የሀገር ሕልውና ስጋት የሆነውን ሙስና ለመከላከል

  ሙስና ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው። በመንግሥት ሌቦችና ሕዝቡ ውስጥ በተወሸቁ ዘራፊዎች ትብብር የሚፈጸመው ይህ አስከፊ ወንጀል፤ ዜጎችን እርቃን የሚያስቀር፣ጥቂቶችን የሚያበለፅግ፣ የመንግ ሥትን ተዓማኒነት የሚሸረሽርና ሕዝብን የሚያማቅቅ አደገኛ ችግር ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙስና ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ ዓለማችን በየዓመቱ በሙስና ወንጀል ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ታጣለች። ችግሩ ጎልቶ ከሚታይባቸው አህጉራት አንዷ ደግሞ ሕዝቦቿ በድህነትና በኋላ ቀርነት የሚማቅቁባት አፍሪካ ነች።

በቅርቡ ዴይሊ ኒውስ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ አፍሪካ ከዓለማችን በሙስና ክፉኛ ከተጎዱ አህጉራት መካከል ቀዳሚ ናት። አህጉሪቱ በየዓመቱ 140 ቢሊየን ዶላር በሙስና ታጣለች፤ 75 ሚሊዮን ሰዎችም ለተለያዩ ፍላጎታቸው መከናወን ጉቦ ይከፍላሉ።

በተመሳሳይ መልኩ የሙስና ችግር በኢትዮጵያም ትልቅ ሀገራዊ ችግር ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። ሀገሪቱም በየዓመቱ ቢሊዮኖችን እንደምታጣም መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ ከባለፉት 20 ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የሙስና ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ እየተንሰራፋ እንደመጣ ይታመናል።

በጊዜውም በሀገራችን የሙስናና ተዋናዮቹ ጉዳይ ክብደት እያጣ፣ ተግባሩም ከመጥፎ አተያይ ወደ መልካምነት እየተለወጠ፤ ሙስናና ተዋናዮቹ የሕዝብና የሀገር ሃብትን ዘርፈው ቅንጡ መንደሮችን ገንብተው ሲኖሩ ታዝበናል። መንግሥትም እንደ ሀገር የተንሰራፋውን ሙስና ለመከላከልና በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች የሚያደ ርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን እስከ መቋቋም ደርሳ ነበር።

ይህ በሆነበት ዓመት መንግሥት በሀገሪቷ ሙስና እና ሙሰኝነት ለመዋጋት ብርቱ ዘመቻ ላይ ነበር። እያስመዘገበ ስለመሆኑም ተደጋግሞ ሲገለጽ ነበር። እውነታ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ ተንሠራፍቶ የሀገሪቱ ብሔራዊ ስጋት የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱን መንግሥትም እራሱ ያመነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እውነታው ከሁሉም በላይ ‘ሙስናን እንዋጋ’ የሚል አፋዊ መፈክር በራሱ ችግሩን መቅረፍ እንደማይችል ተጨባጭ ተሞክሮ ሆኖ አልፏል።

በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት አካሄዱ በተጨባጭ ችግሩን የመዋጋት ቁርጠኝነት የተስተዋለበት ባለመሆኑ፤ የሙስና ወንጀል ተዋናይ የሆኑ የመንግሥት ሹመኞች እና ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ በማድረግ የመቀጣጫ ርምጃዎችን መውሰድ ባለመቻሉ ሁሉም ነገር ከመፈክር ያለፈ ሀገራዊ ተጠቃሚነት ሳያመጣ ቀርቷል።

የሙስና ወንጀል እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም፤ በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ቀጥሎ የሀገር ደህንነት ስጋት መሆኑ በመንግሥት ይፋ ሆኗል። የችግሩ መጠን በተለይም ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን ፈተና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መንግሥት ቀይ መስመር ያለውን ሌብነት ሙሰኞች ቀይ ምንጣፍ በማድረግ ሲረማመዱበት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸው ይታወሳል።

በሀገራችን የሚስተዋለው ሙሰኝነትም በዋናነት በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በፋይናንስና ግዥ፣ በመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት ዘርፎች ላይ የተንሰራፋ ስለመሆኑም በስፋት ተነግሯል። በፀጥታና ፍትህ ተቋማት ዘንድም በተመሳሳይ ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም በአቋራጭ የመበልፀግ የሙስና ወንጀሎች ይስተዋላሉ።

በኢትዮጵያ ሙስና መሠረቱን ጥሎ አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ እንደ ልማድ እየተቆጠረ መጥቶ ብሔራዊ ስጋት መሆኑ በመንግሥት ጭምር የታመነበት ሀገራዊ ችግር ነው። ሀገሪቱም በዚህ ችግር ፈተና ውስጥ ስለመኖራም እያንዳንዱ ዜጋ በእለት ተእለት ሕይወት የሚታዘበው ነው።

በሀገሪቱ በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ያለምንም ምልጃ አገልግሎት ማግኘት ፈተና እየሆነ መጥቷል። የችግሩ አደገኝነት መገለጫው ደግሞ ድርጊት እንደ ብልህነት፣ እንደ ብልጠት መታየቱ ነው። ይህም የመከላከል ሥራውን የበለጠ ፈታኝ እያደረገው መጥቷል።

በርግጥም ስር የሰደደ፣ ሕዝብ ያማረረና ለሀገር የደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመግታት፣ ለመከላከል በመንግሥት በኩል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑ አይካድም። በዘርፉ ያለው ችግር ለመግታት ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱም ለዚህ ማሳያ ነው።

ከዚህ አንጻር መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተወሰደ ያለው ርምጃ መልካም ጅምር ቢሆንም፤ መሬት ላይ ያለው ሃቅ ግን እለት እለት እየገዘፈ ተግባርና ተግባሪዎቹን የመፋለሙ ጥረት ከዘመቻ ያለፈ ስለመሆኑ በዜጎች ዘንድ ጥርጣሬ እየፈጠረ ነው። በተለይ የመንግሥትን ሥልጣንና ወንበርን መከታ አድርገው የሚሰርቁ ሙሰኞች ላይ ቆራጥ ርምጃ ስለመወሰዱ በቂ ማስረጃ ለሕዝቡ በየጊዜው አለመሰጠቱ የሕዝቡን ጥርጣሬ ከፍ እንዲል እያደረገው ይገኛል።

ችግሩ የሀገር ሕልውና ስጋት ከመሆን ጎን ለጎን የዜጎችን የማህበራዊ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት፤ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመተ ማመንን የሚፈጥር ነው። ይህ አለመተማመን ደግሞ መንግሥት በጀመረው ድህነትን ታሪክ የማድረግ የልማት ጉዞ ላይ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ አይቀርም።

በአጠቃላይ የፀረ-ሙስና ትግሉ የሀገር ሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ የሙስና ድርጊትን ማውገዝ፤ መከላከልና ማጋለጥ የሁሉንም ኅብረተሰብ ኃላፊነት እንዲሁም የጋራ ትግልንም የሚጠይቅ ነው። ለዚህም ከሁሉም በላይ በመንግሥት የተቋቋመው የፀረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የጀመራቸውን ሥራዎች ከሕዝቡ ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል። የመገናኛ ብዙኃንም የፀረ-ሙስና ትግሉን በማገዝ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

 ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *