የዛሬው የፍረዱኝ ዝግጅታችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ቦሌ ሚካኤል ይወስደናል።ይኸውም፡
«አቶ ተላይነህ አዱኛ የተባሉ ግለሰብ በካርታ ተለክቶ ከተሰጣቸው መሬት ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ የመንግሥትን መሬት በወረራ ይዘዋል በሚል ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ የተለያዩ አካላት አቤቱታ አቅርበን ነበር። የአዲስ አባበ ከተማ ምክር ቤት፣ ከጸረ ሙስና ሥነ ምግባር፣ ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቡ የተወሰደው መሬት ለመንግሥት እንዲመለስ የሚል ደብዳቤ ጽፈው ነበር። ነገር ግን የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች የታዘዙትን ሊያስፈጽሙ አልቻሉም። በዚህም ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት የፈጠሩትን የመልካም አስተዳደር ችግር የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቶ ይፍረድ፤» ሲሉ በቦሌ በክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብርሃም ወርቁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የመልካም አስተዳደርና ምርመራ ክፍል አቤት ብለዋል።
ዝግጅት ክፍሉም ስለጉዳዩ ከሰዎችና ሰነድ ያገኛቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች በጥልቀት በማየት የደረሰበትን የመጀመሪያ ክፍል እነሆ ብሏል።
ከአቶ አብርሃም አንደበት
የቦሌ ክፍለ ከተማ በመሬት ልማት ማኔጅመንት ጉዳዩን ተመልክቶ ግለሰቡ የያዘውን ቦታ አስመልሼ ወደ መሬት ባንክ አስገብቻለሁ ብሎ ነበር። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ግለሰቡ የሕዝብንና የመንግሥትን መሬት በሕገወጥ መልኩ እንደያዘ ይገኛል። የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንትም አስመለስኩት ያለው መሬትም በትክክል ወደ መሬት ባንክ አልገባም። ስለሆነም አሁንም በወረዳ እና በክፍለ ከተማ በአመራርነት ያሉ አካላት ለግለሰቡ በሚያደላ መልኩ የመንግሥትን መሬት ከልለው ሰጥተዋል።
ከአራት ወር በፊት ከክፍለ ከተማ የመጡ ባለሙያዎች በመሣሪያ በተደገፈ ልኬት ውዝግብ የተነሳበትን ቦታ በመለካትና በመለየት በሕገ ወጥ የያዘውን መሬት አሳውቀው ነበር። ነገር ግን በወረዳ እና በክፍለ ከተማ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮች ከአቶ ተላይነህ ጋር በመተባበር የተወረረው መሬት ለመንግሥት እንዳይመለስ አድርገዋል። ጉዳዩን በተደጋጋሚ ለወረዳ በማቀርብበት ጊዜም በወረራ በተያዘው መሬት ላይ መንገድ ፈልገው እንደሚመላለሱ እየቆጠሯቸው እንደሆነም ነው ለዝግጅት ክፍላችን የተናገሩት።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍልም፣ ለአቤቱታ አቅራቢዎች «ሕገ ወጥ በተባለው ቦታ መንገድ እንዲኖር ትፈልጋላችሁ?» የሚል ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት አቶ አብርሃም፤ ውዝግብ በተነሳበት ቦታ ላይ ቀደም ሲል የእግረኛ መንገድ ነበር። አሁን ይህ መንገድ በግለሰቡ (አቶ ተላይነህ) በወረራ ተይዟል። ይሁን እንጂ የቅድሚያ ቅድሚያ ጥያቄያችን በሕገ ወጥ የተያዘው ቦታ ለመንግሥት ይመለስ ነው። የመንገዱ ጉዳይ በሂደት የሚታይ ይሆናል። በቀጣይ ግን ስለመንገዱ እንደዜጋ እንጠይቃለን ብለዋል።
በሕገ ወጥ መልኩ ተያዘ የተባለው ቦታ፣ ከግለሰቡ ባሻገር አብዛኛው ለትምህርት ቤት ማስፋፊያ ተጠይቆበት መታጠሩን የጠቆሙት አቶ አብርሃም፤ ይሄ መደረጉም አግባብ አይደለም ይላሉ። ለትምህርት ቤትም ማስፋፊያ ሲሰጥ የራሱ የሆነ አካሄድና አሠራር አለው። ለትምህርት ቤቱ ማስፋፊያውን የሰጠው ወረዳ ነው። ወረዳው የትምህርት ቤት ማስፋፊያውን እየደገፈ ያለው አቶ ተላይነህን ለመጥቀም በማሰብ ነው።
ምክንያቱም ወረዳው ለትምህርት ቤቱ የማካተት መብት የለውም። ይህ መብት ያለው የከተማ አስተዳደሩ እና የክፍለ ከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት ብቻ ነው። ወረዳው ለትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ መስጠቱ ከበስተጀርባ ሌላ አሻጥር መኖሩን የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ወደ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመጡትም፤ እየተደረገ ያለውን አሻጥር ለሕዝብ እንዲያሳውቅላቸው በመፈልግ መሆኑን ያስረዳሉ።
ከአቶ ተላይነህ አንደበት
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የአቶ ተላይነህን ሃሳብ ለማድመጥ ወደ እሳቸው ባቀናበት ወቅት ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል፤ «የመንግሥትን መሬት በሕገ ወጥ መንገድ አጥረው ይዘዋል የሚሉ ተደጋጋሚ ክሶች በእስዎ ላይ ይነሳሉ፤ ከወረዳ፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ጀምሮ የሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት በተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ጽፈዋል። ፍሬ ሃሳባቸውም ‘አቶ ተላይነህ አዱኛ ያለአግባብ የያዙትን የመንግሥት መሬት ይልቀቁ የሚል’ ነው። በዚህ ጉዳይ እርስዎ ምን ይላሉ?» የሚለው ይገኝበታል።
እርሳቸውም ሲመልሱ፤ «አቶ ተላይነህ የሕዝብና የመንግሥት መሬት በሕገ ወጥ መሬት ይዟል ይልቀቅ የሚሉ አካላት የአሠራር ሥርዓት የማያውቁ፣ መንግሥታዊ አሠራርን የማይረዱ፣ ድርጅታዊ አሠራር የማይገነዘቡና ያለአግባብ የሚሠሩ ናቸው» በማለት ነበር። አስከትለውም፣ በዚህ ቦታ ላይ ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የኖርኩ ሰው ነኝ የሚሉት አቶ ተላይነህ፤ ከልምዳቸው በመነሳት እስከ ዛሬ በሀገሪቱ መቃለል ያልቻለው ሁነኛ ችግር መመሪያን እና አሠራርን ተመርኩዞ ውሳኔ መስጠት አለመልመድ ነው ብለዋል።
አቶ ተላይነህ እንደሚሉ፤ በወረራ መሬት ይዟል ይልቀቅ ከመባሉ በፊት መጀመሪያ በእርግጥ አቶ ተላይነህ በወረራ የያዘው መሬት አለ ወይ? ተብሎ ማጣራት ይገባል። ቦታው በምሪት የተሰጣቸው ነው። በምሪት ቦታ ከተሰጣቸው በኋላ ደግሞ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን ለአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሁለት ጥያቄዎችን አነሱ። ሁለቱም ጥያቄዎቻቸው ለመኖሪያ ከተመሩት ቤት ጀርባ ከሚገኘው ቦታ ጋር የተገናኘ ነበር።
አንደኛው ጥያቄ፣ ከጀርባ ያለው ቦታ ለ‹‹ሴፍቲ ታንከር›› መሥሪያ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከጀርባ በሚገኘው ቦታ ላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ቤት ሲሠራ ከፍተኛ አፈር በመድፋቱ የተደፋው አፈር በጎርፍ እንዳይወሰድ ቦታውን እናልማው የሚል ነበር።
የአዲስ አበባ ማዘጃጋ ቤትም ጉዳዩን በማስጠናት ሴፍቲ ታንክር እንዲሠሩ መፍቀዱንና ለዚህም ማረጋገጫ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የተሠራ ካርታ መኖሩን ጠቅሰው፤ እስከዛሬ ድረስ የ28 ሰዎች ሴፍቲ ታንከር አንድ ቦታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሁለተኛው እና የተከማቸው ምልስ አፈርም በጎርፍ እንዳይሸረሸር የጠየቁት ጥያቄ ግን በከተማ ማዘጋጃ ቤት ምላሽ ሳያገኝ ቀረ። ይህን ተከትሎ በወቅቱ አካባቢውን ያስተዳድር ለነበረው ቀበሌ 20 ምልስ አፈሩ ያለበትን ቦታ ማልማት እንደሚፈልጉ በአካል ሂደው መጠየቃቸውን ይናገራሉ። የቀበሌ 20 አስተዳደርም ‹‹ቋሚ ንብረት ሳታሳርፍ አጥረህ መጠቀም ትችላለህ›› የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው እና 2ሺ500 ካሬ ሜትር የሚሸፍን መሬት ማልማታቸውን፤ ግብር እየገበሩበትም በርካታ ዓመታት ይዘው መቆየታቸውን ይናገራሉ።
አሁን ላይ ቦታው ለትምህርት ቤት ማስፋፊያ በመፈለጉ በትርፍ ይዘው ሲያለሙት የነበረውን ቦታ ለትምህርት ቤቱ መስጠታቸውን ይናገራሉ። ለልማት ከሆነ አይደለም በትርፍ የሚለማን መሬት ቀርቶ መኖሪያ ቤታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ይናገራሉ።
አቤቱታ አቅራቢው አቶ አብርሃም ወርቁ የተባለው ግለሰብ ከወንድሙ ጋር ተዳብሎ የሚኖርና ራሱ በምሪትም ሆነ በግዥ ያገኘው ቦታ በአካባቢው የለውም የሚሉት አቶ ተላይነህ፤ አሁን ላይ ቅሬታ የሚያነሳበት ዋና ምክንያት ከወንድሙ ቤት ጀርባ በወረራ ለያዘው ቦታና ለገነባው ቤት መንገድ ለማግኘት ፈልጎ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዓመታት ያለሙትንና የገበሩበትን መሬት መንግሥት ለማያውቀው የጨረቃ ቤት መውጫ መግቢያ እንዲሆን መቼም ሊፈቅዱ እንደማይችሉም ይናገራሉ።
አቤቱታ አቅራቢው፣ ለጨረቃ ቤቱ መውጫ የሚሆን መንገድ ለማግኘት በማሰብ የወረዳው አመራሮች በተቀያየሩ ቁጥር በተደጋጋሚ ወረዳ እንደሚሄድ ይገልፃሉ። ሆኖም አመራሮች በተደጋጋሚ በቦታው ተገኝተው በምልከታቸውም ያረጋገጡት ነገር፤ ቦታው ለረጅም ጊዜ በግለሰቡ የለማ እንጂ የተወረረ አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። ወደፊትም ሌላ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ ቢመጣ አቶ አብርሃም ጥያቄውን ሊያነሳ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
የተቋማት እሰጥ አገባ
ጉዳዩ በሁለት ተጎራባች ግለሰቦች መካከል የመሬት ይገባኛል ሲሆን፤ በተካረረው የጎረቤታሞች ግጭት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 አስተዳደር ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደሩ እልባት ለመስጠት ጣልቃ ገብተዋል። በተመሳሳይ መልኩ የመንግሥት ተቋማት በዚህ ጉዳይ በእጅጉ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት፣ አቶ ተላይነህ አዱኛ እና አቶ አብርሃም ወርቁ (የሌሎች ግለሰቦችም ተወካይ በመሆን) ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሆኖ ተገኝተዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥታዊ ተቋማቱ አንዱ በሌላው ላይ በማላከክ ደብዳቤዎችን ይፃፉ እንጂ እስካሁን ለጉዳዩ ሁነኛ መቋጫ መስጠት አልተቻላቸውም። ይሄም ለግለሰቦቹ የማያባራ ሽኩቻና ቅራኔ ውስጥ መግባት ምክንያት ሆኗል። ይሄን የተገነዘበው የምርመራ ቡድኑም ለመሆኑ ለምን ጉዳዩን መቋጨት አልተቻለም? በዚህ ላይ ሰነዶችስ ምን ይላሉ? የሚሉትን ጉዳዮች በማንሳት ለመመልከት ጥረት ተደርጓል።
የሰነድ ማስረጃዎች
ሰነድ አንድ፡- የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በቀን 21/6/2014 ዓ.ም ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ይመለከታል በማለት በፃፈው ደብዳቤ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ክልል ልዩ ስሙ መለስ ፍሬ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተምሮ ማስተማር የሚባል የመኖ/ህ/ስ/ማህበር አባል የሆነት አቶ ተላይነህ አዱኛ ከይዞታቸውና ከካርታቸው ውጪ የመንግሥት ቦታ በሕገ ወጥ በመውረር የያዙት ቦታ መኖሩን በቀረበው ጥቆማ የቦሌ ክፍለ ከተማ የሕዝብ ቅሬታ አቤቱታ ማስተናገጃ ጽሕፈት ቤት አጣርቶ ጥቆማው ትክክል መሆኑን በማረጋገጥ የመንግሥት ቦታውን ነፃ በማድረግ እንዲጠበቅ በቁጥር ቦ/ክ/ህ/ቅ/አ/ማ/ ጽ/ቤት/231/13፣ በቀን 30/10/2013 ዓ.ም የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ አልተደረገም።
ተግባራዊ ባለመደረጉ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን በቁጥር አ.አ/ መ.ል.አ.በ./2-3/1425/14፣ በቀን16/3/14 ለክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ለመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ለሰላምና ፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም ለወረዳ 01 ዋና ሥራ አስፈፃሚ የተፃፈ መሆኑን ይታወቃል። ውሳኔው ተግባራዊ አለመደረጉን ከማዕከል ባለሙያ ቦታው ድረስ በመሄድ በተደረገው ማጣራትና የመስክ ምልከታ እስከ አሁን በወረራ የተያዘው ቦታ ነፃ አልተደረገም። በመሆኑም ያለአግባበ የያዙት ቦታ ከየትኛውም ግንባታ ነፃ ተደርጎ ክፍት ቦታው ወደ መሬት ባንክ እንዲገባና እንዲጠበቅ እያሳሰብን አፈፃፀሙን እንድታሳውቁን እናሳስባለን ይላል።
ቢሮው በመቀጠልም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በቀን 5/14/15 ዓ.ም፣ በቁጥር 23/5015/2015/ ለቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በሕገ- ወጥ የመሬት ወረራ ላይ እየታየ ያለውን የአፈፃፀም ጉድለትን ይመለከታል በማለት ደብዳቤ ጽፏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም፣ በቁጥር 31/541/15 በተፃፈ ደብዳቤ፤ በክፍለ ከተማችሁ ወረዳ 1 ልዩ ቦታ መለስ ፍሬ ትምህርት ቤት አካባቢ ተምሮ ማስተማር የመኖሪያ ቤት ማህበር አቶ ተላይነህ አዱኛ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በ2003 ዓ.ም ከያዙት ይዞታ ውጪ 550 ካሬ ሜትር ትርፍ መሬት በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘ መሆኑን በመግለፅ ከዚህ በፊት ሕገ ወጥ ተግባሩን በመቀልበስ የተወረረውን ቦታ ወደ መሬት ባንክ አስገብታችሁ ሪፖርት እንድታደርጉ ተጠይቃችሁ እንደነበር ገልፀውልናል።
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሰውን ጉዳይ በአግባቡ በማጣራት ያለ አግባብ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የተወረረ ቦታ ከሆነ መመሪያንና አሠራርን መሠረት በማድረግ ፈጽማችሁ በሦስት ቀናት ውስጥ መረጃ እንድትልኩ እየጠየቅን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የተፃፈውን ደብዳቤ ከዚህ ሸኚ ጋር በሁለት ገጽ አያይዘን መላካችንን እንገልፃለን ይላል።
ሰነድ ሁለት፡- የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም በቁጥር 31/541/15 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የጻፈው ደብዳቤ፤ ጉዳዩ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ላይ እየታየ ያለውን የአፈፃፀም ጉድለት ይመለከታል የሚል ሲሆን፤ በዚህም መዘርዝር መሠረት አራት ግለሰቦች አመልካች ሆነው ቀርበዋል።
እንደ ደብዳቤው ከሆነ፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 1 ልዩ ቦታው መለስ ፍሬ ትምህርት ቤት አካባቢ ተምሮ ማስተማር የመኖሪያ ቤት ማኅበር አቶ ተላይነህ አዱኛ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በ2003 ዓ.ም ከያዙት ይዞታ ውጪ 550 ካሬ ሜትር ትርፍ መሬት በሕገ ወጥ መንገድ የያዙ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም፤ እስከ አሁን ድረስ መሬቱ በሚመለከተው ተቋም በኩል ወደ መሬት ባንክ አለመግባቱን፤ ይሄንንም ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ተቋም በጋራ የተዋቀረ የቴክኒክ አጣሪ ቡድን በቦታው በመገኘት ማጣራቱን፤ በዚህም መሠረት መሬቱ ያለ አግባብ በሕገወጥ መንገድ በግለሰቡ መታጠሩንና ችግኝ በመትከል በድንጋይ አጥሮ መያዙን የቴክኒክ ቡድኑ ማረጋገጡን እና ግለሰቡ አስፋፍተውና ከልለው በወረራ የያዙትን የመንግሥት መሬት ነፃ በማድረግ እንድታስጠብቁ በማለት ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በደብዳቤ አሳውቋል።
አመልካች ግለሰቦቹም መሬቱን ነፃ የማድረጉ ተግባርም እስካሁን ተፈፃሚ ባለመደረጉ እና በግለሰቡ በድንጋይ በመታጠሩ ምክንያትም የመውጫና መግቢያ የእግር መንገድ የተዘጋባቸው መሆኑን በመግለጽ በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በኩል ችግሩ ታይቶ መፍትሄ ይሰጠን በማለት አመልክተዋል። በመሆኑም በአመልካቾች የቀረበው አቤቱታ ተጣርቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በቋሚ ኮሚቴ በባለሙያዎች እንዲጣራ ተደርጓል።
በዚህም መሠረት በቦታው ተገኝተን እንደተመለከትነው ከአሁን በፊት ከቢሮውና ከክፍለ ከተማው የተውጣጣው የቴክኒክ አጣሪ ቡድን በቦታው በመሄድ አጣርቶ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ቅሬታ የቀረበባቸው አቶ ተላይህ አዱኛ በሕገ ወጥ መንገድ መሬት የያዙ መሆኑና የያዙት መሬት ወደ ባንክ መግባት ያለበት መሆኑን በመግለፅ፤ በ30/10/2013 ዓ.ም ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በደብዳቤ ያሳወቁ ቢሆንም፤ በወረዳው ሥራ አስፈጻሚ በኩል ተፈጻሚ አለመደረጉ፤ በተቃራኒው በአሁኑ ሰዓት መሬቱ ያለአግባብ በግለሰቡ በቆርቆሮ ታጥሮ እንደሚገኝ አረጋግጠናል።
በተጨማሪም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እና አቶ ተላይነህ አዱኛ ያልሆነ አምባጓሮ ውስጥ ከመግባታቸውም አልፈው ወደ ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ በሚል ቋሚ ኮሚቴውን ክፉኛ እንዳሳሰበው በደብዳቤው ተመላክቷል።
በመሆኑም ከፕላን አንጻር እንደተባለው ከሆነ፤ የመንገድ ጥናት ባይኖርም በዚሁ መሬት ላይ ካሁን በፊት ግለሰቦቹ ሲገለገሉበት የነበረ የመተላለፊያ የእግር መንገድ የተዘጋባቸው መሆኑና ለችግር የተጋለጡ ሲሆን፤ በአካባቢው ላይ የእሳት አደጋ ቢከሰት ሊደርስ የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕገወጥ መንገድ በግለሰቡ የተያዘውን የመንግሥት መሬት በማስለቀቅ መንግሥት ለሚፈለገው ዓላማ እስከሚውል ድረስ ለአንዱ መተላለፊያ መንገድ በመፍቀድ ሌሎችን መከልከል ተገቢ አይደለም።
ለሁሉም አካላት እኩል እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መስተናገድ ያለባቸው እንደመሆኑም ከአሁን በፊት የነበረው የመተላለፊያ የእግር መንገድ እንዲከፈትላቸውና ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር እንዲሁም ከሚመለከታቸው የክፍለ ከተማና የወረዳ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩ በአስቸኳይ እንዲፈታ በማለት እያሳሰብን፤ ይህ ደብዳቤ ወጪ ተደርጎ ቢሯችሁ ከደረሰ በኋላ ሁለት ሳምንት ውስጥ ምላሹን በደብዳቤ እንድታሳውቁን በማለት እናሳስባለን ይላል።
ሰነድ ሦስት፡- የክፍለ ከተማው የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና
በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ክፍል፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 01 መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቀን 15/6/2015 በቁጥር በ/ክ/ከ/የሥ/ም/ክ/850/2015፣ እርምጃ እንዲወስዱ ስለመጠየቅ በሚል ማሳሰብ ጭምር በተሞላበት ደብዳቤው፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 01 ልዩ ቦታ መለስ ፍሬ ትምህርት ቤት አካባቢ በአቶ ተላይነህ አዱኛ የተባሉት ግለሰብ ከሕግ አግባብ ውጪ ለረጅም ጊዜያት በሕገ ወጥ መንገድ አጥረው የመንግሥት መሬት እንደያዙ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጭምር ጉዳዩን በተለያዩ ወቅት ያረጋገጠ ቢሆንም፤ የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሆነውን መሬት ላይ ያሉትን የተለያዩ ግንባታዎች እና ዕቃዎችን ግልጽ አድርገው መሬቱን ባንክ ማስገባት ላይ ከፍተኛ ማዘናጋት ከመኖሩም በተጨማሪ፤ የተለያዩ አካላት ውሳኔዎችን ወደ ጎን በመተው አሁንም ድረስ ችግሩ ባለበት እንዲቀጥል እየተደረገ ይገኛል።
ስለሆነም የወረዳው መሬት አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት ፍቃደኛ ያልሆነበትን ጉዳይ አብራርቶ በዝርዝር መረጃ ይህ ደብዳቤ በደረሳችሁ በአምስት ቀናት ውስጥ እንድታሳውቁን እየጠየቅን፤ በጉዳዩ ማጣራት ሂደት ውስጥ የጠየቅናችሁ መረጃ በእጅጉ ስለሚጠቅመን በተባለው ቀን ውስጥ በአፋጣኝ መልስ እንድትሰጡን በማሳሰብም ጭምር ነው፣ ይላል።
ሰነድ አራት፡- የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት
በድጋሜ ታኅሣሥ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ለአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና ለከተማው ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በቁጥር 31/1292/15፣ ጉዳዩ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ላይ እየታየ ያለውን የአፈፃፀም ጉድለት ይመለከታል ሲል ደብዳቤ ፅፏል።
አመልካቾች በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 1 ልዩ ቦታው መለስ ፍሬ ትምህርት ቤት አካባቢ ነዋሪዎች ሲሆኑ፤ ከአሁን ቀደም ከመኖሪያቸው አካባቢ የሚገኝ የመንግሥት መሬት ይዘው የቆዩ ቢሆንም፣ በ2014 ዓ.ም ሕገ ወጥ መሆኑ ስለተረጋገጠ በወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር እንዲሁም በዋና ሥራ አስፈጻሚ በኩል መሬቱን እንዲለቁ ተደርጓል። ነገር ግን አቶ ተላይነህ አዱኛ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ 550 ካሬ ሜትር የመንግሥት መሬት በሕገወጥ መንገድ በድንጋይና በቆርቆሮ አጥረው እንዲሁም ችግኝ በመትከል የያዙ መሆኑ ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ተቋም በጋራ የተዋቀረ የቴክኒክ አጣሪ ቡድን በቦታው በመገኘት ማጣራቱን ይገልጻል።
መሬቱ ያለ አግባብ በሕገወጥ መንገድ በግለሰቡ መታጠሩንና ችግኝ በመትከል በድንጋይ አጥሮ መያዙን የቴክኒክ ቡድኑ አረጋግጦ ግለሰቡ አስፋፍተውና ከልለው በወረራ የያዙትን የመንግሥት መሬት ነፃ በማድረግ እንድታስጠብቁ በማለት ለወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ በደብዳቤ ያሳወቀ ቢሆንም እስካሁን ተፈፃሚ ያለመደረጉ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት ባደረጉት የማጣራት ሥራ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ አለመግባቱንና በግለሰቡ በድንጋይና በቆርቆሮ ታጥሮ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
በመሆኑም የወረዳው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እና የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሬቱ ባንክ ገብቷል በማለት እየተከላከሉ የሚገኙ በመሆኑና በወረዳው የደንብ ማስከበር ተቋም በኩል ጥበቃ እየተደረገ አለመሆኑ እየታወቀ ከወረዳው ጽሕፈት ቤት በቃል ብቻ የሚሰጠው ምላሽ በቂ ነው ብለን አናምንም በመሆኑም የመንግሥትን ይዞታ ለአንደኛው ወገን መፍቀድና ሌላውን መከልከል አግባብ ባለመሆኑ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮና የከተማው ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በጋራ ባለሙያ በመላክና ወርዶ በማረጋገጥ ታይቶ እልባት እንዲሰጥ በማለት እናሳስባለን ሲል አሳውቋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ምላሽ
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል ስለጉዳዩ ምን እንደሚያውቁ ጥያቄ የቀረበላቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ቸርነት አበበ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት ደግሞ፤ ጉዳዩ በተደጋጋሚ የሚነሳ ነው። ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት ቀርቦ በሚዲያም ጭምር ምላሽ ተሰጥቶበታል። ቦታው ላይ ይገባኛል የሚመስሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ነገር ግን ጥያቄው ከፕላን አንጻር ሳይሆን ከግል ፍላጎት የመነጨ ነው።
ለቀረበው አቤቱታ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ከተለያዩ ባለሙያዎችም ጋር በመሆን ቦታው ድረስ መሄዳቸውን የሚናገሩት ኢንጂነር ቸርነት፤ አቤቱታ የሚያቀርቡት ግለሰብ በወረራ ይዘዋል ብለው ከሚወንጅሉት ግለሰብ ባለፈ በትምህርት ቤት ይዞታው ላይ ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ። ለዚህም ዋና ምክንያት አቤቱታ አቅራቢው በቦታው ለመውጣትና ለመግባት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው።
አቤቱታ በተነሳበት ቦታ ላይ ምንም ዓይነት መንገድ በፕላን ላይ አይታይም። አቤቱታ አቅራቢው የትምህርት ቤቱንም መሬት ለመንገድ ለመጠቀም ፍላጎት አንጸባርቀዋል። አሁን ላይ ውዝግብ የሚነሳበት ቦታም የትምህርት ቤቱ አካል ነው። ትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ የተጠየቀበት ቦታ ደግሞ ወደ መሬት ባንክ የገባ ነው። በመሆኑም አሁን ላይ በግለሰብ ያለአግባብ የተያዘ ቦታ የለም፤ ይህንን ቦታው ድረስ በመሄድ አረጋግጠናል።
ይህን ጥያቄ የሚያቀርበው አካል አቶ አብርሃም ወርቁ የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ የምክር ቤት አባል ናቸው። አንድ ሰው የምክር ቤት አባል ሲሆን የመንግሥትን ሀብት በአግባቡ እንድንጠቀም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ሆኖም የምክር ቤት አባሉ እያቀረቡት ያለው ጥያቄ የመንግሥትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንዳይቻል የሚያደርግ ነው።
ከዚህ በፊት አቶ ተላይነህ ይዘውት የነበረው መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ እና ለትምህርት ቤቱ ማስፋፊያ እንዲሰጥ ተደርጓል። የምክር ቤቱ አባል ግን የሚፈልጉት ከአቶ ተላይነህ የተነጠቀውንና ወደ መሬት ባንክ የገባውንም መሬት ጭምር ነው። ይሄን ለማረጋገጥ እርሳቸውም ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በቦታው ሄደው በነበረበት ወቅት ለአቤቱታ የሚያበቃ የተወረረ መሬት ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍልም፤ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት እና ሌሎች ተቋማት መሬቱን አስለቅቁ እያሉ በተደጋጋሚ ሲጽፉ የነበረው ደብዳቤ ያለ በቂ ማስረጃ ነበር? ሲል ኢንጂነር ቸርነትን ጠይቋል። ኢንጅነር ቸርነት በምላሻቸውም፣ ለአንድ ነገር ጥቆማ ይቀርባል። በጥቆማው መሠረት የማየትና ችግሩን የመቅረፍ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በዚህም የአዲስ በዘመን ጋዜጣ የምርመራ ክፍል ለእናንተ የደረሰው ጥቆማ ሳይሆን ውዝግብ የተነሳበትን መሬት በወረራ መያዙን አረጋግጠናል የሚል ደብዳቤው ነው የደረሳችሁ። በደብዳቤው መሠረት እናንተ ለምን አላስፈፀማችሁም? በተለያዩ ተቋማት በደብዳቤ ለተጠየቃችሁት ጥያቄ የሰጣችሁት ምላሽ ካለ ልታሳዩን ትችላላችሁ? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው፡-
‹‹አሁንም ደግሜ የማረጋግጥላችሁ ቅሬታ የተነሳበትን መሬት ቦታው ድረስ ሄደን አጣርተናል። እናንተም እንደመርማሪ ጋዜጠኛ ቦታው ድረስ ሄዳችሁ ማየት ትችላላችሁ። በወረራ የተያዘ መሬት የለም። ነገር ግን ይህን የሚገለጽ ደብዳቤ እስካሁን ለአዲስ አበባ ምክር ቤትም ሆነ ለጸረ ሙስናና ሥነ ምግባር ጽሕፈት ቤት አላክንም። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ከላይ ለተጠቀሱት ተቋማት መሬት ላይ ያለውን ሀቅ በሪፖርት መልኩ ለመላክ በዝግጅት ላይ ነን›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የምርመራ ቡድንም፣ ከላይ የተጠቀሱትን የሰውም የሰነድም ማስረጃዎች በዚህ መልኩ ለእናንተ ለአንባቢያን ለዛሬው በዚህ መልኩ አቅርቧል። በቀጣይ ከመሬቱ ጋር የተያያዘውን ውዝግብ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምን እልባት አገኙ የሚለውን ተከታትሎ የሚያቀርብ መሆኑን ለመግለጽ ይወድዳል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር እና ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2015