ስለ ሰንደቅ ዓላማ ትርጉም ስናወራ ሰንደቅ ዓላማ ማለት በዘንግ ወይም በመስቀያ ያለ ሰንደቅ ማለት ነው። መስቀያው ዓላማ ሲባል የሀገር ዓርማ የሆነው ባለቀለሙ መለያ ምልክት ደግሞ ሰንደቅ ይባላል። የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላኛው ትርጉሙ ደግሞ ሰንደቅ ዓላማ የሚባለው ባለቀለሙ የመለያ ምልክት ብቻ እንጂ መስቀያውን አይጨምርም ሰንደቅ ዓላማ መባሉም ሰንደቁ የራሱ የሆነ ዓላማ እንዳለው ለማመልከት ነው የሚሉም አሉ።
ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ደግሞ ብዙዎች ብዙ መስዋዕትነትን ስለመክፈላቸውም ነጋሪ የማያሻው ሃቅ ነው። በነገራችን ላይ ሠራተኛው በሥራው፤ ባለሥልጣኑም ሀገር በማገልገል ሙያው ሌላውም ሌላውም ብቻ በተቻለው መጠን ሀገሩን ለመጠበቅ ባንዲራው ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ለማድረግ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ባንዲራ የሀገር ፍቅርና ክብር ሲነሳ ከፍ ብለው የሚነሱት አትሌቶቻችን ናቸው። አትሌቶቻችን ለውድድር በሄዱባቸው ሀገራት ሁሉ የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አደርገው ለማውለብለብ ላቅ ያለ ሚናን ከመጫወታቸውም በላይ እነሱም ልክ አንደ ባንዲራው ከፍ ብለው የሚታዩ የሀገር መገለጫዎችም ናቸው። ይህ ተግባራቸው ደግሞ የሀገር ባለውለታዎች ያደርጋቸዋል።
እኛም ለሀገር ባለውለታ የሆኑ ሰዎቻችንን በምንዘክርበት በዚህ አምዳችን ላይ ለዛሬ ባለውለታነቷን ልንዘክርላት ያሰብናት እንስት አትሌት አለች። ለአትሌት አበበ ቢቂላ ትልቅ ፍቅር እንዳላት የምትናገረው አትሌት ፋጡማ ሮባ የዛሬ የአምዳችን ባለውለታም ናት።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋጡማ ሮባ በአትላንታ ኦሊምፒክ የሴቶች የማራቶን ውድድር በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ማድረግና በሴቶች የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድርን ያሸነፈች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አትሌት መሆኗ ደግሞ እንድንመርጣት አስገድዶናል።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋጡማ ሮባ በአትላንታ ኦሊምፒክ የሴቶች የማራቶን ውድድር በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ማድረግ ከመቻሏም በላይ ሴቶች በኦሊምፒክ በተለይም ደግሞ በማራቶኑ ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆነው ሲወጡ ያሳየች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ብሎም አፍሪካዊት ናት።
ከዛሬ 2ገ ዓመታት በፊት (ሐምሌ 21 ቀን 1988 ዓ.ም) ባስመዘገበችው አስደናቂና አስደማሚ ብሎም ዓለም ወደ ኢትዮጵያ ዓይኑን እንዲያዞር ያስገደደችበት ጊዜም ነበር።
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋጡማ በወቅቱ ከ51 ሀገራት የተወከሉ 86 አትሌቶች የተካፈሉበትን ውድድር በበላይነት ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በወቅቱም ያስመዘገበችው ሁለት ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከአምስት ሴኮንድ (2፡26፡05) በሆነ ተመዝግቦ ይገኛል።
Faaxumaa Roobaa – The First African Woman to Win a Gold Medal in the Olympic Marathon Race በማለትም ዓለም አድንቋታል። ሰንደቃችንም ከፍ ብሎ ተውለብልቧል።
ፋጡማ ሮባ የመጀመሪያውን የሴቶች ማራቶን ፈር ቀዳጅ ድሏን በሞሮኮ ማራካሽ ነበር የተቀዳጀችው። በወቅቱ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ የነበርን ቢሆንም በተለይም ኦሊምፒክ ከዚያ ደግሞ ማራቶን ከፍ ሲል ደግሞ በሴቶች ዘርፍ ያን ያህል ስም የሚያስጠራ ተግባር ላይ አልነበረንም ነገር ግን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነችው አትሌት ፋጡማ ያልታሰበውን በጣም ጣፋጩን ደል እንድንጎናጸፍ መንገድ ሆናናለችና ባለውለታችን ብንላት አይበዛባትም።
አትሌት ፋጡማ ይህንን አስደማሚ ድል እንድናጣጥም ካደረገችን ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ በሮም ማራቶን አሸናፊ ሆነች። ይህም ሌላው ሰንደቃችንን ከፍ አድርጎ ያሰቀለ ዓለም ወደእኛ እንዲያይ ያስገደደ ክስተት ሆኖ አልፏል። ከሮም አሸናፊነት በኋላም እ.ኤ.አ በ1996 በአትላንታ አሜሪካ በተደረገው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ 2 ሰዓት 26 ደቂቃ 05 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ አንደኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቀቀች።
በወቅቱ ፋጡማን በመከተል ሁለት ደቂቃ ዘግይተው የሩሲያዋ ቫለንቲና ይጎሮቫና ጃፓናዊቷ ዩኩ አርሞሪ 2ኛ እና 3ኛ በመሆን ተከታትለው መግባታቸውን ታሪክ ይነግረናል።
እ.ኤ.አ ከ1997 እስከ 1999 የተካሄዱ የቦስተን ማራቶን ውድድሮችን በተከታታይ ያሸነፈችው ፋጡማ የ’ቦስተኗ ንግሥት’ የሚል ቅጽል ስምም አግኝታበታለች።
ለአትሌት አበበ ቢቂላ ትልቅ ፍቅር እንዳላት የምትናገረው አትሌት ፋጡማ ሮባ «አቤን በጣም እወደዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ። አቤን እኔ ብቻ ሳልሆን መላው ዓለም ያደንቀዋል፤ እኔ ግን ከማድነቅ አልፌ ፈለጉን ለመከተል እየሠራሁ ነው» ስለማለቷ ስለ እሷ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለዓመታት ከሀገርና ከአትሌቲክሱ መድረክ ርቃ የቆችው የኦሊምፒኳ ኮከብ አትሌት ፋጡማ ሮባ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለ ሕይወቷ ስትናገር ፤ «እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ፣ ሁሉሌ ካራ በሚባል ስፍራ ነው የተወለድኩት። ገጠር ውስጥ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የወጣሁት። ኑሮዬና ትምህርቴም እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ ነበር የተከታተልኩት። በገጠር እንዳደጉት ልጆችም ከብቶችን ስጠብቅና ቤተሰብን ስረዳ ስለቆየሁ ቶሎ ትምህርት ቤት አልገባሁም። ትምህርት ቤቱም ከቤተሰቤ ርቆ ስለሚገኝ በደንብ ካደግሁ በኋላ በደርሶ መልስ 14 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዤ እማር ነበር» ስትል አስተዳደጓን አስመልክታ ተናግራ ነበር።
አትሌት ፋጡማ «….. ያደግኩበት ገጠር እንደመሆኑ በአካባቢያችን ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ ስላልነበር ስለአትሌቲክስ የማውቀው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚዘጋጅ የሩጫ ውድድር ላይ ግን ንቁ ተሳታፊ ስለነበርኩ ነጥብ ሁላ ይያዝልኝ ነበር። አስተማሪያችን መሃረብ ይዞልን ‘ማን ቀድሞ ይነካል’ እያለ ያወዳድረን ነበር» በማለት የሩጫ መነሻዋን ትናገራለች።
በወቅቱ አትሌት ፋጡማ ከሴቶችም ሆነ ከወንዶች ጋር ሩጪ ስትባል ሁሉንም ቀድማ አንደኛ የምትወጣ የነበረ ሲሆን ፤ ከዚያ በኋላ ከትምህርት ቤቱ ተመርጣ በወቅቱ አውራጃ ወደሚባለው፣ ከዚያ ደግሞ ክፍለ ሀገር ለሚባለው ውከልና አግኝታ ውድድሯን ማድረግ እንደጀመረችም በዚሁ ቃለ ምልልሷ ላይ ትናገራለች። እንዲህ እንዲህ እያለች ለስፖርቱ ፍቅር እያደረባትና የተሻለ ነገር ሠርታ ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረስ ሀገሯን የማስጠራት ህልም ያደረባት፤ ይህንንም ህልሟ እውን ለማድረግ በቀጥታ አዲስ አበባ ገባች። የተለያዩ የስፖርት ቡድኖች መኖራቸውንም አወቀች።
አዲስ አበባ ለመምጣቷ ዋናው ምክንያት ደግሞ ክፍለ ሀገር በውድድር ላይ እያለች አንድ ሰው ያያታል እሱም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክፍል ውስጥ የነበረ ነበርና ይህችን ልጅ ለቡድናችን ማምጣት አለብን በማለት ሃጂ ቡልቡላ ወደ ሚባል ሰው እንደላካትም በቃለ ምልልሱ ላይ ተናግራለች።
የተላከችበት ሰውም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቡድን እንደሚፈልጋት፣ ትምህርቷን እየተማረች ብትወዳደር ደመወዝም እንደሚከፍሏት ስለነገሯት፤ እሷም ቤተሰቧን ስታማክር ብዙም ደስተኛ ካለመሆናቸውም በላይ ልጃቸውን ብቻዋን ወደከተማ መላክን አልፈለጉም ነበር። ነገር ግን ሃጂን ካዩ በኋላ ፈቀዱላትና ወደህልሟ ወደ አዲስ አበባ መጣች።
«እ.ኤ.አ በ1994 ቤልጂየም ሀገር ነበርኩኝ። እዚያም በአጫጭር ውድድሮች ላይ በመሮጥ ተሳተፍኩኝ።
ቤልጂየም በቆሁበት ወቅት አንድ ማራቶን የምትሮጥ ሴትን በፓሪስ ማራቶን ለምን ካንቺ ጋር አልሮጥም ብዬ ጠየቅኳት። እርሷም ነይ አብረን እንሂድ አለችኝ። ከዚያም በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1994 በተካሄደው የፓሪስ ማራቶን ሳልዘጋጅ ተወዳደርኩ» በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
ውድድሩ ሲጀመር ከሌሎች አትሌቶች ጋር መሮጥ አቃተኝ የምትለው አትሌት ፋጡማ ሁሉም ጥለዋት ሄዱ ፤ ይሁን እንጂ ወደ 35ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ብትደርስባቸውም አብራቸው ግን መቀጠል አልቻለችም፤ በድጋሚ ጥለዋት ሄዱ። በጣም ደክሟት ስለነበር ውሃ ጠጣች። ውሃውም ሆዷን ወጥሮ ያዛት። በወቅቱ ውድድሩን መጨርስ ብትችልም ከነበረው ስቃይ አንጻር ግን ሁለተኛ አልሮጥም ብላ ለራሷ ቃል ገብታ ነበር።
ወደ ሀገር ቤት ስትመለስ ግን በርካታ ብርቅዬ አትሌቶቻችንን በማሰልጠን ከእነሱ እኩል ስማቸው የሚጠራውና የሀገር ባለውለታ የሆኑት አንጋፋው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ማራቶን እንድትሮጥ ጠየቋት። እሷም እምቢ አላለችም፤ ይልቁንም ለመጀመሪያ ጊዜ ያለዝግጅት በሮጠችበት ማራቶን የገጠማትን ችግር እንደትምህርት ወስዳ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን እየወሰደችና ማራቶን እንዴት መሮጥ አለብኝ የሚለውን በሚገባ እየተረዳች ሥልጠናዋን በአግባቡ መውሰድ ቻለች። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አደባባይ ስሟን ማስጠራት የቻለችበትን ወደ ሞሮኮ ሄዳ ማራካሽ ላይ ተወዳድራ አንጸባራቂ ውጤት ያመጣችበትን ውድድር ያደረገችው።
ከሞሮኮ ማራካሽ እስከ ቦስተን
እ.ኤ.አ በ1996 የማራካሽ ማራቶን ላይ ብዙም ሥልጠናና ልምምድ ሳላደርግ ነበር የተሳተፍኩት።
በውድድሩም ‘ቢ ካታጎሪ’ የሚባለውን አምጥቼ ተመለስኩ።
ከሁለት ወር በኋላ በሮም ማራቶን ተወዳድሬ፣ ‘ኤ ካታጎሪ’ የሚባለውን ውጤት አምጥቼ በኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችለኝን ነጥብ አገኘሁ።
በዚሁ ልምምድ አድርጌ በ1996 በተካሄደው የአትላንታ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄድኩኝ። ኦሊምፒክ ትልቅ ውድድር ነው። የአትላንታ ኦሊምፒክ ለእኔ ከተሳተፍኩባቸው ሁሉ ትልቁ ውድድር ነበር በማለት ሁኔታውን ታብራራለች።
«…ለውድድሩ በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቼ ነበር። ግን ፍርሃት በውስጤ ስለነበረ አሸንፋለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም። ካሸነፍኩ በኋላ ግን ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። አሰልጣኞቼም በውድድሩ ታሸንፋለች ብለው አልጠበቁም ነበር።
በኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር ላይ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት መሆኔ በጣም አስደሰተኝ። የሚረሳም አይደለም። ከአትላንታ በኋላ በ1997፣ 98፣ 99 በቦስተን ማራቶን ውድድሮች በተከታታይ ለሦስት ጊዜ አሸንፌያለሁ።
ሩጫ ማቆምና ቤተሰብ
እ.ኤ.አ በ2004 ነበር ሩጫ ያቆመችው። በወቅቱ ልጅ ለመውለድ ብላ ነበር ሩጫ ያቆመችው ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተመለሰችበትም ።
አሁን የሁለት ልጆች እናት ስትሆን የመጀመሪያ ልጇ 15 ዓመቱ ሁለተኛዋ ደግሞ 13 ዓመቷ ነው።
ሩጫ ካቆመች በኋላ ምንም እየሠራች ስላልነበርና ሙሉ ጊዜና ትኩረቷን ለልጆቿ ሰጥታ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እነሱም ስላደጉላት አንዳንድ ሥራዎችን ለመሥራት እያሰበች ስለመሆኑም ትናገራለች።
«የአሁኑን አትሌቲክስ ብዙም ባልከታተልም በርካታ ጠንካራ አትሌቶች እንዳሉ አውቃለሁ። እኛ ስንገባበት የነበረውንም ሰዓት እያሻሻሉ ነው። ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ከተስማሙ እና በደንብ ከሠሩ ከዚህ የበለጠ ነጥብ ማምጣት እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ» ብላለች የዛሬ ባለውለታችን አትሌት ፋጡማ ሮባ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2015