የራሽያ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ይጎልብት፤

 ከውጭ ንግድ ከምታገኘው የምንዛሬ ገቢ እስከ 70 በመቶ ወይም እስከ 3 ቢሊየን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ለምታውል፤ ለማዳበሪያ ግዥ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ለምታወጣ፤ ለእዳ ክፍያ 126 ቢሊየን ብር ላቀደች፤ በዓለማቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ ተገቢውን ቦታዋን ለማግኘት ለምትጥር ፤ ወደ 120 ሚሊየን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ላላት፤ በዓለማችን ወሳኝ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለው በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ትልቅ ሚና ለምትጫወት፤ ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ የቀጥታ ኢንቨስትመንትን አብዝታ ለምትሻ ሀገር ፤ የትኛውንም ዕድል አሟጦ የመጠቀም ኃላፊነት አለበት።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያደላ ነው። ግንኙነቱ ከራሽያ ይሁን ከቻይና አልያም ከአሜሪካ ይሁን ከምዕራባውያን ወይም ከሌሎች ሀገራትና ተቋማት ዋና ማጠንጠኛው ይህን ሀገራዊ ግብ ማሳካት ነው። ሀገራችን ከራሽያ ጋር ያላት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይሄን ብቻ ታሳቢ ያደረገ አይደለም። በውስጡ ውለታን ያለመርሳት ቃል ኪዳን አለበት። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምዕራባውያን ዓይንሽን ለአፈር ባሏት ጊዜ፤ አበቃላት፣ አከተመላት በተባለች ጊዜ ራሽያ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ብላ ከጎኗ አልተለየችም።

የሲያድ ባሬ ወይም ዚያድ ባሬ ጦር ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በሚል የቀን ቅዠት ሀገራችን ወሮ እስከ መሐል ሀገር በገሰገሰበት፤ አሜሪካ የገዛነውን የጦር መሣሪያ ለሶማሊያ ወግና በከለከለችን ጊዜ ሶቭየት ሕብረት ከጎናችን ቆማ ሉዓላዊነታችን አስከብራለች። በብድር የሀገራችን ጀርባ በጎበጠበት ጊዜ ዕዳ በመሰረዝ ፋታ እንድታገኝ አድርጋለች። ስለ ራሽያ ከተነሳ አይቀር በዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ኃይል እንድትሆን ያበቋትን ነጥቦችን በአለፍ ገደም ከማንሳቴ በፊት ራሽያን በአጭሩ እንተዋወቅ።

የስላቪክ ሕዝብ መኖሪያ መሆኗን ለመግለጽ እናት ሀገር ራሽያ ሲሏት ኦፊሴላዊ መጠሪያዋ ግን የራሽያ ፌደሬሽን ነው። ኃያልነቷንና የግዛቷን ስፋት ወይም ኢምፓየርነቷንና ንጉሳዊ የነበረውን አገዛዝ ለማስታወስ ደግሞ የ”ዛሮቹ” ምድር ይሏታል። ጥንካሬዋን፣ አልበገር ባይነቷንና ጉልበቷን ለማሳየት ደግሞ “ድቡ” ወይም “The Bear” ፤ የሶቭየት ሕብረትን ግዛት ለማስታወስ ደግሞ ቀዩ ኢምፓየር ፤ የቤዛንታይን ግዛትና የኮንስታንቲኖፕል ባህልና መንፈሳዊ ወራሽ መሆኗን ለመግለጽ፣ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ መናኸሪያ መሆኗን ለማመልከት ደግሞ “3ኛዋ ሮም”ሲሉ ያሞካሿታል።

በእነሱ በረዷማ ክረምት ፀሐይ ስለማትወጣ የሚፈጠረውን ተፈጥሯዊ ትንግርት ለመግለጽ “ነጩ ጨለማ” ወይም “The white nights” ይሏታል። ከእነዚህ ቅጽል ስሞች ጀርባ በየፈርጅ ፈርጁ ጥንታዊነት አለ፣ ስልጣኔ አለ፣ ዘመናዊነት አለ፣ ታሪካዊነት አለ፣ ኃያልነት አለ፣ ሉዓላዊነት አለ፣ የደለበ ባህል ወዘተረፈ አለ። በዚህ የዳጎሰ ስንክሳር የፊትና የኋላ ሽፋን ገጽ ደግሞ እንደ ቅደም ተከተላቸው የቭላድሚር ፑቲንና የነጩ ድብ ምስለ አለ። ሁለቱም የዛሬይቱ ራሽያ ገጾች ናቸው። የጀግንነት፣ የጽናትና የኃያልነት ተምሳሌት ገጾች።

ራሽያ በያዘችው ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ፣ ወታደራዊ አቅም እና ታሪካዊ ተጽዕኖ በዓለማቀፍ ግንኙነትም ሆነ ዲፕሎማሲ የማይተካ ሚና አላት። ራሽያ ዛሬ  ለምትገኝበት ኃያልነት ካበቋት ምክንያቶች ቀዳሚው ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታዋ ነው። ራሽያ በዓለማችን ሁለት አህጉራትን ማለትም አውሮፓንና እስያን የምታካልል እጅግ ግዙፍ ሀገር ናት። ሰፊ ምድር፣ ረጅም ወሰን፣ ከዋና ዋና የውሃ አካላት ጋር ማለትም ከአርክቲክ ውቅያኖስና ከጥቁር ባሕር የሚያገናኝ አቀማመጥ ያላት መሆኗ የገዘፈ ጅኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር አድርጓታል። በአጎራባች ሀገራትና በቀጣናው ከፍ ሲልም በዓለማቀፍ ጉዳዮች ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጓታል።

ዛሬ ለምትገኝበት ዓለማቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያበቃት ሌላው ምክንያት የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል መሆኗ ነው። ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት ሀገራት ወይም ቋሚ አባላት አንዷ መሆኗ በዓለማቀፍ ውሳኔዎች ተጽዕኖዋን እንድታሳርፍ አስችሏታል። ለበረታው ዓለማቀፍ ተጽዕኖዋ ሶስተኛው ምክንያት በዓለማችን ቀዳሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቀች ሀገር መሆኗ ነው። በዓለማቀፍ የደህንነትና የጸጥታ ጉዳዮች ወሳኝ ሚና እንድትጫወት ከማስቻሉ ባሻገር በዲፕሎማሲያዊ ድርድርና በስትራቴጂካዊ አጋርነት የታፈረችና የተከበረች ሀገር አድርጓታል።

በዓለማችን ቀዳሚ ከሆኑ ግዙፍ የነዳጅ፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ የዘይትና የሌሎች የኃይል ምንጮች ባለቤት ከሆኑ ሀገራት አንዷ መሆኗ ኢኮኖሚዋን ከማፈርጠም አልፎ በኢነርጂ ዲፕሎማሲው ተደማጭ አድርጓታል። በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ ኢነርጂ ለጎረቤቶቿና ለአውሮፓ ማቅረቧ ግንኙነቷን ጠንካራ አድርጎት ቆይቷል። ምንም እንኳ ከዩክሬን ወረራ በኋላ ሁኔታዎች አዲስ መልክ እየያዙ ቢመጡም በኢነርጂ ዲፕሎማሲው ዛሬም ከእነ ሳውዲ አረቢያ ባልተናነሰ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት። በቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት አባል የነበሩ ሀገራት ላይ ያላት ተደማጭነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት፤ ወታደራዊ ተሳትፎዋ፣ የሳይበር ደህንነትና መረጃ እንዲሁም ዓለማቀፍ ትብብር ላይ ከፍ ያለ ድርሻ እንዲኖራት አድርጓል።

ሆኖም ራሽያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም እንደ ክፉ የጎን ውጋት ቀስፎ ይዟታል። በአስር ሺዎች የሚቆጠር ማዕቀብ አዥጎድጉዶባታል። በውጭ ሀገራት ባንኮች የሚገኘውን ከ300 ቢሊየን ዶላር በላይ ሀብቷን አግዶ ለዩክሬን ስለመስጠት መላ እየፈለገ ነው። የራሽያ ቢሊየነሮች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል። የራሽያ ነዳጅና ጋዝ ላይ የዋጋ ጣራ አስቀምጧል። ከዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ አግልሏታል። ለዩክሬን በብዙ ቢሊየን ዶላር የሚገመት የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረገ ነው። በሳታላይት የታገዘ ወታደራዊ መረጃ እያቀበለ ነው። በአጠቃላይ ራሽያም ሆነች ፑቲን እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዲፕሎማሲያዊ ባይተዋርነት ላይ ናቸው።

ከብዙ ዓለማቀፍ መድረክ ተገልለዋል። ከዩክሬን ወረራ በኋላ ወደ ራሽያ ያቀኑ የሀገራት መሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። በዚያ ሰሞን በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ ራሽያ ጉባኤ የ49 ሀገራት ተወካዮች የተሳተፉበት ሲሆን ከተሳታፊዎች መካከልም የ17 ሀገራት ጠቅላይ ሚንስትሮችና ፕሬዚዳንቶች ናቸው። በ2019 ተካሂዶ በነበረው 1ኛው የአፍሪካ ራሽያ ጉባኤ ግን ተገኝተው የነበሩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች 43 ነበሩ። በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በራሽያ ላይ በተላለፉ አምስት ውሳኔዎች 19 የአፍሪካ ሀገራት እነ አሜሪካን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።

በአጠቃላይ በራሽያ ላይ በተሰጡ ድምጾች ሀገራችንን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት 52 በመቶ ድምጽ ተዓቅቦ አድርገዋል። ወይም በራሽያ ላይ ድምጽ በሚሰጥበት ቀን ሳይገኙ ቀርተዋል። ይህ ከራሽያ ጎንም ሆነ በተጻራሪው መቆም ምን ያህል ፈታኝ ዲፕሎማሲያዊ ውሳኔ እንደሚጠይቅ አንድ ማሳያ ነው። ሆኖም ራሽያም የዋዛ አይደለችም። በዓለማችን የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ተከትሎ የተከሰተው የኑሮ ውድነት በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ የበረታ ስለሆነ፤ ይሄን አጋጣሚ ተጽዕኖዋን ለማሳረፍ እየተጠቀመችበት ይገኛል።

ባለፈው አመት በቱርክ አደራዳሪነት ዩክሬን በጥቁር ባሕር በኩል ስንዴን ለውጭ ገበያ እንድታቀርብ በመፈቀዱ በዓለማቀፍ ገበያ የስንዴ ዋጋ 14 በመቶ ቀንሶ ነበር። ሰሞኑን ደግሞ ራሽያ ከዚህ ስምምነት መውጣቷንና የዩክሬንን የስንዴ መጋዝኖች ለጥቃቷ ኢላማ ማድረጓን ተከትሎ የስንዴ ዋጋ እንደገና እንዳያሻቅብ ተሰግቷል። ዩክሬንም ለአፍሪካ የረዳሁትን ስንዴ በጥቁር ባሕር በኩል እንዳላስወጣ ራሽያ ከለከለችኝ እያለች ማሳጣት ጀምራለች። ራሽያ ደግሞ ሰሞኑን በተካሄደው የራሽያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ዩክሬን ለአፍሪካ ትልከው የነበረውን ስንዴ እሷ በነጻና በተመጣጣኝ ዋጋ እንደምታቀርብ ፕሬዚዳንት ፑቲን ቃል ገብተዋል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን የጥቁር ባሕር እህል ስምምነትን ላልተገባ ጥቅም በማዋል “እፍረተ ቢስ” ድርጊት ፈጽመዋል በማለት የወቀሱ ሲሆን ለአፍሪካ ነፃ እህል ለማቅረብ ቃል ገብተዋል። በሀገራቸው እና በአህጉሪቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በ2022 ከደረሰበት የ18 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያድግ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። በሴንት ፒተርስበርግ ከሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በፊት በሰጡት መግለጫ፣ አፍሪካ በቡድን 20 እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ከጥቁር ባሕር የእህል ስምምነት መውጣታቸውን አስመልከተው በሰጡት አስተያየት፣ “ምዕራባውያን ስምምነቱን የአሜሪካ እና የአውሮፓ የንግድ ድርጅቶችን ለማበልጸግ ያለ እፍረት ጥቅም ላይ አውለውታል” በማለት ተችተዋል። አፍሪካን ቢዝነስ እንደዘገበው ከዩክሬን የሚላከው እህል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች እንጂ ለአፍሪካ እና እህሉ ለሚያስፈልጋቸው ሌሎች ሀገሮች እምብዛም እንደማይሄድ ተናግረዋል።

በተጨማሪም እህል እና ማዳበሪያ ወደ ታዳጊ ሀገራት ለመላክ ሩሲያን ከቅጣት ነፃ ከማድረግ ጋር ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መካከል አንዳቸውም ስላልተፈጸሙ፣ የስምምነቱ ሰብዓዊ ዓላማ በዚህ ምክንያት ከሽፏል ብለዋል። ሩሲያ ለአፍሪካ የምግብ አቅርቦት ሁሌም “ከፍተኛ ትኩረት” እንደምታደርግ፣ በ2022 ብቻ 11.5 ሚሊየን ቶን እህል ወደ አህጉሪቱ እንደላከች፣ በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ ደግሞ ከማዕቀብ ጋር እየታገለች ወደ 10 ሚሊየን ቶን የሚጠጋ ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ እህል እንደላከች ገልጸዋል።” በሽያጭም ሆነ በነፃ የዩክሬይንን እህልን ለመተካት ሀገራችን ብቃት ያላት መሆኗን ማረጋገጫ መስጠት እፈልጋለሁ፤ በተለይም በዚህ ዓመት ከፍተኛ ምርት ስለምንጠብቅ ይህን እናሳካለን ብለዋል ፕሬዚዳንት ፑቲን።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የምዕራባዊያን ማዕቀብ ሞስኮ እህሏን እና ማዳበሪያዋን ወደ ውጭ ለመላክ አስቸጋሪ ያደረገባት ቢሆንም፤ ኤርትራን ጨምሮ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሺ እስከ 50 ሺ ቶን እህል በነጻ እንደምትሰጥ አስታውቃለች። በሚቀጥሉት ከ3 እስከ 4 ወራት ውስጥ ለቡርኪናፋሶ፣ ዚምባብዌ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ኤርትራ ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሺ እስከ 50 ሺ ቶን እህል ለማቅረብ ዝግጁ እንሆናለን ብለዋል።

ሩሲያ ወደ አፍሪካ የምትልከውን የነዳጅ መጠን እንደምትጨምር፤ በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን በ2023 የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ለአህጉሪቱ የሚቀርቡ የነዳጅ ምርት በሦስት እጥፍ ማደጉን ገልጸዋል። የሩሲያ ኩባንያዎች ለአፍሪካ የኃይል አቅርቦት የሚውሉ የሎጂስቲክስ እና የፋይናንሽያል መሠረተ ልማቶችን እያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም ለኃይል አቅርቦቱ መሻሻል አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሞስኮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አፍሪካ የላከቻቸው የፔትሮሊየም ምርቶች እና የተፈጥሮ ጋዝ በ2.6 እጥፍ ጨምሯል ሲሉ ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል። እንደ አርቲ ዘገባ በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራትም የነዳጅ ምርቶች አቅርቦት በሦስት እጥፍ አድጎ ስምንት ሚሊዮን ቶን መድረሱ ተገልጿል። ለአፍሪካ ለልማት ሥራዎች የሚውል ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምትመድብ፤ ለአፍሪካ ሀገራት የ23 ቢሊየን ዶላር የእዳ ስረዛ ማድረጓን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቀዋል።

በሴንት ቢተርስበርግ በተካሄደው 2ኛ የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው ሀገራቸው ለአፍሪካ የእዳ ስረዛ ማድረጓን የገለጹት። በጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግርም የአፍሪካ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ሚና እያደገ መጥቷል ማለታቸውን አርቲ ዘግቧል። “የምዕራባዊያን ሀገራት ተጽዕኖ በተቃራኒው እየቀነሰ መጥቷል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “አፍሪካ አዲስ የኃይል ማዕከል እየሆነች ነው” ሲሉም አክለዋል።

ይሁንና በአፍሪካ አሁንም የቅኝ ግዛት አመለካከት አልተወገደም የሚሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፤ ይህ አመለካከት በቀድሞ ቅኝ ገዢ ሀገራት በግልጽ ይንጸባረቃልም ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር የበለጠ ተቀራርባ መሥራት እንደምትፈልግ እና የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱ እያደገ ይሄዳል። ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ የጋራ ጥቅምን መሠረት ባደረገ መንገድ እንዲመራ ሩሲያ እና አፍሪካ የየራሳቸውን ኃላፊነቱ መወጣት እንዳለባቸው፤ ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት በዶላር መገበያየት እንደማትፈልግም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ሻሎም ! አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *