የሕክምናውን ዘርፍ በማዘመን ተጨማሪ የውጪ ምንዛሪ ምንጭ ለማድረግ

በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ የዓለማችን ሀገራት በተለይ የህክምና አገልግሎትን እንደ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ይጠቀሙታል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም፣ የህክምና ጉዞ ወይም ሜዲካል ቱሪዝም ጅማሮውን ያደረገው ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት በግሪክ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመንም አገልግሎቱ ተስፋፍቶ ሰዎች የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ወደ ተለያዩ ሀገራት ይበልጡን ሲጋዙ ማስተዋል የተለመደ ሆናል።

በአሁን ወቅትም በህክምናው ትምህርትና ቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ የዓለማችን ሀገራት ዘርፉን የገቢ ማግኛ መንገድ አድርገው እየሰሩ ብሎም ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው። ለአብነትም አሜሪካ፣ ታይላንድ፣ ህንድ፣ ካናዳ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ አገራት መጥቀስ ይቻላል።

ከእነዚህ አገራት አንፃር የኢትዮጵያ የሕክምና አገልግሎት አቅም፣ ጥራትና ተደራሽነት ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም። ትላንትም ሆነ ዛሬ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ብዙ እንግልትና ውጣ ውረድ ለመጋፈጥ ሲገደዱ ይስተዋላል። በተለይ ዘመናዊ ቴክኖሊጂዎችን ማሟላት ቢቻል በቀላሉ ታክመው መዳን የሚችሉ እንደ ኩላሊት፣ የልብና መሳል በሽታዎች ሕክምናን ሳይቀር በሀገር ውስጥ መስጠት የሰማይ ያህል እሩቅ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅትም የሕክምና አገልግሎት እጦት የበርካቶች ህልውና መሰረት የመኖርና የመሞት ምርጫ ፈተና ሆኗል። የገንዘብ አቅም ያላቸው ገንዘባቸውን ፈሰስ አድርገው በውጭ ሀገራት ህክምና ለማግኘት ሲታደሉ አቅም የሌላቸው ዜጎች በአንፃሩ ሕክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ለሞት ሲዳረጉም ይስተዋላል።

የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከግዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የስፔሻሊስት እና የሰብ እስፔሻሊስት ሕክምና በሀገር ውስጥ በሚፈለገው ልክ መስጠት ባለመቻሉ በአማካይ በዓመት ከ10 ሺ በላይ ዜጎች ለሕክምና ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ጉዞ ያደርጋሉ። ለዚህም ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጭ ያደርጋሉ። ይህ ከፍተኛ ገንዘብ ሀገሪቱ አንዳንድ የግብርና የማዕድን ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ጋር የሚስተካከል ነው።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 90ንኡስ አንቀፅ 1 “የሀገሪቱ ዓቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንፁሕ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማህበራዊ ዋስትና እንዲኖረው፤ በአንቀፅ 92 ንኡስ አንቀፅ 1 ደግሞ መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁሕና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመስራት ኃላፊነት እንዳለው በግልፅ ተደንግጓል።

በተጨማሪም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 35 ንኡስ አንቀፅ 9 ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል መብት ያስቀመጠ ሲሆን እንዲሁም በአንቀፅ 36 ንኡስ አንቀፅ 1 ስለ ህፃናት በሕይወት የመኖር እና ጤንነት መጠበቅን ይደነግጋል። በአንቀፅ 44 ንኡስ አንቀፅ 1 ደግሞ ሁሉም ሰዎች ንፁሕና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው ይጠቅሳል።

በደርግ ውድቀት ማግስት በተመሰረተው የሽግግር መንግስት የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ሽፋን ከነበረበት እጅግ አነስተኛና ኢፍትሐዊ ደረጃ ለማሻሻል እና የሕዝቡን የጤንነት ሁኔታ ለመቀየር የሚያስችል የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በ1986 ዓ.ም. ተዘጋጅቷል።

የጤና ፖሊሲው በዋና ዋና ለጤና ጠንቅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሕብረተሰቡን ግንዛቤ፤ እምነት፤ ባህሪና ድርጊት ለመለወጥና ብዙዎቹን የጤና ችግሮች ለማስወገድ በተለይም ደግሞ አብዛኛውን የገጠሩን ህብረተሰብ፣ አርብቶ አደሩን እና ደሃ የከተማውን ነዋሪ ታሳቢ ያደረገ እና በሽታን አስቀድሞ በመከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።

በ2010 ከመጣው የመንግስት ለውጥ ወዲህ የጤና አገልግሎት እና ተደራሽነቱን ለማሻሻል እና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ስራዎች ስለመሰራታቸው በመንግስት ይገለፃል፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ የፓርላማ ንግግራቸው በሽታን ቀድሞ መከላከል ላይ አተኩሮ የቆየው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ውጤት አምጥቷል፤ ነገር ግን መከላከሉ ብቻ በቂ ስለማይሆን እርሱ እንዳለ ሆኖ አክሞ ማዳን የሚያስችል የህክምና አቅም ላይ ለመድረስ እንደሚሰራ ተናግረው ነበረ።

ይህንን ለማሳካት የሚያስችል ስራ ለመስራት እና ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በጤናው ዘርፍ የህክምና አገልግሎት፣ በሰው ኃይል ትምህርት እና ስልጠና ብሎም ቴክኖሎጂ ጠንካራ ስራዎች በመስራት ዘርፉን ማዘመን ፋይዳው ጉልህ ነው። ይህ እንደመሆኑም በዘርፉ በትኩረት መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ወሳኝ የቤት ስራ ነው።

ዘርፉን ለማሳደግ በተለይ የግል ባለሀብቱ የጤናውን ዘርፍ ተቀላቅሎ ዘመናዊ ህክምና በኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ በሚሰራው ሥራ የራሱን ሚና እንዲጫወትና እራሱንም ሀገሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማስተዋወቅም ብሎም መተግበርም ያስፈልጋል።

በሜዲካል ቱሪዝም ቢዝነስ የተሰማሩ በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል ስልጠና የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ የተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ለአብነት በግብፅ ፣ በደቡብ አፍሪካ፤ በእስያ ደግሞ በታይላንድ፣ ህንድና ሌሎች መሰል ሀገራት ተሰማርተው ውጤታማ መሆን እንደቻሉት ሁሉ በኢትዮጵያም መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አሰራሩን ቀላልና በቢሮክራሲ ያልተወሳሰበ እንዲሆን ማድረግ የግድ ይላል።

በዚህ ረገድ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማበረታታት ኢንቨስተሮች መዋእለነዋያቸው ፈሰስ እንዲያደርጉ ማድረግ ቢቻል በኢትዮጵያ የህክምና ቱሪዝም መናኸሪያ ማድረግ ቀላል ይሆናል። ከሁሉ በላይ ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ከሞት ከመከላከል ባሻገር አገሪቱ ለዜጎች ሕክምና በየጊዜው ለማውጣት የምትገደደውን ከፍተኛ ገንዘብ ከማዳን ባሻገር በሜዲካል ቱሪዝም ከፍተኛ ሃብትን እንድታገኝ አቅም የሚፈጥርላት ይሆናል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የአህጉሪቱ መዲና መሆኗ፤ ከአሜሪካ ኒውዮርክ እና ከስዊዘርላንዷ ጄኔቫ ከተማ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማቲክ ከተማ መሆኗ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ቀልጣፋ እና ምቹ አገልግሎት ለዘርፉ ውጤታማነት አጋዥ መሆን የሚችል ነው።

በተጨማሪም የአገሪቱ የጂኦፖለቲካ አቀማመጧም አመቺ በመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዘርፉን ለማሳደግ ከተሰራ የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት አልፎ የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል በመሆን ገቢ ማግኘት የምትችልበት ዕድል ለመፍጠር ያስችላል።

ክብረአብ በላቸው

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *