የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት

በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግለው የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፤ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በፖሊሲና አሰራሮች ትግበራ ሂደት ባጋጠሙ እንቅፋቶች ላይ በመነጋገር፣ መፍትሔ ማፈላለግና የማሻሻያ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ ቀዳሚዎቹ ናቸው። ለዚህም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት የሚችልበትን አስቻይ ሁኔታዎች ለመፍጠር በተለያዩ ጊዜያት የምክክር መድረኮችን ሲያዘጋጅ መቆየቱም ይታወሳል።

ላለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የጋራ መድረኩን ማካሄድ ሳይቻል ቢቀርም፤ በቅርቡ ሀገር አቀፍ የመንግሥትና የግል ዘርፍ ተቀራርበው መሥራት የሚችሉበትን ዕድል ለማስፋት እንዲሁም፤ ለችግሮቻቸው መፍትሔ በማፈላለግ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ብሔራዊ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክን (Na­tional Public-Private Dialogue) ማካሄድ ተችሏል።

በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የጋራ ትብብር በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ የቱሪዝም እንዲሁም ኢ-ኮሜርስ (ዲጅታል ኢኮኖሚ) ዘርፎች ውይይት ተደርጎባቸዋል። እነዚህ የትኩረት ዘርፎች የመመረጣቸው ምክንያትም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ብዝሀነትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆናቸው ነው።

በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና ያለው የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ መወጣት የሚችለው ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ሲችል እንደሆነና መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ ተመካክረውና ተቀናጅተው ሲሠሩ ለሀገር ግንባታና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚኖራቸው አበርክቶ የላቀ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በአንድ ሀገር ዕድገት ውስጥ ዋና ዋና የልማት ተዋናዮች መንግሥት፣ ሕዝብና የግል ባለሃብቱ መሆናቸውን የሚጠቅሱት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ ማድረጋቸው እጅግ ጠቃሚና ተገቢ እንደሆነ ነው ያስረዳሉ። ‹‹መንግሥት ሕግ በማውጣት፣ ስትራቴጂ በመንደፍና የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን ለማሳለጥ ይሠራል›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ የግሉ ዘርፍም ይህን ተከትሎ በተለያዩ ዘርፎች ተሳታፊ በመሆኑ በጋራ ተቀናጅተው መሥራታቸው የግድና ወሳኝ ነገር እንደሆነ ነው ያነሱት።

‹‹ሀገራዊ ዕድገት ከኢንቨስትመንት ውጭ አይታሰብም፤ የኢንቨስትመንት ዋናው ምንጭ ደግሞ ባለሃብቱ ወይም የንግዱ ማህበረሰብ ነው›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ መንግሥት ስትራቴጂ ሲነድፍና ሕግ ሲያወጣ ያላስተዋላቸው ክፍተቶች፣ ችግሮችና የተለያዩ እንቅፋቶች ካሉ በተገቢው መንገድ የሚለዩት በግሉ ዘርፍ እንደሆነ አንስተው፤ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር የምክክር መድረክ መፍጠሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎችን ውጤታማና የተሻለ ለማድረግ ይረዳል። ይህም በየጊዜው እየተገናኙ ሊያከናውኑት የሚገባ ነው ብለዋል።

መንግሥትና የግሉ ዘርፍ መደበኛ በሆነ መንገድ በተወሰነ ጊዜ በጋራ ተቀራርበው መወያየት ከቻሉ፤ ችግሮችን በቀላሉ መለየት ያስችላቸዋል። ከዚህም ባለፈ ለተለዩት ችግሮች መፍትሔ እያፈላለጉ መጓዝ ያስችላቸዋል። በዚህም ኢንቨስትመንት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ነው የተናገሩት። እሳቸው እንዳሉት የንግዱ ዘርፍ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ በተለይም ውጤታማ ባልሆኑ እንደግብርና ባሉ ዘርፎች የግሉ ዘርፉ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲችል ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይገባዋል። እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በንግዱ ዘርፍ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት ያስችላል ነው ያሉት።

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅቶ በአጋርነት የመሥራት ተግባር (Public-Private Partnership) በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚታወቅ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ ምንጊዜም ቢሆን መንግሥት እንደ ሕግ አውጪነቱና ስትራቴጂ ነዳፊነቱ የንግዱ ዘርፍ የተሻለ እንዲሆን መሥራት ይጠበቅበታል። ለዚህም በዘርፉ ምን መካተት አለበት በሚል ከግሉ ዘርፍ ጋር መመካከር ዘርፉን ማሳደግና አጠቃላይ ኢኮኖሚው ከዚያ ተጠቅሞ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመዘገብ ማድረግ አስፈላጊና የሚጠበቅ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ‹‹ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነቱ የጋራ የምክክር መድረክ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር መደበኛ በሆነ መንገድ ሲካሄድ አይስተዋልም›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ምክክሩ ዕቅድ ተይዞለት መደበኛ በሆነ መንገድ መካሄድ እንዳለበትና በዚህም ኢኮኖሚው ላይ በሚያሳድረው በጎ ተፅዕኖ ሀገርና ሕዝቡ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ነው ያብራሩት።

በተመሳሳይ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅተው ባለመሥራታቸውና የምክክር መድረክ ባለማካሄዳቸው በተለይም የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማየት አንጻር ብዙ ክፍተት መፈጠሩን ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ የግል ባለሃብቶች የት ላይ ቢሳተፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ፤ መንግሥትም በየትኞቹ ዘርፎች ለተሳተፈ የግሉ ዘርፍ የተሻለ ድጋፍ እንደሚያደርግ መወያየት ሲችሉ በኢንቨስትመንት ውስጥ በተሻለ ሁኔታ የመሳተፍ ዕድል የሚፈጠርላቸው ይሆናል። ይህም የግሉ ዘርፍ ግልጽ በሆነ መንገድ ትርፋማ ሊያደርጋቸው በሚችሉ የኢንቨስትመንትና የንግድ አማራጮች በመሳተፍ እራሳቸውን ጠቅመው ለማህበረሰቡና ለሀገር መትረፍ የሚችሉ እንደሆኑ ተናግረዋል።

‹‹የግል ዘርፉና መንግሥት በጋራ ተቀናጅተው ሲሰሩ የሚገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ የግል ዘርፉ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ምርት ማምረትና ገበያ መፍጠር እንደሚችል አንስተው ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ ማስመዝገብ የሚችሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁንና መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርቦ ካልሠራ እንዲሁም በየጊዜው ምክክር ማድረግ ካልቻለ እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያጣል። ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የንግዱ ዘርፍ የሚቀጭጭ እንደሆነና አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ማካሄድ ካልቻሉ የግሉ ዘርፍ በተሰማራበት ዘርፍ የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘት አይችልም። እንዲሁም አዳዲስ በሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የመሰማራት ዕድልና ፍላጎት አይኖረውም›› የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ ይህም ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝ አይነተኛ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፤ ‹‹ኢንቨስትመንት የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ ኢንቨስትመንት እንዳይቀጭጭ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ ነው፤ ኢንቨስትመንት ቀጨጨ ማለት ኢኮኖሚው ቀጨጨ ነው፤ ኢኮኖሚ ቀጨጨ ማለት ደግሞ ሀገር ቀጨጨ ማለት ነው›› በማለት አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

የንግድ ማህበራት ዘርፍ የተቋቋሙበት ዋና ዓላማ መንግሥትንና የሚወክሉትን የንግዱን ማህበረሰብ ድልድይ ሆኖ ማገናኘት እንደመሆኑ ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶክተር ሞላ፤ የንግድ ማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት ንቁ ሆኖ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። እሳቸው እንዳሉት መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥሮ የግሉን ዘርፍ ማዳመጥ ካልቻለ እነሱ በር በማንኳኳት መነጋገርና መወያየት ይጠበቅባቸዋል። ይህም ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ ተነሳሽነትም የሚጠይቅ ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር የጋራ ምክክር ያደረገባቸው ዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች የኢኮኖሚ ምሰሶ ተብለው ከተለዩት መካከል ግብርና፣ ቱሪዝምና ኢ ኮሜርስ (ዲጅታል ኢኮኖሚ) ሲሆኑ እነዚህ የትኩረት ዘርፎች ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ናቸው። በተለይም ግብርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ያለው ድርሻ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ አንስተዋል። ከ90 በመቶ በላይ የሀገሪቱ የወጪ ንግድ የተመሰረተው በግብርና ዘርፍ ላይ በመሆኑ እንዲሁም ማህበረሰቡን በሰፊው የሚጠቅም እንደመሆኑ አንዱ የትኩረት ዘርፍ ሆኖ መመረጡ ተገቢነት ያለው ነው በማለት አመላክተዋል።

ኢ-ኮሜርስና ቱሪዝምም እንዲሁ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ወሳኝ ጉዳዮች እንደሆኑ ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ ኢ ኮሜርስ ዓለም እየተከተለው ያለና የንግድ እንቅስቃሴውን በእጅጉ ለማሳለጥ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን አስገዳጅ የሆነበት ጊዜ ነው። ይህን ማድረግና ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን መጠቀም ካልተቻለ ተወዳዳሪ መሆን የማይቻል እንደሆነና ወደ ኋላ በማስቀረት ኢኮኖሚውን የሚጎዳ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቱሪዝምን በተመለከተም ቱሪዝም ከግብርናው ቀጥሎ ሃብት በማመንጨት ረገድ ሰፊ ድርሻ ያለውና ብዙ የሚጠበቅበት ዘርፍ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን እስካሁን ባለው ሂደት ሃብቱን በሚፈለገው መጠን መጠቀም እንዳልተቻለ ነው ያነሱት። እሳቸው እንዳሉት፤ ሌሎች ሀገራት የኢትዮጵያን ያህል ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የሆኑ የቱሪስት መስህቦች ቢኖራቸው የት ሊያደርሱት እንደሚችሉ መገመት ቀላል መሆኑን ጠቅሰው፤ የቱሪዝም ዘርፉ ገና ያልተነካና ብዙ ሊሠራበት የሚችል ዘርፍ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

በአጠቃላይ ግብርና፣ ቱሪዝምና ኢ ኮሜርስ ኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በመሆናቸው በእነዚህ የትኩረት ዘርፎች መንግሥት የግሉን ዘርፍ አቅርቦ መወያየትና ምክክር ማድረግ መቻሉ እጅግ የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ እንደሆነ አመላክተዋል። አያይዘውም የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትና የምክክር መድረክ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ አቅጣጫን ለመምራት የሚያስችል ግብዓት የሚገኝበት በመሆኑ የምክክር መድረኩ ብልጭ ድርግም በሚል አካሄድ ሳይሆን፤ በዕቅድ ተይዞ በየጊዜው እየተገመገመ መካሄድ ያለበት እንደሆነ ነው ያስረዱት።

እሳቸው እንዳሉት ከመንግሥት ባለፈ የግል ዘርፉ ተነሳሽነት ኖሮት ምክክርና ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል። በንግዱና በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ አቅጣጫ መጠቆምና መንገድ ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህን ተግባር በቀጣይነት ማካሄድ ሲቻል ኢኮኖሚው ያድጋል። ኢኮኖሚው ሲያድግ ደግሞ አጠቃላይ የሀገሪቱ ነዋሪ በተለያየ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ የሚረጋገጥ እንደሆነ አመላክተዋል።

በተመሳሳይ በንግዱ ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ የግል ባለሃብቶች ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር በቅንጅት ተናበው መሥራት ከቻሉ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያነሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገና ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት፤ የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር በሚፈጥረው ቅንጅት በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመለየት ባሻገር ለችግሮቹ መፍትሔ ማፈላለግ ይቻላል። ‹‹ችግሮችን በተግባር መፈተሽ የሚቻለው መሬት ላይ ባለውና ተጨባጭ በሆነ ጉዳይ ነው። ለዚህም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በማጠናከር ተቀራርበውና ተቀናጅተው መሥራት ይጠይቃቸዋል። ይህም ለሀገር እድገትና ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋልና ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል›› በማለት የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጎላ ሚና ያላቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

‹‹የግሉ ዘርፍ እና መንግሥት ተቀናጅተው መሥራት ሲችሉ፤ በአጭር ጊዜ የሚፈቱና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን በቀላሉ መለየትና ወደ መፍትሔ መሄድ ያስችላቸዋል›› ያሉት አቶ ክቡር ገና፤ በተለይም በንግዱና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከዓመት ዓመት እየተነሱ ነገር ግን መፍትሔ ሳያገኙ ቀርተው ይንከባለሉ የነበሩ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመፈታት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረኩ ወሳኝ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ተቀናጅቶ መሥራት ካልቻለ የንግዱ ዘርፍ ይቀጭጫል። በዛው ልክ ሀገር እንዲሁም መንግሥትን በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፈታት የሚችሉ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ለመፍታት የምክክር መድረኩ ወሳኝ ነው። ከምክክርና ውይይት ባለፈም የግሉ ዘርፍ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት የመንግሥትን በር ማንኳኳት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ላለው ዕድገት የግሉ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ያነሱት ክቡር ገና፤ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ከመንግሥት ጋር የሚደርገው የምክክር መድረክ እጅግ ጠቃሚና መፍትሔ ጠቋሚ እንደሆነ ነው ያስረዱት። ግብርና፣ ቱሪዝምና ኢ ኮሜርስ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ሰፊ ድርሻ በማንሳት ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ከተኪ ምርቶችና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በእነዚህ ዘርፎች የተሰማራው የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት መሥራት ሲችል ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን በተሻለ ደረጃ ማሳለጥ የሚችል እንደሆነ አስረድተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 26/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *