“የሩጫ ስፖርት ወግ” – ለማሕበራዊ ሂስ

የወጋችን መንደርደሪያ ምሳሌዎች፤

ተጠባቂና ያልተጠበቁ ውጤቶችና ክስተቶች ከሚስተናገዱባቸው ተዘውታሪ የሰው ልጆች መዝናኛዎችና መፈተኛዎች መካከል የስፖርት ውድድር አንዱና ተቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። “ስፖርት” በሚል የወል ስሙ ጠቀስነው እንጂ ዲሲፕሊኑ አቅፎ የያዛቸው የውድድር ዓይነቶች በባህርያቸውም ሆነ በዓይነታቸው እጅግ በርካቶች ናቸው። ከስፖርት ዓይነቶች መካከል ጥንታዊ ተብሎ በአንጋፋነት ከሚጠቀሱት አንዱ የሩጫ ውድድር ስለሆነ ትኩረት የምናደርገው በዚሁ ዘርፍ ላይ ይሆናል።

የሩጫ ስፖርት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ሳይቀር ተደጋግሞ ተጠቅሶ እናነባለን። የስፖርት ምሳሌ ለማነጻጸሪያነት ጥቅም ላይ የዋለው የሃይማኖት ቤተሰቦች የሆኑ ምዕመናን ሰማያዊ የጽድቅ ሽልማታቸውን ለመቀበል እንደ ሯጭ ስፖርተኛ ተግተው ለአሸናፊነት እንዲበቁ መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር ነው። አንዱን ጥቅስ ብቻ እንደሚከተለው እናስታውሳለን።

“በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደሆኑ፤ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ። ለውድድር የሚዘጋጅ ማንኛውም ሰው በሁሉም ነገር ራሱን ይግዛል…” (1ኛ ቆሮንቶስ 9፡24)።

የሩጫ ስፖርት ብዙዎችን የሚያሳትፍ ጥቂቶችን የሚያሸልም መሆኑ በትንሹም ሆነ በትልቁ ዘንድ የታወቀ ነው። ፀሐይና ቁርን ተቋቁሞ ልምምድ ማድረግ፣ ሜዳና ተራራ ሳይመርጡ ሰውነትን መግራት፣ እያማረጡ በመብላትና በመጠጣት የፈሰሰውን ነጩን ላቤን መተካት አለብኝ ብሎ ምግብ ሳይመርጡ ለአምሮት መሸነፍና የጤንነትን ሁኔታ በአግባቡ ያለመቆጣጠር ከስፖርተኛው የሚጠበቁ ድርጊቶች አይደሉም። አሰልጣኞችም ቢሆኑ ሯጩ ስፖርተኛ ራሱን እንዲጠብቅና አቋሙን ዝቅ እንዳያደርግ የመጠበቅና የማረቅ ኃላፊነት አለባቸው።

ከላይ የተዘረዘሩት መስፈርቶች በሙሉ ተሟሉ ማለት ግን ሯጩ ድሉን አስተማማኝ አድርጎ ለሽልማት ያበቃዋል ብሎ እንደመደምደም ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም። ተገቢው ልምምድና ዝግጅት ተደርጎም እንኳን ቢሆን በተለያዩ የሯጩ የግል ችግሮችና ውጭያዊ ተጽእኖዎች ምክንያት በለስ ላይቀና ይችላል።

ለሽንፈት የሚዳርጉት ሰበቦችና አጋጣሚዎች ብዙ ስለሆኑ ምክንያቶቹን ለመዘርዘር ከመሞከር ይልቅ የሩጫ ስፖርት በተካሄደባቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የተፈጸሙ አስገራሚ ክስተቶችን በምሳሌነት በማስታወስ በዋናው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ላመለከትነው “ወቅታዊና ሀገራዊ ችግሮቻችንና ተግዳሮቶቻችን” በስሱና እጅግም ጫን ሳንል እንደ ማነጻጸሪያ የሂስ ግብዓትነት ልንጠቀምባቸው እንሞክራለን። ከጸሐፊው የግል ትንታኔ ይልቅ አንባቢያን እያንዳንዱን ታሪክ እንደ ተግዳሮት ለሚያዩት ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳይ ማሳያነት ቢጠቀሙበት ደግሞ ይበልጥ የተሻለ ይሆናል።

ሀ. ትክክለኛውን መንገድ በመሳቷ ሽልማት ያመለጣት የሀገራችን አትሌት፡- ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም የአሜሪካን የነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በጆርጂያ ክፍለ ግዛት በአትላንታ ከተማ ፒችትሪ ጎዳና ላይ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት በተደረገው የሩጫ ውድድር በብዙዎች ዘንድ ለአሸናፊነት የተገመተችው ብርቱ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ነበረች። ነገር ግን ከፊት ለፊት ሆኖ ሯጮቹን መንገድ ይመራ የነበረው አንድ ሞተረኛ ሩጫው ወደ ፍጻሜ መቃረቡን አረጋግጦ ተወዳዳሪዎችን ከኋላ አስከትላ እየመራች የነበረችውን ሰንበሬን ትቶ ወደ ቀኝ ሲታጠፍ ሰምበሬም ትክክለኛው መስመር መስሏት አብራ ወደ ተሳሳተ መንገድ በመታጠፏ ከኋላዋ የተከተሏት ሯጮች ስለቀደሟት ድሏ ሊጨነግፍ ችሏል።

በሪዮና በቶኪዮ ኦሎምፒኮች በ5000 ሜትር ውድድሮች ሀገሯን ወክላ በመወዳደር አምስተኛና ስድስተኛ የወጣችውና መንገድ በሳተችበት የአምና ውድድር በዚያው በአትላንታ ከተማ አሸንፋ የተጨበጨበላትና በከፍተኛ ሁኔታ ለአሸናፊነት ተገምታ የነበረችው ሰንበሬ ተፈሪ የአንደኝንቱን ድል ለሀገሯ ልጅ ለፎቴን ተስፋዬ እና የሁለተኛነቱን ደረጃ ደግሞ ለኬኒያዊቷ ለጄሲካ ቼካንጋቴ በማስረከብ የአሥር ሺህ ዶላር አሸናፊቷ አምልጧት ለሦስተኛ ደረጃ ክብሯ ሦስት ሺህ ዶላር ብቻ ልትሸለም ችላለች። ብዙ የዓለም ሚዲያዎች በመቀባበል ሞተረኛውንና አዘጋጆቹን በመውቀስ ዜናውን ለመላው ዓለም ቢያስተጋቡም “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ” እንዲሉ የሰንበሬን ጉዳት ጉዳዬ የሚል አካል በመጥፋቱ የሸናፊነቷ ድል ከእጇ ሊወጣ ግድ ብሏል።

ለ. የራስን ክብር ለሌላው አሳልፎ የሰጠ አትሌት፡- እ.ኤ.አ በዲሴምበር 2 ቀን 2012 ዓ.ም በስፔኗ ክፍል ሀገር በቡርላዳ ከተማ አንድ አስደናቂ ክስተት በሩጫ ጎዳና ላይ ተከናውኖ ነበር። ኬንያዊው ሯጭ አቤል ሙታያ ይወዳደርበት በነበረው የሀገር አቋራጭ ሩጫ በቀዳሚነት እየመራ የመጨረሻዋን የአሸናፊነት ጥብጣብ ሊበጥስ አሥር ያህል ሜትሮች እንደቀሩት ሩጫውን በአሸናፊነት ያጠናቀቀ መስሎት ወደ ዳር ወጥቶ ደስታውን ሊያበስር መዘጋጀቱን ያስተዋለውና እንደተሳሳተ የገባው በሁለተኛነት ይከተለው የነበረው ስፔናዊ ሯጭ ኢቫን ፈርናንዴዝ ኬኒያዊው አቤል መሳሳቱን ይረዳል። ስለዚህ ከመዘናጋቱ የተነሳ ዕድል ፊቷን ልታዞርበት የነበረውን ኬኒያዊ ሯጭ እየጮኸ “አቤል ውድድሩን አልጨረስክም። ገና ጥቂት ሜትሮች ይቀሩሃል! ሩጫህን አታቋርጥ!” እያለ ቢጮኽም በቋንቋ ለመግባባት አልቻሉም።

ስለሆነም ፈርናንዴዝ አንድ ርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ ኬንያዊውን ሯጭ እየገፋና እየጎተተ በአንደኝነት ጥብጣቡን እንዲበጥስ አደረገው። ይህንን አስደናቂ ትዕይንት ይከታተሉ የነበሩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ከአሸናፊው ከአቤል ይልቅ ፈርናንዴዝን ከበው በጥያቄ ያጣድፉት ገቡ። “እንዴት ማሸነፍ እየቻልክ እድልህን አሳልፈህ ልትሰጥ ቻልክ? ስለምን አንተ ቀድመኸው አልገባህም?”

የፈርናንዴዝ መልስ አጭርና ግልጽ ነበር። “አሸናፊነት ስለማይገባኝ ነው። ስህተት ባይፈጽም ኖሮ ሊያሸንፍ የሚችለውን አትሌት ባለማወቅ በፈጸመው ስህተት ቀድሜው ሜዳሊያ በአንገቴ እንዲጠለቀልኝ በመስገብገብ ስለምን ባለማወቅ በፈጠረው ስህተት እኔ ባለ ድል ሆኜ ወንድሜን እሳለቅበታለሁ።

ሽልማቱ የሚገባው ለእርሱ እንጂ ለእኔ ሊሆን አይገባም። ስህተት የሠራን ሰው አርሞ ድል እንዲቀዳጅ ማድረግ በተንኮል ከሚገኝ ክብር በእጅጉ ይሻላል። ስለዚህም ነው በቋንቋ መግባባት ቢያቅተንም እየጎተትኩና እየመራሁት እርሱ አንደኛ ወጥቶ እንዲያሸንፍና እኔ የደከምኩበትን የሁለተኛ ደረጃ ማዕረግ ለማግኘት የወሰንኩት።” – ይገርማል! ዜናውን የተከታተሉት የዓለም ዜጎች በሙሉ “ጀግናው አሸናፊ አቤል ሳይሆን ፈርናንዴዝ ነው” በማለት ዛሬም ድረስ ማሞገሳቸውን አልተውም።

ሐ. የሀገሩን ክብር በማስቀደሙ አድናቆት የተዥጎደጎደለት ውራ አሸናፊ፡- ታንዛኒያዊው ጆን ስቴፈን አክዋሪ እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም በሜክሲኮ ተደርጎ በነበረው የኦሎምፒክ ማራቶን ከ75 ሯጮች መካከል አንዱ ነበር። የውድድሩ ማስጀመሪያ ፊሽካ እንደተነፋ ሁሉም ሯጮች መስመራቸውን ይዘው መሮጥ የጀመሩት በትልቅ የአሸናፊነት ወኔ ነበር። ነገር ግን ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን እንደሮጡ በሙቀት የታፈነው አየር የብዙ ሯጮችን ትንፋሽ እያሳጠረ ስላስጨነቃቸው አስራ ስምንት ያህሉ ውድድራቸውን አቆርጠው ለመውጣት ተገደዱ።

ታንዛኒያዊው ጆን እስቴፈንም ውድድሩን አቋርጠው እንደወጡት ተፋላሚዎች አየሩ ከብዶት መጨነቁ አልቀረም ነበር። ቢሆንም ግን እንደምንም ራሱን እየተቆጣጠረ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን እንደሮጠ ድንገት አደናቅፎት ይወድቃል። አወዳደቁ ትንሽ ጠንከር ያለ ስለነበር የእግሩ ቁርጭምጭሚት ቦታውን ስለለቀቀ ሕመሙ ከፍ ብሎ ያሰቃየው ጀመር። እግሮቹና ጉልበቶቹ አካባቢ እና ትከሻው ላይ የመንገዱ አስፓልት ክፉኛ ስለቀጠቀጠው በርትቶ ለመነሳትና ውድድሩን ለመቀጠል በፍጹም አላስቻለውም ነበር። ስለዚህም የድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ሰጭ ሐኪሞች በፍጥነት ደርሰውለት የመጀመሪያ እርዳታ በመስጠት ለቀጣዩ ሕክምና ወደ ሆስፒታል ሊወስዱት ጥረት አደረጉ።

እስቲፈን ግን ትንፋሹ መለስ እንዳለለት ጥያቄያቸውን ከመቀበል ይልቅ እያነከሰና በፋሻ የተጠቀለለውን እግሩን እየጎተተ ሐኪሞቹን በቆሙበት ትቷቸው በሶምሶማ ሩጫ ወደፊት ይገሰግስ ጀመር። የሩጫው ውድድር ተጠናቆ፣ አሸናፊዎቹም ሽልማታቸውን ተቀብለው፣ ተወዳዳሪዎቹ ሁሉ ከተበታተኑ በኋላና አብዛኞቹ ተመልካቾች ስቴዲዬሙን ለቀው ወጥተው ውር ውር ከሚሉ ጥቂቶች በስተቀር አካባቢው ጭር ብሎ ቆየው። ፀሐይዋ ደብዘዝ ብላ ወደ መጥለቂያዋ ስትቃረብ አንድ ሯጭ እያነከሰ ወደ ስቴዲዬሙ ሲገባ ታየ። ታንዛኒያዊው ጆን እስቲፈን ነበር።

በአካባቢው የተገኙት ጥቂት ግለሰቦችና በስቴዲዬሙ ውስጥ የቀረፃ መሳሪያቸውን ይሸክፉ የነበሩ የሚዲያ ተቋማት ያንን ውራ የወጣ ሯጭ ሲመለከቱት ነገሩ ግር እንዳለቸው ቀርበው በጥያቄ ያጣድፉት ጀመር። እስቲፈን ግን ሁኔታው እጅግም አላስደነገጠውም፤ አላሳፈረውምም። ማነህ? ለምንስ ዘገየህ? ጉዳት እንደገጠመህ ስለምን ውድድሩን አቋረጠህ አልወጣህም? አሁንስ ውራ ሆነህ ውድድሩ ከተዘጋ በኋላ በመድረስህ ምን ይሰማሃል?

አትሌቱ እስቴፈን እንደተረጋጋ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤- “ሀገሬ ወክላ የላከችኝ የ5000 ማይል ሩጫ እንድጀምር ሳይሆን 5000 ማይሉን ሮጬ እንዳጠናቅቅ ነው። ስለዚህም የሀገሬን አደራ ማክበር ስለነበረብኝ ጉዳት ቢደርስብኝም እንኳን ሕመሜን ታግሼ ሩጫዬን በትእግሥት መጨረስ ነበረብኝ።” በርካታ የዓለም ሕዝቦች ይህንን መልሱን ካደመጡበት እለት ጀምሮ ዛሬም ድረስ “እውነተኛ የሀገሩ አምባሳደር” በማለት እያከበሩትና ስሙን እየዘከሩ ይገኛሉ።

የታሪኮቹ ፋይዳ፤

የሰንበሬ ተፈሪ ታሪክ ለአመራር ጥበብ ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችል ምሳሌ ነው። “ከግባችሁ እንድትደርሱ መንገዱን እናመላክታችኋለን፤ እንመራችኋለንም” የሚሉ ብዙ የዓለማችን መሪዎች ከዋናው የመነሻ ዓላማቸው ፈንገጥ በማለት ሕዝባቸውን አሳስተው ምን ያህል ጥፋት በምድራችን ላይ እንደተፈጸመ ብዙ ታሪካዊ ማጣቀሻዎችን ማስታወስ ይቻላል።

የሩቁን ማሳያ እንኳን ለጊዜው ትተን በሀገራችን ዐውድ የተፈጠሩትን ብዙ ታሪካዊ ምሳሌዎች ብናስታውስም ሕዝብ አጨብጭቦ በዕልልታ የተቀበላቸው በርካታ ቀዳሚ መሪዎች ሕዝቡን እንደምን ለመከራ አሳልፈው እንደሰጡ መመልከት ይቻላል። ማን? መቼ? በየትኛው ዘመን? የሚሉትን ጥቅል ጥያቄዎች አንባቢያን መልሱን ራሳቸው ቢሰጡበት ስለሚሻል እጅግም ጠልቄ በጉዳዩ ላይ ትንታኔ አልሰጥም።

“የአመራር ጥበብ” በሚል ርዕስ በ2001 ዓ.ም ባሳተምኩት መጽሐፍ ውስጥ የእንደነዚህ ዓይነት አሳሳች መሪዎችን ባህርያት በዝርዝር ለማመልከት ስለሞከርኩ መጽሐፉ ቢነበብ ለተሻለ መረዳት ያግዝ ይመስለኛል። ተመሪዎችም ቢሆኑ የመሪውን አካሄድና ዙሪያ ገባ በሚገባ በመመርመር ራስን ከስህተት ጠብቆ ካሰቡት ግብ ለመድረስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባ ይመስለናል። በተረፈ የሰንበሬ ተፈሪን ገጠመኝ በብዙ መልኩ እየተነተኑ ለማስተማሪያነት መጠቀም ይቻላል።

ሌላው ትምህርት የምንቀስምበት ታሪክ ኬንያዊውን አቤልን የረዳው የፈርናንዴዝ ድርጊት ነው። ብዙ ሰዎች ሌላውን እየጠለፉ በመጣል እነርሱ ብቻ እንዲገንኑ በሚፈለግበት በዚህ ዘመን ቁጥራቸው ይነስ እንጂ የራሳቸውን ጥቅም መስዋዕት በማድረግ እኛን ከፍ የሚያደርጉ የመልካም ክንድ ደጋፊ ግለሰቦች እንዳሉም ማሰብ ይኖርብናል። ስንስት የሚያቃኑን፣ ስንባዝን የሚፈልጉን ቅኖችም ዙሪያችንን እንደ ደመና እንደከበቡን ልናምን ይገባል። ብዙ ጊዜ በክፉዎች ድርጊት ብቻ ተስፋ ቆርጠን ከምንንገዳገድ በበጎነት የተሸለሙ ግለሰቦችም እንዳሉ በማሰብ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትእግሥት መሮጡ እንደሚያዋጣ በአግባቡ መገንዘቡ ጥበብ ነው።

በምናያቸው የሚጎረብጡ ሀገራዊ ክስተቶች ተስፋችን ቀጥኖ ተሽመድምደን ወድቀን ከሆነ የጆን ስቲፈን ምሳሌነት ትምህርት ሊሆነን ይገባል። በተለይም ለራስና ለራስ ብቻ እያለሙና እያነፈነፉ መኖር የደስታና የእርካታ ምንጭ እንደማይሆን የታንዛኒያዊ ሯጭ ታሪክ ሊሞግተን ይገባል። ማንም ይበለው ማን “ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብሎ ከማላዘን በፊት እኔ ለሀገሬ ምን ፈየድኩላት ብሎ” ከራስ ጋር ሙግት መግጠሙ ማስተዋል ነው።

እናጠቃለው፡- አንዳንድ ከራሳቸው ጋር ጠብ የፈጠሩ ወበከንቱዎች ሌላውም ሰው ሰላም እንዳያገኝ ቀን ከሌት እያደቡ በጨለማ ውስጥ ሲንደፋደፉ ያሸነፉ እየመሰላቸው ሊኩራሩና ከእኔ ወዲያ ላሳር ብለው በትምክህት ሊሰየጥኑ ይችሉ ይሆናል። በክፋት ተንኮል መንገድ ለማስቀየስ መሞከር፣ በሴራ ሌሎችን ጠልፎ በአሸናፊነት ለመውጣት ማለም ውጤቱ ለጊዜው ያረካ ካልሆነ በስተቀር ውሎ አድሮ ኅሊናን አወፍፎ ጨርቅ ማስጣሉ የሚቀር አይሆንም። “ልጄ ሆይ እንደምትኖር ሆነህ ሥራ፤ እንደምትሞት ሆነህ ኑር” የሚለው የታላላቆች ምክር ቁምነገሩ ከፍ ያለ ስለሆነ ከሯጮቹ ታሪክ ለራሳችን የሕይወት ሩጫ ትምህርት እንውሰድ። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም መልካም ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 26/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *