በበጎ ስብዕና በጎ ሀገር እንገንባ!

አንድ ሀገር የእድገትና የስልጣኔ ምንጭ ከሆኑ የማህበረሰብ እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው መልካም ስብዕና ነው። መልካም ስብዕና የሌለው ሀገርና ህዝብ ነውር የሚያውቅ አዲስ ትውልድ መፍጠር አይቻለውም። ካለ መልካም ስብዕና መልካም ሀገርና ትውልድ አይፈጠርም።

ታላቅ ሀገርና ህዝብ ለመፍጠር ከመነሳታችን በፊት መጀመሪያ እኛ የታላቅ አስተሳሰብና ስብዕና ባለቤቶች መሆን ይኖርብናል። ማንም ሰው የሌለውን ለሌሎች ሊሰጥ አይችልም ለትውልዱ መልካም አርዐያ መሆን ካለብን መጀመሪያ ራሳችንን ተገቢ አድርገን መቅረጽ ይኖርብናል።

ሀገር የዜጎቿ የአስተሳሰብ ውጤት ናት። በየትኛውም እውቀት ቢመዘን ሀገር ዜጎቿን ትመስላለች፤ እኛ የኢትዮጵያ መልኮች ነን፣ ኢትዮጵያም የእኛ መልክ ናት። በሀገራት መካከል የሚታየው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የስልጣኔ ልዩነት በዛች ሀገር ላይ የሚኖሩ ህዝቦች የፈጠሩት የአስተሳሰብ ልዩነት ነው።

ስብዕና ማረፊያው አስተሳሰብ ነው። በአስተሳሰቡ የላቀ ማህበረሰብ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው የላቀ ሀገርና ህዝብ ይፈጥራል። ስብዕና ከግለሰብ የሚጀምር ሰፈርና መንደርን አካሎ ሀገር ላይ የሚያርፍ የዘመናዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው። እንደ ሀገር የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የስብዕና ግድፈት የፈጠራቸው መሆናቸው አጠራጣሪ አይደለም።

ለሰላም የሚሆን ሀሳብ አጥተን ሩቅ በማይወስድ የጥላቻና የመበላለጥ መንፈስ ውስጥ የገባነው ኢትዮጵያን የማይመስል አጉል ልማድ ስለተለማመድን ነው። ሀገራችን እንድትስተካከል እኛ መስተካከል አለብን። ለትውልዱ መልካም ስንቅ ባልቋጠረ የፉክክር ፖለቲካ ውስጥ የምትፈጠር በጎ ሀገር የለችም።

ዘመናዊነት መነሻውም መድረሻውም ማህበረሰብ ነው። ማሰብ ስንጀምር በእውቀት፣ በማስተዋል ስንበረታ ከማንም በፊት ቀድመን የምናየው ማህበረሰባችንን ነው። ሀገር ለምንም ነገር የመጀመሪያውም የመጨረሻም ጉዳይ ናት። አሁን ላይ ብዙዎቻችን ይሄን እውነት የሳትን ይመስላል። ከሀገር በፊት ራሳችንን አስቀድመን የምንኖር እየሆንን ነው።

ከሀገር በፊት ራስን ማስቀደም አሁን ላይ በብዙዎቻችን ላይ እየታየ ያለ ልክ ያልሆነ የስብዕና ግድፈት ነው። ይሄ ግድፈት ለጦርነት በር ከፍቶ ሰላም ናፋቂ ህዝቦች እያደረገን ነው። ይህ አስተሳሰብ የወለደው የስልጣን ሽኩቻ ሀገራችንን በተረጋጋ መንገድ ላይ ቆማ መራመድ እንዳትችል ተግዳሮት እየሆነባት ነው።

በበጎ ስብዕና ሀገር ካልሰራን በእኩይ ስብዕና ሀገር እናፈርሳለን። ሀገራችን አጀንዳ አጥታ አታውቅም። ስለሰላም እያወራን ባለንበት በአሁኑ ሰዐት እንኳን ስለመልካም አስተዳደርና ስለሙስና እንጨነቃለን። ስለኑሮ ውድነት እየተጨነቅን ባለንበት በዚህ ጊዜ ስለፖለቲካ፣ ስለ ኢኮኖሚ፣ ስለማህበራዊ ቀውስ እንሰጋለን።

በብዙ ስጋት ውስጥ ነን። አብዛኛው ስጋት የተፈጠረው ደግሞ ኃላፊነት በጎደለው የስብዕና ግድፈት ነው። ባለስልጣኖቻችንን ብንፈትሻቸው ከሙስና የጸዱ አይደሉም። ተራውን ማህበረሰብ ብናየው ለምንም ነገር አቋራጭ መንገድን የሚመኝ ሆኖ እናገኘዋለን።

የአሁኑ ፈተና የሆነብን ፅንፍና ፖለቲካ፣ የራስወዳድነት ልክፍት ከእኩይ የፖለቲካ ስርዐት ተምጦ የተወለደ ነው። ያ ማለት ፖለቲከኞቻችን ብቻ አይደሉም ፖለቲካችንም በራሱ የስብዕና ግድፈት እንዳለበት የሚጠቁም ነው። ለብዙዎቻችን ስልጣኔ ከራስ እውነትና እሴት መራቅ ነው የሚመስለን።

ከራስ እውነት መሸሽ፣ ከራስ ማህበራዊ ልማድ ማፈንገጥ ነው የሚመስለን። ስልጣኔ በምንም መልኩ ራስን አያስክድም። በምንም መልኩ ባህልና ስርዐትን አይደፍርም። የዘመነ ጭንቅላት ከነውር አይወጣም። የዘመነ ጭንቅላት መገለጫው ጨዋነት ነው። ጨዋነት እውቀት ብቻ ሳይሆን ከጥበብና ከማስተዋል ከስክነትም የተቀዳ ማንነት ነው። ሀገራችን አሁን ላይ ያጣችው ግብረገብነት እና ከስክነትም የተቀዳ ማንነት ነው። እንደማህበረሰብ የምንገዳገደው በእነዚህ ሁለት እጦት ነው።

ጨዋነት የሰላም ቦታ ነው። ጨዋ በሆነና በግብረገብነት በተቃኘ ማንነት ውስጥ ነውጥና ጦርነት የሉም። ግብረገብነት ወደተሻለ የህይወት ምእራፍ የሚወስድ ብቸኛና አስተማማኝ የለውጥ ህግ ነው። ይሄ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የታመነና ተፈትሾ የተረጋገጠ ማንነት ነው። እንደ መንግስት፣ እንደዜጋ ግብረገብነትን ልንለማመድ ይገባል።

መልካም ነገሮች ያሉት በመልካም አመለካከት ውስጥ እንደሆነ በአግባቡ ልንረዳ ይገባል። በአንድ ሀገር ላይ ለውጥ ለማምጣት ትምህርትና የመሳሰሉ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ብቻቸውን በቂዎች አይደሉም። እውቀት ያለ መልካም ስብዕና ዋጋ የለውም። ትምህርት ያለግብረገብነት ምንም ነው። ለምን እንደምንማር እኮ እናውቀዋለን፤ ትምህርቱ ያበላል እያልን የምንማር ነን።

ድሀ ሀገር ለማገልገል ሳይሆን ራሳችንን ለማገልገል ተምረን የተመረቅን ብዙ ነን። ይሄ በትምህርት ስርዐቱ ላይ የታየው የስርዐት ክፍተት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። እንደምሳሌ ይሄን አነሳን እንጂ ብዙ ነገሮቻችን ሀገርና ህዝብ የሌሉበት ለራስ የተኖሩ ናቸው። በሰላም እጦት ዝቅ ያለችውን ሀገራችንን ቀና የምናደርገው ለሀገራችን መኖር ስንጀምር ነው። በድህነትና በኋላቀርነት የተጎሳቆለውን ህዝባችንን የምንታደገው ጨዋነትን ስናስቀድም ነው።

በሀገር ጉዳይ ላይ ተነጋግሮ መግባባት ሳንችል እንዴት ነው ለውጥ ልናመጣ የምንችለው? ለውጥ እኮ መነሻው ሀሳብ ነው። ሀሳብ ደግሞ ጨዋነት ይፈልጋል። ጨዋ ያልሆነ ሀሳብ ጨዋ ሀገር አይሰራም። ጨዋ ያልሆነ ሀሳብ ጨዋ ማህበረሰብ ሊሰራ ከቶ አይቻለውም።

ከምንም በፊት የሀሳብ ጨዋ መሆን ወሳኝ ነው። በሀሳባችን ከተገራን በምግባራችን ጨዋዎች እንሆናለን። ሀገር አንዋሽም፣ ከሀገር አንሰርቅም ባጠቃላይ እኔነትና ራስወዳድነት አይጎበኘንም። አሁን ላይ እክል እየፈጠሩብን ያሉ እንቅፋቶች ጨዋነት ከጎደለው አእምሮና ልብ ውስጥ የወጡ ሀሳቦቻችን ናቸው። እንዳንግባባ መንገድ የሚዘጉብንን እንቶፈንቶ ሀሳቦቻችንን በጨዋ ደንብ ማረቅ ለነገ የማንልም ግዴታችን ነው።

ሀገር ገንቢ መልካም ስብዕናዎች ከባህልና ከታሪክ የሚመነጩ ናቸው። ሀገር ገንቢ ስብዕናዎች ከሀገር ፍቅር የሚነሳ ነው። በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ ህልምና ምኞት ከሌለን ስብዕናችንን መፈተሽ ይኖርብናል። አሁን ላይ ለሀገራችን ችግር እየሆኑ ያሉት ግለሰባዊ እኩይ ስብዕናዎች ናቸው።

ግለሰባዊ እኩይ ስብዕናዎች በጊዜ ካልታረቁ ማህበራዊ እኩይ ስብዕናን መሆናቸው አይቀርም። እኚህ ደግሞ ሀገር ብለን በምንጠራው በትውልድ አብራክ ውስጥ እጅግ አደገኛ የጥላቻ መንፈስን የሚፈጥሩ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ አይነት ሀሳብና ራዕይ አጥተን የምንገፋፋው እኚህ እኩይ ስብዕናዎቻችን በፈጠሩብን ተጽዕኖ ነው።

በጣም የሚገርመው ደግሞ በስብዕናቸው ሀገር እየጎዱ ያሉት የተማሩ ግለሰቦች መሆናቸው ነው። ከትላንት እስከዛሬ የስጋታችን ምንጮች ፊደል የቆጠሩ እናውቃለን ባዮች ናቸው። ብዙ ያልገቡን ነገሮች እንዳሉ ይሄ አንዱ ማሳያ ነው። ትምህርት ለአንድ ሀገር የስልጣኔ ዋልታና ማገር ሆኖ ሳለ እኛ ጋር ለምን የሀገር ችግር ምንጭ ሆነ ? ልንጠይቅ ይገባል።

መማር ከትላንት እስከዛሬ ችግር የሆነባት ሀገር ላይ ነን። መማር እኮ ክፉ ነገር ሆኖ አይደለም፣ መማር መቼም የትም ክፉ ሆኖ አያውቅም..እንዳውም ዓለም የአሁኑን ስልጣኔ ያገኘችው ፊደል በቆጠሩ አእምሮአውያን ነው። ችግሩ ያለው ከእኛ ነው። ስንማር በጎዶሎ ዓላማ ነው፣ ስናልፍ በኩረጃ እና በሙስና ነው። ወደ ስልጣን መተንም እጅ መንሻ በመስጠትና በመቀበል የተካንን ነን። ታዲያ በዚህ እኩይ ስብዕና እንዴት ነው ሀገር የምናቆመው?

ሀገር የተባረከ ልብ ትሻለች። በልባችን ውስጥ ለሀገራችን ሰፊ ቦታ ካለን ከሌሎች ጋር መግባባትና መደራደር አይቸግረንም። ፍቅርን የሚያውቅ ልብ በደልን አይቆጥርም። ብሄርተኝነትን አያቀነቅንም። እኔ ብቻ ይመቸኝ አይልም። በመልካም ስብዕና ያጠፋን በመውቀስ፣ ጥሩ የሰራን በመመረቅ ወደ ፊት መሄድ እንጂ ሀገር በማያሻግሩ ትላንትናዊ ትርክቶች ላይ መጠመድ ችግራችንን ከማባባስ ባለፈ እሴት አይጨምርልንም።

ለሀገር ክብር ስንል ከምንም በፊት ጥሩነትን እንማር። ከምንም በፊት ሰውነትን እንልመድ። ከምንም በፊት ፈጣሪን እንፍራ። ይሄ ሁሉ በሌለበት ሁኔታ ተምረንም ሆነ ባንማር የምናመጣው ለውጥ የለም። ውስጣችን ርህራሄ ይኑር። በመልካምነት ስንቃኝ ብቻ ነው የሀገራችንን ችግር የምንቀርፈው።

የእስካሁኗ ኢትዮጵያ ተምረናል በሚሉ በብዙ ክፉ ልቦች የደማች ናት። ከእንግዲህ ለምትፈጠረው አዲሲቷ ምድር ግን መባረክን እናስቀድም። የተባረከ ልብ ባይማር የተማረ ነው። የተባረከ ልብ በወዳጁ ላይ ክፉ አያደርግም። የተባረከ ልብ ለስርዐት የተገዛ ነው። በጨዋነት የሚያምን ነው።

ጨዋነት በአባቶቻችን ልብ ውስጥ በዝቶና ተትረፍርፎ ነበር። እንደዛማ ባይሆን ባልሰለጠነ ዓለም ላይ ቆመው ለዘመናዊው ዓለም ትዕንግርት ባልሆኑ ነበር። እንደዛ እማ ባይሆን በአንድነቷና በህብረቷ የተደነቀችን ኢትዮጵያ አይፈጥሩም ነበር። እንደዛማ ባይሆን ከእኔና ከእናንተ ተሽለው ዛሬም ድረስ በመልካምነት አይጠሩም ነበር።

ሀገር ከትላንት ወደዛሬ የመጣች ወደነገም የምትቀጥል የባህል፣ የስርዐት የወግና ልማድ ቋት ናት። አባቶቻችን የሰጡን ብዙ ነገር ነው። ዛሬም ድረስ እነሱ በሰጡን ጨዋነትና ኢትዮጵያዊነት የምንጠራ ነን። የእኛ ኢትዮጵያ ግን ገና አልተፈጠረችም። ለትውልዱ የምናስረክባት ኢትዮጵያ ወዴት እንዳለች አልደረስንባትም።

በመልካም ስብዕና በአንድነትና በወንድማማችነት ኢትዮጵያን ካልፈለግናት አናገኛትም። ዛሬም ድረስ ተሰውራብን የቆየችው በቀና ልብ ስላልሻትናት ነው። ሰላም አጥተን ከወንድማማቾቻችን ጋር እየተገዳደልን፣ ማንነትን ከኢትዮጵያዊነት በላይ አግነን እየኖርን የምትፈጠር ሀገር የለችም።

ስብዕና የማይገባበት የህይወት ስፍራ የለም። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ባላቸው ሀገራት ላይ ድርሻው የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን። ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የስብዕና ልዕልና ያስፈልጋታል። በተለያየ ቦታ ከኢትዮጵያ ባህልና ስርዐት ያፈነገጡ በርካታ የነውር ድርጊቶችን እየሰማን ነው።

ወጣቱ የስብዕና ብልጽግና ያስፈልገዋል። በአእምሮና በስነልቦና ያልተገነባ ወጣት ጥፋት እንጂ ልማት አያውቅም። ዓላማችን ታላቅ ሀገርና ህዝብ ከሆነ ወጣቱ በስነ ምግባር መታነጽ አለበት፤ ያ ካልሆነ ህልማችን ፍሬ አያፈራም። መልካም ዘር ነው መልካም ፍሬ የሚያፈራው። የመልካም ፍሬ ዛፍ ጥላ ነው። መልካም ፍሬ በማፍራት ሀገራችንን ለማጥላት በበጎ ስብዕና እንመራ።

ስለሀገራችን ስንል የምንተዋቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። እንደ መንግስት፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ፣ እንደ ዜጋ የማያግባቡን ብዙ ነገሮች መኖራቸው የማይካድ ሀቅ ቢሆንም ስለ ሀገራችን ስንል ልዩነቶቻችንን ማጥበብ ግን አንዱ የመልካም ስብዕና መገለጫ ነው። ወዴትም ይሁን ለምናደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ ሰው መሆን ከፍ ያለ ዋጋ አለው። የምንራመደው በእግራችን ቢሆንም፣ የምናስበው በጭንቅላታችን ቢሆንም የምንመራው ግን ውስጣችን በተከልነው ማህበረሰባዊ እሴት ነው …እርሱም ስርዐት ይባላል።

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *