሰራው በጎ ሥራ ይበልጥ እርካታን የሚሰጠው እንደሆነ ይናገራል። ለዚህም ከማምረት በበለጠ ስልጠና በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ለመሥራት የማምረቻና የማሰልጠኛ ቦታ ጥያቄ አለው። በመሆኑም መንግሥት ጥያቄውን መመለስ ሲችል በዘርፉ ትልቅ ውጤት ማምጣት የሚቻል እንደሆነ አቶ አምላክቸር በጽኑ ያምናል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2015