መላ የክርስትና አምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ! ዛሬ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገበት የትንሳኤ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ስርአቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንዲሁም የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን የመልካም ምኞት መግለጫዎችን ሰጥተዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የክልል ርእሳነ መስተዳደሮችና ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትም የመልካም ምኞት መግለጫዎችን አውጥተዋል።
በተለያዩ በዓላት እንደሚደረገው ሁሉ በእዚህ በትንሳኤ በዓልም የመረዳዳት በዓልን አብሮ የማክበር እሴቶች ጎልተው እየታዩ ናቸው። ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና ምንም ገቢ ለሌላቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት ሥራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሠሩም ናቸው፤ በየአብያተ ክርስትያናቱም ምእመናን ተመሳሳይ የድጋፍ መርሀ ግብሮች ያደርጋሉ። ሕብረተሰቡም በየአካባቢው በየተሰማራበት ተቋም ይህንኑ እያደረገ ነው።
ይህ የትንሳኤ በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶች እየተከበረ ሲሆን፣ የእምነቱ ተከታዮች ያለፈውን አብይ ጾም በመጾም፣ በመጸለይና በመመጽወት ጥንካሬያቸውንና ትብብራቸውንም እንዳሳዩ ሁሉ ፣ ይህን የትንሳኤ በዓልም ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ በተጓዳኝ በልዩ ልዩ ባሕላዊ ስርዓቶች በመተሳሰብና መልካምን ሁሉ በማድረግ ያከብሩታል።
የእምነቱ ተከታዮች ባለፈው ዓርብ የስቅለት በዓልን በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እንዳከበሩት ሁሉ፣ የዛሬውን የትንሳኤ በዓልም በሃይማኖታዊና በቆዩ ባሕላዊ ስርዓቶቻቸው እያከበሩት ይገኛሉ። የትንሳዔ በዓልም ትናንት ምሽት በሃያማኖታዊ ሰርዓት ሲከበር አምሽቶ ሌሊት ላይ የክርስቶስ መነሳት በሃይማኖቱ አባቶች ሲገለጽ ምእመናንም ደስታቸውን በመግለጽ በልዩ ልዩ መንገዶች በዓሉን ወደ ማክበር ገብተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር የሚገኘው የየረር በር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤልና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ዋና ጸሀፊ ሊቀ ማዕምራን መልካሙ ውዱን ስለትንሳኤ በዓል ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የአከባበር ሥርዓት ጠይቀናቸዋል። ከ2003 እስከ 2015 ድረስ በአራት አብያተክርስቲያናት በዋና አስተዳደሪነትም ያገለገሉት ሊቀ ማዕምራን መልካሙ ስለ ዛሬው የትንሳኤ በዓል ከመግለጻቸው በፊት ስላለፈው የሕማማት ሳምንትና ስለ ዓርቡ የስቅለት በዓል አብራርተዋል።
ያለፈውን የሕማማት ሳምንት፣ ሞትን እያሰብን ስንጸልይ ቆይተናል ያሉት ዋና ጸሀፊው፣ ፈጣሪያችን የጨለማውን ዘመን እንዲያሳልፍን ብርሃን እንዲገልጽልን የጸለይንበት ሳምንት ነበር ይላሉ።
የስቅለት በዓል እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ከባርነት ነጻ እንዲወጡ በመስቀል ላይ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት መሆኑን አመልክተው፤ የትንሳዔ በዓል ሶስት ማዕልትና ሶስት ሌሊት በመቃብር ማሳለፉን፤ ድንጋይ አንሱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በሶስተኛው ቀን በመንፈቀ ሌሊት ከእንቅልፉ እንደ ነቃ ሰው ድንጋዩን አንከባሎ የተነሳበት መሆኑን ገልጸዋል ።
የዘንድሮው የ2017 ዓ.ም የትንሳኤ በዓል ሀገራችን ካለችበት ችግር ተላቃ ሰላምና እንድነት ሰፍኖ የሰው ልጆች በአንድ ድምጽ እግዚአብሄርን የሚያመሰግኑበት፣ በአንድ ልብ ሆኖው የሚያልሙበት፣ ሀገራቸውን የሚጠብቁበት የሰላም በዓል እንዲሆንም ዋና ጸሃፊው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የትንሳኤ መልእከቱ የሰው ልጅ ተቀብሮ አለመቅረቱን ክርስቶስ ተቀብሮ አለመቅረቱን መነሳቱን ለሰው ልጅ ብርሃን ሆኖ መገኘቱን ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመናት በጨለማ ውሰጥ የነበሩትን የሰው ልጆችም ነጻ ማውጣቱን ወደ ቀደመ ክብራቸው መመለሱን ያሳየናል ብለዋል።
በዓሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል በቤተክርስያኗ ሥርዓት መሰረት ይከበራል። ምእመናኑም በእዚሁ ሃይማኖታዊ እንዲሁም በባሕላዊ ስርአት በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል።
ሊቀ ማዕምራን መልካሙ በቤተክርስቲያኗ ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ለሀማርያም የሚባል መጽሀፍ ይነበባል። ከዚያም የቅዱስ ያሬድ ዜማ እየተዘመረ ይመሻል፤ መንፈቀ ሌሊት ላይ ክርስቶስ ተንስአ የሚል ድምጽ ይሰማል። ይህ መባሉም ታስረው የነበሩ የተፈቱበት ስለሆነ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዋና ጸሃፊው እንዳሉት፤ የበዓሉ ስርዓት በቤተክርስቲያን በቅድሚያ ከተከናወነ በሁዋላ ምእመናን እንኳን አደረሰህ! እንኳን አደረሰሽ፤ አደረሳችሁ! እየተባባሉ ያከብሩታል። ቤተክርስቲያን ለነዳያን፣ ለችግረኞች በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አማካይነት ድግስ እያዘጋጀችም በዓሉን ስታከብር ኖራለች፣ በየደብሩ ከሶስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ነዳያንና ችግረኞች ዘይት፣ ዱቄትና የመሳሰሉት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። በዚህም ከላቸው ጋር እኩል በዓሉን ማክበር እንዲችሉ ይደረጋል።
ከሃይማኖታዊ ስርዓቱ በተጨማሪ በዓሉን የሚያደምቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ ባሕላዊ ስርዓቶችም አሉ። ስለእዚህ አይነቱ የበዓል አከባበር መሰረትና ፋይዳ እንዲያብራሩልን የጠይቅናቸው ዋና ጸሃፊው፣ ‹‹ሲወርድ ሲዋረድ ከአባቶቻችን እንደተረከብነው ገብረ ሰላማ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ እያሉ አባቶች ካህናት ለምእመናን ቄጤማ እንደሚሰጡ ጠቅሰው፣ ቄጣማውንም በሚሰጡበት ወቅት አዳም ተመረመረ፤ ዲያቢሎስ ታሰረ የምስራች እንደሚሉ፣ ምእመናኑም ምስር ብሉ ሲሉ የምስራቹን እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።
በበዓሉ ዕለትም በየቤቱ የተደፋውን ዳቦ አባቶች ካህናት ይባርካሉ፤ አባቶች ካህናት በሌሉበት ደግሞ አባወራው ይባርካል፤ ከዚያም ምእመናን እየተጠራሩ በአንድ ላይ ሆነው እንኳን ለትንሳኤው በዓል አደረሳችሁ አደረሰን እየተባባሉ ገብረ ሰላማ የሚባለውን ዝክር ክርስቶስ ሞተ ተነሳ እያሉ በመቋደስ ደስታቸውን ይገልጻሉ ሲሉ አብራርተዋል።
የትንሳዔ በዓል ከሌሎች በዓላት አንጻር ሲታይ በተለያዩ የበዓል አከባበር ሥርዓቶቹ ይለያል። በዚህ በዓል አከባበር ስርዓት ልጆች ለእናት አባታቸው የአክፋይ ይወስዳሉ፤ የክርስትና ልጆች ለክርስትና አባቶቻቸውና እናቶቻቸው ፣ ምእመናን ለነፍስ አባታቸው ወዘተ አከፋይ ይወስዳሉ። ለአክፋዩ የሚወሰደውም እንደየአቅሙ ሙክት፣ መጠጥ፣ ዳቦ ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል። ልጆች በአጻፋው የአባቶችና እናቶችን ምርቃት ይቀበላሉ። ይህን ሁሉ በማድረግም ለበዓሉ ያላቸውን መልካም ምኞት ይገልጻሉ።
ሊቀ ማዕምራንን ስለማክፈል ሲያብራሩም፣ ‹‹አክፍሎቱ የክርስቶስን መከራ በማሰብ የሚፈጸም ነው›› ብለዋል። ‹‹ስለእኔ ተገረፈ፤ ስለእኔ መከራ ተቀበለ፤ ስለእኔ ታመመ እያሉ አንዳንዶች ሁለትና ሶስት ቀናት ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ ድረስ እንደሚያከፍሉ ተናግረዋል። ብዙዎች ደግሞ ከዓርብ አስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ቅዳሜ ሙሉ ቀንና ሌሊት እንደሚያከፍሉ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ምእመናን ለንስሃ አባቶቻቸው ቀሚስ፣ ካባ፣ ወዘተ ገዝተው እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ቤታቸው ድረስ ይሄዳሉ። አባቶቹም በቤታቸው ሆነው እንኳን አደረሳችሁ ገብረ ሰላማ፣ ትንሳኤው ገለጸልን እያሉ የንስሃ ልጆቻቸውን ይጠይቃሉ፤ ስለክርስቶስ መሞት፣ መነሳት ሳምንቱን በሙሉ ሲያዜሙ የሰነበቱ አባቶች ገንዘብ ሲይዙ ገብረ ሰላማ እያሉ በዓሉን ከካህናት ጋር ሆነው የሚያከብሩበት ሁኔታም አለ።
መጽሀፍ ቅዱሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ ቤተክርስቲያኗ ሰባት አባቶች እንዳሏት ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው አባት ዓለምን የፈጠረው ክርስቶስ ሲሆን፣ ሁለተኛው አባት ወላጅ አባት ነው። ከዚያም፣ የጡት አባት/ ዓለማዊ ነው፤ የሚያሳድግ ማለት ነው/፣ የክርስትና አባትም ሌላው ነው ብለዋል።
ይህን አይነቱ አከባበር እንዲቀጥል ለማድረግ ሃይማኖታዊ በዓሎች ሲከበሩ እንኳን አደረሰህ አደረሰሽ እየተባባለ እየተጠራራ አብሮ የሚበላበትና የሚጠጣበት የሚጨዋወትበት ሁኔታ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፣ ይህም ለመከባበርም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል። ትልቁ ትንሹን ፣ ትንሹም ትልቁን ሳይንቅ ተከባብረው በዓላቱ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ማድረግ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ፤ፈታልሽ በማለት በዓሉ እንደሚከበር ጠቅሰው፣ ይህም ትርጉም እንዳለው ነው ያስገነዘቡት። ይህ አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ልደት ድረስ በነበረው የፈተና ዘመን አልፎ ክርስቶስ ተወልዶ፣ ተጠምቆ፣ ስርአት አሳይቶ ዓርባ ሌሊት ዓርባ ቀናት ጾሞ በትንሳኤ ሁላችንንም አንድ አደረገ እንደማለት ነው ሲሉ አብራርተዋል። እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታልህ ማለት እንኳን ከታሰርክበት ተፈታህ፣ እንኳን ለስጋ ወደሙ አበቃህ ማለት ነው ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮች ለእዚህ በዓል በሬ አርደው ቅርጫ ያደርጋሉ፤ በግ ወይም ፍየል ፣ ዶሮ ያርዳሉ። ዳቦው፣ መጠጡ፣ወዘተ ይዘጋጃል። ቄጤማ ይጎዘጎዛል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ምእመናን በዓሉን የሚያከብሩት ነጭ በነጭ ነው። ነጭ ለብስ የሌለው ካለም፣ ያለውን አጥቦ ፣ ልብስ ሌላቸው ልብስ ሰጥቶ በዓሉን በቅድሚያ በቤተክርስቲያን ያከበራሉ፤ ከዚያም በቤቱ ከቤተሰብ ጋር፣ ከጎረቤት ጋር በመሆንም ተሰባስበው በድምቀት ያከብራል።
የትንሳኤ በዓል ለአንድ ሳምንት ይከበራል። ይህም ከሌሎች በዓላት የተለየ ያደርገዋል። ሊቀ ማዕምራን መልካሙ፤ በዓሉ ከትንሳኤው እስከ ዳግም ትንሳኤ በእያንዳንዱ ቀን እንደሚከበርም ጠቅሰው፤ እነዚህ የሳምንቱ ቀናት በየራሳቸው በአላት ሆነው እንዲከበሩ ማደረጉንም ተናግረዋል። በሊቃውንቱም ዳግማ ትንሳኤ ድረስ ያሉት ቀናት ትልቅ በአላት ተብለው እንደሚታወቁ አመልክተዋል።
ትንሳዔን ተከትሎ ሰርግ ይበዛል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ በዚህ ወቅት በድንግልና የጸኑት በስርዓተ ተክሊል ጋብቻቸውን ይፈጽማሉ፤ በድንግልና ያልጸኑት ደግሞ ራሳቸውን በካህን አስመርምረው፣ ፈጣሪያቸውን ፈርተው በቁርባን ጋብቻቸውን ይፈጽማሉ።
‹‹ሰርግን ባርኮ የሰጠ ጌታችን መዳህኒታች እየሱስ ክርስቶስ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ እየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ማርያምና ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሆኖ ጥር 13 የቃና ዘገሊላ እለት በአንድ ሰርግ ላይ ተግኝቶ ውሃውን ወይን አርጎ ታምሩን በማሳየት ሰርግን ባርኮ መስጠቱንና መነሻውም ይሄው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ፋሲካም ማግስትም ሰርጉ እንደሚቀጥል፣ በእነዚህ ወቅቶች ሀዘን፣ መከራ የለም። ሁሉም በደስታ ፈጣሪን እያመሰገነ የሚቆይባቸው ወቅቶች እንደመሆናቸው የደስታና የሰርግ ወቅቶች ናቸው ብለዋል።
ይህ የትንሳኤ በዓል በሃይማኖታዊም በባሕላዊም መንገድ ስርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር የሃይማኖት አባቶችና ምእመናን ማድረግ ስላለባቸውም መክረዋል። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የሃይማኖት አባቶች 318ቱ ሊቃነ ጳጳሳት በሲኖዶሳቸው የደነገጉትን አጽዋማትና በዓላት ምእመናን በአግባቡ መፈጸም ይኖርባቸዋል።
በዓሉን በዘፈን፣ በስካር፣ በዝሙት እንዳያከብሩት፣ ነጭ በነጭ ለብሰው በቤተክርስቲያንም በቤታቸውም እንዲያከብሩት ሊቃውንት ያስተምራሉ። ከዚያ ያለፈውን ደግሞ በለቅሶ ቤት፣ በሰርግ፣ በምረቃ ቤት እየተገኙ ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩም አስታውቀዋል። ይህ ትውፊት ሊጠበቅ የሚችለው ሊቃውንት መከባበርን ዘወትር ሲያስተምሩ መሆኑንም አስገንዝበው፣ ይህን ማስፈጸም የቤተክርስቲያን ድርሻ መሆኗንም አመልክተዋል።
ቤተክርስቲያን መከባበር እንዲኖር በሁሉም ቋንቋዎች እያስተማረች መሆኗን ተናግረዋል። ስለሰላምና አንድነት ፋይዳ ዘወትር እንደምታስተምር ጠቁመው፣ ዘንድሮም 2017 ዓመተ ምህረትን በሙሉ ስለሰላምና አንድነት መስበኳን ገልጸዋል።
እንደ ዋና ጸሀፊው ማብራሪያ፤ የበዓሉ ሃይማኖታዊ እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ይገባል፣ በዚህ በኩል ቤተክርስቲያን አጥብቃ ትሰራለች። ቤተክርስቲያን ለተሾመው ሁሉ ተግዛለች፡ ይህ ማለት ያለእግዚአብሄር ፈቃድ የሚሾም የለም። ከሹማምንትም በቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ፣ጳጳሳት ሊቃውንት አሉ፤ ካህናት ዲያቆናት አሉ። ሁሉም ተባብረው መቀጠል ሲችሉ ምእመናን የእነሱን ስርአት ተከትለው ለመሄድ አያዳግታቸውም።
ለበዓላት ድምቀት በመሆን ሲያገለግሉ የኖሩት ባሕላዊ ስርዓቶችም እንዲጠበቁ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ‹‹ይህን የሚጥስ የውጭ ሕግ ይበዛል፤ አለባበሳችን በአብዛኛው የውጭ ነው›› ሲሉ አስገንዝበው፣ ይህ አመለካከት እንዲለወጥ ቤተክርስቲያንም አጥብቃ ማስተማር አለባት ብለዋል። ‹‹እናቶቻችን ሲያሳድጉን የፈትል ቀሚስ እየለበሱ ነው፤ አባቶቻችንም ረጅም እጅ ጠባብ እየለበሱ ነው ያስተማሩን›› ብለዋል።
‹‹ምእመናን የስዓርት ሰው መሆን አለባቸው፤ ስርዓት ጠብቀው ማስጠበቅ ግዴታቸውም ነው። እናንተም/ሚዲያውን ማለታቸው ነው/በተሰጣችሁ ጥበብ /ጥበብ ከእግዚአብሄር ነው የተሰጣችሁ/ እነዚህ እሴቶች ለሁሉም ለመላው ዓለም ተደራሽ እንዲሆኑ ጠንክራችሁ መስራት አለባችሁ›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
የበዓሉ አከባበር ለቱሪዝም ዘርፉ ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ሲያብራሩም እንዳሉትም፤ የመጀመሪያው ቱሪዝም የተፈጠረው በቤተክርስቲያን ነው። በአብረሃ ወአጽብኃ ዘመን የተሰሩ የኦሪት መስዋአት የሚደረግባቸው አብያተክርስቲያናት ፣ እነ መርጦ ለማርያም፣ እነ አክሱም ጽዮን ወዘተ፣ ቱሪዝም ናቸው። ከዚያ ውጪ ቤተክርስቲያን ለቱሪዝም ዘርፉ የሚጠቅሙ ፋይዳ ያላቸው ዛፎች የሚገኙባትም ናት። ፍልፍል ዋሻዎቿ፣ ውቅር አብያተ ክርስትያናቷ፣ የቱሪዝም መስህብ ናቸው። ሁሉም ዓለምን በእጅጉ ይስባሉ።
ቤተክርስቲያን ለቱሪዝም ዘርፉ ትላልቅ ስጦታዎችን አበርክታለች። በዘርፉ ትልቅ ሚና አላት ሲሉም ጠቁመው፣ እነዚህ እሴቶች እንዲጠበቁ በማድረግ በኩል ብዙ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሊቀ ማዕምራን መልካሙ እንዳስታወቁት፤ በማሕበረ ቅዱስን በኩል የቤተክርስቲያን መጻህፍት በሙሉ ቅርስነታቸው እንዲጠበቅ፣ ባሕላዊ ትውፊቱ እንዲጠበቅ በስፋት ይሠራል፤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ጽህፈት ቤት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እስከ ጠረፍ ድረስ ይህ ይሠራል። ሃይማኖታዊ ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቤተክርስቲያኗ ባሏት ሙዚየሞች ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ ለሕዝብ እንዲታዩ እንዲታደሱ በማድረግ እየሠራች መሆኗንም አስታውቀዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም