የዛሬ የወቅታዊ እንግዳችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ አብረሓም ታደሰ ናቸው። የተሰጣቸውን የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት በመወጣት ላይ ብቻ አልተወሰኑም። በሚመሩት ተቋም ውስጥ በሚከናወነው የበጎፈቃድ አገልግሎት አንዱ በሆነው “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው‘ በሚል መርሃግብር ውስጥ በመሳተፍ የድርሻቸውን እየተወጡ ጭምር ነው። በሚሠሩት ሥራ ውስጥ እራስንም ተሳታፊ በማድረግ ሌሎችን ማስተባበር ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጀምሮ የተለመደ መሆኑንም ነግረውናል። ተሳታፊ ሆነው በሚመሩት ተቋም ውስጥ እየተሠራ ስላለው ሥራ ጊዜ ሰጥተውን ቆይታ አድርገናል።
አዲስዘመን፡- እስኪ በቅድሚያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትርጉምና አስፈላጊነቱ ላይ ሃሳብ ይስጡን።
አቶ አብረሓም፡- በጎፈቃደኝነት አንድ ሰው ማንም ሳያስገድደው በፈቃዱ ተነሳስቶ የሚሳተፍበት ነው። በጎፈቃድ ክፍያ የማይከፈልበት ነፃ አገልግሎት የሚሰጥበት፤ ለህሊና እርካታ ሲባል የሚሠራ ሥራ ነው። ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ጭምር ያለው አገልግሎት ነው።
አዲስዘመን፡- ሰዎች በግላቸው የበጎፈቃድ ሥራ ሲሠሩ ይስተዋላል። በአጠቃላይ ግን ስለበጎፈቃድ በማኅበረሰብ ውስጥ ያለው ግንዛቤስ ምን ይመስላል?
አቶ አብረሓም፡- የበጎ ሥራዎች ለኢትዮጵያውያን እሴቶቻችን ናቸው ማለት ይቻላል። የመተጋገዝ፣ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖር የሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው። በቀደመው ጊዜ በመንደር ውስጥ የማዋለድ አገልግሎት ይስጡ የነበሩ እናቶች ለማዋለድ ሲፈለጉ ክፍያ ሳይጠይቁ ውለውና አድረው ነው አገልግሎት የሚሰጡት።
አካባቢ ላይ ሰው ሲታምም እንዲሁ በሸክም ሆስፒታል ለማድረስ የአካባቢው ማኅበረሰብ በበጎ ፈቃድ ነው የሚያግዘው። በእርሻ ሥራ ላይም እንዲሁ ደቦ በሚባል የጋራ አገልግሎት ይሰጣል። በከተማም እንዲሁ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል የዳበረ ነው።
ነገር ግን ይህ በማኅበረሰብ ውስጥ ባህል ሆኖ የቀጠለው በጎ ተግባር በተደራጀ መንገድ የሚከወን ባለመሆኑ በጎ ተግባርን በተደራጀ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት አለመቻላችንን ነው እንደክፍተት የምናነሳው። በእርግጥ የተቋም ቅርጽ ይዘው የሚንቀሳቀሱ እንደ ኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር፣ የወጣቶች፣ የሴቶችና የተለያዩ አደረጃጀቶችን መጥቀስ ይቻላል። በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የበጎፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥም እነዚህን አደረጃጀቶች በመያዝ ነው እንቅስቃሴ ሲደረግ የቆየው።
እንቅስቃሴው ቢኖርም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ውስኑነቶች ነበሩ። በአመት አንዴ ክረምት ጠብቆ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት ተማሪዎች በነፃ እንዲያስተምሩ ማድረግ፣ የዛፍ ችግኝ ተከላ ማከናወን የመሳሰሉት በአጠቃላይ አገልግሎቱ ከጥቂት ተግባራት ያለፈ አልነበረም።
የነበሩትን ሥራዎች አጠናክሮ ለመቀጠል ተቋማዊ አደረጃጀት አስፈላጊ እንደሆነ መንግሥት ትኩረት ያደረገው ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ ነው። በተቋም እንዲመራ በማድረግ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ሥራ በመግባት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሀገርም ቀዳሚ ይመስለኛል። አስተዳደሩ ኮሚሽን ከማቋቋሙ በፊትም በተለያየ አደረጃጀት ቀድሞ የተጠናከረ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
አዲስዘመን፡- ተቋማዊ አደረጃጀት ከተፈጠረ በኋላ እንቅስቃሴው ላይ ምን ዓይነት ለውጦች ተገኙ?
አቶ አብረሓም፡- የመጀመሪያ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ መመስራት ተችሏል። በሁለተኛ ደረጃ የኅብረተሰብ ተሳትፎን መጨመር ተችሏል። ለአብነትም ከአመታት በፊት የኅብረተሰብ ተሳትፎ ከአንድ መቶሺና ከሁለት መቶሺ የበለጠ አልነበረም። በገንዘብም እንዲሁ ከሁለት መቶ ሺብር ያልበለጠ የበጎፈቃድ አገልግሎት ነበር ሲሰጥ የነበረው። ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ግን በተሳትፎም በገንዘብም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል። ይሄ ደግሞ የሚሰጠው አገልግሎት ጭምር ከፍ እንዲል አስችሏል። አዳዲስ ሥራዎች ተጨምረው ሰፊ ሥራ መሥራት ተችሏል።
ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በሚገመት ገንዘብ የበጎፈቃድ አገልግሎት መስጠት ተችሏል። 2014 ዓ.ም ላይ ደግሞ ወደ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ከፍ ባለ ገንዘብ አገልግሎቱን መሥጠት ተችሏል። በ2015 በጀት አመት ደግሞ ሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎፈቃድ አገልግሎት ተሰጥቷል።
በየጊዜው ለውጥ ማስመ ዝገብ የተቻለው ባለሀብቶችን ጨምሮ የሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ እየጨመረ በመምጣቱ ነው። ለዚህም በማሳያነት ከሚጠቀሰው የመኖሪያቤት እድሳት አንዱ ነው። ቀደም ሲል የመኖሪያ ቤቶችን ባሉበት የመጠገን ሥራ ነበር የሚከናወነው። በ2013 ዓ.ም በጀት አመት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ከተማና በቂርቆስ ክፍለከተሞች ባለሁለት ወለል የሆኑ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማው ነዋሪዎች ተሰጥቷል። በዚህ መልኩ በመቀጠል በ2015 በጀት አመት ላይ ግንባታቸው በሕንፃ ደረጃ የተከናወነ እስከ 11 ወለል ያላቸው ከ130 በላይ የቀበሌ መኖሪያቤቶች ለነዋሪዎች ተሰጥተዋል።
የበጎፈቃድ አገልግሎቱ ሰዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ በከተማዋ የውበት ገጽታ ላይም አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህን የተለያየ ጥቅም ያለውን አገልግሎት በማሻሻል ረገድ ደግሞ በግንባታው ሥራ አዲስ ሀሳብ መጥቶ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዟል። የሚገነቡት ሕንፃዎች መኖሪያና የንግድ ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ ነዋሪዎቹ የገቢ አቅም እንዲፈጥሩ የማስቻል በጎተግባር ነው በሥራ ላይ እየዋለ ያለው።
ቤት ተገንብቶ የሚሰጣቸው ብዙዎቹ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው በመሆናቸው ኑሮአቸውን ለመለወጥም ሆነ ለዕለት ጉርሳቸው የሚሆን ገቢ እንዲያገኙ ታስቦ የገቢ ማስገኛ ጭምር ግንባታ እንዲከናወን ነው እየተደረገ ያለው።
አዲስዘመን፡- መኖሪያ ቤታቸው እንዲታደ ስላቸው የሚመረጡት ሰዎች የሚመረጡበት መስፈርት ምንድን ነው?
አቶ አብረሓም፡– የሚመረጡት በብሎክ አደረጃጀት አማካኝነት ነው። እዚያው ኅብረተሰቡ ቤት ሊታደስላቸው የሚገባቸውን ሰዎች በቀጥታ ይመርጣል፤ ይወያያል፤ ይወስናል። የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽንም በጎ ፈቃደኞችን አስተባብሮ ግንባታውን ያከናውናል።
በአጠቃላይ የበጎፈቃድ አገልግሎት ሥራው በብሎክ አደረጃጀት ነው የሚመራው። በአዲስ አበባ ደረጃ ወደ 4992 ብሎኮች ተደራጅተዋል። ብሎኮቹንም ያደራጀውና የሚመራው የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ነው። ለብሎኮቹ ካርታ ተሠርቶ ነው ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገው። ዓላማውም ሞዴል መንደሮችን በመፍጠር ተሞክሮን እያሰፉ ስኬታማ የሆነ የበጎፈቃድ አገልግሎት ሥራ ለማስመዝገብ ነው። ማነው ድጋፍ የሚያስፈልገው?፣ ምን ዓይነትስ ድጋፍ ነው ሊደረግለት የሚገባው? የሚለውን የሚለዩት በብሎክ የተደራጁት ናቸው። ኮሚሽኑም ይህንን መሠረት አድርጎ ነው ተልዕኮውን የሚወጣው።
በአጠቃላይ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቶችን ማዕከል አድርጎ እየተሠራ ያለው በነዚህ ብሎኮች አማካኝነት ነው። የብሎክ አደረጃጀቱ እየሠራን ላለነው የበጎፈቃድ አገልግሎት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በእስካሁኑ እንቅስቃሴያችን መገንዘብ ችለናል። በተጨማሪም ማህበራዊ ድረገጾችን (ሶሻል ሚዲያ)ን ለበጎፈቃድ አገልግሎት በማዋል የበለጠ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው።
አዲስዘመን፡- በበጎፈቃድ አገልግሎቱ የትኛዎቹ የከተማዋ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለው? የመለያ መስፈርትስ ምንድነው?
አቶ አብረሓም፡- ሁሉም ዓይነት የማኅበረሰብ ክፍሎች ይገኙበታል። በጥንካሬያቸው ጊዜ ሀገርን አገልግለው አሁን ደግሞ አቅማቸው ደክሞ የተጎሳቆሉ የሀገር ባለውለታ ተብለው የሚታወቁም ተካትተውበታል። ግን ደግሞ አካልጉዳተኞች ሆነው ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ላይ የተለየ ትኩረት ይደረጋል። ምክንያቱም ችግራቸው ተደራራቢ በመሆኑ ነው። ሴቶችም በተለየ ሁኔታ ይታያሉ። እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች በጤናቸው፣ በኢኮኖሚያቸው ላይ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ከተቻለ የከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ዐሻራ እንዳሳረፈ አድርጎ ይወስደዋል። የከተማ አስተዳደሩ ይህን የበጎፈቃድ አገልግሎት ለመወጣት እንዲያስችለው የ10 አመት ፍኖተካርታ አዘጋጅቷል።
አዲስዘመን፡-ባለሀብቱን ጨምሮ በማኅበ ረሰቡ እና በተቋማት ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አብረሓም፡- ሁሉም አቅሙ በፈቀደው መጠን እየተሳተፈ ይገኛል። በወጣቱ በኩል በተለይ በደም ልገሳ እየተከናወነ ባለው አንቅስቃሴ ከ10ሺ ዩኒት በላይ ዘልቆ የማያውቀው የደም ልገሳ በአሁኑ ጊዜ ግን እስከ 60ሺ ዩኒት ደም እየተለገሰ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ እየተቻለ ነው። በተቋማት በኩል ደግሞ የግሎችን ጨምሮ የጤና ተቋማት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሕክምና በነፃ ለአቅመደካሞች ለመስጠት ያለው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
በመዲናዋ ለሚከናወን አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ነዋሪው ጥሪ በተደረገበት ጊዜ ሁሉ ከፍተኛ ተሳትፎ እያሳየ ነው። በጽዳት ዘመቻ ላይም እንዲሁ
በተመሳሳይ ድርሻውን እያበረከተ ነው። ስለዚህም ሁሉም ኅብረተሰብ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከልቡ ተቀብሎ እየተሳተፈበት ይገኛል።
አዲስዘመን፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሠፋ መጥቷል፤ በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ?
አቶ አብረሓም፡– እንደተባለውም የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠናቸውም በሚያሳትፉት የሕዝብ መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እምርታ አሳይተዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ 14 ፕሮግራሞችና 18 መርሃግብሮች ናቸው በመተግበር ላይ የሚገኙት። አንዳንዶቹ የቆዩ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ አዳዲሶች ናቸው።
ለምሳሌ በ2013 በጀት አመት በሕፃናት ላይ የተጀመረው የበጎፈቃድ አገልግሎት በአዲስነቱ ይጠቀሳል። ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ለደረሱ ተማሪዎች አጋዥ(ስፖንሰር)በማፈላለግ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ እንዲታገዙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ለ171 ሕፃናት ድጋፍ ማግኘት የሚያስችል አቅም መፍጠር ተችሏል። በጎፈቃደኛ ተሳታፊዎቹም ባለሀብቶች ናቸው። በቅርቡ ደግሞ ለ100 ሕፃናት ሰዎች በተመሳሳይ ደጋፍ የሚያደርጉ ተገኝተዋል። ስለዚህም የበጎ ፈቃድ ሥራ በየአመቱ አዳዲስ ፕሮግራሞችን እያካተተና አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ይገኛል።
አዲስዘመን፡-በአሁኑ ጊዜ በጎ ሥራ በግለሰቦችና በግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ነው፤ እዚህ ጋ የመንግሥት ሚና ምንድን ነው?
አቶ አብረሓም፡- መንግሥት የማስተባበር ሚና ነው እየተወጣ ያለው። የበጎ ሥራ አገልግሎትን በዋናነት መሥራት ያለበት ወይንም ይዞ መቀጠል ያለበት ማኅበረሰቡ ነው። ለምሳሌ በከተማ አሰተዳደሩ ማዕድ የማጋራት መርሃግብር ይከናወናል። የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው አመት ብቻ ከ860ሺ በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ማዕድ አጋርቷል። በዚህ መርሃግብር ቢያንስ ለአንድ ሰው ለሦስት ወር የሚሆን ፍጆታ ወይንም አስቤዛ የሚሆን ነው የሚያበረከተው።
መርሃግብሩ የሚተገበረው በመስፈርት ወይንም በስታዳርድ ነው። መርሃግብሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ከ14ሺ900 የሚሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎችን አስተሳስረናል። አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው በሚል መርሃግብር ነው እንዲተሳሰር የተደረገው። ይሄ የማስተሳሰር መርሃግብር አንድ ሰው አጠገቡ ያለውን ሰው ወይንም ቤተሰብ ያለበትን ችግር ያውቃልና እንደፍላጎቱ ድጋፍ ያደርጋል። የጤና ሊሆን ይችላል። ወይንም ሌላ ችግር። ያንን ክፍተት አይቶ መሙላት ማለት ነው። በእንዲህ ያለው የማስተሳሰር መርሃግብር ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይቻላል።
በጎረቤቱና በአካባቢው የሚያየውን የተቸገረ ሰው እንዲሁም የሀገር ባለውለታን መርዳትና መተጋገዝ የኢትዮጵያ እሴት ነው። ነገር ግን በተለያየ መንገድ በመዳከሙ እንደገና ማነቃቃትና ማስተሳሰር ያስፈልጋል። በተፈጠረው የብሎክ አደረጃጀት ማኅበረሰቡ እርስበርሱ እንዲረዳዳ ማድረግ እንደሚያስፈለግ በመታመኑ ነው የከተማ አስተዳደሩ ይህን አሠራር ተከትሎ እየሠራ የሚገኘው። በአሁኑ ጊዜም በተደራጀው በእያንዳንዱ ብሎክ ስምንት ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥም በሕዝብ የተመረጡ 39ሺ936 ሰዎች በኮሚቴ ውስጥ እየሠሩ ይገኛሉ።
ከነዚህ ውስጥም 4ሺ992 የበጎፈቃድ ሥራውን የሚመሩ ናቸው። አባላቱ በኅብረተሰብ ውስጥ ግንዛቤ የመፍጠር፣ እርስበርስ የማስተሳሰር፣ ድጋፍ የሚያስፈልገውን ሰው የመለየት ሥራ ይሠራሉ። ይህ ሁሉ ሥራ የሚሠራው ኅብረተሰቡ የበጎፈቃድ ሥራን በራሱ እንዲመራው ለማስቻል ነው።
በቅርቡም በተካሄደው የኅብረተሰብ ተሳትፎ ምክርቤት ከተሳታፊዎች የተገኘው ግብረመልስ የመፍትሔው ባለቤት መሆን ያለበት እራሱ ማኅበረሰቡ እንደሆነ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎትም ይሄው ነው። ማኅበራዊ መስተጋብሩ እያደገ ሲሄድ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች አይዘነጉም። በሌላ በኩል በሰላም በጎ ፈቃድ ላይ እንሠራለን። የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ የሚያስከብሩ 215ሺ የሰላም በጎፈቃደኞች ናቸው በዚህ ወቅት እየተሳተፉ ያሉት። የአካባቢያቸውን ሰላም ነው የሚጠብቁት። ሰላምና ጸጥታን በፖሊስ ብቻ ማስከበር ስለማይቻል የእነዚህ ማኅበረሰብ ክፍሎች እገዛ መተኪያ የሌለው ነው። እነዚህ የሰላም ጓዶች አካባቢያቸው ላይ የተለየ እንቅስቃሴ ሲያገኙ በቀላሉ መለየት ስለሚችሉ ውጤታማ ይሆናሉ። በተደራጀ መንገድ እየተሠራ ያለው የፀጥታ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰላም ሰራዊት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለውጥ እያስገኘ ነው። ይህ ሁሉ ውጤት የተገኘው እራሱ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት መሳተፍ በመቻሉ ነው።
አዲስዘመን፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ምን የታሰበ ነገር አለ?
አቶ አብረሓም፡– የበጎ ፈቃድ ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ እንዳይሆን መንግሥት በየአመቱ ዕቅድ ውስጥ አካቶ እየሠራበት ነው። ከዚህ ባሻገር ፍኖተካርታ ተቀርጾ በማዘጋጃቤታዊ ተቋማት እንደገና ለማቋቋም ምክርቤቱ በአዲስ ሥራ ሲጀምርም የበጎ ፈቃድ ሥራ በአዋጅ ነው ሥልጣንና ተግባር የተሰጠው።
ከዚህ በፊት በዘመቻና ክረምት ወቅት ብቻ ተጠብቆ ሲፈጸም የነበረው የበጎ ፈቃድ ሥራ አሁን አመቱን በሙሉ ነው እየተተገበረ የሚገኘው። ይህ በመሆኑም ባለፈው በጀት አመት በመኖሪያቤት ግንባታ ብቻ 6415 ቤቶች እድሳትና ግንባታ በማከናወን ማስተላለፍ ተችሏል። ይሄ አመት ሙሉ በተከናወነ ሥራ የተገኘ ውጤት ነው። በቁጥር ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ያልነበረ የሕንፃ ግንባታ መከናወኑም ለየት ያደርገዋል።
በበጎ ፈቃድ ሥራ መንደሮችን የቀየረ ሥራ ነው የተሠራው። ከፍተኛ ሀብትና የሰው ኃይል ማሳተፍ የተቻለውም በመንግሥታዊ መዋቅር በመከናወኑ ነው። በተቋም መመራት ከጀመረ ወዲህ ነው 7ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሥራ ላይ ማዋል የተቻለው። መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ መሥራት ከመጀመሩ በፊት በበጎ ሥራ ላይ የሚውለው ሀብት አንድ ቢሊዮን ብር እንኳን አይሞላም ነበር። በተሳታፊዎችም ረገድ በመቶሺዎች የሚቆጠር የበጎፈቃድ ሥራ ነው ሲሠራ የነበረው።
ስለዚህም መንግሥት ኃላፊነቱን ከወሰደ በኋላ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በከፍተኛ ሁኔታ አድገዋል። ዛሬ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ለከተማችን ነዋሪዎች አዲስ አይደሉም። የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤት መገንባት፤ ደም መለገስ፤ ችግኝ መትከል፤ የትራፊክ አገልግሎት መስጠት፤ ተማሪዎችን በትምህርት መደገፍና የመሳሰሉት ዛሬ ባህል ሆነዋል። መንግሥት እንኳን ቢያቆመው ሌላው ዜጋ ያስቀጥለዋል።
ዛሬ ሕዝቡ ባለቤት ሆኗል። ሥራው ከዘመቻነት ወጥቶ እንደ ከተማ ብሎም እንደሀገር ባህል እየሆነ ነው። ከሕዝቡ አልፎ መሪዎቻችንም በጎፈቃደኞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜም ከአምስት ሺ በላይ የሚሆኑ አመራሮች ከደመወዛቸው በማዋጣት ማዕድ ያጋራሉ። አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው የሚለውም በአመራሩ ይተገበራል።
አዲስዘመን፡- የከተማ አስተዳደሩ የበጎፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ለከተማዋ ነዋሪ ነው። ነገር ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ፈልሰው በከተማዋ ለሚኖሩ ወገኖችስ ምን የታሰበ ነገረው አለ?
አቶ አብረሓም፡- ግንባር ቀደም ፈተና ከሚባሉ አንዱ ያልተመጣጠነ የፍልሰት ሁኔታ ነው። በበጎፈቃድ አገልግሎት ውስጥ እየተከናወነ ባለው የመኖሪያቤት እድሳትና ግንባታ ሥራ ተጠቃሚ የሚሆኑት ነዋሪነታቸው የተረጋገጠ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። በዚህ ላይ የቤቶች አስተዳደርም ይሳተፋል። ነዋሪ የሚለው የራሱ መስፈርት ስላለው በዚህ በኩል አሠራሩ ግልጽ ነው። ፈልሰው በከተማዋ ለሚኖሩት ሁሉ ቤት እየሰጡ መቀጠል የሚታሰብ አይደለም። ነገር ግን በምገባ ማዕከላት ውስጥ በሚሰጠው አገልግሎት የራበው ሰው ሁሉ ምግብ እንዲያገኝ ይደረጋል። ከየት መጣህ ሳይባል ሁሉም ምግብ ያገኛል።
አዲስዘመን፡- የበጎፈቃድ ለመስጠት ቃል ከገቡት ጋር ተናብቦ የመሥራቱ ሁኔታስ ምን ይመስላል? በተለይ ባለሀብቶች ቃል በገቡት ልክ እየሠሩ ስለመሆናቸው መከታተያው መንገድ ምንድን ነው?
አቶ አብረሓም፡– በግሌ በዚህ ዘመን አድጓል ብዬ ከማነሳው አንዱ የበጎፈቃድ አገልግሎት ነው። በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ደረጃ በሥራው ውስጥ ቆይቻለሁ። ባለሀብቱም፤ ተቋማትም አጠቃላይ ማኅበረሰቡም የበጎ ፈቃድ ሥራን ለመርዳትና ለመደገፍ ያለው ፍላጎት አድጓል። ችግሮች አይኖሩም ማለት ባይቻልም የተሻለ ነገር እየታየ ነው። በአሁኑ ወቅት የጤና ተቋማት በነፃ ሕክምና ለመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። ባለሀብቱም አሳማኝ ነገር እስካገኘ ድረስ የበጎ ፍቃድ ሥራ ለመደገፍ ወደ ኋላ አይልም። በጎፈቃድ የውዴታ ግዴታ ተደርጎ ተወስዷል።
አዲስዘመን፡- የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ለሌብነትና ለብልሹ አሠራር እንዳይጋለጥ የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ይመስላል ?
አቶ አብረሓም፡- እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ካሉ በአሠራር ነው የሚፈታው። እርምጃ በመውሰድ ጭምር ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህ ረገድ ግን ጎልቶ የሚገለጽ ችግር በእኛ በኩል እስካሁን አላገኘንም።
አዲስዘመን፡- እስካሁን በመጣችሁበት ሂደት ያጋጠሟችሁ ተግዳሮቶች ካሉ ቢገልጹልን?
አቶ አብረሓም፡– በማኅበረሰቡ ውስጥ የመጣው አስተሳሰብና ተሳትፎ በጠንካራ ጎን ይወሰዳል። በተግዳሮት ከምናነሳው አንዱ በፖሊሲ አለመደገፉ ነው። ፖሊሲ አቅም ስለሚሆን ወደተግባር የሚገባበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ ነው። ለምሳሌ አንድ በጎፈቃደኛ ጉዳት ቢደርስበት፣ እርሱ በጎፈቃድ በመስጠቱ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ ምን ቅድሚያ ማግኘት አለበት የሚለው በፖሊሲ ነው የሚፈታው። ስለዚህ ፖሊሲ አለመኖሩ እንደተግዳሮት የሚጠቀስ ነው።
አዲስዘመን፡- በአጠቃላይ እንደ ሀገር ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምን አገኘን ?
አቶ አብረሓም፡– የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ሀገር የሚሰጠው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው። የእርስበርሱ መስተጋብር የተጠናከረ ማኅበረሰብ በመፍጠር፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረለትና ሰላማዊና የተረጋጋ ማኅበረሰብ እንዲኖር ያስችላል። በተለይም እየላላ የመጣውን ማኅበራዊ መስተጋበብር በማጠናከር፤ የተረሱ እሴቶችን መልሶ በማነቃቃት በሀብት እጥረት ምክንያት ሳይተገበሩ የቆዩ ሥራዎችን እንዲሠሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅም የፖሊስ አጋዥ ኃይል ሆኗል። እና እንደሀገር ከዚህ በላይ ጥቅም የለም። በፖለቲካም ቢሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተረጋጋ ሰላም መፍጠር የተቻለው በበጎፈቃድ ሥራ ጭምር በተሠራው ሥራ ነው።
አዲስዘመን፡- በመጨረሻ መልዕክት እንዲያ ስተላልፉ ዕድል ልስጥዎት
አቶ አብረሓም፡-የበጎፈቃድ አገልግሎት ሥራ የሚያደክምና የሚያለፋ ሥራ ነው፤ ግን ጠንክሮ ከመሥራት ውጪ አማራጭ የለም። ሁሉም ኅብረተሰብ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ። በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በሀሳብ በበጎፈቃድ እየተሳተፉ ያሉት ምስጋና ይገባቸዋል።
አዲስዘመን፡- ለሰጡን አስተያየት በአንባ ቢያን ስም አመሰግናለሁ።
አቶ አብረሓም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2015