በሠራዊቱ ላይ የተከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ለመመከት

ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡት፤ በሀገራቸው ዘርተው የሚቅሙት፣ ወልደው የሚስሙት፣ ሠርገው የሚድሩትም ሆነ የሞተን የሚቀብሩትና የሚያስተዛዝኑት ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም ሲጠበቅ ተማሪው ከመምህሩ ተገናኝቶ ዕውቀት ይገበያል፡፡ በከተሞች ያሉ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ያለችግር ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡

የመንግሥት የመጀመሪያ ሥራው የዜጋውን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ከመሆኑ አንጻር፣ የሰላም ጉዳይ ፈተና ሲያጋጥመው መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያሰማራል፤ ነገሩ ከከፋ ደግሞ መከላከያ ሠራዊት ስምሪት ስዶ የሕዝቡን ሰላም ያጸናል፡፡ ይህ የመንግሥት ሥርዓት እውን መሆን ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ያለ እውነታ ነው።

በኛም ሀገር የሕዝብ ሰላም ፈተና ውስጥ ሲወድቅ መንግሥት ካለበት ሕጋዊና የሞራል ኃላፊነት አንጻር፤ የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅ አማራጭ እርምጃዎችን ይወስዳል፤ በመውሰድም ላይ ይገኛል። በዚህም በሀገሪቱ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህንንም ተከትሎ ለሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ችግር የሆኑ የተለያዩ ኃይሎች በሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከከፈቱ ውለው አድረዋል፡፡ የአሉባልታ ወሬዎችን ፈጥሮ በማናፈስ፤ ተልዕኮውን ለማደናቀፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

እነዚህ ኃይሎች ከፍጥረታቸው ጀምሮ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት፤ ከግጭቱ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ረጅም ርቀት ሄደው ታይተዋል። ጽንፈኝነትን በሕዝቦች መካከል በመዝራት የሀገርን ሕልውና ስጋት ውስጥ ጨምረው፤በዚህም ሲፈነድቁ ተስ ተውለዋል።

በሚያስተዳድሯቸው የመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚያሰራጯቸው አሉባልታዎች ለሀገር ሕልውና የቱን ያህል የአደጋ ምንጭ እንደሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደሀገር ከፈጠሩት አደጋና አደጋው ሀገርና ሕዝብን ካስከፈለው ዋጋ ለመረዳት አይከብድም፡፡

አባቶች ‹‹ሳይደርቅ በርጥቡ፣ ሳይርቅ በቅርቡ›› እንደሚሉት በነዚህ አካላት ላይ የሚመለከታቸው አካላት ፈጥነው እርምጃ ካልወሰዱ፤ ችግሩ ጊዜ ተሰጥቶት ከገነገነ ከትናንት በበለጠ ሀገርና ሕዝብን ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ነው፡፡ ድንገትም ለሀገር አንድነት ሕልውና የከፋ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉበት እውነታ ሊያነጋግር የሚችል አይሆንም።

‹‹እህልን አላምጦ ነገርን አዳምጦ›› እንደሚባለውም መላው ሕዝባችን የእነዚህን ኃይሎች አሉባልታ ወደ ጎን ትቶ እንደሀገር ነገዎቻችንን የተሻለ ለማድረግ የጀመርናቸው የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም በተሠማራበት የሥራ መስክ በርትቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ሐሰተኛ መረጃዎችንና ዘገባዎችን ንቆ መተውና ራስንም ከአሉባልታ ዘገባዎች ማራቅ ይጠበቅበታል፡፡

በሐሰተኛ መረጃዎች ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ሐሰተኛ መረጃ ሦስት ዓይነት መልኮች አሉት፡፡ የመጀመሪያው መረጃ ማዛባት (Disinformation) የሚባል ሲሆን መረጃው ሙሉ ለሙሉ ውሸት የሆነና አንድን ማኅበረሰብ፣ ቡድን ወይም ግለሰብን በቀጥታ ለመጉዳት ታስቦ ለገንዘብ፣ ለፖለቲካዊ ትርፍና ውዝግብ ለመፍጠር የሚሰራጭ ነው፡፡

ይህ ያልተከሰተና ያልተፈፀመ ነገርን እንደተከሰተና እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርብበት መንገድ ነው፡፡ ሰው በመኪና ተገጭቶ ሳለ የተጎዱ ሰዎችን ምስል በከፊል እያሳዩ የመንግሥት ሠራዊት ሕዝብ ላይ ጥቃት ፈጸመ በሚል የሚሰራጩ መረጃዎች ዓይነት ነው፡፡ ዋንኛ ዓላማቸው ሕዝብን በተሳሳተ መረጃ ማወናበድ ነው።

ሌላው ደግሞ መረጃ ማሳሳት (Misinforma­tion) ነው፡፡ ይህም ትክክል ያልሆነ መረጃ ነው። ይህ መረጃ ሆን ተብሎ አንድን ማኅበረሰብ ወይም ቡድን ለማጥቃት የሚፈፀም አይደለም፡፡ መረጃው የተሳሳተ መሆኑን ሳይገነዘቡ ሳያጣሩ መልቀቅን የሚመለከት ነው። የዚህ ዓይነት መረጃ ሰውን ለመጉዳት ታስቦ ባይሆንም መረጃው የሚሰራጨው ከዚህ በፊት መልካም መረጃን በሚሰጡ ሰዎች ሊሆን ስለሚችል የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

 ሌላው የሐሰተኛ መረጃ ዓይነት መረጃ መበከል (Malinformation) ነው። ይህ የሆነ መረጃ ላይ ውሸት በመጨመር ወይም በትክክለኛ መረጃ ላይ የሐሰት ፎቶ ወይም ቪዲዮ ቀይጦ በማሰራጨት የሚከናወን እጅግ አደገኛ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር በተለይ መረጃ ከአንዱ ወደ ሌላው ሲተላለፍ መረጃውን በመቀነስ ወይም በመጨመር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜም ለማደናበር፣ ለማስደንገጥና ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል ሆን ተብሎ ሊሰራጭም ይችላል።

በቅርቡ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ስም የሚያጎድፉ መረጃዎች በተለያዩ በተለያ መንገዶች እየተሰራጩ መሆንን አመልክተው እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍያለ መስዋዕትነት በመክፈል ሀገርን ከመፍረስ አደጋ መታደግ፤ በዚህም ለሀገርና ለሕዝብ ያለውን ታማኝነት በተጨባጭ ማሳየት ችሏል። በሕዝቡም ውስጥ በርግጥም ከሕዝብ ወጥቶ ሕዝቡን እያገለገለ ያለ ሕዝባዊ ኃይል መሆኑን አስመስክሯል።

ይህ ሕዝባዊ ኃይል ዛሬም ቢሆን ለሀገር ሰላምና ሕልውና የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ፤ በየመንደሩ የመንደርተኝነት መንፈስ ተላብሶ ዜጎችን ሰላም የሚነሱ ጽንፈኛ ኃይሎችን አደብ ለማስገዛት መስዋዕትነት የሚጠይቁ ስምሪቶችን ወስዶ እየተንቀሳ ቀሰ ነው።

ይህንን ተከትሎ ከውስጥም ከውጭም ያሉ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች በሠሩቱ ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ከፍተው በተቀናጀ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ነው። ሐሰተኛ መረጃዎችን ፈጥሮ ከማሰራጨት ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ስም የሚያጎድፉ አሉባልታዎችን በስፋት እያሰራጩ ነው፡፡

የነዚህ ኃይሎች ዋንኛ ዓላማ ሀገርን ሕዝብን ሰላምና መረጋጋት በመንሳት፤ ሕዝቡ ተስፋ ያደረጋቸውን ነገዎች ማጨናገፍ ነው። ከዚህ አንጻር ዜጎች ከትናንት ሆነ ከዛሬ ማንነቱ ስለ መከላከያ ሠራዊቱ ማንነት በቂና ከበቂ በላይ እውቀት ያለው ነው ። በሠራዊቱ ሕዝባዊነት ዙሪያም ነጋሪ የሚሻ አይደለም።

ከዚህ የተነሳም እያንዳንዱ ዜጋ በሠራዊቱ ላይ የተጀመረውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ዓላማ ምን እንደሆነ በአግባቡ ተገንዝቦ ለስም ማጥፋት ድምፆች ጆሮውን ሊሰጥ አይገባም። የስም ማጥፋት ዘመቻውን ለመቆጣጠርና ለመግታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይቤ ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 29/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *