የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት መንገጫገጭን ተከትሎ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከቶችን ርዕዮተ ዓለሞችን/ የያዙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ኢድህ ወዘተ ተፈጥረዋል ።

በወቅቱ የነበረውን የለውጥ ፈላጊ ምሑሩን ጥረት በማምከን ሁሉንም ነገር በኃይል ገርስሶ ሥልጣን የተቆናጠጠው ወታደራዊው መንግሥት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓን) በመመሥረት በሀገሪቱ ብቸኛው ፈላጭ ቆራጭ የፖለቲካ ፓርቲ በመሆን ለሁለት አስርተ ዓመታት ያህል ሀገሪቱን ገዝቷል ።

በደርግ ዘመነ መንግሥት በፖለቲካ ፓርቲ ተደራጅቶ መንግሥትን መፎካከር ይቅርና ግለሰቦች ሁለትና ሦስት ሆኖ በጋራ መንቀሳቀስ በራሱ ለአደጋ ይጋብዝ ነበር። ሀሳብን በነፃነት ለመግለጽ የሚያስችል መድረክም አልነበረም። “ለምን መብቴ ተነካ” ብሎ መጠየቅ በራስ ላይ የሞት ፍርድ እንደመፍረድ ይቆጠር ነበር።

ሁሉ ነገር በጠመንጃና በጉልበት መልስ በሚሰጥበት ዘመን ሀሳብን በሀሳብ መሞገት የማይታሰብ ሆነ። ሀሳብን በሀሳብ የመታገያ ሜዳ መጥፋቱ ደግሞ ነጭ ሽብርን ወለደ። የነጭ ሽብርን አጸፋ ለመመለስ ቀይ ሽብር ተጧጧፈ። በዚህም ሀገር አኬል ዳማ ሆነች። የፖለቲካ ፓርቲ መታገያ ሜዳው የአንድ ፓርቲ የበላይነት የነገሠበት ሆነ።

አምባገነኑ ወታደራዊው መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በኃይል ከመደፍጠጡም በላይ እንደ ሥጋት የሚያያቸውን አያሌ የመብት ተሟጋቾች፣ ወጣቶችና የመንግሥት ሠራተኞችን እንዲሁም የጦር መኮንኖችን ጭምር በግፍ እየገደለ፣ ቶርች እያደረገና እያሳደደ እስከአሁንም ድረስ ፖለቲካና ኮረንቲን አንድ አድርጎ በምናቡ የሚስል ዜጋ ምድሩን እንዲሞላው የገፋ መጥፎ ዘመን የታለፈበት ነበር፡፡

የአምባገነን መንግሥታት መጨረሻቸው ውርደት እንደመሆኑ፤ አምባገነኑ ደርግም የውርደትን ካባ ተከናንቦ ዳግም ላይነሳ በሕዝብ ትግል ተንኮታኩቶ ወደቀ። በደርግ ዙፋን ላይ የተተካው ኢሕአዴግ ከሚከተለው ርዕዮተ ዓለም አንጻር የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን (multi party system) በወረቀት ላይ አስፍሮ የአገዛዝ ሥርዓቱን ጀመረ።

በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ዜጎች በነፃነት ተደራጅተው ለሥልጣን የሚበቁበትና ለመድበለ ሥርዓት የሚረዳ የፖለቲካ ተሳትፎ ባያደርጉም፤ በሕገ መንግሥታዊ የምርጫ ሥርዓት መሠረት ወቅታቸውን የጠበቁ ምርጫዎች መካሄዳቸው በበጎ ጎን የሚጠቀስ ነው። እንዲሁም ዕድሜው 18 ዓመት የሞላውና በአካባቢው ሁለት ዓመት የኖረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በምርጫ እንዲሳተፍ የሚያስችል አዋጅ 11/1984 ወጥቶ ሁሉም ዜጋ በነቂስ መመዝገብና በምርጫ መሳተፍ የሚችልበት እድሉ መመቻቸቱ ሌላውኛው በመልካም ጎን የሚጠቀስ ነው።

ይሁን እንጂ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በተወዳዳሪዎቹ ላይ የሚያደርሰው ጫና ማየል፣ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት አለመከበር፣ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ አለመለያየት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን እንዳቀጨጨው የዘርፉ ምሑራን ይናገራሉ።

የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዐውድ አለመኖሩ፣ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫዎች አለመደረጋቸው፣ የሕግ የበላይነት መደፍጠጥ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለመጠናከር እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እና ግለሰቦች ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ገንዘብ እንዳይደግፉና እንዳይደጉሙ ገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ያሳድር ነበር። አለፍ ሲልም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሀብቶችን ዘብጥያ ያወርድ ነበር። በዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፋይናንስ ድጋፍ ስለማያገኙ ርዕዮተ ዓለማቸውን ወደታች ወርደው በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማስረጽ ይቸገሩ ነበር።

በአንጻሩ መንግሥት ተላላኪዎቹን የዳቦ ስም እየሰጠ በፖለቲካ ፓርቲ እንዲደራጁ ያደርግ ነበር። በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደአሸን እንዲፈሉ ሆኗል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት በራሱ ደግሞ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱ እንዳይጠናከር አድርጓል።

ገዢው ፓርቲ እራሱን አውራ ፓርቲ አድርጎ፤ በመርሕ እና በዓላማ ተቀርጸው የተደራጁ እውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ገበያ ላይ ወጥተው እንዳይሸጡ ከማድረጉ ባለፈ እንዲከስሙ አድርጓል።

ይህም አልበቃ ያለው አውራ ፓርቲው የተፎካካሪ የፓርቲ አመራሮች ባልዋሉበትና ባልፈጸሙበት “ሽብርተኛ” የሚል የሐሰት ታርጋ በመለጠፍ ዘብጥያ እንዲወርዱ በማድረግ ጥፍር ሲነቅል፣ ሲያኮላሽ እንደነበር ሀገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። በዚህም ገሚሶቹ ከሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማምለጥ ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። ሰላማዊ የትግል መስመሩ ሲዘጋባቸው ሳይወዱ በግድ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገቡ ተገፍተዋል።

ባለፉት 30 ዓመታት የፖለቲካ ፓርቲ መታገያ ሜዳው እጅጉን እየጠበበ በመምጣቱ በመጨረሻም በጨረባ ምርጫ አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ ድምጽ አገኘሁ እስኪል አድርሶታል። ይሁን እንጂ ገዢው ፓርቲ “መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ” ብሎ በተናገረ ማግስት በሀገሪቱ ሕዝቦች በተፈጠረው የለውጥ ፍላጎትና ግፊት እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው የለውጥ እንቅስቃሴ መነሻነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣት ችሏል።

የለውጥ መንግሥቱ ወደ ሥልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ማሻሻያ አድርጓል፣ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ፣ አኩርፈው ከሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ የተገለሉ እንዲሁም ተገፍተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ ከሀገሪቱ ውጭ የነበሩ ፓርቲዎች በነፃነት ሀሳባቸውን ተንቀሳቅሰው እንዲሸጡ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይዳብር “እግር ከወርች” አስረው አላሠራ ያሉ የምርጫ ሕጎችን በማሻሻል እንዲሁም ሌሎች የዴሞክራሲ ምሕዳርን ለማስፋት የሚረዱ ድንጋጌዎችን በማካተት አዲስ የምርጫ ሕግ እንዲወጣ ተደርጓል። ከዚህ ባሻገር የምርጫ ቦርድን የመሰሉ ወሳኝ የዴሞክራሲ ተቋማት ለከፋ የገለልተኝነት ሥጋት የተጋለጡ ነበሩ። ለሀገሪቱ እውነተኛ የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት በገለልተኛ አካላት እንዲመሩ ተደርጓል። ሌሎች እጅግ ብዙ ለውጦችን መጥቀስ ይቻላል።

ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከተፈጠረው ምቹ ሁኔታ አኳያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቁጥር ከሚበዙ ይልቅ ሰብሰብ ብለው ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆኑ ዘንድ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተለያዩ አካላት /ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር / ምክር ተለግሷል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን አሁንም የተጠናከረና ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት መፍጠር አለመቻላቸው እና ግልጽ የሆነ ርዕዮተ ዓለም ባለቤት አለመሆናቸው ዛሬም ቢሆን በአደባባይ ከሚስተዋሉ ችግሮቻቸው በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው።

በዚህ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል አማራጭ ሐሳቦችና የአመለካከት ብዝኃነቶች እየተስተናገዱ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ ሀገር በሚፈጠርበት ጊዜ እንኳን (ለአብነት በኮሮናን ወቅት) ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሮ ሕዝብና ሀገርን ለማስቀደም ዳገት ሲሆንባቸው ተስተውሏል።

አሁንም አብዛኞቹ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በብሔርና ማንነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ሰብሰብ ብለው የተሻለ እና የበሰለ ሃሳብ እንዳያመነጩ እክል እንደሆነባቸው ይገለጻል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን ገብረ ዮሐንስ፣ ‹‹Political Parties Party Program Matocity and Party System in Post 1991 Ethiopia›› በሚል ርዕስ ባደረጉት ጥናት ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ አመላክተዋል።

በዚሁ ጥናታቸው፤ የፓርቲዎቹ አመሠራረት በራሱ ብሶትን ለማርገብ፣ በብሔር ዙሪያ ተደራጅተው ሀገራዊ ከሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ይልቅ ክልላዊ አስተሳሰቦች ላይ ማተኮራቸው እና የጠራ የርዕዮተ ዓለም አለመያዛቸው፣ አማራጭ የሆኑ ሐሳቦችን በማመንጨት ለሕዝቡም አማራጭ በማቅረብ የመንግሥትን ሥልጣን ያያዘውን/ገዢውን ፓርቲ መሞገት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከብሔርና ማንነት ተኳር አደረጃጀት ወጥተው ሰብሰብ ብለው የተጠናከረ አደረጃጀት በመፍጠር፣ ሀገራዊ አማራጮችን በመቅረፅ፣ የጠራ የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ አቋም በመያዝ፤ በሴራ አንዱ አንዱን ጠልፎ ለመጣል ከመሯሯጥ ይልቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር ተቀራርበው በመሥራት ጭምር ተገዳዳሪ ፓርቲ ሆነው መውጣት የሚችሉበትን የመፍትሔ ሃሳብ በጥናታቸው አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የብዙዎቹ ፓርቲዎች መሠረታዊ ችግር የዲሞክራሲን መሠረታዊ መርሆዎች ጠንቅቆ አለመረዳት እንደሆነ የዘርፉ ምሑራን አክለው ይናገራሉ። ይህም በየጊዜው አዳዲስ ፓርቲዎች እንደአሸን እየተፈለፈሉ በሀገሪቱ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲኖሩ አድርጓል።

የተለያዩ ሐሳቦች አስተናግደው በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር አንድ ለመሆን ከፍተኛ ፍጭት አድርገው፣ በሃሳብ የበላይነት አምነው፣ በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመኖራቸው ገዢውን ፓርቲ የሚገዳደር ፓርቲ ዛሬም አልተፈጠረም።

የዚችን አገር ሕዝቦች ለዘመናት ወደ ኋላ ከጎተቷት ፖለቲካዊ ጉዳዩች መካከል ቂም፣ በቀል፣ የደቦ ፍርድ፣ የኃይል አደረጃጀት ብሎም የደፍጥጠህ ግዛ የጭቆና ቀንበር ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ‹‹የሚደራጁ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ስብሰብ ሳይሆኑ ብሶት፤ ቂም በቀልና ምሬት የወለዳቸው ፓርቲዎች እንዲኖሩ ማድረጉን›› ምሑራን ይናገራሉ።

በጥቅሉ አብዛኞቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለውን ችግር ተቋቁመው ዳር ለመድረስ የሚያስችል ዓላማና ራዕይ አልሰነቁም። የጠራ ርዕዮተ ዓለም አልቀረጹም፤ የፖለቲካ አቋም አልያዙም። በዚህም በተለይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለውጡ ከመጣ በኋላ በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር ወደ ፖለቲካ መታገያ ሜዳው የገቡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ፓርቲያቸውን በይፋ ለቀው ሲወጡ ይስተዋላል።

‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› እንዲሉ ከነበሩበት የፖለቲካ ፓርቲ ወጥተው ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ሲሯሯጡ ይስተዋላል። በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከሰላማዊ ትግል ወጥተው ፋሽኑ ባለፈበት የትጥቅ ትግል አዘቅት ውስጥ እየዳከሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓቱን የሚያቀጭጭ፣ ሀገርንና ሕዝብን ወደ ኋላ የሚያስቀር ነው።

በርግጥ በየትኛውም ሀገር የሚገኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ችግር አልባ ነው ብሎ መናገር የሚያስችል ዓለም አቀፍ እውነታ የለም፤ አሁን አሁን በፓርቲ ፖለቲካ ዘመናቸውን የቆጠሩ ሀገራት ጭምር የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል ። ይህ እውነታ በእኛም ሀገር ችግር አልባ ነው ብሎ ለማሰብ የሚቀል አይደለም ።

ይህንን ተግዳሮት ለመሻገር ሆነ ለገዥው ፓርቲ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው፣ ግልጽ ራዕይ ሰንቀውና የጠራ ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው ለመጭው ምርጫ እራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት አለባቸው።

ምርጫ ሲቃረብ ነጥብ ለማስቆጠር ከማቅረብ ቀደም ብሎ እራሳቸውን ጠንካራ ተወዳዳሪ አድርገው ማቅረብም ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ማድረግ ሲችሉ ነው ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እያበረከቱ ነው ሊባል የሚችለው ።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *